Saturday, April 20, 2024

ኦዲተሩን የማይሰሙ ጆሮዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

1997 ዓ.ም. ተደርጎ የነበረውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በፓርላማ መቀመጫ አግኝተው እንደነበር ይታወሳል። እነዚህ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በሰኔ ወር 1998 .. በፓርላማው መደበኛ ስብሰባ ለመታደም  መቀመጫቸውን ይዘዋል፡፡

በወቅቱ የአቀማመጥ ሥነ ሥርዓት መሠረት ለተቃዋሚና ለአጋር ፓርቲዎች ከተደለደለው በስተግራ ረድፍ በተቃራኒ  በኩል  የሚገኘው የፓርላማው መቀመጫም፣ ኢሕአዴግን የወከሉ አባላት በሙሉ ታድመውበታል። ዕለቱ የ1999 .. በጀት የሚፀድቅበትና የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም የሚገኙበት በመሆኑ፣ ከሕዝብ ተወካዮቹ የቀረ ያለ አይመስልም ነበር።

ፓርላማው ትርጉም ያለው ድምፅ የነበራቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በአጀንዳነት የተያዘው የቀጣዩ ዓመት በጀት ከመፅደቁ በፊት፣ የመንግሥት የበጀት አፈጻጸምን በጥያቄ መወጠር ይዘዋል፡፡ የመንግሥትን የበጀት አጠቃቀምና የፋይናንስ አስተዳደር እንዝላልነት በሰላ ትችት ለማውገዝም፣ በወቅቱ የነበሩት ዋና ኦዲተር በዚያው ሰሞን ያቀረቡትን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርገው መሞገታቸውን ቀጥለዋል። 

የወቅቱ ዋና ኦዲተር የነበሩት አቶ ለማ አርጋው ባቀረቡት ሪፖርት በ1997 .. የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች የሰጠውን 7.2 ቢሊዮን ብር የበጀት ድጐማ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለመቻላቸውን በመግለጻቸው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ትኩረት ያደረጉበት የክርክር ርዕስ ቢሆንም፣ ዋና ኦዲተሩ አቅርበውት የነበረው ሪፖርት ግን ሌሎች በርካታ ቢሊዮን ብሮች የፋይናንስ ሕጋዊነት ችግሮች እንደነበሩባቸው ያሳይ ነበር፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮቹ ለክልሎች በድጎማ የተለቀቀው በጀት ምን ላይ እንደዋለ አለመታወቁን፣ እንደጠፋ ወይም እንደተመዘበረ አድርገው መቁጠራቸው በጊዜው ምላሽ ለመስጠት በፓርላማው ተገኝተው የነበሩትን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አስቆጥቷቸው ነበር። 

በተቃዋሚዎቹ የሰላ ወቀሳ የተበሳጩት አቶ መለስ፣ ‹‹ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት የሚያገኙትን የበጀት ድጐማ ከፈለጉ ማቃጠል ይችላሉ፤›› በማለት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ንግግራቸውም በቀጥታ በቴሌቪዥን እየተላለፈ ነበር።  አቶ መለስ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ በጊዜው ዋና ኦዲተር የነበሩትን አቶ ለማን፣ ‹‹የኦዲት ሥነ ምግባር የሌላቸውና ሕገ መንግሥቱንም  የጣሱ፤›› ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡

ይህ ክስተት መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትንና ዋና ኦዲተር የነበሩትን አቶ ለማ አርጋውን፣ በሕዝብ ዘንድ በይበልጥ ያስተዋወቀ ነበር በማለት ማሰብ ይቻላል። ይህ ክስተት በሰኔ ወር ከተፈጠረ ከወራት በኋላ በኅዳር ወር 1999 .. አቶ ለማ በጡረታ እንዲሰናበቱ መደረጉ ተነገረ፡፡

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውንም ድጎማ ቢሆን ኦዲት እንዲያደርግ በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የተሰጠው ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃራኒውና በማይገባ መንገድ መናገራቸው፣ ለፓርላማው መንግሥትን ለመቆጣጠር  ተግባር እንደ ቀኝ እጅ በሚወሰደው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ተቋማዊ ነፃነት ላይ ጉዳት ማድረስ ነው ሲሉ በወቅቱ ትችት ተሰንዝሮባቸዋል፡፡

አቶ ለማ በጡረታ ቢገለሉም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ግን ሥራውን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ ከ1998 ዓ.ም. ክስተት ወዲህ የፌዴራል መንግሥት በየዓመቱ ለክልሎች ስለሚሰጠው ድጎማ በጀት አጠቃቀም ኦዲት አድርጎ አያውቅም። ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሥራውን በመቀጠል የመንግሥትን የፋይናንስ አስተዳደር ዝርክርክነትና ለመመዝበር የተጋለጡ ሀብቶች ማጋለጥ ቢገፋበትም፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍም ሆነ ለመቀነስ ትብብር ሲያደርግ ማየት ለተቋሙ ዘበት እየሆነበት ይመስላል።   

ለዚህ የሚሆኑ ማሳያዎችም ታይተዋል፡፡ በመጀመርያ በ2000 .. የታየው የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መንግሥት ከሕግ ውጪ የተበደረውን ገንዘብ በማጋለጡ ምክንያት የተፈጠረ ነው፡፡ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ መበደር ያለበት የበጀት ጉድለቱን 25 በመቶ ብቻ እንደሆነ በሕግ ተደንግጎ እያለ፣ በ1999 .. የተበደረው ግን ከዚህ በላይ መሆኑን የሚጠቁም ነበር፡፡

ይኼንን የኦዲት ግኝት መንግሥት ሊቀበለው ባለመቻሉ ፓርላማው ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ አጣሪ ኮሚቴው በመጨረሻ ይዞ የመጣው ሪፖርት መንግሥት ከሕግ ውጪ አለመበደሩን የሚገልጽ ቢሆንም፣ በዚያው ዓመት መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የፈለገውን ያህል መበደር እንዲችል የሚፈቅድ ሕግ በብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በተደረገ ማሻሻያ እንዲካተት ተደረገ፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት ዋና  ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የተሾሙት በ2000 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ተቋሙን በማጠናከር ተግባር ላይ በመጠመዳቸው በቅጡ ወደ ኦዲት ሥራቸው የገቡት በ2004 .. ነበር፡፡ ዋና ኦዲተሩ በ2004 ዓ.ም. ባቀረቡት ሪፖርት ኦዲት መደረግ ያልቻለ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበ በጀት ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዙት የፀጥታ ተቋማት ናቸው፡፡ በተለይም የመከላከያ ሚኒስቴርና የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ በተጨማሪም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አብዛኞቹ በኦዲት ችግር ውስጥ ተዘፍቀው የነበረ በመሆኑ፣ በርካታ የገዥው ፓርቲ የፓርላማ አባላትን አስቆጥቶ ነበር፡፡

2005 .. የቀረበው የኦዲት ሪፖርት የለወጠው ነገር አልነበረም፡፡ ከዚህ ይልቅ ኦዲት መደረግ ያልቻለው ገንዘብ ከፀጥታ ሚኒስትሮች ጋር የተገናኘ በመሆኑ እንዴት ኦዲት ይደረግ? ዓለም አቀፍ ተሞክሮው ምን ይመስላል? የሚሉት ጥያቄዎች ጎልተው ወጥተዋል፡፡ በመሆኑም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሌሎች አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር፣ እነዚህ ተቋማት እንዴት ኦዲት መደረግ እንደሚችሉ በማጥናት ለፓርላማው የጥናት ውጤቱን ሪፖርት እንዲያደርግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይህንን ጥናት እያከናወኑ ባለበት ወቅት፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በ2006 .. የተለያዩ ወራት የመከላከያ ሚኒስቴርን፣ የመረጃ ደኅንነትና ኢሚግሬሽንና የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ ለፓርላማው ባቀረበው ማሻሻያ ዋና ኦዲተር የደኅንነት ሚስጥሮችን የማየት ሥልጣን እንደሌለው በማሻሻያው አንስቶ አፅድቋል፡፡

በ2006 ዓ.ም. ባቀረቡት ሪፖርት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰበ ሒሳብ፣ 785 ሚሊዮን ብር ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ፣ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሠራበትን በጀት ዋና ኦዲተሩ ይፋ አድርገው ነበር፡፡

በግንቦት 2008 ዓ.ም. የቀረበው ሪፖርትም የተለየ አልነበረም፡፡ በሦስት መሥሪያ ቤቶች 196 ሚሊዮን 544  ሺሕ ብር ጉድለት፣ በ94 መሥሪያ ቤቶች 780  ሚሊዮን ብር በደንቡ መሠረት ያልተወራረደ ሒሳብ ተገኝቷል፡፡

34 መሥሪያ ቤቶችና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ባሉ አሥራ አራት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ ያልተሰበሰበ 118. 7 ሚሊዮን ብር እንዳለ ታውቋል። ይሁን እንጂ የተወሰደ ዕርምጃ አልነበረም፡፡ 

2009 .ም. በቀረበው ሪፖርት ደግሞ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤትና በሥሩ ባሉ አሥራ አምስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ ብር 5.1 ቢሊዮን ብር ሳይሰበስቡ መገኘቱን፣ በግብር ከፋዮች ለቀረበው የቅሬታ አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴው በወቅቱ ውሳኔ ባለመስጠቱ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥሪያ ቤትና በሁለት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በወቅቱ ያልተሰበሰበ በድምሩ 3.5 ቢሊዮን ብር ብር ውዝፍ ገቢ መኖሩን ዋና ኦዲተሩ አቅርበዋል፡፡ ችግሩ ከመባባሱ ውጪ ግን የተወሰደ ዕርምጃ አልታየም፡፡

በ2007 ዓ.ም. ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዋና ኦዲተር ገመቹ ፈታኝ ከሆኑባቸው ጉዳዮች አንዱ በኦዲት ግኝት ላይ ዕርምጃ ያለመውሰድ ነው እንደሆነ ተናግረው ነበር፡፡ እኔ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ፣ ግን ሥራዬን አልጨረስኩም፡፡ ሥራዬ የመጨረሻውን ውጤት ሲያመጣ ነው መርካት ያለብኝ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት አላስገኘም፡፡ የእኛ የኦዲት ግኝት በሚዲያ ስለተሰማ ሥራ ተሠርቷል ማለት አይደለም፡፡ ስህተቱ ታርሞ ሳይ ነው ተሳክቶልኛል ብዬ መናገር የምችለው፡፡ ይህ አለመሆኑ ለእኔ ትልቅ ፈተና ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በ2006 ዓ.ም. በዋና ኦዲተሩና በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ መካከል በተደረገ ስምምነት በ2006 ዓ.ም. ሪፖርት ላይ የሚገኙ የኦዲት ግኝቶች እስካሁን በነበረው ግዝፈት የሚቀጥሉ ወይም የማይሻሻሉ ከሆነ፣ ሕጋዊ ቅጣት በመሥሪያ ቤቶቹ ኃላፊዎች ላይ ለመውሰድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ አንድም የተወሰደ ዕርምጃ የለም፡፡ ይልቁንም ነገሮች በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመሩ ቀጥለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ያቀረቡት ሪፖርት የዚህ ማሳያ ነው፡፡

ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት በዚህ ሪፖርት በተለያዩ የኦዲት ዘርፎች ማለትም ያልተሰበሰቡ ውዝፍ ገቢዎች፣ ያልተወራረዱና ደረሰኝ ያልተገኘላቸው ወጪዎች፣ ለማን እንደሚከፈሉ ያልታወቁና ለረዥም ዓመታት የተወዘፉ ተከፋይ ሒሳቦች፣ ሕግን ያልተከተሉ ግዥዎችና ከበጀት በላይ በመጠቀም በድምሩ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ችግር ያለበት ሪፖርት ይዘው ቀርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥም የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት፣ ከአምስት መሥሪያ ቤቶች 927,522 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡ የሒሳብ ሰነድ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ116 መሥሪያ ቤቶች 5.8 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱን፣ ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አስረድተዋል፡፡

በሌሎች አሥር መሥሪያ ቤቶች 1.3 ቢሊዮን ብር ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተያዘና ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ባለመኖሩ፣ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች መሠረት የመንግሥት ገቢ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በሌሎች ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 1.5 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት 6.2 ቢሊዮን ብር በወቅቱ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መገኘቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግብር ከፋዮች ያቀረቡት ቅሬታ በፍጥነት መፍታት ባለመቻሉ 1.6 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በ68 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 5.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ ደግሞ 98 መሥሪያ ቤቶች ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ዋና ኦዲተሩ በአሁኑ ወቅት ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ፡፡ ‹‹ይህ ዘጠነኛ ሪፖርቴ ነው፣ ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረብኩ ነው ያለሁት፤›› በማለት ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ዕርምጃ ቢወሰድና መቅጣት ቢጀመር ኖሮ ችግሮቹ አንድ ቦታ የሚቆሙበትና መፍትሔ ተሰጥቶ፣ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሻገር የሚቻልበት ዕድል ይፈጠር እንደነበር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -