Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም . . . !›

ሰላም! ሰላም! እንዴት ከርማችኋል? ባሻዬ በጠዋት ከዚህ ዓለም የተለዩዋቸውን ጓደኞቻቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ያላደለው በአየር ሳይበር በመኪና ብቻ ተጓጉዞ ያልፋል፤›› ብለው ተመስጦ ውስጥ ሲገቡ፣ ልጃቸው፣ ‹‹ያደለውንስ ምን ልትል ነው?›› ቢላቸው፣ አቅርቅረው ትንሽ አሰብ አደረጉና፣ ‹‹ያደለውማ የታላቁ አየር መንገድ ባለቤት ይሆናል፤›› ብለው ወደ ተመስጧቸው ተመልሰው ገቡ፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ የቢራም ሆነ የሌላ ቢዝነስ አክሲዮኖችን አልገዛም፤›› እያለ ሲቋምጥ ነበር፡፡ ‹‹መቼም ወደፊት ልጆችችን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእኛ ነው እንደሚሉ መገመት አያዳግትም፤›› በማለት የተሰማውን ደስታ አጫውቶኛል፡፡ አንዳንዱን የሚያስደስተው አንዳንዱን እያስደነገጠው ስለሆነ ነገር ዓለሙ ተዘበራርቆብኛል፡፡

ባሻዬም ቢሆኑ ከቴሌ አክሲዮን የመግዛት ዕቅድ አላቸው፡፡ ‹‹ከውጭ አገር ባለሀብቶች ጋር ተፎካክሬ የድርሻዬና የአቅሜን አክሲዮን መግዛቴ አይቀርም፤›› ብለው ከዓለም ዋንጫው በላይ የቴሌ ባለአክሲዮን ባለቤትነት የሚያረጋግጥላቸውን አክሲዮን ለመግዛት እየቋመጡ ይገኛሉ፡፡ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹መቼም በቀን የሚደርሱንን በርካታ የማስታወቂያ መልዕክቶች የማታስቀርልን ከሆነ ዞሮ ዞሮ ‹ጉልቻ ቢቀያየር . . . › የተባለው ነገር በአንተም ላይ እንደሚፈጸም አትጠራጠር፤›› ብሎ ገና ሳይጀመር ከአሁኑ በነገር ሸንቆጥ አደረጋቸው፡፡

እሳቸውም ቢሆኑ ሲያወሩ ለተመለከታቸው አክሲዮኑን ገዝተው በእጃቸው የሚገኝ ነው የሚመስለው፡፡ እንዲህም በማለት ቀጠሉ፣ ‹‹እንግዲህ በርካታ ለውጦችን እንደምናመጣ መጠራጠር የለባችሁም፡፡ አንደኛ የታሪፍ ማሻሻያ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ ፈለጋችሁት ቦታ ደውላችሁ ወዳጅ ዘመዱን የሚያናግርበትን መንገድ እንቀይሳለን፤›› እያሉም ባሻዬ ዕቅዶቻቸውን ሁሉ አውጥተው ጨርሰዋል፡፡ ‹‹የኢንተርኔት ዋጋን በተመለከተማ በነፃ በሚባል ታሪፍ ነው የምንመጣው፡፡ ዓላማችን ለእኛ ጥቂት ትርፍ ለማኅበረሰቡ ደግሞ በርካታ ጥቅሞችን ማጎናፀፍ ነው፤›› በማለት ባሻዬ ዛሬ ከወሬያቸው የሚገታቸው ሰው ጠፍቷል፡፡ ‹‹ሕዝባችንን የኢንተርኔት ዋጋ ቀንሰንለት ዕውቀት በዕውቀት ነው የምናደርገው፤›› ሲሉም ተደመጡ፡፡

ሁሌም በሦስተኛ ዓይን ማየት የሚወደው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹መንግሥት ይህንን የዘየደው መቼም የሆነ ነገር ፈልጎ ነው፡፡ የእነዚህ ታላላቅ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ መዛወራቸው ጉዳይ ከበስተጀርባውማ አንድ የማናውቀው አጀንዳ ይኖረዋል፤›› በማለት ብዙም ያልተረዳሁትን ሐሳብ አጫወተኝ፡፡

ለነገሩ እኔና ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽም ብንሆን ቴሌ ልዩ አስተያየት አድርጎልን፣ እስከ ዛሬ የገዛናቸውን የአየር ሰዓት ቆጥሮልን፣ የቋጠርናትን ጥሪት አክለን ቢያንስ አንድ አክሲዮን የመግዛት ዕቅድ አለን፡፡ ባሻዬ ብዙ ካሰላሰሉ በኋላ ይኼ ነገር ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ካልዋለ ፋይዳ የለውም ብለው ሲሠጉ ነበር፡፡ የሥጋታቸው ምንጭ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ የምናውቃቸው ባለሀብቶች አክሲዮኖቹን ጥርግርግ አድርገው እንዳይወስዷቸው የሚል ነው፡፡ ልጃቸውም ይህንን ሥጋታቸውን ተመልክቶ፣ ‹‹እርግጥ ነው አባቴ ላለው ይጨመርለታል፤›› በማለት ጨዋታው ከዚህ ውጪ እንደማይሆን ሲያብራራላቸው ነበር፡፡

መቼም እኔ አንዲት አክሲዮን መግዛት ቢያቅተኝ ከሳዑዲ ዓረቢያ አንድ በነዳጅ ሽያጭ የሰከረ ባለሀብት አምጥቼ ማሻሻጥ አያቅተኝም፡፡ ብቻ በዚህ ዘመን ላይ ለልጅ ልጆቼ የሚተርፍ እንጀራ ሳላበስልላቸው ስሜን ብቻ አውርሻቸው መሞት አልፈልግም፡፡ ቢሆንልኝ ከመሞቴ በፊት ማድረግ የምፈልገው ኑዛዜ ቢኖር ልጆቼ በአልጋዬ ዙሪያ ቆመው፣ ከአሁን አሁን አባታችን ምን ሊል ነው እያሉ ሲጠብቁ፣ ‹‹ልጆቼ ሆይ! አንተኛው የመጀመርያዬ ነህና የአየር መንገዱን አክሲዮን ውሰድ፣ አንቺ ደግሞ የቴሌውን ውሰጂ፣ አንተ ትንሹ ደግሞ የኃይል ማመንጫው አክሲዮን፣ የአንተ ነው . . . ›› ስል ባሻዬ፣ ‹‹የምታወራው ሁሉ ሊጨበጥ የማይችል የቀን ቅዠት ነው፤›› በማለት አላገጡብኝ፡፡

ወዳጆቼ የዓለም ዋንጫን ለማየት ምን ያህል እየተዘጋጃችሁ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ እኔም ብሆን ከደላሎች ጋር ቡድን መሥርተን ዱብ ዱብ እያልን ኳስ መጫወት ጀምረናል፡፡ እኔማ ጅማት ጅማት የመሰሉ የደላላ እግሮችን ተመልክቼ በሳቅ ፈርሻለሁ፡፡ ‹አመድ በዱቄት ይስቃል› ያለኝንም ጓደኛዬን አላግጬበታለሁ፡፡ እኔ በሌላው ስስቅ በእኔ ደግሞ የሚስቀው ሰው ብዙ ነው፡፡ ባይሆን ባሻዬ፣ ‹‹መሳቅስ በራስ ነው፤›› እያሉ አንዳንዴ እንደ እብድ ብቻቸውን ይስቃሉ፡፡ ሽበታቸውን እያዩ ሲገረሙ ሲስቁ አያቸውና ማንጎራጎር እጀምራለሁ፡፡ በነገር ልሸንቁጣቸው ብዬ፣ ‹‹እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ . . . ›› እያልኩ ሳንጎራጉር፣ ‹‹እርጅናን ያላየ ወጣትነትን ያደንቃል፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ባሻዬ መቼም እርጅና ከወጣትነት ይሻላል ብለውን ወደማይሆን ክርክር ውስጥ እንዳንገባ፤›› ስላቸው እሳቸውም ረጋ ብለው፣ ‹‹እንግዲህ በእርጅና ውስጥ ያለውን ብዙ ማስተዋልና ጥበብ ደርሰህ እየው፡፡ በዚህ አካሄድህ እንኳን የምትደርስም አይመስለኝም፤›› በማለት በነገር ወጋ አደረጉኝ፡፡ ይግረምህ ብለው ነው መሰለኝ፣ ‹‹አስመራ ጎዳና ላይና ቀይ ባህር ‹ሰልፊ› ሳልነሳ የምሞት መስሎሃል?›› በማለት ቀለዱ፡፡ ባሻዬ ወጉን ይችሉበታል፡፡ ከእሳቸው ጋር ማውጋት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ እንደ መማር ነው፡፡  

የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ባድመን ውሰዱ ኤርትራን መልሱልን፤›› እያለ ማንጎራጎር እየቃጣው ነበር፡፡ ንግግሩ ትንሽ ግራ ቢያጋባኝ ማብራሪያ ቢጤ ፈልጌ ዓይን ዓይኑን ተመለከትኩት፡፡ ይኼን ጊዜ፣ ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ ለመተያየት፣ አብሮ ቡና ለመጠጣት ልቡ ይፈልጋል፡፡ ይህ የተነፋፈቀ ሕዝብ ድንበር ሳይገድበው እንደ ድሮው ተገናኝቶ የልቡን ቢጫወት ይመኛል፡፡ ስለዚህ ከባድመ ይልቅ ሕዝቡ ይበልጥብናል፤›› በማለት ለጥያቄዬ መልስ ሰጠኝ፡፡ ያን ጊዜ ነበር የባሻዬ ልጅ ጥማት የእኔም ጥማት የሆነው፡፡ ባሻዬ በነገራችን ላይ ባድመ ላይ ለተሰውት ወገኖቻችን አሁንም ያለቅሳሉ፡፡

አንድ ደላላ ወዳጄ፣ ‹‹የዚያ ሁሉ ወጣት ነፍስ የጠፋበትን ቦታ እንዲሁ አንስቶ መስጠት አግባብ አይደለም፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ታዲያ ተጨማሪ ሰዎች ይሙቱ? አሁንም እንዋጋ ነው የምትለኝ?›› ብዬ የጠየቅኩትን ጥያቄ መመለስ አቅቶት፣ ‹‹ኧረ ከፈለጉ አሜሪካና ሰሜን ኮሪያ ይዋጉ፡፡ እኛ የጦርነት ኮታችንን ጨርሰናል፡፡ ከዚህ በኋላማ  ከፈለጉ ሩሲያና አሜሪካ፣ እንዲሁም እስራኤልና ፍልስጤም ይዋጉ . . . ›› እያለ ለውጊያ ያለውን ጥላቻ አንፀባረቀልኝ፡፡

የባሻዬ ልጅ ደግሞ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ እንኳንስ ከወንድሞቻችን ይቅርና ከጠላቶቻችን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፤›› በማለት አቋሙን አጫውቶኛል፡፡ እሱማ እንደ አባቱ ባድመ ላይ ለተሰውት ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ነፍስ ይማር የሚል ፀሎት ወደ ላይ ልኳል፡፡ አሁንም ግን ለበርካታ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ስንጠብቅ የነገሮች ፍጥነት ደግሞ ግራ እያጋቡን ነው፡፡ ከሁሉ ከሁሉ እዚያች ግሮሰሪ ውስጥ እኔና የባሻዬ ልጅ ቢራ ስንጠጣ አንዱ በፉጨት፣ ‹ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም . . . ›› እያለ ሲያቀነቅን፣ የፍጥነቱ ነገር መላ ያስፈልገዋል አልን፡፡ መልካም ሰንበት!   

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት