Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውኃ በወንፊት!

እነሆ መንገድ። ከመገናኛ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። የሆነ ሐሳብ አርግዘን በክፉና በደግ ምግባር እየተመደብን እንዲሁ ከመዋለል ሳናርፍ ወደየታዛችን እንሯሯጣለን። “አንተ ይኼን ሁሉ ሰው አጉረህ ኋላ ነግሬያለሁ፤” ይላሉ አንዲት ጠና ያሉ ተሳፋሪ። “ግድየለም ቀለል ያለ የእንቅቅልሽ ጥያቄ አለ። እሱን ለመለሰ ሦስት ተሳፋሪ ነፃ ነው፤” ይላቸዋል ወያላው። “እኛ ነፍሳችንን አልንህ እንጂ ገንዘብ ማውጣቱን መቼ እንቢ አልን?” ወይዘሮዋ አንዴ ወደ ተሳፋሪው አንዴ ወደ ወያላው እያስተዋሉ ተናገሩ። “ዘንድሮ እኮ ነፍስም ብትሆን ያለገንዘብ ዋጋ አልኖራት ብሏል። ይልቅ የመጀመሪያው ጥያቄ ለእርስዎ ነው፤” ብሎ ሊጀምር ሲል፣ “ኧረ እዚያው። የኑሮዬን እንቆቅልሽም ፈትቼ አልጨረስኩም፤” ብለው አሽሟጠጡ። “ኑሮ እና ህልምማ እንደ ነዋሪውና እንደ አላሚው ነው የሚፈታው፤” ብሎ ወያላው ሳይጨርስ ወደ መሀል መቀመጫ ተጣብቆ የተቀመጠ ወጣት “ምን ዋጋ አለው በሰው እንጀራ ጣታቸው የሚወጡ አላስቀምጥ አሉ፤” አለው።

“የምን እንጀራ አመጣህ ወንድም? ማን ነው ደግሞ በግዢ እንጀራ ጣቱን የሚያወጣው?” ብሎ ከጎኑ የተሰየመ ተሳፋሪ ጠየቀው። “ተገዛ ተጋገረ እንጀራ ያው እንጀራ ነው። ምን ልዩነት አለው?” ብሎ ወጣቱ መልሶ ቢጠይቀው፣ “አለው እንጂ። ሳይጋግሩ መብላት ተበድሮ እንደ መገንባት በለው። ስትጋግር እኮ ሌማት ሙሉ ነው። መቼም ለአንድ እንጀራ የሚሆን የሚያቦካ ሞኝ መሆን አለበት፤” ብሎ ከወጣቱ አጠገብ የተሰየመው ማለት የፈለገውን አለ። ይኼኔ ወይዘሮዋ፣ “በል ልጄ ያንተ እንቆቅልሽ ምንድነው? ዓይኑ የጠፋ እንጀራ እየጋገሩ በጨለማ ልቦናችንን ከሚያጨልሙትስ ያንተ ሳይሻል አይቀርም፤” አሉት። “ጫፍ ወራጅ ነን ሲሏት ተሻግሮ ግብር ብሉ ያለችው ማን ነች?” ከማለቱ ሦስተኛው ረድፍ ከአጠገቤ የተሰየመች ድምፀ መረዋ “ትራንስፎርሜሽን ነቻ፤” ብላ ከትከት። ወይዘሮዋ፣ “በል ተተው…” ብለው ዝም፡፡ የትራንስፎርሜሽ ጊዜ ሲሆን ግን ሰው ጫፍ መውረድ የሚያምረው ለምንድነው?

ተንቀሳቅሰናል። “እስኪ ድምፁን ከፍ አድርገው፤” ይላል ከሾፌሩ ኋላ ከወይዘሮዋ አጠገብ የተሰየመ ጎልማሳ። በደቡብ አሜሪካ አገሮች ስለተከሰተው አዲሱ የዚካ ቫይረስ ሕመም ሀተታ ይደመጣል። “ጉድ ነው ዘንድሮ። ደግሞ ብሎ ብሎ ሌላ ቁጣ በነፍሰ ጡሮች መጣ?” አሉ ወይዘሮዋ። “ኧረ ቁጣ አይደለም ቫይረስ ነው፤” ይላል ወያላው። “አንተ አታምጥ። ምኑን ታውቀዋለህ? ምናለበት ይኼን ይኼን ለእኛ ለአጠባነው ብትተውልን?” ሲሉት ተሳፋሪው ተሳሳቀ። “ይተውት እማማ። የሚጋፋበት ጋሻ መሬት ቢያጣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትንሽ ትልቁ ሐሳብ መጋፋት ስለጀመረ ነው፤” አለቻቸው መሀል መቀመጫ ላይ ሦስተኛ ተደርባ የተቀመጠች ተሳፋሪ። “እንዴት ሆኖ? ሰው በአገሩ የእኔ የሚለው መሬት አጥቷል ነው የምትይኝ?” ወይዘሮዋ ከፊል ወደኋላ ተጠማዘዙ።

“ኧረ ዝም ብላ ነው። ያጣም አለ፣ ያገኘም አለ። መቼም ምን ሲያደርግ አጣ? ምን ሲያደርግ አገኘ አይሉኝም፤” አላቸው ጥጉን ይዞ የተኮራመተው ወጣት። “እሱንማ እንዴት እጠይቅሃለሁ ልጄ? እንዲያው ይኼን ያህል የግፊያ አምሮቱን ማብረጃ እስኪያጣ ድረስ ሐሳብ መጋፋት ላይ መድረሱ ገርሞኝ እንጂ፤” ብለው ወደ ወያላው ዞሩ። “ይኼ የመረጃ ዘመን አሰስ ገሰሱን እየከመረብን ስለተቸገርንም ነው። ምን እኮ በእውቀትና በመረጃ መሀል ያለው ልዩነት ተሳክሮብናል፤” ብሎ እንዳበቃ፣ “ልክ በማወቅና በማስተዋል መሀል ያለው ልዩነት እንደተሳከረብን?” ብለው አንጀታቸው ቅቤ መጠጣቱን በድምፀታቸው አወጁ። “እንዲያው እኛ አገር የሚገባው ሥልጣኔ ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚሆንብን ለምን ይሆን?” ብለው ከአፍታ በኋላ ቢጠይቁ አጠገቤ የተሰየመችው በስርቅርቅ ድሜጿ፣ “እንጃ ወንፊታችን መቼ እንደተቀደደ፤” አለቻቸው። ብቻ አጣሪ ኮሚቴ ይቋቋምለት እንዳይባል እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው!

“ይኼው ይኼ ጽንስ እንደተወለደ የሚገል አልያም የጭንቅላት መጠኑን አሳንሶ የልጁን ጤንነት እስከ ዕድሜ ልክ የሚያጓድል ቫይረስ ወሬ ሰምታ፣ ባለቤቴ ለመጪው አምስት ዓመት ልጅ አንወልድም አለች። ታሪክ እኮ ነው እናንተ፤” ብሎ ወደ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ወጣት ገመናውን ዘከዘከው። “እንዴ! አምስት ዓመት? የገዢውን ፓርቲ አባል ስታገባ ገና ይኼ እንደሚመጣ ማወቅ ነበረብህ፤” ብላ ከጎኔ የተሰየመችው ንቁ ተሳታፊ አፋፋመችው። “ኧረ የእኔ ሚስት እንኳን ፖለቲካ ውስጥ ልትነካካ የፐ ዘሮችን ተጠቅማቸው አታውቅም፤” አለ በምስኪን ድምፅ ዱብ ዕዳ የወረደበት። “ታዲያ አንተ ምን አልካት?” ሲለው ከጎኑ የተሰየመው፣ “እኔማ ያው ቫይረሱ ገና አትላንቲክን እንዳላቋረጠና እኛን እንደማያሰጋን ሚዲያ ላይ የሰማሁትን ደጋግሜ ነገርኳት፤” ብሎ ለወያላው ታሪፉን እጁን ትከሻዬን ላይ አስመርኩዞ አሻግሮ ከፈለ።

“ታዲያ እሷ ምን አለች?” አለው መልሶ። “ድርቅ አለች፤” ከማለቱ በቃ “ተወው ወንድሜ። ተደብቃህ አባል ሆናለች ማለት ነው፤” ብሎ ጎማ ላይ ተሳቆ የተቀመጠ ተሳፋሪ አስደነገጠው። “የምን አባል?” የሚስቱ አቋም አስጨንቆት የሚያስጨንቀን ተሳፋሪ በድንጋጤ ሲጠይቅ፣ “የዓለም ጤና ድርጅት አባል እንበልህ? ጨቀጨቅከን አቦ!” ብሎ ከጎኑ አሸማቀቀው። “ይኼማ ደስ አይልም። ምነው ቢጨንቀው እኮ ነው የሚያዋየን፤” ነገር ሊያለዝቡ ወይዘሮዋ መሀል ሲገቡ፣ “ምነው ባለቤቱስ ብትሆን ስንት አጠገቧ ያለ የሚያሳስብ ችግር እያለ አኅጉር ተሻግራ በሰው ችግር ለእኛ መትረፍ አለባት እንዴ?” አለቻቸው አጠር ቀላ ያለች የደስ ደስ ያላት ከመጨረሻ ወንበር። “ባለችግሮቹ ለችግሩ የሰጡት ትኩረትና ለዜጎቻቸው ደኅንነት ያሳዩት ተነሳሽነት ቦታን እስከመርሳት አድርሷት ይሆናላ፤” ብሎ አረፈዋ ጎልማሳው። ከበሽታና ከችግሩ ብዛት የአስታማሚ እንክብካቤ ናፋቂዎች ባንበልጥ ለነገሩ ስለስደት እልፍ ዘፈን ባልተቀዳን ነበር!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው በሞባይሉ መብራት እየታገዘ መልስ ያድለናል። “ኧረ ይቆጥርብሃል ብዙ አትጠቀም፤” ይለዋል አንዱ። ወያላው “እኔን ነው?” ይጠይቃል። “ለአንተም ለሞባይልህም የተላለፈ መልዕክት ነው። ቴሌ ካልጻፈው በቃ መልዕክት አናነብም ማለት ነው?” ይላል መጨረሻ አካባቢ ሌላው። “ምነው የእናንተ ቤት አከራይ ቴሌ ነው እንዴ መብራት አጥፉ ብሎ የሚልክባችሁ?” ጎልማሳው ነገሩን ወዳመጣው ተሳፋሪ ዞሮ ጠየቀ። “እሱስ ለጨዋታ አልኩኝ እንጂ ሁላችንም በየቤታችን መብራት እልም ሲል አድብቶ ነው፤” ብሎ ማለት። “አድብቶ ስትል?” ብላ ከጎኔ ያለችው በጥያቄ ማፋጠጥ። “ልንጋግር ስንል፣ ገና ቁሌት ስናቁላላ፣ ሞባይላችን ቻርጅ አድርጉኝ ከማለቱ፣ ወዘተ ነዋ…፤” አላት። “ይቅርታ አድርግልኝ አሁን ከጠቀስካቸው ነገሮች ሁሉ አድብቶ የሚያስብል ነገር አላገኘሁም፤” አለው ከወደ ጋቢና።

“እንዴ መብላት የህልውና ማገር እንደሆነ ለማስመስከር ተደራጅተን እናብስል? ዘንድሮ እኮ የተናጠል መብት አላዋጣም ጎበዝ፤” አለ ሰውዬው። “ስንቱ የመብራት መቆራረጥ ንግዱንና ሥራውን እያስተጓጎለበት ግፋ ቢል ፌስቡክ ከፍቶ የሚፈዝበት ስልኩ ቻርጅ ሲጨርስ መብራት ሄደብኝ ብሎ ሰው የአገሩን ገመና አጋልጦ ይሰጣል?” ስትለኝ ከጎኔ ሰውዬው ሰምቷት ኖሮ፣ “እሱስ ልክ ነሽ። ከመብራት መቆራረጡ በላይ እርስ በርሳችን የጋራ ችግራችንን በተመለከተ የአቋም መዋዠቅና መቆራረጥ እያለብን እኔም ሰው አገኘሁ ብዬ ይኼን መናገር አልነበረብኝም፤” ብሎ በነገር ጎሸማት። እንዲህ ተፋጠን መሽቶ እየነጋ የኃይል መቆራረጥ ችግር በአንድም በሌላ ካላቆራረጠን እንላቀቃለን ታዲያ? “ደግሞ ይኼን ሰምታችሁ መስመሩን ቆራርጡት አሉዋችሁ፤” ሲሉ የምንሰማቸው ወይዘሮዋን ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንዱ ስማርት ፎኑን ቦግ አድርጎ አብርቶ የሆነ ነገር እያየ ይስቃል። አጠገቡ የተቀመጠች እንስት፣ “እኛም እንሳቃ?” ትለዋለች። “አንዱ ምን ብሎ ፖስት ቢያደርግ ጥሩ ነው? ‘ነፍሰ ጡር ሚስቴ ካልጠፋ ነገር ስብሰባ አማረኝ ትለኛለች። እባካችሁ ጥሩ የስብሰባ ማዕከል ጠቁሙኝ።’ እውነት ይሁን ውሸት እንጃለቱ፤” ይላታል። “እውነቷን ነው። የሥራ ሰዓት በስብሰባና በግምገማ እየተቃጠለ ሙሉ ደመወዝ በሚገኝባት አገር ከዚህ በላይ ምን ሊያምራት ይችላል?” አጠገቤ ያለችው ጮኸች። “የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ይዘሃት ሂድ አትለውም ታዲያ? ምን ትጠብቃለህ?” ይላል መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት አንዱ። “አሪፍ ሐሳብ። እንዲያውም የዘንድሮው ስብሰባ መሪ ሐሳብ ሴቶች ላይ አነጣጥሯል እየተባለ ነው። ግን ብቻ?” ከወይዘሮዋ ጎን የተሰየመችው ወጣት በእንጥልጥል ተወችው። “ጨርሺው እንጂ” ሲሏት ወይዘሮዋ፣ “አልወለድም ቢልስ ልጁ?” ብላን አረፈችው።

“ድርሰት አረግሺው እንዴ? ጽንስ እኮ ነው፤” ጎልማሳው የሚላት ጠፍቶት። “ምን ይታወቃል? ትናንት ድርሰት ነው የተባልነው ዛሬ ገሃድ ሆኖ እያየን ነው። እንዲያው ብቻ ከመሪዎቹ ስብሰባ ላይ እናቱ በሆዷ ይዛው ሲታደም የሚሰማው ነገር ቢያስደነግጠው . . . ማለቴ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ተጎትቶ ቢሰማ አፍ አውጥቶ አልወለድም ሊል ይችላል። ያለፉት ወራት ብዙ ሺሕ የአፍሪካ ልጆች በረሃ አቋርጠው በሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ የሚገጥማቸው አስከፊ ነገር በካሜራ ሲቀረፅ ሰንብቷል። ስደትን ምርጫው ያደረገ ትውልድ በዚህ አኅጉር ላይ ተነስቷል። ከዚህ የበለጠ የሙሉ ጊዜ መወያያ ችግርና ሁሉን ዳሳሽ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ አይኖርም። መፈክሩም ‘ስደት ይቁም ስደት ይብቃ አፍሪካን ለአፍሪካውያን’ ወዘተ ሊሆን በተገባ ነበር። አይደለም? በፆታም ሆነ በምንም ነገር ከመከፋፈላችን በፊት እኮ ማናችንም ሰው መሆናችን ይቀድማል። ታዲያ ይኼ አልወለድም አያስብልም ያስብላል?” ብትል መልስ አጣን። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። ከፈረሱ ጋሪው በቀደመባት አኅጉር አልወለድም! የሚል ድምፅ ሰማሁ ልበል ወይስ ጆሮዬ ነው? ውኃ በወንፊት ሆነ እኮ ነገሩ! መልካም ጉዞ!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት