Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ክቡር ሚኒስትር በቅርቡ ታስረው ከተፈቱ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ወጣት ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]

 • እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ዊኬንድህ እንዴት ነበር?
 • እንደዚህ የሚያናድድ ዊኬንድ አሳልፌ አላውቅም፡፡
 • ምነው በእስረኞቹ መፈታት አልተደሰትክም እንዴ?
 • የእስረኞቹ መፈታት እንኳን አይደለም ያናደደኝ፡፡
 • ታዲያ ምን ሆነህ ነው? የመብራቱ መቆራረጥ ነው?
 • ኧረ ቤቴ ጄኔሬተር ስላለኝ እሱም ብዙ አያስጨንቀኝም፡፡
 • ምንድነው ታዲያ ያበሳጨህ?
 • ቅዳሜ አመሻሹን ወደ ከተማ አልወጡም ነበር?
 • ኧረ ትልቁ ሆቴል አካባቢ ነበርኩ፡፡
 • ያ ሁሉ ሕዝብ ተገልብጦ መውጣቱን አላዩም ነበር?
 • ባለሀብቱ ተፈቱ እንዴ?
 • ኧረ የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ነበር፡፡
 • አንተ ታዲያ ምን አበሳጨህ?
 • ሊቨርፑል ላይ የተሠራውን ግፍ አላዩትም?
 • አንተ የሊቨርፑል ደጋፊ ነህ እንዴ?
 • አይ እኔ እንኳን ደጋፊ ሆኜ ሳይሆን፣ የተሠራው ግፍ ስላናደደኝ ነው፡፡
 • የምን ግፍ ነው?
 • ሊቨርፑሎች የተጫወቱት በጣም ማራኪ ኳስ ነው፡፡
 • ጨዋታቸው በእርግጥ ይማርካል፡፡
 • በዛ ላይ ደግሞ ቡድኑ በወጣት ተጫዋቾች ብቻ የተገነባ ነው፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • ማለቴ እንደ ሳላህ ዓይነት ማራኪ ጨዋታ የሚጫወት ተጫዋች በእነ ራሞስ ግፍ ተሠርቶበት ሲወጣ አያናድድም?
 • ስማ ራሞስ አንጋፋ ተጫዋች መሆኑን አትርሳ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ራሞስ በሸርና በተንኮል የተሞላና ጡረታ ሊወጣ የሚገባው ተጫዋች ነው፡፡
 • ስማ ለእኔ ደግሞ ጀግናና ክለቡን ለዘመናት እየታደገ የሚገኝ ተጫዋች ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ወጣቱ ሳላህ የሚጫወተውን ጨዋታ አይወዱትም?
 • ስማ እንደ እሱ ዓይነት ሕዝበኛ ተጫዋች መጨረሻው አያምርም፡፡
 • እንዴ ክቡር ሚኒስትር ሳላህ እኮ ኳስን ጥበብ አድርጎ ብዙዎችን የሚያስደስት ተጫዋች ነው፡፡
 • ራሞስ ደግሞ አርቆ ዓላሚ በመሆኑ ክለቡን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡ ዋናው ደግሞ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው ቁምነገሩ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የአገራችን ፖለቲካ ችግርም እኮ ይኼ ነው፡፡
 • እንዴት?
 • የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን እንደ እርስዎ ዓይነቱ ይዞ አለቅም እያለ ነዋ፡፡
 • ኳስና ፖለቲካ ምን አገናኛቸው?
 • ይገናኛሉ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፣ ይኸው ለእኛ ለወጣቶቹ አለቅ ብላችሁ የሙጥኝ ብላችኋል፡፡
 • ስማ ኳስና ፖለቲካ ይለያያሉ፡፡
 • በነገራችን ላይ የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ከጨዋታው በኋላ የተናገሩት ነገር አለ፡፡
 • የተሸናፊ ቡድንማ ሁሌ እንዳወራ ነው፡፡
 • ራሞስ ለዚህ ቆንጆ ጨዋታ ካንሰር ነበር ብለዋል፡፡
 • ተሸናፊ ብዙ ሊያወራ ይችላል፡፡
 • በነገራችን ላይ ለአገራችን ፖለቲካም እናንተ አንድ ነገር ናችሁ፡፡
 • ምን?
 • በሽታ!

[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን ቢሯቸው ያስጠሩታል]

 • እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ለምኑ?
 • ለግንቦት 20 ነዋ፡፡
 • በዓሉን እንዴት አሳለፍከው?
 • በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ነው ያሳለፍኩት፡፡
 • ደስ በሚል ሁኔታ ካሳለፍከው አንዳንድ ጥያቄዎች ልጠይቅህ፡፡
 • የምን ጥያቄ ነው?
 • ጥያቄ ሳይሆን ፈተና ነው የምፈትንህ?
 • እንዴ ሳልዘጋጅ የምን ፈተና ነው?
 • ይኼ ልክ እንደ ፖፕ ኩዊዝ ነው፡፡
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ አንተ ራስህን ፈልገህ አግኝተሃል?
 • በየቀኑ ነዋ ራሴን ፈልጌ የማገኘው፡፡
 • ምን ማለት ነው?
 • ከእርስዎ ጋር መሥራት ማለት በራሱ ራስን ማግኘት ማለት ነው፡፡
 • አልገባኝም?
 • በየቀኑ ስለኢትዮጵያ ህዳሴ፣ ስለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ስለልማታዊ መንግሥት ሲነግሩኝ ራሴን እዛ ውስጥ እያገኘሁት ነው፡፡
 • አንተ በሚገባ ገብቶሃል ማለት ነው፡፡
 • በሚገባ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እሺ ከተጣላኸው ጎረቤትህ ጋር ታረቅህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ራሱ እንዳጠፋ ባውቅም ይቅርታ ልለው ቤቱ ድረስ ሄጃለሁ፡፡
 • ታዲያ ታረቀህ?
 • እኔ እንደ መንግሥት ነው አቋሜ፡፡
 • እንዴት ማለት?
 • መንግሥት ከአንዴም ሁለቴ ለኤርትራ መንግሥት የእርቀ ሰላም ጥሪ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ግን መንግሥት አሁንም ጥረቱን አላቆመም፡፡
 • ስለዚህ አንተም ጥረትህን ትቀጥላለህ?
 • በሚገባ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • የታሰሩና የታመሙ ሰዎችን ትጠይቃለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከፈለጉ ቂሊንጦ፣ ከፈለጉ ዝዋይ፣ ከፈለጉ ሸዋሮቢት ሄደው ለጠባቂዎቹ ፎቶዬን ቢያሳዩዋቸው በደንብ ነው የሚለዩኝ፡፡
 • ታማሚስ ትጠይቃለህ?
 • እስቲ ሌላ አስታማሚ ይግባ እስክባል ድረስ ነው ሆስፒታሉን የማጨናንቀው፡፡
 • አንተ በጣም ልዩ ሰው ነህ ማለት ነው፡፡
 • ምንም አይጠራጠሩ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ለመሆኑ ታነባለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከአዲስ ራዕይ እስከ ዮሐንስ ራዕይ ምንም አይቀረኝ፡፡
 • በጣም ጥሩ የግል ጋዜጣ ታነባለህ?
 • ኧረ በፍጹም ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • በቃ እነሱን ማንበብ አያስፈልግህም፡፡
 • እሺ አካባቢህን ታፀዳለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር ከራሴ አልፎ በጎረቤት አጥር ላይ ተንጠልጥዬ ግቢያቸው ቆሻሻ ካለም አፀዳለሁ፡፡
 • አንተ ወሳኝ ሰው ነህ ማለት ነው፡፡
 • ይኸው አካባቢያችንን በየቀኑ ቆሻሻ እያቃጠልኩ ኅዳር ሚካኤል ነው የማስመስለው፡፡
 • በጣም ጥሩ መስመር ላይ ነው ያለኸው፡፡
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሴቶችንስ ታከብራለህ?
 • ክቡር ሚኒስትር እኔ ከሰው አልፎ ሴት እንስሳትን ሳይቀር ከወንዶቹ እኩል ነው የማየው፡፡
 • አስገራሚ ውጤት ነው ያመጣኸው፡፡
 • እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
 • ከስድስት ስድስት ነው ያመጣኸው?
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ስለዚህ አንተ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ነው የምትሆነው፡፡
 • የምን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ?
 • የአዲሱ ፖለቲካ ፓርቲ፡፡
 • ምን የሚሉት?
 • ግንቦት 6!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከልጃቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ዳዲ ሰሞኑን ጠፍተሃል?
 • ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡
 • ስብሰባችሁ ቅዳሜና እሑድ ነው አልተባለም እንዴ?
 • አይ እነዚህ የጎንዮሽ ስብሰባዎች ናቸው፡፡
 • አንተ ግን አይበቃህም እንዴ?
 • ምኑ ነው የሚበቃኝ?
 • ማለቴ ለምን ጡረታ አትወጣም?
 • አገሪቱን ለማን ጥለን?
 • ለእኛ ለወጣቶቹ ነዋ፡፡
 • ገና በሥርዓቱ ሱሪህን መታጠቅ ያልቻልክ እንዴት ነው አገር የምትመራው?
 • ዳዲ ፌስቡክን የመሳሰሉ ትልልቅ ኩባንያዎችን እኮ የመሠረቱት ወጣቶች ናቸው፡፡
 • እና ምን ይጠበስ?
 • አንተ ብልጥ ከሆንክ ለወጣቱ ነው በጊዜ ሥልጣንህን አሳልፈህ መስጠት ያለብህ፡፡
 • በፍጹም አላደርገውም፡፡
 • እንዴት ነው የማታደርገው?
 • በቃ አላደርገውም፡፡
 • ይኼ እኮ ነው ችግሩ?
 • እንዴት ማለት?
 • ወጣቱ የሚፈልገው ሌላ፣ እናንተ የምታደርጉት ሌላ፡፡
 • ምን እያልክ ነው?
 • አዲሱ ወጣት በድሮ አስተሳሰብ ሊመራ አይችልም፡፡
 • አየህ ወጣቱ ኒዮሊብራል የሚባል አስተሳሰብ ገብቶበት ተመርዟል፡፡
 • ኦ… ዳዲ፡፡
 • ምን ሆንክ?
 • ይኼ ኒዮሊብራሊዝም የምትለውን ጂኒ ጃንካ ወደዚያ ጣለው፡፡
 • ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ፡፡
 • የምን ችግር?
 • የምትከተሉት ርዕዮተ ዓለም ስለሌላችሁ በየነፈሰበት ትሄዳላችሁ፡፡
 • ርዕዮተ ዓለም ምናምን ምንም አይጠቅመንም፡፡
 • ይቺን አገር እዚህ ያደረሳት እኮ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፡፡
 • ይኼ ስብከትህ እኔን አይገባኝም፣ ዋናው ጥያቄ አገሪቱ ምን እያገኘች ነው?
 • አገሪቱማ እያደገች ነው፡፡
 • በምትሉት ዕድገት ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ነው ወይ?
 • አንተም ተበክለሃል እንዴ?
 • በምንድነው የተበከልኩት?
 • በዚህ በቀለም አብዮት?
 • የምን የቀለም አብዮት ነው?
 • በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዋነኛ ችግር የቀለም አብዮት ነው፡፡
 • የአገሪቷ ችግር የአመራር እንጂ የቀለም አብዮት አይመስለኝም፡፡
 • የምን የአመራር ችግር?
 • እናንተ አለቅም ማለታችሁ ነዋ፡፡
 • የቀለም አብዮት ችግር ማለት ይኼ ነው፡፡
 • እንደገባኝ አንተም ጓደኞችህም በጣም ቀለም ትወዳላችሁ፡፡
 • እ…
 • እንዲያውም ጡረታ ስትወጣ አንድ ፋብሪካ ብትከፍት ደስ ይለኛል፡፡
 • የምን ፋብሪካ?
 • የቀለም!

[ክቡር ሚኒስትር በቅርቡ ታስረው ከተፈቱ የመንግሥት ባለሥልጣን ጋር ተገናኝተው እያወሩ ነው]

 • እንኳን ደስ አለህ፡፡
 • እንኳን አብሮ ደስ አለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እንኳን ለቤቶችህ በሰላም አበቃህ፡፡
 • አመሰግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎ ብቻ ነዎት እንዲህ ደፈር ብለው የሚናገሩኝ፡፡
 • ያው አሥራ አምስት ቤቶች ኖሮህ እንዴት ለቤት ብቻ አበቃህ ልበልህ?
 • እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ባይገርምህ እኔ ራሴ ዘረፋ ውስጥ የገባሁት አንተን ዓይቼ ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር እስር ቤት ቀላል ነገር እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ሕዝብም ምን ያህል እንደተበደልን ዓይቶ ስላስፈታን እናመሠግናለን፡፡
 • ምን አልክ?
 • እኛ አይደለም አሥራ አምስት፣ አርባ ቤቶች ይገቡን ነበር፡፡
 • እሱስ ልክ ነህ፡፡
 • ለማንኛውም ያስፈታንን ሕዝብ በጣም ማመሥገን እፈልጋለሁ፡፡
 • ለመሆኑ በቀጣይ ዕቅድህ ምንድነው?
 • በርካታ ባለሀብቶችን እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ አግኝቼ ኔትወርኬን አስፍቼዋለሁ፡፡
 • ምን ልታደርግ?
 • ለመዝረፍ ነዋ፡፡
 • እኔም ብታሰር ይሻለኝ ነበር ልበል?
 • ምንም አያስፈልግም በትብብር መሥራት እንችላለን፡፡
 • ምን ዓይነት ሥራ?
 • አንድ አማካሪ ድርጅት ብናቋቁም ጥሩ ነው፡፡
 • ምን የሚያማክር?
 • ሌብነትና ዝርፊያን፡፡
 • ተጠናክረህልኝ ነዋ የወጣኸው፡፡
 • አሁን እስር ቤት ስላሳለፍኩት ሕይወት ቅልብጭ ያለች መጽሐፍ ጽፌያለሁ፡፡
 • በጣም ጥሩ ነው፡፡
 • ያው ማተሚያ ቤት ስላለዎት እርስዎ ዘንድ ትታተም፡፡
 • ምን ዓይነት መጽሐፍ ነው?
 • አጭሩን የሕይወት ትግሌን የምታሳይ መጽሐፍ ናት፡፡
 • የመጽሐፉ ርዕስ ምንድነው?
 • ሰርቀህ ብትታሰርም ትፈታለህ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ የቢሮ ሥራቸውን አጠናቀው ከውጭ አገር የመጣ ወንድማቸውን ለመጠየቅ ያረፈበት ገስት ሀውስ ሲደርሱ ወንድማቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ፕሮግራም በመገረም እየተከታተለ አገኙት]

ውይ መጣህ እንዴ? እስኪ አረፍ በል፡፡ ምንድነው እንዲህ ያስደነቀህ? ተደንቄ ሳይሆን ግራ ግብት ብሎኝ ነው። ምኑ ነው ግራ ያጋባህ? የድልድይ ማስመረቅና የድልድይ ማፍረስ ነገር ነዋ። አልገባኝም? አለቃችሁ ድልድይ ሲያስመርቁ የተናገሩትን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በዓሉን በመኖሪያ ቤታቸው እያከበሩ ነው። ባለቤታቸውም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዳቦ ባርከው እንዲቆርሱ ለሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

በል ዳቦውን ባርክና ቁረስልንና በዓሉን እናክብር? ጥሩ ወዲህ አምጪው... አዎ! በል መርቅ... ከዓመት ዓመት ያድርሰን... ኧረ በሥርዓት መርቅ ተው? ከዓመት ዓመት ያድርሰን አልኩኝ እኮ ...አልሰማሽም? ከዓመት ዓመት መድረሱ ብቻ ምን...

[ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ይፋ ያደረገውን ንቅናቄ አመራሮችና ቤተሰቦቻቸው በግንባር ቀደምትነት እንዲቀላቀሉ መታዘዙን ለባለቤታቸው እያጫወቱ በዚያውም ወደተከፈተው የባንክ ሒሳብ ገንዘብ እንዲያስተላልፉ እያግባቧቸው ነው]

በይ እስኪ ሞባይልሽን አውጪና ወደዚህ የባንክ ሒሳብ አንድ ሺሕ ብር አስተላልፊ? ለምን? መንግሥት ያስጀመረውን ንቅናቄ አመራሩ ከነቤተሰቡ ግንባር ቀደም ሆኖ እንዲደግፍ ታዟል። የምን ንቅናቄ ነው መንግሥት ያስጀመረው? ‹‹ፅዱ...