Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለአምስቱ ነገሥታት ክብር የሰጠው የአሜሪካው መድረክ

ለአምስቱ ነገሥታት ክብር የሰጠው የአሜሪካው መድረክ

ቀን:

በዳያስፖራ የሚኖሩ በየአገሩ የተበታተኑ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (ኢት ዘር) በእንግሊኛው ምሕፃር ሲድ/SEED (the Society of Ethiopians Established in the Diaspora) ይባላል፡፡

በአሜሪካ ከተመሠረተ ከሁለት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው ሲድ በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለፉትን ነገሥታት መሪዎች በማሰብና በማክበር ያለፈውን አገራዊ ታሪክ ሕያውነት ለማስቀጠል የሚሠራ ተቋም መሆኑ ይገለጻል፡፡

ማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (ኢት ዘር) 26ኛ ዓመታዊ በዓሉን በዋሽንግተን ዲሲ ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ባከበረበት አጋጣሚ ‹‹አምስቱ ዕፁብ ድንቆች ነገሥታት›› በሚል በ19ኛውና በ20ኛው ምዕት ዓመት ከነገሡት ሰባቱ ነገሥታት መካከል ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ፣ ለራብዓዊ አፄ ዮሐንስ፣ ለዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ ለንግሥተ ነገሥታ ዘውዲቱና ለቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሽልማቱን አበርክቷል፡፡

- Advertisement -

በኢት ዘር መግለጫና የሽልማት መርሐ ግብር መሠረት ስለነገሥታቱ ሕይወትና ሥራ ንግግር ከቀረበ በኋላ ነው ሽልማቱ የተበረከተው በመርሐ ግብሩ ቅደም ተከተል መሠረት ስለ አፄ ዮሐንስ ንግግር ያደረጉትና ሽልማቱንም የተቀበሉት የልጅ ልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ናቸው፡፡

ስለአፄ ቴዎድሮስ ገጸ ታሪክ ያቀረቡት ደግሞ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ ሲሆኑ ሽልማቱን የአፄ ቴዎድሮስ አምስተኛ ትውልድ አቶ መሸሻ ካሳ ናቸው፡፡ ስለዳግማዊ ምኒልክ ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ፣ ስለ ንግሥት ዘውዲቱ ዶ/ር አበባ ሐረገወይን ትውስታዎችን ሲያቀርቡ ሽልማቱን ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ተቀብለዋል፡፡ ስለመጨረሻው ተሸላሚ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የአመራር ዘመን ምስክርነት ያቀረቡት ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ ሲሆኑ፣ ሽልማቱን የልጅ ልጆቻቸው ልዕልት ማርያም ሥና አሰፋወሰን፣ ልዑል በዕደማርያም መኰንንና ልዑል ኤርሚያስ ሳህለ ሥላሴ መቀበላቸው ታውቋል፡፡

አንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዋ ድምፃዊትና የግራሚ ሽልማት ዕጩ ወይና ወንድወሰን የሙዚቃ ድግስ ሲያቀርቡ የቪዲዮ ትዕይንትም ቀርቧል፡፡

ዕፁብ ድንቆቹ ነገሥታት

ከሰማንያ ዓመታት በላይ አንድነቷ ርቆ በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችውን ኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት በማላቀቅ ለአሐዳዊት ኢትዮጵያ መነሳት በቀዳሚነት የሚጠቀሱት አፄ ቴዎድሮስ (1812-1860) ናቸው፡፡

ዳግማዊ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂ ለማበልጸግ በመወጠን፣ ሰባስቶፖል መድፍን መሥራታቸው፣ ማዕከላዊ ቤተ መዘክር መመሥረታቸው፣ ወታደሩ በሥርዓት በመንግሥት ሥር እንዲደራጅ መወጠናቸው ይጠቀስላቸዋል፡፡

‹‹አባ ታጠቅ›› በሚል የፈረስ ስም የሚታወቁት ዳግማዊ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከተሰዉ በኋላ በመንበራቸው ላይ ለሦስት ዓመት የተቀመጡት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ከሳቸው በኋላ ‹‹ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ‹‹ተብለው ዘውዱን በ1864 ዓ.ም. የጻፉት “አባ በዝብዝ”›› በሚል የፈረስ ስም የሚያውቁት አፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (አራተኛ) ናቸው፡፡ በአፄ ቴዎድሮስ የተጀመረውን የአንድነት መንገድ በማጠናከርና ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪዎች (ከግብፅ፣ ከቱርክ፣ ከጣሊያንና ከእንግሊዝ) ለመታደግ በጉንደት፣ ጉራዕ፣ ዶግዓሊ ወዘተ.) በርካታ ጦርነቶችን አድርገው በድል ተወጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹Innovation and Misoneism during the Reign of Emperor Yohannes IV (1872.1889)›› በሚለው ጥናታቸው እንደገለጹት አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሥርዓት በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በከተማ ልማት (ደብረ ታቦርና ደሴ)፣ በዘመናዊ ሕክምና፣ በክትባት፣ በክሊኒክ ምሥረታ (ዓድዋና ጎንደር) ቅርስ ከእንግሊዝ በማስመለስ (ክብረ ነገሥትና ዕደ ጥበባት)፣ የባርያ ንግድን የማስቆም ድንጋጌንም በማውጣት ይጠቀሳሉ፡፡ መተማ ላይ ከድርቡሾች (ሱዳን) ጋር ባደረጉት ፍልሚያ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ ሥልጣኑን በ1881 ዓ.ም. የተረከቡት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በፈረስ  ስማቸው አባ ዳኘው ናቸው፡፡

ዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ፋና ወጊ ካሰኛቸው ዋናው አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማስተዋወቃቸው ነው፡፡ ባንክ፣ ፖስታ፣ ባቡር፣ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ቴሌግራም፣አውቶሞቢል፣ ቧንቧ፣ ወዘተ. ማስገባታቸው ነው፡፡ የሚኒስቴር አደረጃጀትም ተልመዋል፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ ኅልፈት በኋላ ለሦስት ዓመት በሥልጣን ከቆዩት ልጅ ኢያሱ ቀጥሎ በ1909 ዓ.ም. የመጡት ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ናቸው፡፡ በንግሥቲቱ ከተፈጸሙት ተግባራት መካከል ኢትዮጵያ የወቅቱ የዓለም መንግሥታት ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አባል መሆኗ፣ አውሮፕላን መግባቱ፣ ስለባሮች የነፃነት ደንብ መውጣቱ፣ ከመቅደላ ተዘርፎ የነበረው የአፄ ቴዎድሮስ ዘውድ መመለሱ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መሾማቸው ይጠቀሳሉ፡፡

የማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ 26ኛ ዓመታዊ በዓል ላይ ስለግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ ካቀረቡት ምስክርነት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተጀመረውን የልማት ጥረት በእጅጉ ወደፊት በማራመድ፣ ኢትዮጵያ የዘመናዊ ሥልጣኔ ተካፋይ እንድትሆን የሚያስችላትን ተግባራትን በመፈጸም፣ ለአገራችን ዘመናዊ ዕድገት ጽኑ መሠረት ለመጣል የበቁት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡››

የንጉሠ ነገሥቱን አርቆ አስተዋይነትና ብልህነትን የተላበሰ አመራር ለማሳየት አራት ዓበይት የአገልግሎት ዘርፎችን በማሳያነት ያነሱት የዘመናዊ ብሔረ መንግሥት ግንባታ፣ የትምህርት ዕድገትና መስፋፋት፣ የውጭ ግንኙነቶች ጥንካሬና የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት ዕድገት ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር ዳዊት ዲስኩር፣ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አርቀው ካሰቡበትና ከተለሟቸው ተግባራት ቀዳሚው፣ የተሟላ ብሔረ መንግሥት ግንባታ ላይ ያነጣጠረው ሥራቸው ነው፡፡ ለአንድ አገር ሕዝብ የሰከነ ወደፊትን ለማረጋገጥ፣ የተማከለ ዘመናዊ የመንግሥት አመራርና አስተዳደር ዘይቤን መዘርጋት ወሳኝ መነሻ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ ረገድ ያደረጉት ትግልና ጥረት ውጤታማ ነበር ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አንድ መንግሥት ከቆመችበት ጊዜ ጀምሮ ከሕግ ውጭ ባትኖርም አስተዳደሩ መንፈሳዊውና ሥጋዊው የተዋሃደበት ነበር፡፡ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ደግሞ ‹‹ፍትሐ ነገሥት›› በሚል ስያሜ [ፍትሕ መንፈሳዊና ፍትሕ ሥጋዊ] በአንድነት ሲሠራባቸው ቆይተዋል፡፡

ንጉሠ ነገሥቱ የአገሪቱን አመራር ቅርፅ ዘመናዊ ለማድረግ፣ በቁርጠኝነት በመነሳት ዘውድ በጫኑ በዓመቱ በ1924 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የተጻፈ ሕገ መንግሥት ፈቅደው በሥራ ላይ ማዋላቸው፣ የዜጎች ሐሳብ የሚደመጥበትና እንደራሴዎችም የሚመክሩበት ፓርላማም ማቋቋማቸው፣ በ1948 ዓ.ም. ይህንን ሕገ መንግሥት ሲያሻሽሉም አርቆ አስተዋይ ዓላማቸው፣ ሕዝቡ በዕውቀትና በኑሮው ሲበረታ የአገር አስተዳደር ኃላፊነቱን ለመረከብ እንዲችል መንገዱን ለመቀየስ ነበርም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ዳዊት በዲስኩራቸው ማሳረጊያ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ከማሳሰብ አላለፉም፡፡ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ከእኚህ ታላቅ መሪ ሕይወት ልንማር የምንችለው እጅግ ብዙ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ ለዛሬ ምሽት አንዷን የመሐሪነታቸውን ስንኝ ብቻ ነቅሰን በማውጣት፣ ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለን ንስሐ እንግባ፡፡ የታሪካችንን ጽኑ ኢትዮጵያዊነት ተመርኩዘን በአሁኑ ወቅት ብልጭ በማለት ላይ በሚታየው የተስፋ ድባብ ጭምር ተነሳስተን ታሪካችንን ለማደስ የጥላቻ ፖለቲካን እናስወግድ፡፡ ችግሮቻችንን ደረጃ በደረጃ በዕውቀትና ብልህነት በታገዘ አመራር እየፈታን ጃንሆይ በጣሉት ጽኑ መሠረት ላይ በመቆም በጎ በጎውን ይዘን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...