Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢሕአዴግ ባድመ ለኤርትራ እንድትሰጥ የወሰነውን የአልጀርስ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መቀበሉን አስታወቀ

ኢሕአዴግ ባድመ ለኤርትራ እንድትሰጥ የወሰነውን የአልጀርስ ስምምነት ሙሉ በሙሉ መቀበሉን አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በትልልቅ የልማት ድርጅቶች የግል ባለድርሻዎች እንዲሳተፉ ወሰነ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማክሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2010 .ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፣ ባድመ ለኤርትራ እንድትሰጥ የወሰነው የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እንደወሰነ አስታወቀ፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አመሻሸ ላይ ባወጣው መግለጫ ከ20 ዓመታት ውዝግብና እሰጥ አገባ በኋላ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድንበር ማካለል ኮሚሽን የወሰነውንና በሁለቱ መንግሥታት በአልጀርስ የተፈረመውን ስምምነት እንደሚቀበል ይፋ ሲያደርግ ምክንያቱ ምን እንደሆነ አሥፍሯል፡፡ ‹‹በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሠራ መሆኑን መግለጽ ይፈልጋል፤›› ብሏል፡፡

- Advertisement -

 የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን አቋም በመመልከት ተመሳሳይ የሰላም ሐሳብ እንዲያራምድ ኢሕአዴግ ጠይቋል፡፡ ‹‹የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ፣ በሁለቱም ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሠራ እንጠይቃለን፤›› በማለት በመግለጫው አስታውቋል፡፡  

ኢሕአዴግ ሰፊ ሐተታ በሰጠበት በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት ጉዳይ ያወጣው መግለጫ፣ ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም፣ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች አገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል፡፡ የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት 20 ዓመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት እንዳላመጡ አስታውሷል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ አገሮች መካከል እውነተኛ ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ እንደሚያስፈልግ፣ ሁለቱ መንግሥታትም ለሕዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ መሆን እንደማይገባቸው በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል 1990 .ም. ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ‹‹በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺሕ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ የመኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱገሮች መካከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱምገሮች ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፡፡ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የሥጋት ሥነ ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፤›› በማለት የገለጸው ሲሆን፣ ‹‹በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱምገሮች ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል፤›› በማለት የጦርነቱን አስከፊነት አብራርቷል፡፡

 ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ አገሮችና አካባቢው ቀውስ መብረድና መረጋጋት፣ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ዘላቂው መፍትሔ እንደሆነም ኢሕአዴግ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እየተዳከመ የመጣውን የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አፈጻጸም፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ የገቢ ማሰባሰብ አቅም፣ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደገመገመና እነዚህን ችግሮች መፍታትም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ዜጎችን አካታች በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ለማድረግ መወሰኑን ያስታወቀው ኢሕአዴግ፣ በአገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአክሲዮን ባለድርሻነት እንዲሳተፉ መወሰኑን ይፋ አድርጓል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ተወስኗል፡፡ ለዓመታት በመንግሥት ብቸኛ ባለቤትነት እንደሚተዳደሩ አቋሙን ሲያስተጋባ የቆየባቸው ተቋማት ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች የአክሲዮኖች ድርሻቸው እንዲሸጡ ከወሰነባቸው መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ተጠቅሰዋል፡፡

በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ መንግሥት አሁንም ከፍተኛ ባለድርሻነቱን እንደሚያስጠብቅ፣ በተቀረው የአክሲዮን ድርሻ ላይ ግን የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲገቡ እንደሚደረግ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህም ከፍተኛ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን የሚያሳይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል ከተደራዳሪ አገሮች ከሚቀርቡላት ጥያቄዎች መካከል እነዚህን ተቋማት ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንድታደርግ የሚጠይቁ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገሮች መንግሥት በሞኖፖል የያዛቸውን ትልልቅ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ያዛውር በማለት ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡ 

እነዚህ ድርጅቶች ስትራቴጂካዊ በመሆናቸው ፕራይቬታይዝ እንደማይደረጉ ጥብቅ አቋም የነበረው መንግሥት፣ በድንገት ይህንን የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉ ገረሜታ ፈጥሯል፡፡ ይሁንና ቁልፍ ከተባሉት ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉን በሚመለከት በኢሕአዴግ መግለጫ አልጠቀሰም፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ የልማት ሥራዎች ውስጥ ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት ለማረጋገጥና የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል፣ በተጨማሪም ዕውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ሲባል ይህ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን አስታውቋል፡፡

የዚህ ፖሊሲ አፈጻጸም የልማታዊ መንግሥት ባህርያትን በሚያስጠብቅ፣ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራና ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፕሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንደወሰነ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...