Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቴሌቪዥኑን በዓይናችን እንየው ወይስ በጆሮአችን?

ሰላም! ሰላም! እኔ ምለው ምንድነው እንዲህ ቫይረስ በቫይረስ የሆነው ወሬው ሁሉ? ጉንፋን ተብዬውንማ ተውት ባናነሳው ይሻላል። መንግሥታችን የዜጎቹ በሽታ የመከላከል አቅም ማነስ መሆኑን አውቆ የፍራፍሬ መሸጫ ዋጋ ላይ ተመን ካላወጣ በስተቀር ዋጋም የለን እያልኩ ነው። ‹‹የሥጋ እንጂ መቼ የፍራፍሬው አስቸገረን?›› ሲለኝ ነበር የባሻዬ ልጅ። ጁስ መዝናኛችን፣ ቁርጥና ክትፎ መቆለፊያችን መሆኑን ዓይቶ ነዋ። ይመስለኛል ለአመጋገብና ለአለባበስ ባህል እንክብካቤና ዕድገት የቆመው ሕገ መንግሥታዊ መብት፣ ሥጋ ቤት ውሎ ስቴኪኒ ሰክቶ የሚዞረውን የልብ ልብ ሳይሰጠው አልቀረም። ታዲያ አንድ ቀልደኛ ወዳጄ ምን ይላል መሰላችሁ? ‹‹የመሰብሰብ መብት የተፈቀው ሥጋ ቤት ብቻ ነው እንዴ?›› አይገርማችሁም? ሊያያይዘኝ እኮ ነው። እኔም ተራዬን፣ ‹‹የመበተን ግዴታ ሲተገበር ያየኸው ሌላ የት ነው?›› እለዋለኋ። ማምሻም ዕድሜ ነዋ። አይደል እንዴ? እንዲያው ግን (ይህቺን ግን ብሎ ሥልታዊና ስትራቴጂካዊ በሆነ አረማመድ ቀኝ ኋላ መመለስ ስወዳት) እያደር የምሰማው የቫይረስ ብዛት አሳስቦኛል። በአዕምሮም በሥጋም በመንፈስም ላይ ሆኗላ የሚራባው ቫይረሱ። ይኼን የአፍሪካ መሪዎች በመዲናችን ተሰባስበው ዝናው በገዛ ሚዲያዎቻችን በልጧቸው ቁጭ ያለውን ዚካ የሚሉትን ቫይረስ አይደለም የማወራችሁ። ኡጋንዳ ይሁን አንጎላ ዜጎች ቆዳቸውን የሚያነጣ ቅባት ሲለቀለቁ እየዋሉ የቆዳ ችግር በራሳቸው ላይ ፈለሰፉ ሲባል የሰማሁትን ነው። ካላመናችሁ ሲኤንኤን የሚባለውን ጣቢያ ጠይቁት። ዘንድሮ መቼም ጣቢያ በመቀያየር የወሬ አምሮታችን ይረካ እንደሆነ እንጂ፣ ታራሚና ተመካሪ መሆን አቅቶናል። እናም ፈረንጅ ለመሆን ምንትስ የሚባል ቅባት አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎችን ጉድና መዘዙን ከፊል በአስተርጓሚ ከፊል በነሲብ ተረድቼ ‘ይኼ ደግሞ ምን የሚባለው ቫይረስ ይሆን?’ ስል ሰነበትኩ። ይኼኔ እኮ እንግሊዝኛ በማስተርጎሜ ‘ምኑ ፋራ ነው’ ብሎ የሚንቀኝ አይጠፋም! መቼም መናናቅ እንደ ወንዛችንና እንደ ቀዬያችን የሚጀምረው ከመተዋወቅ ነው ይባላል። ምን ይባላል ነው እንጂ። “የምን ፈራ ተባ” አሉ ባሻዬ ሀቅ ይዘው ሰው ሲሞግቱ። እንደ አለመታደል ሆኖ ቀሪው ዓለም ተዋውቆም ሳይተዋወቅም ሲከባበር እኛ ሳንተዋወቅ ተገለማምጠን፣ ስንተዋወቅ ‘ክፍ እርክስ’ ስንባባል የዕድሜ ጀንበር ታዘቀዝቃለች። በነገራችን ላይ ቀላል ልማድ ትመስላለች። ችግሯ ታዲያ ወዳጆቼ፣ ይኼው የምታዩት አለመግባባትና አለመደማመጥ ሁነኛ መሠረት እሷ መሆኗ ነው። ፖለቲከኛው ሲፖተልክ አይደመጥ፣ ጋዜጠኛው ሲተነትን አይደመጥ፣ መምህሩን ተማሪው አይሰማው፣ ተማሪውን መምህሩ ዞሮ አያየው፣ ሴቶች አይደመጡ፣ ወንዶች አይደመጡ . . . ምኑ ቅጡ! ለምን? ተዋወቅንና ተናናቅና! ‹‹እህ መቼ ነው ‘እኔ ማውቀው አለማወቄን ነው’ ብሎ የአገሬ ሶቅራጦስ የሚነሳው?›› ብዬ የባሻዬን ልጅ አዋየኝ ስለው ‹‹የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ከተዘጋ አልቆየም እንዴ?›› ብሎ እሱ እኔን መጠየቅ። ‹‹እኔ ምን አውቃለሁ›› ስለው ‹‹ለነገሩ በሶቅራጥስ ጊዜ ዩኒቨርስቲ አልነበረም።›› አለኝ ጥልቅ ሐሳብ ውስጥ እየዋኘ። ነገሩ ገብቶኛል። ‘ዛሬ በአለባበስና በዩኒቨርሲቲ ራሳችንን በበቂ ሁኔታ በቻልንበት ዘመን እንዴት ይኼን ይኼን የሚያስገነዝብ የኅብረተሰብ ሳይንስ ምሁር ይጠፋል?’ ለማለት እንደሆነ ገብቶኛል። ነገርማ ብዙዎቻችንን ቶሎ ይገባናል እኮ። ትምህርት የማይገባን የበዛው ነገር ቦታውን ይዞበት ይሆን ታዲያ? እውነቴን እኮ ነው። ሁሌ በብዛትና በጥራት እየተጨቃጨቅን በነገር ተዋውቀን በነገር እንደተናናቅን ልንቀር እኮ ነው። እስኪ አንዳንዴ ያልተጠየቀም እንጠይቅ ጎበዝ። ነው ጥያቄም መኮረጅ ማርክ ያሰጣል ዘንድሮ? ወይ ነዶ! እናላችሁ ሰሞኑን ከአንዲት ምስኪን እናት ጋር የቪትስ ዋጋ ሳነፃፅር ነበር የነበትኩት። ‹‹እነዚህ ሲያዩዋቸው ጨርቅ የለበሱ የሚመስሉ ቪትዞች ይሰነብታሉ ግን?›› ይሉኛል ዓይን ዓይኔን እያዩ። ‹‹አይ እማማ። በጥሩ ሁኔታ ካልተያዘ እንቁላልስ መቼ ይሰነብታል?›› እላለሁ ‘ትቼዋለሁ’ እንዳይሉኝ ሰግቼ። ‹‹እሱስ ልክ ነው….›› ብለው ሲቆዝሙ ‘ለማን ለምን’ መኪኖቹን እንደሚገዙ አወጣጣቸው ጀመር። ‹‹ይኼውልህ ትንሹ ልጄ ገና ኮሌጅ እንደገባ ‘ማሪዋና’ ነው የሚሉት? . . . ብቻ ጭሳጭስ ለምዶ ይህቺን አከለ። ተው ብል ማን ሰምቶኝ? ሽቅብ ያዩሃል የዘንድሮ ልጆች። እያደር ስሜቱ ሁሉ ቀዘቀዘ። ትምህርቱን ተወው። ያልወሰድኩበት ሐኪም ያልወሰድኩት ፀበል የለም። አሁን ምን እንደነካው ሳላውቅ ተለውጦ ሁለት ‘ቪትስ’ ግዢልኝና እያከራየሁ ልደግ አለኝ። ድንግሊቷ ፀሎቴን ሰማች። ይኼው ውጭ ያሉ ወንድሞቹን ሙሉልኝ ብዬ ካንተ ጋር እንከራተታለሁ፤›› ሲሉኝ ቅስሜ ተሰበረ። የምለው ጠፋኝ። ‹‹የወለደ . . .›› ብዬ ብቻ ዝም። እንዲህ ብዬ ሳቀረቅር፣ ‹‹ምነው ግን ልጄ ካልጠፋ ነገር የትውልዱ መጠመጃ ጭሳጭስ ሆነ?›› ብለው አፈጠጡብኝ። የአቅሜን ያህል ተጣጥሬ ሻል ባለ ዋጋ ያልተጫሩና ያልተኮረኮሙ ሁለት ቪትዞች አጋዝቻቸው ስንለያይ አንጀቴ ተንቦጫቦጨ። ሄጄ ለባሻዬ እንደ ወትሮው ውሎዬን ሳጫውታቸው፣ ‹‹በአገር የመጣ ነው አንበርብር…›› ብለው ይባስ ቅስሜን አያነክቱት መሰላችሁ? ‹‹ታደያ ምነው አገር አልሰማው አገር አላወራው?›› ስላቸው፣ ‹‹ገመና እንዴት ይወራል አንበርብር? ያውም የልጅ? ምንም ቢሆን ሥጋ ሥጋ ነው። ስንቱ ነው በልጁ የተገኘ? ነፃነትና ልቅነት መለየት እስኪያቅተን ድረስ ተቀላቅለውብን ስንቱ ነው የሚሸነግልበት? የሚሸልምበት ያጣ? ጥርሱን ነክሶ ልጁን በቁም የቀበረ? ስንቱ?›› እያሉ አላቆም አሉ። ይኼን ብሶት ማጠራቀም ትተን ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ የምንዘምትበት ጊዜ ቅርብ ይሆን? ወየው በሆነ! እንዲሁ ስገረም፣ ነፍሴ ስትገነዝ፣ ስቆጣ፣ ስለዝብ፣ ሳሻሽጥ፣ ሳለዋውጥ፣ ሳከራይ እየዋልኩ ፀጉሬ ማደጉን አላስተዋልኩም። ማንጠግቦሽ ‹‹ኧረ ሽፍታ መሰልክ ተቆረጠው፤›› ስትለኝ ጊዜ እንደማይሰጠው ገባኝ። ይገርማችኋል ማንጠግቦሽ ፀጉሬና ፂሜ የልማዱን ከፍ ሲልና በጣም ሲያድግ ተመሳሳይ አነጋገር አትጠቀምም። እንደ ነገሩ መዘዝ መዘዝ ሲል፣ ‹‹ምነው አንበርብር ይኼን ፂምህን እኔ እያስታወስኩህ ባትላጨው?›› ነው የምትለው። በጣም ሲያስቀይማት ግን ‘ሽፍታ’ የምትለዋን ቃል አውቃ ትጠቀማለች። እኔ ደግሞ በሽፍታና በኪራይ ሰብሳቢነት እንዳልታማ በእጅጉ የማደርገውን ጥንቃቄ አሳምራ ታውቃለች። መቼም በደካማ ጎናችሁ አንዴ አለመገኘት ነው። ነገሩን ካነሳሁት አይቀር ስስ ብልታችን እየነካኩብን እንዳሻቸው የሚቀልዱብን መብዛታቸውንም ልጠቁም። እኛም ታዲያ ‹‹አንዱን በቴስታታ አንዱንም በካልቾ ነበር ልማዳችን፣ ሚስት አገባንና ልጆች ወለድንና ፈሰሰ አሞታችን…›› ብለን እጅ ሰጠን። ታዲያ እንዳልኳችሁ ማንጠግቦሽ ‘ሽፍታ’ የሚሉትን የማልወደው ቃል ስለተጠቀመች እጅ ሰጥቼ የዘወትር ፀጉር ቆራጭ ደንበኛዬ ዘንድ ስሄድ፣ ‹‹መብራት የለም›› ብሎ ጥፍሩን ሲቆርጥ ደረስኩ። ዛሬማ በመቀስም ቢሆን አስመድምጄው አድራለሁ እንጂ እንዲህ ሆኜ አልመለስም እያልኩ በጄኔሬተር ኃይል ነፍስ ወደ ዘራ ‘ሞል’ ዘው። ምን እንደነካኝ አላውቅም። የፀጉር ማስተካከያ ቤት ፈላልጌ አገኘሁና ‹‹ፓንክ›› አልኩት ቆራጩን። በሦስት ቁጥር መድምዶኝ ሲያበቃ ጨርሻለሁ ብሎ ሰላሳ ዓይነት ቅባት ቀባብቶ ውረድ አለኝ። የደንበኛዬ እጅ ይግደለኝ እያልኩ ማጠሩን ብቻ አይቼ ሒሳብ ስል ‹‹ሁለት መቶ ብር›› ተባልኩ። ‹‹የባሕታዊ ፀጉርም ይኼን ያህል አይከፈልበት?›› ከማለቴ ‘ቶንዶሱ ሪል የጃፓን ስሪት፣ ቅባቶቹን ቀጥታ ከአሜሪካ የምናስመጣቸው፣ ወንበሩ የጣሊያን’ ተባልኩ። እኔም የአንድ ፈረንጅ አገር ፀጉር እስካበቅል ምን አደርጋለሁ ብዬ ከፍዬ ወጥቼ ሄድኩ እላችኋለሁ። ያለ ሠፈራችን እያሳደደ የሚጫወትብን መብራት እንደሆነ መቼ አጣነው አትሉም! በሉ እንሰነባበት። ሰሞኑን የአፍሪካ መሪዎች ሲገቡና ሲወጡ አልነበር? ‹‹መውረድና መውጣት ላይ እንጂ መግባትና መውጣት ላይ ችግር የለባቸውም፤›› ያለኝ ማን ነበር እባካችሁ? ብቻ ሎቤድ አሻሻጬ ስለነበር ‘ኮሚሽኔን’ ተቀብዬ ወደ ቤቴ ስጓዝ መንገድ ተዘጋ። ወዲያው ሁለት ፖሊሶች የእግረኛ መንገዱን ዘግተው ‹‹ባላችሁበት›› የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡ። ‹‹ምን ገዶን›› ብለን በተለመደው ጨዋነትና እንግዳ አክባሪ ባህላችን መሠረት ትዕዛዝ ተቀብለን ቆምን። አንዳንዱ ሳይታዘዝ አለመቆሙም ሲያበሳጨው አይቻለሁ። የሆነ ግንብ ነገር ተደግፌ ዙሪያዬን መቃኘት ጀመርኩ። ከማያቸው አንዱ፣ ‹‹ለእንግዶቻችን በትዕዛዝ ምርጥ በለጬ ያሉበት ድረስ እናደርሳለን›› የሚለው ጽሑፍ ነው። አጠገቤ የቆሙትም አንብበውት ኖሮ፣ ‹‹ጭራሽ! ሳይቅሙ አርባ ሃምሳ ዓመት እየገዙ መርቅነውማ ሁለት መቶ ዓመት ይለቁልናል?›› ይላል አንዱ። ‹‹ኧረ ደንበኞቹን የሚመለከት ማስታወቂያ እንጂ ገዢዎቻችንን አይመስለኝም፤›› ይላል ሌላው። ‹‹በቃ አገሩ ጫት ቤት ብቻ ሆኖ ቀረ?›› ስትል ከወዲያ ግድም፣ ‹‹ምክር ቤቱም፣ መሥሪያ ቤቱም፣ ከፍተኛ ትምህርት ቤቱም እንቅልፍ እንቅልፍ ሲል በማን ይፈረዳል?›› ይላታል አጠገቧ የቆመ። ደግሞ ዘወር ስል ጠባብ በረንዳ ያላት ካፍቴሪያ ጢም ብሎ ለተሰበሰበ ደንበኛ ሰብስባ ሻይ ቡና ስትጋብዝ አስተውላለሁ። ‹‹የምር ግን ቤታችን ሻይ ማፍላት እያቃተን ነው ካፍቴሪያ እየተሰበሰብን በትኩስ ነገር የዛልነው?›› ይላል አንዱ። ‹‹የመሰብሰብ መብታችንን የሚጋፋ ጥያቄ ይመስላል፤›› ትለዋለች ዘንካታ ወጣት ፈገግ ብላ። ‹‹ከሥራ ሰዓታችን የሻይ ሰዓታችን አበዛዝ?›› ይላል ሌላው። ‹‹አይ አፍሪካ! በመሰብሰብና በመቀመጥ ቢሆን ይኼኔ ማን እንደኛ!›› ሲል ቆንጂት ተቀብላ፣ ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው ሲባል አልሰማህም?›› አለችው። መንገድ ተለቆ መጓዝ ተፈቀደልን። እኔ በልቤ፣ ‹‹የተቀማጭ ዕድሜው ስንት ነው?›› እያልኩ ሳሰላስል፣ ‹‹ዕድሜ ዘልዛላው ስንቱን ያሳየናል…›› የሚል ወፈፌ ከሩቅ ይሰማኝ ነበር፡፡ አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ዕድሜ የፈጣሪ ፀጋ ነው፡፡ ዘልዛላውማ እኛ ነን እንጂ…›› እያለ ብቻውን ሲያወራ ሰማሁት፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኧረ ሰሞኑን በዚህ በዛገ ቴሌቪዥን ጣቢያ የምናየው ምንድነው? በዓይናችን እንየው ወይስ በጆሮአችን?›› ሲል ጉድ ነው ከማለት ሌላ ምን ይባላል? ሌላው ደግሞ መልሶ፣ ‹‹ይኼ ሃምሳ ዓመት ሞላኝ እያለ የሚለፍፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ከቀድሞ ገዢዎች መዳፍ ተላቆ የዴሞክራሲ ተምሳሌት፣ የሕዝብ ብሶት ማስተጋቢያና የሕዝቡ አንጡራ ሀብት ሆኗል ሲባል፣ ኧረ ቀልድ አቁሙ የሚል ይጥፋ? ወይስ ዓይንና ጆሮአችን ሥራ አቁመዋል?›› ሲባል ደግሞ ሳቄ መጣ፡፡ ይኼንን ሁሉ የሚሰማውስ ዓይን ነው ጆሮ ነው? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት