Tuesday, February 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነ የምሕረት ቦርድ ያቋቁማል

የምሕረት ውሳኔን የሚያፀድቀው ፓርላማው ይሆናል

የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ ረቂቅ አዋጁ ምሕረት የሚሰጥባቸውን ጉዳዮች እንዴት እንደሚለዩ፣ የምሕረት ውሳኔ አሰጣጥና የምሕረት ቦርድ የሚቋቋምበትን ሁኔታ ይዘረዝራል፡፡

ምሕረት የአገርን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶችና በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሒደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈጸም ይልቅ፣ ምሕረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ መሆኑን የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም ለፓርላማው አስተዋውቀዋል፡፡

አቶ አብርሃም እንደገለጹት የበርካታ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ምሕረት የሚሰጠው መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ ከሚደረግ የወንጀል ድርጊት በኋላ፣ ከእርስ በርስና ከዓለም አቀፍ ጦርነት በኋላ የሚኖሩ ፖለቲካዊ ብጥብጦችንና አለመግባባቶች ለማርገብ፣ በብጥብጡ ምክንያት በተከፋፈለ ማኅበረሰብ የአገር ሰላም የማደፍረስ ድርጊት ለፈጸሙና ወደ ሰላማዊ አኗኗር ለሚገቡ ሰዎች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት የማኅበረሰቡን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ ምሕረት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ምሕረት የሚሰጥበትን ሥነ ሥርዓት በሕግ መደንገግ ስለሚያስፈልግ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት የምሕረት ቦርድ ይቋቋማል፡፡ የቦርዱ ተጠሪነትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚሆን በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

የቦርዱ አባላት ደግሞ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወከል አንድ ዳኛ፣ መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰየሙ ሁለት ሰዎች የቦርዱ አባላት እንዲሆኑ እንደሚደረግ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

የቦርዱ ሥልጣንና ተግባርም የምሕረት ጥያቄን መቀበል፣ መመርመርና የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ ይገኙበታል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅሞችን መሠረት በማድረግ በራሱ ተነሳሽነት ወይም ከክልሎች በሚቀርብ ጥያቄ መሠረት ምሕረት የሚሰጥባቸውን ወንጀሎች፣ በወንጀል የተጠረጠሩ፣ የተከሰሱ ወይም ፍርድ የተላለፈባቸውን ሰዎች ለይቶ ለምሕረት ቦርድ የማቅረብ ኃላፊነት ረቂቅ አዋጁ ይሰጠዋል፡፡

ምሕረትን በመስጠት ከግምት ውስጥ የሚገቡ ሁኔታዎችን በተመለከተም ረቂቁ መሥፈርቶችን ዘርዝሯል፡፡ እነዚህም ምሕረት የተጠየቀበት የወንጀል ድርጊት በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚያስከትለው ወይም ያስከተለው ተፅዕኖ፣ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ምሕረት የተሻለ አማራጭ ስለመሆኑና ምሕረት የሚደረግላቸው ሰዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚያሳዩት ፍላጎት ናቸው፡፡

ቦርዱ ተስማምቶበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበውን የምሕረት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተስማሙበት፣ የሕግ አወጣጥ ሒደትን ተከትሎ የምሕረት ጥያቄው የምሕረት አዋጅ እንደሚዘጋጅለትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማ እንደሚላክ፣ ፓርላማው የምሕረት አዋጁን ሲያፀድቀው ተግባራዊ እንደሚደረግ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡

ምሕረት የሚያስከትለው ውጤትን በተመለከተ በሚዘረዘረው አንቀጽ ሥርም ቅጣት ተወስኖ ከሆነ ቅጣቱ የሚያስከትለውን ማናቸውም የወንጀል ውጤቶች የሚያስቀር፣ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳልነበር ተቆጥሮ ከወንጀለኛ መዝገብ ላይ የመሠረዝ፣ የወንጀል ምርመራንም ሆነ ክስ እንዳይጀመር ወይም እንዳይቀጥል እንደሚያደርግ ተዘርዝሯል፡፡

ይህ የምሕረት አሰጣጥና አፈጻጸም ከይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ የምሕረት አሰጣጥ አዋጅ ረቂቅ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 28(1) መሠረት፣ እንዲሁም ከወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 30 መሠረት የሚፈቀደውን ምሕረት ለመስጠት ነው የተዘጋጀው፡፡

ይሁን እንጂ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ምሕረትን ከይቅርታ ጋር በማምታታት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹እስረኞችን ፈተን ከጨረስን በኋላ ለምንድነው ይህ ሕግ የመጣው? ሕጋዊ ለመምሰል ነው?›› ሲሉ ወ/ሮ ሙሉ ገብረሕይወት የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ጠይቀዋል፡፡

‹‹የፖለቲካ ሙስና ተፈጽሞ እስረኞች ከተለቀቁ በኋላ ለምንድነው ይህ ሕግ ለፓርላማ የመጣው?›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ሌሎች በርከት ያሉ አባላት የሙስና ወንጀል ምሕረት ሊሰጥበት ስለማይገባ በመሆኑም እንዲካተት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ምክር ቤቱም በስተመጨረሻ ረቂቁን ለዝርዝር ዕይታ ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...