Wednesday, April 17, 2024

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ሪፎርም ማድረግ ለምንና እንዴት?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአገሪቱ ከደኅንነት ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ኃይል የአደረጃጀት ችግር እንዳለበትና ወገንተኝነት የሚስተዋልበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ትችት ይቀርብበታል፡፡

የመከላከያ ኃይሉ የተመሠረተበት አግባብ ማለትም ከሕዝብ ጦር ወደ ሙያዊ አገር መከላከያ ኃይል ሲያድግ የመጣባቸው ሒደቶች፣ ብሎም ከጊዜው ሁኔታ ጋር ሲለዋወጡ የነበሩት ተልዕኮዎቹ ተጠባቂውን ለውጥ እንዳያመጣና በሕዝቡም ዘንድ ተዓማኒ እንዳይሆን አድርገውታል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ይህንን ለመቀየር የሚያስችሉትን የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ከደርግ ጋር የነበረው ትግል እየሰፋ ሲመጣ፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር በነበረው መለያየት ወቅት ባጋጠሙ ግጭቶች፣ የሶማሊያ አልኢታድ የማስፋፋት ትልም ወቅት ባጋጠሙ ግጭቶችና ጦርነቶች፣ ተያይዞም የተከፈሉ መስዋዕትነቶችን ተከትሎ የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡

በእነዚህም ሒደቶች የመከላከያውን ሙያዊ ብቃት (ፕሮፌሽናሊዝም) ለማሳደግ የሚያስችሉ የኢንዶክትሪኔሽንና የአደረጃጀት ማስተካከያዎች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም መከላከያው ሙያዊ አደረጃጀቱን ለማሳደግ አሁንም ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠበቅበት እንደሆነ በርካቶች የሚስማሙበት ነው፡፡

በተለያዩ መንግሥታት ሥር የነበሩ የመከላከያ ኃይሎችም የነበረባቸው ዋነኛ ችግር የሙያዊ ብቃት ችግር እንደነበረም የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ሙሉጌታ ገብረ ሕይወት፣ ‹‹The Ethiopian Post-Transition Security Reform Experience: Building a National Army from a Revolutionary Democratic Army›› በሚለው ጥናታቸው፣ የኢትዮጵያ ልምድ ሕዝባዊ ወታደራዊ ኃይልን ወደ ብሔራዊ ሠራዊት የሚቀየርበት ሒደት ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከአብዮት የወጡ ተዋጊዎች በብዛት ከነባሩ ጦር ጋር ሲቀላቀሉ ወይም ትግላቸውን ያለምንም ጉልህ ውጤት ሲቀጥሉ የሚታይባት አፍሪካ ላይ ልዩ ምሳሌም እንደሆነ ያሳይሉ፡፡ ይህም ቀድሞ ከነበሩት የአገሪቱ የአገር መከላከያ ሠራዊት አደረጃጀቶች የተለየ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ኃይል ታሪክ በዋናነት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሚጀምር ሲሆን፣ በንጉሡ ዘመንም ይህን ተከትለው በመጡት የደርግና የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መንግሥታት በተመሠረቱ የወታደር አደረጃጀቶች በግልጽ የሚታዩ የአደረጃጀት መሠረታዊ ችግሮች እንዳሉ የሚገልጹ አካላትና ሰነዶች አሉ፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊትን ሪፎርም ማድረግ ለምንና እንዴት?

 

በንጉሡ ዘመን የነበረው የመከላለከያ ኃይል አደረጃጀት ልማዳዊ/ባህላዊ የነበረና ሙያዊ ያልነበረ በመሆኑ፣ የጣሊያን ወረራን መከላከል ሳይችል ቀርቶ በውጭ ኃይል ዕገዛ ነበር መመከት የተቻለው፡፡ የንጉሡን መሪነት ማስቀጠልና የአገሪቱን ወረራ ለመመከት የተቻለው ንጉሡም ከስደት ከተመለሱ በኋላ፣ የመከላከያ ኃይሉን እንደገና በማደራጀትና በማሠልጠን ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይህም ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ግዳጅ ተሰማርቶ ኮሪያ ኮንጎ የዘመተ ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን የንጉሣዊው ወታደሮች ውስጣዊ ተቃውሞዎችን ለማስቆም የሚውሉ መሣሪያዎች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም የንጉሡ ፖሊሲዎች ለአገር ውስጥ ፍላጎቶች የሚሰጡት ትኩረት ስላልነበረ ነው፡፡

በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ወቅት የነበረው ሠራዊት ተልዕኮ በዋናነት አብዮቱን መጠበቅ ሲሆን፣ አገሪቱን በመምራትም ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡

የወታደራዊው መንግሥት የወታደሮች ቁጥር በየጊዜው እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ ከሙያዊ ብቃት አንፃር ግን እጅግ የሚተች ነበር፡፡ በተለይም ሠራዊቱ አገራዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን ጥቅም ላይ ይውል ስለነበር፣ የወታደሩ ሙያዊ አደረጃጀቱ ዝቅተኛ ስለነበረም መንግሥት ከውጭ አገሮች በቁሳቁስና በሰው ኃይል ድጋፎችን ይቀበል ነበር፡፡

ከዚህ በዘለለም ሠራዊቱ የተደራጀ የውትድርና አስተሳሰብ ቢኖረውም በኢሠፓ የተቃና ስለነበር፣ አደረጃጀቶቹና የሥራ እንቅስቃሴዎቹ በውጭ የውትድርና አማካሪዎች ጭምር ይመሩ ነበር፡፡ የወታደሩ አስተሳሰብም በዋናነት በሶቪየት የውትድርና አማካሪዎች የተቃኘ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ወታደሩ ውስጡ በክፍፍል፣ በቅናትና በሴራ የተተበተበ ነበር፡፡ ይህም መንግሥት አመራር ላይ በነበሩ እጅግ የሚፈለግ የሠራዊቱ ባህርይ ሆነ፡፡ ይህም የዕዝ መፈራረስንና በወታደሩ ላይ የሚደረግ ቁጥጥር እንዳይኖር አደረገ፡፡

በትግሉ ጊዜ ከነበረው ዓላማ ባለፈ አገር የመከላከልና የአገር ደኅንነት ሥጋቶች ናቸው ተብለው በመንግሥት የተለዩ ሁኔታዎችን በመገምገም ትግል ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደገና የተደራጀው የአሁኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም፣ ከቀደሙት ሠራዊቶች የወረሳቸው ባህርያት እንዳሉት የሚስማሙ በርካቶች ናቸው፡፡

በተለይ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት መንግሥት በፖሊስ ኃይል በአገሪቱ ተቀስቅሶ የነበረውን ተቃውሞ ለማስቆም ባለመቻሉ፣ ወታደሩ ጣልቃ እንዲገባ በተደረገለት ጥሪ ፀጥታውን ለመቆጣጠር ያደረገው ሒደት የሠራዊቱን ሙያዊ ተልዕኮና በተለይም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነበር፡፡

መከላከያውም መንግሥት ቢቀየር ምን ያህል ከአዲሱ መንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት ቁርጠኛ ነው የሚለው ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ መልስ ያላገኘ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ግንቦት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ለከፍተኛ የመከላከያ ኃይሉ መኮንኖችና ኃላፊዎች በተገኙበት ባደረጉት ገለጻ ትኩረት ያደረጉትም በዚህ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ኃይል በኩል ያለው ዋነኛ ቁልፍ ሪፎርም ጉዳይ የሠራዊቱን ፕሮፌሽናሊዝም ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመዋል ብሏል፡፡

ይህም ሲባል የሠራዊቱን ሙያዊ ብቃት፣ ኃላፊነት የመውስድና የተሟላ ሰብዕና የተላበሰ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ሠራዊቱ በመርህ የሚገዛና ለወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተፅዕኖ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ የሕዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር ያደርገዋል ብለዋል፡፡ በቅርቡ በተደረገው የመንግሥት ሥልጣን ሽግግር ወቅትም ሠራዊቱ ያሳየውን ሙያዊ ዲሲፕሊን ያደነቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ፕሮፌሽናሊዝም መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹የመከላከያ ሠራዊት ዋነኛ ዓላማ በሲቪል አስተዳደሩ የሚቀመጡ አገራዊ ሥጋቶችና የደኅንነት ሥጋቶችን በተቀመጠለት ትርጓሜ መሠረት በላቀ ብቃት ግዳጁን የማስፈጸም፣ የሕዝብን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስከበርና የአገር ክብርና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው፤›› ሲልም መግለጫው ያክላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመከላከያ አባላት በሰጡት ማብራሪያም፣ ‹‹የመከላከያ ኃይሉ የሥርዓት ለውጥን ተቀብሎ መቀጠል የሚችል ከሆነ መላመድና መቀጠል የሚችል ነው ማለት ነው፤›› ‹‹ኃይለ ማርያም ተነስቶ ዓብይ ሲመጣ መቀበል የሚችል ሠራዊት ከሆነ ለውጥን መላመድ የሚችል ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ባለፈም፣ ‹‹ኢሕአዴግ ፖለቲካዊ ሥራውን መሥራት አቅቶት በራሱ ስንፍና የወደቀ እንደሆነ፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብ ከመረጠው ፓርቲ ጋር መቀጠል የሚችል ሠራዊት መሆን አለበት፤›› ሲሉ መከላከያ ኃይሉ በምን ልክ ራሱን ማሳደግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሪፎርም ዕቅድ በተመለከተ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ‹‹ሪፎርም ወሳኝ ነው፣ የደኅንነት አካላት ሪፎርም እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ የተናገርነውና ዋነኛ ትግላችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን አቶ የሺዋስ ሪፎርሙን በደፈናው ከመጫን ችግሩ ምን እንደሆነ መለየትና መታወቅ እንዳለበት፣ ከዚያም ጥናት ተጠንቶ በዚያ መሠረት ለውጡ መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

‹‹በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ስንጠይቅ ስለነበር ድርድር ይኖራል ብለን ጠብቀን ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ብቻውን የሚያደርገው ለውጥ ዘላቂ ለውጥ ይሆናል ብዬ አላምንም፣ ነገር ግን እንደ ጅምር መታሰቡ በራሱ መልካም ነው፤›› ሲሉም ጅምሩን ይሁን ይላሉ፡፡

አቶ የሺዋስ ሪፎርሙ ለዴሞክራሲ ምኅዳሩ መስፋትም ትልቅ ሚና ስለሚሆነው ጠቃሚነቱ የጎላ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን አንድ ፓርቲ እንዲያሸንፍ ያደረጉትም እነዚህ ተቋማት ስለሆኑ፣ ገለልተኛ ተቋማት ቢኖሩ ኖሮ በዚህች አገር ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድና የተዘጋውን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋት ያስችላል ብለው እንደሚያምኑም ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖትም መከላከያው ሪፎርም ያስፈልገዋል ብለው እንደሚምኑ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ሪፎርም የሚያስፈልገው የመንግሥት ተቋማት በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየሠሩ ስላልሆነ ነው፤›› የሚሉት ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ ለአንድ ድርጅት የመጨረሻ መሸሸጊያ ከመሆን ለመውጣት ሪፎርሙ ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡

እንደሳቸው ምልከታ የመከላከያው ሪፎርም በዋናነት ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሚያስወጣው፣ ዘመናዊ የሆነና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የሚያስችለው፣ ብሎም ለመከላከያው አባሉና ለሌላው ዜጋ በሕገ መንግሥት የተሰጡ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩበት አግባብ ሊኖር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹የሆነ ድርጅት ተቀጥያ እንዳይሆንና ፖለቲካው ውስጥ እጁን እንዳያስገባ ሪፎርም ያስፈልገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንንም ለማድረግ ሪኢንዶክትሪኔሽን (ዳግም እነፃ) እንደሚያስፈልጋቸውና የአደረጃጀት፣ የአስተሳሰብ፣ ግፋ ሲልም የሰዎች ለውጦችን ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከአሁን ቀደም ባልነበረ ሁኔታ፣ በቅርቡ የምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹመቶች መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ግን ከአጠቃላይ የደኅንነት ዘርፍ ሪፎርም ጋር መቃኘት ያለበት ነው የሚሉት ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ የምክትል ኤታ ማዦር ሹመት በሌላ አገር የሚሠራበት፣ ነገር ግን በእዚህ አገር የዘገየ እንደሆነ ያወሳሉ፡፡

ይህ ለውጥ እንዲመጣ የገፉ ምክንያቶች በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየው የሕዝብ ተቃውሞ፣ ‹‹በፀረ ዴሞክራሲያዊ አሠራር አልገዛም›› በማለቱ ሪፎርሙን አሁን ላይ ማድረግ የግድ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ዛሬ ካልሆነ ነገ ሊደረግ አይችልም፡፡ አሁን ካልሆነ አገሪቱ አደጋ ውስጥ ልትገባ ትችላለች፤›› ይላሉ፡፡

ይሁንና ይህ ሪፎርም በቀላሉ ተፈጻሚ እንደማይሆን ያምናሉ፡፡ ለሪፎርሙ ዋነኛ ፈተና ሊሆነው የሚችለው ኢሕአዴግ መራመድ እያቃተው ስለሆነ፣ ለውጥ የማይፈልጉ የድርጅቱ አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳስባሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊወጡት ይችላሉ ብለው ያምናሉ፡፡

መከላከያው አሁን የብሔር ተዋጽኦ ያሟላ ስለሆነና አንድ ሰው ብቻውን ስለማያዘው ከለውጡ ጋር ትግል መግጠም ይኖራል ብለው እንደማያምኑም ይናገራሉ፡፡

‹‹ከመከላከያው ተቃውሞ ይኖራል ብዬ አላስብም፤›› ሲሉም ይደመድማሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ አገሪቱ በሌሎች የውትድርና ዘርፎች የበላይነትን እንዳስመዘገበች ሁሉ፣ በባህር ኃይልም ይህንኑ መድገም እንደሚቻልም አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ያሉባት የደኅንነት ሥጋቶች ውስብስብና በየጊዜው የሚለዋወጡ ናቸው፡፡ ይህም በጦር ሜዳ ያሉ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ እያደገ የመጣው ሳይበርና ያልተለመዱ ዓይነት ጥቃቶችም ጭምር ናቸው፡፡ የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ቀጣይነት ያለውና ፈጣን የሆነ የመቋቋም አቅምን መገንባት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

አሁን እየታቀደ ካለው የመከላከያ ማሻሻያ ቀደም ብሎ የአሁኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ተደጋጋሚ ሪፎርሞችን አድርጎ ነበር፡፡ ነጩ ወረቀት የሚባለውና  እ.ኤ.አ. በ2012 የወጣው የደኅንነትና የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ የአገሪቱ ጠላት ድህነት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህም ለአገሪቱ ዘላቂ ደኅንነት ድህነትን ማስወገድ አስፈላጊ እንደሆነ ያትታል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተቋማዊ አደረጃጀቱን ለማስፋትና ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን በመቀበል ረገድ ብዙ ርቀት የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ግን ብዙ የፕሮፌሽናሊዝም ጥያቄዎች ያነሱበታል፡፡ ይህም በተለይ ለፓርቲ ያልወገነና ገለልተኛ ሠራዊት መሆን ላይ በሰፊው መነጋገርያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -