Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ባሕር ማዶ የዘለቀው ስኬት

ከሁለት አሠርታት በፊት ጀምሮ የየመን እግር ኳስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተያይዞ ይነሳል፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ለፕሮፌሽናልነት መንደርደሪያቸውን የመን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ያጨዋወት ክሂል የተመለከቱት የየመን እግር ኳስ ክለቦችና ፌዴሬሽኑ ትኩረታቸውን ከተጫዋቾች ባሻገር አሠልጣኞችም ላይ አሳርፈዋል፡፡ በየመን የጦርነትና የርስ በርስ ግጭት እስከጀመረበት ድረስ ኢትዮጵያውያን አሠልጣኞችና ተጫዋቾች በየመን ሊግ ውስጥ መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ ዲቪዥኖች ቡድኖችና ፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን በማሠልጠን የሚታወቀው አብርሃም መብርሃቱ በየመን ከክለብና ከብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት ባሻገር የየመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር እስከ መሆን ደርሷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የየመን ኦሊምፒክ ቡድንን ይዞ ለእስያ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ያሳለፈው አብርሃም፣ የመን በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ በተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ በሚቀጥለው ዓመት ለሚዘጋጀው የእስያ ዋንጫ እንድታልፍ አድርጓል፡፡ በእርስ በርስ ጦርነትም ለአራት ዓመታት እየታመሰች ያለችውን የመን ብሔራዊ ቡድኗን በስደት አገር ካታር በማዘጋጀት ለድል ያበቃውን አብርሃም መብራቱን የየመኑ ፕሬዚዳንት አብደሮቦ ሃዲ ዕውቅናና ክብር በሳዑዲ ሪያድ መስጠታቸው በሚዲያው ተዘግቧል፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ኢንስትራክተር የሆነው አብርሃም በአሠልጣኝነት ሕይወቱና የመን ባስመዘገበው ስኬት ዙርያ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- የአሠልጣኝነት ሕይወትህ እንዴት ተጀመረ?

አብርሃም፡- መጀመሪያ ማሠልጠን የጀመርኩት ስጫወትበት የነበረውን የቀበሌ 40 ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ በያዝኩበት ዓመትም ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ በመቻሉ የፀባይ ዋንጫ ተሸላሚ መሆን ቻለ፡፡ በወቅቱ የነበረኝን እንቅስቃሴ ሲመለከቱ የነበሩ የእርሻ ሰብል ቡድን አመራሮች ለቡድናቸው እንድሆን ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ ይኼም አጋጣሚ የተፈጠረው የእርሻ ሰብል አሠልጣኝ ለሥራ ወደ ክፍለ አገር መሄዱን ተከትሎ ነበር፡፡ ከዚያም የአዲስ አበባ ታዳጊዎች ሻምፒዮና መሆን ቻልን፡፡ በጊዜውም እነ ዳግማዊ አሊ፣ አንዋር ያሲንና ጌታቸውን የመሰሉ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ከዚያ ጉምሩክ ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ከተወዳደሩት ውስጥ በወቅቱ ከሩሲያ በእግር ኳስ ማስተርስ ያለው ልዑልሰገድ የሚባል በዋና አሠልጣኝነት ሲመረጥ እኔ በምክትልነት ተመረጥኩ፡፡ ቡድኑ በአዲስ መልክ በ1988 ዓ.ም. በመደራጀቱም የአዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና መሆኑን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ከፍተኛ ሊግ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ሊግ ውስጥ ገብተን አንድ ዓመት ከተወዳደርን በኋላ በገንዘብ አቅም ምክንያት ቡድኑ ፈረሰ፡፡ በወቅቱ የክለቡ ተጫዋቾች ወርኃዊ ደመወዝ በአግባቡ ሳይሰጣቸው ነበር ዓመቱን የጨረሱት፡፡ ቡድኑ ሁለት ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድንና ሦስት ተጫዋቾችን ደግሞ ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ማብቃት ችሏል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ እነ ፀጋ ዘአብ አስገዶም፣ ስንታየሁ ቆጬ፣ ሰሎሞን፣ ኪሮስ ተመርጠው የሴካፋ ዋንጫ ማስገኘት ችለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጉምሩክ እንደወጣህ ማረፊያህ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና ነበር፡፡ እንዴት ነበር ቆይታህ?

አብርሃም፡- ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሳመራ ሁለት ዓይነት ስሜት ነበረኝ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ቡና በአገሪቷ ውስጥ ትልቅ ደጋፊ ያለውን ክለብ እንዴት ማሠልጠን እንደሚቻል ልምድ ለመውሰድ፣ ሁለተኛ ደግሞ ስመ ጥር ከሆኑ አሠልጣኞች ጋር ሆኖ ትምህርትና ልምድ መውሰድ የሚያስፈልገኝ ጊዜ መሆኑ ነበር፡፡ ከዚያ የሥዩም አባት ረዳት አሠልጣኝ ሆኜ ተቀጠርኩ፡፡ ሥዩም አባተ ረዳት ሆኜ ስሠራ የምሥራቅ አፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ለኢትዮጵያ ነሐስ አስገኘን፡፡ የግብፅን አል አህሊን ከውድድር ውጪ ያደረግንበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ ስዩም በተለያዩ ምክንያቶች ክለቡን ሲለቅ፣ ለ1991 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ክረምት ላይ ቡድኑን የማዘጋጀት ኃላፊነት ለእኔ ተሰጠ፡፡ ከዚያም በዋና አሠልጣኝነት ቡድኑን እየመራሁ ደብረ ዘይት ላይ አዘጋጀሁና ውድድር ሲጀመር ውጤቱ ጥሩ አልነበረም፡፡ በወቅቱ የነበረኝ አቅም ቡናን የሚያክል ቡድን መምራት እንደማያስችለኝ ካወቅኩ በኋላ የመልቀቂያ ደብዳቤ ለቦርዱ አቀረብኩ፡፡ ቦርዱ ሁለት አማራጭ ሰጠኝ፡፡ አንድ ሌላ አሠልጣኝ እንቀጥራለን በምክትልነት ቀጥል የሚልና ሁለተኛ ደግሞ ልቀቅ የሚለው ነበር፡፡  

ሪፖርተር፡- ወደ የመን እግር ኳስ እንዴት አመራህ?

አብርሃም፡- ከቡና እንደተለያየሁ የክልል ክለብን ለማሠልጠን ወደ ወንጂ አመራሁ፡፡ ከዚያም ቡድኑን ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳደግኩት፡፡ ቡድኑ ፕሪሚየር ሊግ እንዲቆይ ካደረግኩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ፈለግኩ፡፡ በ1998 ዓ.ም. መድንን ማሠልጠን ከጀመርኩ በኋላ ቡድኑ ለወድድር ዝግጅት አጠናቀን ወደ ድሬዳዋ ስናመራ አውቶብሳችን ፍሬን በጥሶ የተወሰኑ ልጆች ጉዳት ደርሶባቸው፣ የተወሰኑ ጨዋታዎችን ስናደርግ ቆየን፡፡ በዚህ መሀል ቡድኑ አራት ውስጥ መግባቱን ካረጋገጥኩ በኋላ እኔ ወደ የመን ለመሄድ ዕድል አገኘሁ፡፡ ቡድኑ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ተከትሎ የቡድኑ አመራር በመልካም ተቀብሎኝ ከዚያም ወደ የመን አመራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በ1999 ዓ.ም. ወደ የመን ያመራህበት ወቅት ነበር፡፡ ዕድሉን እንዴት አገኘህ?

አብርሃም፡- መጀመሪያ ወደ የመን ሳመራ አል ሄልአል የሚባል ክለብን ነበር ማሠልጠን የቻልኩት፡፡ ክለቡን ለማሠልጠን ሁለት ሰዎች ነበሩ ሁኔታውን ያመቻቹልኝ፡፡ አንደኛ አቶ ሰይድ የሚባሉ የቡና ደጋፊ ነበሩ፡፡ በጊዜው የየመን ክለብ ተጫዋች ነበር የሚፈልገው፡፡ ከተጫዋች ደግሞ በጊዜው ጎበዝ የነበረውን ብርሃኑ ቃስሚን አስፈረሙ፡፡ ከዛም ብርሃኑ ቃሲም በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና በሚያስቆጥራቸው ግቦች ተማርከው ነበር፡፡ ከዚያም የወቅቱ አሠልጣኝ ተደራራቢ ሽንፈቶች ሲገጥመው ለምን ኢትዮጵያዊ አሠልጣኝ አንቀጥርም የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ በዚህም በገባሁበት ዓመት የአገሪቱ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ አሸናፊ መሆን ቻልን፡፡ ከዚያም የእስያ የክለቦች ውድድር ላይ ገባን፡፡

ሪፖርተር፡-  የመን ላለፉት ሦስት ዓመታት ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ በዚህ ውስጥ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ እስያ አገሮች ዋንጫ ውድድር ማብቃት ሒደት እንዴት ነበር?

አብርሃም፡- ካለው ነባራዊ ሁኔታ የነበረን ጉዞ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጨዋታ የማጣሪያ ማጣሪያ ነበር፡፡ የመን ይኼን የማጣሪያ ማጣሪያ ማለፍ ካልቻለች እ.ኤ.አ. 2019 ድረስ ከማንኛውም ጨዋታ ውጪ ትሆናለች፡፡ የመን ለቀጣይ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እንድትሳተፍ ለማድረግ የደርሶ መልስ ጨዋታውን በጥንቃቄ መጫወት ያስፈልግ ነበር፡፡ ባመጣነው ውጤት ሁሉም ደስተኛ ነበር፡፡ ምክንያቱም አገሪቷ ያለችበት ሁኔታ እዚህ ደረጃ ያደርሳታል ብሎ ማሰብ ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህ ባመጣነው ውጤት በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- በጦርነት ውስጥ የመንን ብሔራዊ ቡድን እዚህ ደረጃ የማድረስ ሒደት ምን ይመስላል?

አብርሃም፡- የኦሊምፒክ ቡድኑ በያዝኩበት ወቅት ጦርነቱ ከቀጣና ቀጣና ይቀያየር ስለነበር፣ አካባቢ እየለወጥን ነበር ስንዘጋጅና ስንጫወት የነበረው፡፡ ተጫዋቾችን የነበራቸውን ችሎታ አውቅ ስለነበር እንዲሁም ኦሊምፒክ ቡድን ውስጥ የነበሩትን ተጫዋቾች ይዤ ከዋና ቡድን ውስጥ ሦስት ተጫዋቾች በመምረጥ በወጣት የተከገነባ ቡድን ይዘን ቀረብን፡፡ የመን ላይ የነበረው ያለመረጋጋት የልጆቹ ችሎታ አጉድሎታል ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ 40 ተጫዋቾችን በመያዝ ጥሩ ብቃት ላይ ያሉትን በመጠቀም ውድድሩን ማካሄድ ቻልን፡፡ ቴክኒካል ዳይሬክተር በነበርኩበት ወቅት ችሎታቸውን እየገመገምኩ እይዝ ስለነበር በውድድሩ ላይ መያዝ እምችለው 25 ቢሆንም ተጫዋቾች ሲጎዱብኝ እየተካሁ ማካሄድ ቻልኩ፡፡

    ብሔራዊ ቡድኑን ስይዝ ደግሞ የአገር ውስጥ የሊግ ውድድር ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ስለነበር፣ ተጫዋቾቹን ብቻ መርጠን ዝግጅቶችን ስናደርግ የነበረው ካታር ላይ ነበር፡፡ ካታር የመንን ለማስተናገድ በመስማማቷ፣ በሜዳችን የምናደርገውን ጨዋታ ሙሉ ወጪ በመቻል በሜዳዋ እንድናከናውን ፈቀደች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2016 ጀምሮ ሁሉንም ጨዋታዎቻችንን በካታር ነው ያደረግነው፡፡ ትልቅ ችግር የሆነብን ውድድር አልነበረም፡፡ ተጫዋቾችን መምረጥና ብቃታቸውን ማየት አልቻልንም፡፡

ሪፖርተር፡- ዝግጅቱን ከአገራችሁ ውጪ ማድረጋችሁ የነበረው ድጋፍና ባልለመዱበት የአየር ንብረት ማዘጋጀት ሒደትስ? ድልድሉንስ እንዴት አገኘኸው?

አብርሃም፡- ቡድኑን እዚህ ውድድር ላይ ለማድረስ ሌላኛው ችግር የሆነብን በተመልካች ፊት አለመጫወትና ባለመዱበት የአየር ንብረት መጫወት ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህ ጥቅሞች ድጋፍ ለማግኘት የቻልነው በካታር የነበሩ የመናውያንና ኢትዮጵያውያውያን ትልቅ ድጋፍ ያደርጉልን ነበር፡፡ ሌላው በቂ ዝግጅት ለማድረግና የተጫዋቾችን ብቃት ለማወቅ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ አለመቻላችን ችግር ነበር፡፡ ስለዚህ የምንፈልገውን ያክል የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም ሌሎች አገሮች ካልጋበዙን በስተቀር እኛ መጋበዝ አልቻልንም ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ ላይ ግን ለአገራቸው አንድ ትልቅ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የሥነ ልቦና ሥራ ሠርተንባቸዋል፡፡ ይኼ ከምንም በላይ ለውጤቱ መሳካት ረድቶናል፡፡

ምድብ ድልድሉን በተመለከተ ከኢራን፣ ኢራቅና ቬትናም ጋር ነው የተመደብነው፡፡ ኢራን በካርሎስ ኪሮዥ ነው የምትመራው፡፡ ትልቅ አሠልጣኝ ነው፡፡ ሁለት ጊዜ ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ማሳለፍ ችሏል፡፡ የኢራቅ ብሔራዊ ቡድንም ቢሆን፣ የኦሊምፒክ ውድድር ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ በተጨማሪም ሁለቱም አገሮች በእስያ ዋንጫ ላይ ትልቅ ልምድ አላቸው፡፡ ስለዚህ የሚያጋጥመን ነገር ጠንካራ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ቢሆን ግን ጠንካራ ዝግጅት አድርን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንጥራለን፡፡

ሪፖርተር፡-  በቀጣይ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ያለህ ሁኔታ ምን ይመስላል?

አብርሃም፡- እስካሁን ድረስ ምንም ያሰብኩት ነገር የለም፡፡ ሰኔ መጀመርያ ላይ ቦርዱና ቴክኒክ ኮሚቴው የጋራ ስብሰባ ይኖረናል፡፡ ስብሰባው ላይ የሚወሰኑ ነገሮች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ እንዴት ታየዋለህ? በውጪ አገር ያሉ የእግር ኳሱ ባለሙያዎች እንዴት ኢትዮጵያን መርዳት ይችላሉ?

አብርሃም፡- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙም ሩቅ አይደለሁም፡፡ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር በመሆኔ በአገር ውስጥ የሚሰጡ የኤ፣ ቢ እና ሲ የአሠልጣኞቻችን ኮርሶችን አገራችን ላይ ላሉ የሁሉም ውድድር አሠልጣኞች በየዓመቱ ከሌሎች የሙያ ባልደረቦቼ ጋር እሰጣለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች ያላት ትልቅ አገር ናት፡፡ ይኼን ነገር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የፊፋ ባለሙያዎች መሬት ላይ ያለውን ነገር መመስከር ችለዋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ታዲያ አያይዘውም በአገሪቷ የሚገኙት ተጫዋቾችን አዲስ የሥልጠና አካሄድ በመከተል ልጆቹን ማብቃት እንደሚያስፈልግ ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም በወቅቱ የተሠራ ነገር የለም፡፡ ቀደም ሲል ይከናወኑ የነበሩትን የፕሮጀክት ውድድሮች የተመለከቱ ሙያተኞች የሰጡት አስተያየትም እስካሁን ድረስ የተገበረ የለም፡፡ ስለዚህ ከሥር መሠረት እየሠሩ ወደ ላይ ማሳደግ ዋነኛ ሥራ መሆን ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ ሌላ ችግር በተለያዩ ሊጎች ውድድር ይካሄድና ዓመቱ ሲጠናቀቅ ከነችግራቸው ለቀጣይ ሲተላለፉ ይታያል፡፡ የእኛ ሊግ በተጀመረበት ወቅት የአገራችን ሙያተኞችና አሠልጣኞች ቁጭ ብለው ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ ስህተታቸውን የገመገሙበትና ግምገማው ደግሞ ለቀጣይ ሊግ አቅጣጫ ያስቀመጡበት ጊዜ የለም፡፡ ስለዚህ ሙያተኞች በራሳቸው እየተገናኙ ካልገመገሙና ስህተታቸውን ካልተመለከቱ መቼ ነው ማስተካከል የሚቻለው? ስለዚህ የተለያዩ ባለሙያዎችን ወደ አገር እየጋበዙ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ሥልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ላለፉት 16 ወራት አሠልጣኞቻችንን ምንም ዓይነት የማሻሻያ ሥልጠና አልወሰዱም፡፡ በሌላው አገር በየሦስት ወር ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በአግባቡ እንኳን እርስ በርሳቸው የማይገናኙ ባለሙያዎችን በሜዳ ጨዋታ አምጣ ማለት ከባድ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...