Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይሁና!

ከሰሚት ወደ ጎሮ በሚሄድ ታክሲ ውስጥ ተሳፍረናል፡፡ ከታሪፍ ብዙ እጥፍ ከፍለናል፡፡ ምክንያት ደግሞ ‹ተመላሽ አናገኝም› የሚል ነበር፡፡ በሌላ ነገር ቀድሞ ተናዶ ያመሸ የሚመስል ሰው፣ ‹‹እናንተ ተመላሽ ስለማታገኙ እኛ የሚመለሰውን ሰው ጭምር መክፈል አለብን?›› በማለት ይጠይቃል፡፡ ወያላው ቆፍጠን ብሎ ይመልሳል፣ ‹‹አዎ!››፡፡ ይኼን ጊዜ ታክሲው በውጥረት ይሞላል፡፡ ከአሁን አሁን ተቧቀሱ ስንል የተናደደው ሰውዬ፣ ‹‹ራሞስን ይዘዝብህ እንጂ ሌላ ምን እልሃለሁ?›› በማለት ተራገመ፡፡

 ሁለት ወንድና ሴት ቁጭ ብለው በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እየተጨቃጨቁ ነው፡፡ ‹‹መጀመርያውኑ አንቺ ለወንዶች ፊት አትስጪ አላልኩሽም ነበር?›› እያለ በምሬት ይናገራል፡፡ ይኼን ጊዜ ሳይጠሩት አቤት ማለት የሚወደው ወያላ፣ ‹‹ወንዶች መቼ ፊት ጠይቀው ያውቁና ነው ፊት አትስጪ የምትላት?›› በማለት በማያገባው ጥልቅ አለ፡፡ ሁላችንም ድንግጥ አልን፡፡ ምናልባት ሰውዬው አፀፋውን መልሶ ነገርዬው ወደ ፀብ እንዳያመራ ሠግተን፡፡ ወያላው ‹ፀብ የለሽ በዳቦ› ዓይነት ነገር ነው፡፡

ከኋላ የተቀመጠ ትንሽ ሞቅ ያለው የሚመስል ጎረምሳ በወያላው የተበሳጨ ይመስላል፡፡ እንዲህም በማለት ጠየቀው በተሳሰረ አንደበት፣ ‹‹ምነው አንተ አለሁ አለሁ አልክ?›› ሲለው፣ ‹‹ባይሆን አንተ እኮ የለህም፡፡ ምነው ይኼን ያህል መጠጣትን ምን አመጣው?›› በማለት ጥያቄውን አዞረበት፡፡ ወያላው ቀጠለ፣ ‹‹እንኳን ጠጥተህ እንዲሁም ሰካራም ነው የምትመስለው፡፡ ካንተ ጋርማ አልጣላም፤›› ሲል ሞቅ ያለው ወጣት ለምን እንደ ጠጣ ሦስት ምክንያቶችን አስቀመጠ፡፡ ‹‹አንደኛ . . . አለ፡፡ ‹‹ . . . የግንቦት ሃያ ሰሞን ስለሆነ ተደስቼ ደስታዬን ለመግለጽ፣ ሁለተኛ ቡድኔ ሊቨርፑል በሚያሳዝን ሁኔታ ተሸንፎ ዋንጫውን ስለተቀማ፣ ሦስተኛ ደግሞ በተፈቱልን ሰዎች ተደስቼ ቅይጥ ሐሳብ ውስጥ ሆኜ ነው የጠጣሁት፤›› እያለ አብራራ፡፡ ጠፍቶ የቆየው ሾፌር ለመጀመርያ ጊዜ አስተያየት መስጠት ጀመረ፣ ‹‹በዚህ ዓይነት አካሄዱ መንግሥት ከቀጠለ . . . ›› በማለት አፉን ሲያሟሽ ትንሽ ትኩረት ተሰጠው፡፡ የተሳፋሪዎችን ትኩረት ያገኘው ሾፌር ፈገግ እያለ፣ ‹‹ . . . ወህኒ ቤቶቻችን ባዶ እንደሚቀሩ ምንም ጥርጥር የለኝም፤›› በማለት ተነፈሰ፡፡

ይኼን ጊዜ መኖራቸውን እንኳ ማንም ሰው ልብ ያላላቸው አንድ አዛውንት መናገር ጀመሩ፡፡ የሾፌሩ ሐሳብ የነካቸው ይመስላሉ፡፡ ‹‹እንደ አፍህ ያደርግልን ልጄ፡፡ ወህኒ ቤቶቻችን ሁሉ ባዶ ይቅሩልን፤›› በማለት ምርቃታዊ አስተያየት ሰጡ፡፡ ከግማሽ የሚሆኑት ሰው ‹አሜን› በማለት አጀቧቸው፡፡ ከሁሉም ሰው ሐሳብ ጋር ሲጋጭ የነበረው ወያላ አሁንም በሾፌሩና በሽማግሌው ሐሳብ አልተስማማም፡፡ እንዲህ በማለት ሙግት አመጣ፡፡ ‹‹ፋዘር ምን ነካዎት? ለአንድ አገር ዋና ከሚባሉት ነገሮች ውስጥ ወህኒ ቤትና ፖሊስ ናቸው፡፡ በተለይ ፖሊስ ከሌለ ሰበብ ፈልጎ ማን ይቀጠቅጠናል?›› በማለት የተቃውሞ ሐሳቡን አሰማ፡፡

ይኼን ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹አንተ በቃ ሲፈጥርህ ለተቃውሞ ነው፡፡ ምንም ነገር ከመቃወም ውጪ በጥሩ ጎኑ መመልከት አትችልም ማለት ነው?›› በማለት ሌላ ጥያቄ አመጣለት፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ታዲያ ትንሽ አታፍሩም እንዴ? ወደፊት ወህኒ ቤቶች ተዘግተው በቦታቸው ላይ ኮንዶሚኒየም ቤት ይሠራል እያላችሁኝ እኮ ነው፡፡ መቼም ወህኒ ቤቱ ላይ ለሚሠራው ኮንዶሚኒየም እስረኛ ከነበሩ ውስጥ ዕጣ የሚያወጣ ይኖራል ብዬ አልገምትም፤›› በማለት ቀለደ፡፡ የወያላው ቀልድ ያልገባቸው አባት፣ ‹‹ለምንድነው የማይሳተፉት? እነርሱም እኮ መብታቸው ነው፤›› በማለት ሲያብራሩ ወያላው እየሳቀ፣ ‹‹እንደሱ ሳይሆን ፋዘር ለብዙ ዘመናት የታሰሩበት ቦታ ድጋሚ መኖር ጀምረው የቀድሞ ትዝታቸውን እንዳይቀሰቅስባቸው ብዬ እኮ ነው፤›› ብሎ ብቻውን ሳቀ፡፡

አንዲት ሴት መናገር ጀመረች፡፡ አሁን አሁን ሴቶቻችንም ታታሪ የእግር ኳስ ተመልካች ሆነዋል፡፡ በሊቨርፑልና በማድሪድ መሀል የተደረገውን የፍፃሜ ውድድር ተመልክታ ሳምንቱን ሙሉ ስትበግን የቆየች ጉብል ቢጤ ናት፡፡ ‹‹ይኼ ሰርጂዮ ራሞስ ነው ሳምንቴን ያመሰቃቀለው ዓመቱ ይዘበራረቅበትና፤›› በማለት መራገም ጀመረች፡፡ የመጀመርያው አብራው የተቀመጠችውን ሴት በግምት እጮኛው ትሆናለች ብለን የጠረጠርነው ሰውዬ፣ ታክሲ ውስጥ ከሚነፍሰው ወሬ አንዱ እንኳን ተሳስቶ የሰማ አይመስልም፡፡ ይልቁንም ፀንቶ በማስጠንቀቂያው ገፍቶበታል፡፡ ወንድ ለተባለ ፍጥረት ፊት እንዳትሰጥ፣ ስልክ ቁጥር እንዳትሰጥ፣ ፈገግታዋን እንዳትሰጥ ብቻ ምንም ነገር እንዳትሰጥ ፀንቶ እያስረዳት ይገኛል፡፡

በሰርጂዮ ራሞስ የተማረረችውም ሴት መራገሟን ገፍታበታለች፡፡ ‹‹ትከሻው ይበጠስና እንዲያው የአባቴ አምላክ እስከ ዓለም ዋንጫ አያድርሰው፤›› እያለች መራገም ጀመረች፡፡ ይኼኔ ልማደኛው ወያላ መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ምናለበት ስፖርትንና ጥንቆላን ባታደባልቁት፡፡›› እሱም እኮ ለማሸነፍ ነው የገባው፤›› በማለት ለራሞስ ድጋፍ መከራከር ጀመረ፡፡ ወጣቷ የባሰ ተበሳጨች፡፡ ‹‹ስፖርት ‹ፌር ጌም› መሆን አለበት እንጂ አንዱ ጥሎ የሚከብርበት መድረክ አይደለም፡፡ ምነው አንተን ቆረጠህሳ? እንዲያውም ይውጣልህ አዎን የአባቴ አምላክ እስከ ዓለም ዋንጫው አያድርሰው፤›› በማለት ተማራ ተራገመች፡፡

ወያላው፣ ‹‹የአንቺ ብቻ አባት ይመስልሻል እንዴ አምላክ ያለው? የእርሱም አባት እኮ አምላክ አለው፡፡ እስከ አውሮፓ ሻምፒዮን አድርሶታል፡፡ እስከ ዓለም ዋንጫም እንደሚያደርሰው በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ፤›› በማለት አፍ አፏን አላት፡፡ ከወዲሁ ወዲያ በሚጨቃጨቁ ሰዎች ታክሲያችንን መሞላቷ አስገርሞናል፡፡ ዳሩ ግን ሁሉም የሚቆስልበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡

ነገርዬውም ያላማራቸው አዛውንት፣ ‹‹እስቲ ረጋ በሉ ልጆቼ? እነ እሱ እንኳን ታርቀው ነገሩን በተውበት ሰዓት የእናንተ እንደ አዲስ መጣላት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? ደግሞም እነሱን ሊዳኝ የተቀመጠው አካል ይዳኛቸው፡፡ ምንድነው እዚህ ቁጭ ብሎ ጨጓራን መላጥ?›› በማለት አባታዊ ምክራቸውን ሰነዘሩ፡፡

ልማደኛው ወያላ አሁንም የተቃውሞ ሐሳብ ያለው ይመስላል፣ ‹‹አይደለም አባት እህታችን ላይ እየተጫወተባት ያለው ጋኔል ነው፡፡ ሦስት ሰባት ብትጠመቅ ለቋት ይሄዳል፤›› በማለት ቀለደባት፡፡ ልጅቷም የወያላው ተንኮል ስለገባት ጭጭ አለች፡፡ በመጨረሻም ቢሆን ዝምታዋን የተቀበለው አይመስልም፡፡ ድጋሚ አፉን በማላቀቅ፣ ‹‹መሸነፍ የለብሽም፣ እጅ መስጠት የለብሽም፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ በሙሉ ኃይልሽ መሟገት አለብሽ፡፡ አለበለዚያማ ገና ስትጀምሪ ነው ከጨዋታ ወጪ የምትሆኚው፤›› በማለት ዝምታዋንም ሞግቶ ረዥም ማብራሪያ ሰጣት፡፡ ልጅት ከዝምታዋ ጋር ተባብራ በፀጥታዋ ገፋች፡፡

በጨለማ የጀመርነው ጉዞ ወደ መገባደጃው እየደረሰ ነው፡፡ ወደ ሰሚት ከመድረሳችን በርካታ ሰዎች ታክሲ አጥተው ቆመዋል፡፡ ወዲያው እኛን ሸኝቶ ወያላው የእኛ እንኳን ከቦታው መንቀሳቀስ ሳይጠብቅ፣ ‹‹ቦሌ ሃያ ብር . . . ሃያ ብር . . . ›› ማለት ጀመረ፡፡ ነገርየው ያማረረው የሚመስል ሰው፣ ‹‹ለምንድነው ሃያ ሃያ ብር የምታስፈክለን? ከታሪፍ ውጪ . . . ›› በማለት ቢጠይቀው፣ ‹‹ተመላሽ አላገኝም፡፡ ከተስማማህ ግባ ካልተስማማህ በላዳ መሄድ ትችላለህ፤›› እያለ አውርዶ ሸኘን፡፡ ይኼኔ ነበር አንዱ፣ ‹‹ይሁና! ይሁና! ጨፍሩብን እንጂ . . . ›› ሲል ነው በየፊናችን የተበታተንነው፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት