Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ​‹‹… ስንፍ ይዞ ድርሰት››

​‹‹… ስንፍ ይዞ ድርሰት››

ቀን:

ለደራስያን በሙሉ የምመክረው አንድ ነገር አለ፡፡ ንቃትም፣ ትጋትም ያጠጠበት ዘርፍ መስሎ የታየኝ ነገር ስላለ፡፡ ድርሰት ትልቅ ዝግጅትን ይጠይቃል፡፡ ከዝግጅቶቹ አንዱና መሠረታዊው ዕውቀትን በመመልከት፣ ዙሪያን በመቃኘት፣ በተለይ ደግሞ በማንበብና ያነበቡትን አጣጥሞ ራስን በመመርመር አእምሮን ከልቡና ጋር ማዳበር ነው፡፡ ዝም ብለን፣ አንድ ቀን ወፈፍ ጨምደድ ያደረገን ዕለት ተነሥተን እስቲ ወደገበያ ልውጣ እንደሚባለው፣ እስቲ ድርሰት ልጻፍ አይባልም፡፡ ድርሰት ከባዶ ስለማይፈልቅ፣ ያለፉትን፣ የቀደሙትን ዘመናትና ደራስያን ድርሰቶችን ማንበብ ያስፈልጋል፡፡ ሳል ይዞ ስርቆት ቂም ይዞ ጸሎት በሚለው ላይ ስንፍ ይዞ ድርሰት የለም የማለውን እጨምራለሁ፡፡ አፈ ታሪኩን፣ ተረታ ተረቱን፣ ሚቶሎጂውን፣ ሃይማኖታዊ መጻሕፍቱን፣ ታሪክን፣ ፍልስፍናን ማንበብ ለደራሲ የምርጫ ጥያቄ መሆን ያለበት አይመስለኝም፣ ሙያዊ ግዴታም፣ የሰብአዊነት መርህም እንጂ፡፡ ዕውቀታችን ግልብ ከሆነ፣ ድርሰታችን እንደዚያው ቀላል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የንባብ ዋጋ ከመድረስ ዋጋ ቢበልጥ እንጂ አያንስምና ቀደምት ድርሰቶች ዘርታችሁ ልታፈሩ ላሰባችኋቸው ድርሰቶች ግብኣት ይሁኗችሁ፡፡

ዮናስ አድማሱ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ‹‹መድበለ ጉባኤ›› (2001)

****************

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሆድ ይፍጀው ሆድ ፈጀ

አሰስ ግሳንግሱን እያመነዥገ

                   እየቆረጠመ፤

እየተረተረ እየጠመጠመ፤

እየጠቀጠቀ እየተመተመ፤

ነገር እየበላ ነገር እየጠጣ

ሆድ ዕቃ ታመመ፡፡

እየተደለለ ሆድ ቻል እንደ ፈረስ፤

ሲወጠር ሲነፋ ሲቀበተት አለ

                                      ነገር ሲጎሰጎስ፡፡

          ‹‹መቻል ምን ይከፋል፤

ሆድ ካገር ይሰፋል፤››

          እየተቀኘለት እየተበጃጀ

ነገር በሆድ ኹኖ ሆድ ይፍጀው

                   ሆድ ፈጀ፡፡

  • መላኩ ደምለው ወ/ጊዮርጊስ ‹‹ብልጭታ››

*******************

ራስን መቆጣጠር

በጥበበኞች ዓይን ከኃይለኛ ዝሆን ጋር የሚፋለም ሰው ጀግና አይባልም፡፡ እንደ ዕውነቱ ከሆነ ጀግና ማለት በተናደደ ጊዜ ራሱን የሚቆጣጠርና ክፉ የማይናገር ሰው ነው፡፡

ሰዎችን መጠየቅ ምንም ጉዳት የለውም፡፡ ጉዳት የሚኖረው ሰዎች ሰልችተው በቃ እስቲሉ መመላለስ ነው፡፡ ራስክን መቆጣጠር የቻልክ እንደሆነ ከሌሎች ወቀሳ አይደርስብህም፡፡

*****************

ራስ ወዳድነት

ርህራሄ ወደ ራቀው ሰው ፍጹም አትመልከት፤ ሚስቱንና ልጆቹን ለስቃይ ዳርጐ የራሱን ድሎት ብቻ የሚሻ በመሆኑ ምንጊዜም አይቀናውምና፡፡

በተቸገረ ጊዜ እጆቹን ወደ አምላኩ ዘርግቶ የሚማጸን፣ ለምጽዋት ሲጠየቅ ግን እጆቹን አጣምሮ ብብቱ ስር የሚወትፍ ደኃ ፀሎቱ ምን ይፈይደዋል?

እርካሽ ሰዎች ራሳቸውን ካዳኑ በኋላ ‹‹መላው ዓለም እንኳን ቢጠፋ እኛ ምን ተዳችን?›› ይላሉ፡፡

አንድ ሰው በረሃብ [ቢሞት] እኔን ምን ያስጨንቀኛል? እኔ አልጐደለብኝ! [ይላሉ] የውኃ ማጥለቅለቅ ዳክዬን ለምን ያስፈራታል?

***********************

ራስን ማፍቀር

አንዲት ቆንጆ ልጃገረድ አድናቂዋን በእርጋታ ምን ብላ እንዳለችው ሰምታችኋልን? እንዲህ አለችው፡- ‹‹በራስህ ፍቅር የታወርክ ሰው እስከሆንክ ድረስ በዓይኖችህ ዘንድ የእኔ ውበት ዋጋው ምን ሊሆን ይችላል?››

ራሳችሁን በማፍቀር የተጠመዳችሁ ሁሉ በፍጹም እውነተኛ አፍቃሪዎች ልትሆኑ አትችሉም፡፡ ያፈቀራትን ማግኘት ያልቻለ ሰው በፍለጋዋ መሞት እንዳለበት ፍቅር ያስገድደዋል፡፡

*************

 

 

ራስን ማክበር

አንበሳ ምድማዱ ላይ እንደተኛ በረሃብ ይሞታል እንጂ የውሻን ትራፊ አይበላም፡፡ በረሃብ ቸነፈርንና ችግርን ቻል፡፡ ከርካሽ ሰው ዕርዳታ በመጠየቅ ክብርህን በፍጹም በገዛ ራስህ አትጣ፡፡ መልካም ሥነ-ምግባር የሌለውን ሰው እርሳው፤ እንዲሁም ዋጋ-ቢስነቱን ዕወቅ፡፡

ወደ ልመና የሚያደላ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ምን ጊዜም ለማኝ ነው፡፡ በቃኝ ባይ አእምሮ ያለው ሰው ሁልጊዜ የተከበረ ነውና ስግብግብ አትሁን፡፡

የጉልበትህ ውጤት የሆነ ኾምጣጤና ጎመን ከባለ ሥልጣን እንጀራና ዝግን በእጅጉ ይበልጣል፡፡

  • በራስ መተማመን በሌለበት ቦታ አክብሮት የለም፡፡ አክብሮት በሌለበት ቦታም በራስ መተማመን ሊኖር አይችልም፡፡              (ሄንሪ ጊልስ)
  • ባይለየኝ ጣሰው ‹‹የሶኖዲ ጥበቦች›› (2004)

***********************

 

ሁለተኛ ቋንቋ ለመማር ጥሩ ዕድሜ

ሌላ ቋንቋ ለመማር የልጅነት ዕድሜ ዓይነተኛ ጊዜ እንደሆነ በብዙዎች የሚታመን ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ይህን በጥናት ማረጋገጥ ሳይቻል መቅረቱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ አሁን ግን አእምሮን ስካን በማድረግ እንዲሁም ሌሎች ስታትስቲካል መንገዶችን በመጠቀም ዕድሜ በገፋ ቁጥር ሁለተኛ ቋንቋን የማቀላጠፍ ነገር እየቀነሰ እንደሚሔድ ማረጋገጥ መቻሉን የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡ ጥናቱ ለሕፃናት በዙሪያቸው የሚነገርን ቋንቋ በቀላሉ ማወቅ ቀላል እንደሆነም ያሳያል፡፡ ሕፃናት ከአዋቂዎች በተሻለ የቋንቋ ብቃት ኖራቸው ለሚለው፣ በብዙ ነገሮች ከሚወጠሩ ትልልቅ ሰዎች ይልቅ ሕፃናት ለሁለተኛ ቋንቋ ትኩረትና ጊዜም መስጠት ስለሚችሉ መሆኑ እንደ አንድ ምክንያት ተቀምጧል፡፡ የጥናቱ ውጤት ትክክለኛውን ሁለተኛ ቋንቋ የማወቅ ዕድሜ ይህ ነው ብሎ ለማመላከት ባያስችልም፣ ልጆችና ታዳጊዎች ሁለተኛ ቋንቋን ለመማር የተሻሉ እንደሆኑ ያሳያል፡፡

**********************

የጐረቤት አትክልት በልቷል የተባለ ፍየል የሰባት ዓመት እስር ተፈረደበት

በጐረቤት የሚገኙ አበቦችንና ሌሎች የጓሮ አትክልትን በተደጋጋሚ በመብላት ጥፋት አድርሷል የተባለ ፍየል፣ የሰባት ዓመት እስር እንደተፈረደበት በማዕከላዊ ህንድ የቻታስጋራህ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ሚረር ዩኬ ፖሊስንና የህንድ ቴሌቪዥን ጣቢያን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አትክልቱ የተበላበት ሰው በተደጋጋሚ ለፍየሉ ባለቤትና ለፖሊስ አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ግን የፍየሉ ባለቤት፣ ፍየሉን ማገድ አልቻለም፡፡

እንደፍየሉ የእስር ፍርድ የተቆረጠለት የፍየሉ ባለቤት አብዱል ሀሰን፣ ‹‹ፍየሉ በጐረቤቴና በእኔ ቤት መካከል ያለውን አጥር በመዝለል እየገባ አበባና ሌሎች የጓሮ ተክሎችን በልቷል›› ሲል አምኗል፡፡

***************************

ስሎቫኒያ የቢራ ፋውንቴን ልትገነባ ነው

ስሎቫኒያ በሚገኘው ዛሊክ ከተማ 400 ሺሕ ዶላር የሚያወጣ ፋውንቴን ሊገነባ መሆኑን ዩፒአይ ዘግቧል፡፡

የቢራ ፋውንቴኑ የሚጠቀመውም፣ በአገር ውስጥ የሚመረቱትንና ለመጠጥ የሚውሉትን የቢራ ዓይነቶች ነው፡፡

የዛሊክ ከተማ ካውንስል በከተማዋ የቢራ ፋውንቴን ለመገንባት የቀረበውን ዕቅድ ያፀደቀው በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አጽድቆታል፡፡ ሀሳቡን የተቃወሙት ደግሞ ለከተማዋ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ተግባራዊ ቢሆን የተሻለ ነበር ብለዋል፡፡

የቱሪስት መስህብም ይሆናል ተብሎ የታቀደው የቢራ ፋውንቴን ግንባታ ሲጠናቀቅ፣ ከፋውንቴኑ ቢራ ለመጠጣት የሚፈልጉ ለአንድ የቢራ ብርጭቆ 6.75 ዶላር እንደሚከፍሉ ዘገባው ያሳያል፡፡

በስሎቫኒያ የሚገነባው የቢራ ፋውንቴን፣ በአውሮፓ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ለአገሪቱ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆንም ደንቪንክ ድረ ገፅ ዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...