Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መገኘትስ ቀድሞ ነው!

ሰላም! ሰላም! በምርጡ ዘመን ላይ ለተፈጠራችሁ ሁሉ፡፡ ጮማ ዘመን ይሏል ይኼ ነው፡፡ አሸዋ ዘርተው ወርቅ የሚበቅልበት፣ ትንሽ ሠርተው ብዙ የሚያጭዱበት ምርጥ ዘመን፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ቅዠት ነው ወይስ ሕልም ነው? እንደ እውነቱ ተምታትቶብኛል፡፡ ያየሁትን ፎቶ ማመን አልቻልኩም ነበር . . . ›› በማለት ሲደመም ነበር፡፡ ወዳጆቼ ጉዳዩ እኔንም እግጅ አስደምሞኛል፡፡ ባሻዬማ እንደለመዱት ወደ ቤተስኪያናቸው አቀኑ፡፡ ልጃቸውም፣ ‹‹አባዬ ደግሞ አደራህን አሰናብተኝ ብለህ እንዳትጸልይ፡፡ ከዚህ የሚበልጥ የምታየው በርካታ ነገር አለ፤›› እያለ ሲነግራቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን እሳቸው የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው አቀኑ፡፡

አንድ መኪና የሚያከራይ ደንበኛ አለኝ፡፡ ወዳጄ ከተማ ውስጥ ውር ውር ከሚሉት ቪትዞች ውስጥ ሲሶዎቹ የእርሱ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሚገርመው ሁሉንም አከራይቷቸው አንዳንዴ በታክሲ ሲሄድ አገኘዋለሁ፡፡ ታዲያ አሁንም ተጨማሪ መኪና ፈልጎ አጋዛሁት፡፡ መቼም ወርኃዊ ዕቁቡን ባጫውታችሁ ግራ ሊያጋባችሁ ይችላል፡፡ ከተማችን ውስጥ ከዚህ የሚበልጥ ዕቁብ እንዳለ አላውቅም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ስምንት ገደማ ቪትዞች ነበሩት፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ቪ ኤይት›› በሚል ቅፅል ስም ነበር የሚጠራው፡፡ ዛሬ እርስ በእርስ ተዋልደው ከቁጥር በላይ ሆነውለታል፡፡

ባሻዬ፣ ‹‹ሰውን ሰው ያደረገው ዕቁብ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ሁሉም ሰው ጦሙን አድሮም ቢሆን ቢያንስ አንድ ዕቁብ ሊኖረው ይገባል፤›› እያሉ ይመክራሉ፡፡ ልጃቸው እንኳን የሠራውን ገንዘብ ባንክ ማስቀመጡን አያምኑበትም፡፡ ‹‹ባንክ ማስቀመጥ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ባይሆን ዕቁብ መግባት ነው የሚያዋጣው . . . ›› እያሉ ይነዘንዙታል፡፡ በነገራችን ላይ ባሻዬ ዕቁብ የላቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ስለዕቁብ ሰውን ሁሉ ያበረታታሉ፡፡ እኔም ታዲያ ከባሻዬ ሕይወት ሳይሆን ከትምህርታቸው ተስማምቼ ምን የመሰለ ዕቁብ ገብቻለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ከማንጠግቦሽ ጋር ተማክሬ የአመጋገብና የወጪ ሥርዓታችን ላይ ልዩ ማዕቀብ አድርጌያለሁ፡፡

 ማንጠግቦሽዬም ብትሆን እንደ ከዚህ በፊቱ አንድ ጊዜ ቤተሰቦቼ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አየሩ፣ ቀዬው ናፈቀኝ እያለች ወጣ ማለቱን ገትታለች፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ማውጣት የለብንም፡፡ የሚመጣውን ገንዘብ ሁሉ ሰብስበን ዕቁብ እየጣልን ነው፡፡ እኔም ብሆን ሥጋ ሲያምረኝ ምስር፣ ቢራ ሲምረኝ ድራፍት፣ ድራፍት ሲያምረኝ ደግሞ ውኃዬን ጭልጥ እያደረግኩ ነው የማሳልፈው፡፡ ጓደኞቼ ሁሉ ሌሊቱን ሙሉ፣ ‹‹ምንድነው ሐሳብ ሁሌ ጭንቀት . . . ›› እያሉ አሸሸ ገዳዬ እያሉ ሲያሳልፉ ከእነሱ ጋር ተቀላቅዬ መፈንጠዝ ቢያምረኝም፣ ለማንጠግቦሽዬ የገባሁላትን ቃል አክብሬ ዕቁቤን አስቤ እያማረኝ ወደ ቤቱ አዘግማለሁ፡፡

ቤቴም ስገባ ‹ይቆጥቡ፣ ይሸለሙ› የሚል የማስታወቂያ መዓት በቴሌቪዥኑ መስኮት በኩል ይጠብቃኛል፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የሚቆጠብ ነገር ከየት ይመጣና ነው?›› በማለት ማስታወቂያዎቹን ይተቻል፡፡ ሲቀጥልም፣ ‹‹አብዛኛው ማኅበረሰብ እኮ ብዙ ሐሳብ ጥቂት ገንዘብ ብቻ ነው ያለው፡፡ ይህች ያለችውን ጥቂት ገንዘብ ደግሞ እንኳን ሊቆጥባት፣ ከወር ወር በምጥ ተይዞ ማርያም ማርያም እያለ ነው የሚያደርሳት፡፡ ባይሆን ሐሳብን መቆጠብ ቢቻል መልካም ነገር ነው፡፡ ጥሩ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ቢበረታቱና ቢሸለሙ፣ ሐሳባቸውንም የሚገዟቸው ባለሀብቶች ቢመቻቹላቸው እሰየው የሚያሰኝ ነው፤›› በማለት ይመራመራል፡፡

የወደፊቱን የደላላነት ምኅዳር ለማስፋትም ሲባል መቼም ብዙ ካሽ ይዞ መገኘት ለድርድር የማይቀርብ ትልቁ የደላላነት ምሶሶ እየሆነ እንደሚመጣ ቅድመ ትንበያዬን ለመስጠት እደፍራለሁ፡፡ በተለይ ወደፊት የሚፈጠሩትን ባለ ብዙ ሚሊዮን ብር ባለቤት የሆኑ ደላሎችን ሳስብ፣ ከአሁኑ ትንሽ ሥጋት ቢጤ በጨረፍታ ቦረሽ አድርጎኝ ያልፋል፡፡ ጉዳዩ ወዲህ ነው፡፡ አሁን አሁን እየተጀመረ ያለው የደላላነት መንገድ እንደሚያስቡት አይደለም፡፡

ለምሳሌ ደላላው አንድ የሚሸጥ ቦታ ለመደለል ገዥ ፍለጋ የሚንከራተትበትን ዘመን ሸኝቶ፣ በአዲሱ የደላሎች ዘመን ውስጥ ደላላው የሚሸጠውን ቤትም ሆነ መኪና ካሽ ከፍሎ በራሱ ቁጥጥር ሥር ያሳድረዋል፡፡ እርግጥ ነው ለዚህ በቂ ካሽ ያስፈልጋል፡፡ ዘንድሮ ደላላ ኢንቨስተር ለመሆን ሩብ ጉዳይ ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ታዲያ በካሽ የገዛውን ንብረት የሚፈልገውን ጨምሮ ለአዲስ ገዥ አክለፍልፎ በመሸጥ ከዝግ ያለፈ መገንጠል ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ ሻጩም አሻሻጩም ደላላው ይሆናል ማለት ነው፡፡ እኔም ይህንን አንድ ምዕራፍ የቀደመ የደላላነት መረብ ለመቀላቀል ነው የማገኘውን ኮሚሽን ሁሉ እየወሰድኩ ወደ ዕቁቤ የምሰንገው፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ የኢንቨስተር ወዳጅ ካላቸው ደላሎች ጋር ለመወዳደርና ለማሸነፍ፣ የግድ ይዞ መገኘት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡

መቼ ዕለት የተፈጠረው ይኼው ነበር፡፡ አንድ ቤቱን ሸጦ ወደ ውጭ አገር ጉዞ ያደርግ የነበረ ሰው ሙሉ ካሽ መስጠት ቢያቅተኝ፣ ሌሎች ባለሀብት ደላሎች ገብተው ከጨዋታ ውጪ እንዳያደርጉኝ በመሥጋት ወዲያው የቤቱን ዋጋ አንድ አራተኛ በመክፈል የባለቤትነቱን በትር ተቆጣጠርኩ፡፡ እሱን እንኳን ለመክፈል ያልፈነቀልኩት ድንጋይ አልነበረም፡፡ በመጨረሻም የባሻዬና የልጃቸውን ርብርቦሽ ጨምሮ የታሰበው ነገር ተሳካልኝ፡፡ ታዲያ ቤቱ የእኔ መሆኑን አረጋግጬ በተሰጠኝ የሁለት ሳምንት ገደብ ውስጥ አክለፍልፌ ጆሮ ግንዱን አቀመስኩት፡፡ ሌሎች ደላሎች ሲደርሱ ሁሉ ነገር አልቆ ቤቱም የደላላው አንበርብር ምንተስኖት ንብረት ሆኖ ነበር፡፡ ‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ› እንዲሉ፡፡ ይህንንም ሲያውቁ አብዛኞቹ ደላሎች በቆመጥ ወገቡን እንደተመታ ውሻ ጭራቸውን ቆልፈው ጠፉ፡፡ እኔም ብሆን የምኮራበት ድላላ ይኼ ነው፡፡ በራሴ መኩራት ጀምሬያለሁ፡፡ ታዲያ ከሥራ በኋላ ከግቡ በኋላ፣ ከሽቀላ በኋላ እንደሆነ ልብ ይበሉልኝ፡፡

እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እግሬን ሰቅዬ ጭንቅላቴን በእጆቼ ደገፍ አድርጌ ዘና ፈታ ብዬ ከተቀመጥኩ፣ የሆነ የጣልኩት ግዳይ አለ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ፈታ ብዬ በተቀመጥኩበት ነበር፣ ቤቱን ለመደለል መስመር ላይ ተገናኝተን የነበረውን ጓደኛዬን ያገኘሁት፡፡ እሱም በተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ሆኖ፣ ‹‹ቀደምከኝ አይደለም እንደዚያ የለፋሁበትን ቤት?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡ እኔም ይባስ እየተደላደልኩ፣ ‹‹ሳይሰገድብህ ስገድ የሚለውን አባባል ለዚህ ልናውለው እንችላለን፤›› እያልኩ ተራቀቅኩበት፡፡ እሱም መሸነፉን አምኖ፣ ‹‹በል አሁን ቢራ ጋብዘኝ፤›› እያለ አለቃቀሰ፡፡ ‹‹ኧረ ምን ችግር አለው ማነህ ሁለት ሳጥን ቢራ አምጣለት፤›› ብዬ ቁጭ ብሎ ቢራውን እየኮመኮመ ስለኔ ፍጥነትና ቅልጥፍና ማውራት ጀመረ፡፡

በዚህም ብቻ አላበቃም ቢራውን ልፎ እንደ ጨረሰ ለመሄድ ሲሰናዳ፣ ‹‹በሚቀጥለው ግን ቀድሜ እሰግድብሃለሁ፤›› በማለት ዝቶብኝ ከአጠገቤ ተሰወረ፡፡ ዳሩ ግን እርሱ ያልገባው ነገር እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሌላ መሬት ለመግዛት ከጫፍ መድረሴን ነበር፡፡ ከዚህ ደላላ ወዳጄ የሚገርመኝ ሌላው ነገር ሰው ሲጋብዘው አንድ በርሜል ቢራ ቢጠጣ እንኳን ወይ ፍንክች አይሰክርም፡፡ ዳሩ ግን በራሱ ገንዘብ ከፍሎ ገና ሁለት ጠርሙስ ቢራ ሲጠጣ ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ መዝፈን ይጀምራል፡፡ ዛሬም ይኼው ነው፡፡ ወዳጆቼ ቀድሞ መገኘት፣ በልጦ መገኘት፣ አሸንፎ መገኘት . . . ለድርድር ከማይቀርቡ ጥያቄዎች መካከል ዋና የምለው ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሸፍጥና ተንኮል ወይም አሻጥር በሌለበት መንገድ ወደረኞቻችንን እየዘረሩ የአሸናፊነቱን መንበር መቆጣጠር ለእኛ የተሰጠን ድርሻችን ነው፤›› ያለኝን ነገር የሕይወት መፈክር አድርጌዋለሁ፡፡ ወዳጆቼ የእኔ ድርሻ ማሸነፍ ነው የእናንተስ? ዋናው ቁም ነገር ቀድሞ መገኘት ነው አትሉም? ማን ነበር ‹‹የበላ ቀደመኝ የሮጠ አመለጠኝ› ያለው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት