በ1969 ዓ.ም. አካባቢ እንደተመሠረተ በሚነገርለት ሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ልጆች ናቸው፡፡ በትምህርት ቤቱ በስተቀኝ ሰንበሌጥ የለበሰ ሰፊ ሜዳ ይገኛል፡፡ ከሜዳው አለፍ እንዳሉ የትምህርት ቤቱን ዕድሜ የሚናገር በጭቃ የተሠራ 5 የመማሪያ ክፍሎች የያዘ ይታያል፡፡ ይህ የሦስተኛና የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚማሩበት ሲሆን፣ በአንድ ክፍል ውስጥም እስከ 70 የሚሆኑ ተማሪዎች ይማራሉ፡፡
በክፍሉ ውስጥ ተበታትነው የሚታዩት ዴስኮች በብዛት መቀመጫም ሆነ መደገፊያ የላቸውም፡፡ የሕንፃው ጀርባ አልፎ አልፎ ከተገጠገጠ እንጨት ውጪ ምንም ዓይነት ከለላ የለውም፡፡ ክፍተቱ ከባዱን የአካባቢውን ሙቀት ለመከላከል ሆን ተብሎ የተተወ ቢሆንም የቀትሩን ፀሐይ ሰተት ብሎ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ሕንፃው ከማርጀቱ የተነሳም በተማሪዎች ላይ ተንዶ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ ይመስላል፡፡ ከዚህ ጀርባ ወላጆችና መምህራን ለመሥራት ያስጀመሩት ባለሁለት ወለል ሕንፃ ግንባታ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ ዘመናት እንዳስቆጠረ የዛጉት የአርማታ ብረቶች ምስክሮች ናቸው፡፡
ቀጥሎ ደግሞ መደዳውን የተሠሩ ሦስት የመማሪያ ሕንፃዎች ይገኛሉ፡፡ የሕንፃዎች መስታወቶች እንደ ዳንቴል የተተለተሉ ሲሆኑ፣ ምንም ሳይንካቸው ድንገት እየረገፉ በዙሪያቸው ያሉትን ያስደነግጣሉ፡፡ ለመርገፍም ተንጠልጥለው ጊዜያቸውን የሚጠብቁ ይታያሉ፡፡ ከነዚህ ክፍሎች ጎን በቆርቆሮ የተሠሩ ሁለት ክፍሎች ያሉት የአፀደ ሕፃናት መማሪያ ክፍሎች አሉ፡፡ አልፎ አልፎ የዛጉ የሕፃናቱ መጫወቻዎች ይታያሉ፤ የአካባቢ ሙቀት እንኳንስ ለሕፃናት ማቆያነት ለአዋቂም ከባድ ነው፡፡
በግቢው ውስጥ 700 የሚደርሱ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች በአካቶ ትምህርት ፕሮግራም ይማራሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ የልብ ቅንነት ካለ ተዓምር መፍጠር እንደሚቻል ማሳያ ነው፡፡ ተማሪዎቹ ለዘመናት ቤት ውስጥ ተቆልፎባቸው የተገኙ ሕፃናት፣ በራሳቸው መፀዳዳት የማይችሉ ነበሩ፡፡ ማኅበረሰቡ ያገለላቸውን እነዚህን ታዳጊ በፍፁም ልባዊ ትህትናና ትዕግስት ቃኝቶ ወደ ኅብረተሰቡ መመለስ በነመምህርት ሃይማኖት ተመስገን ላይ የወደቀ ኃላፊነት ነው፡፡
በቀበሌና በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቤት ለቤት በተደረገው አሰሳ ተገኝታ ነበር ማህሌት (ስሟ ተቀይሯል) የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎች ወደ ሚማሩበት የልዩ ፍላጎት አካቶ ትምህርት ቤት የመጣችው፡፡ መምህሯ ወ/ሮ ሃይማኖት እንደምትናገረው የታዳጊዋ ዕድሜ በግምት 15 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህ የዕድገት ዕክል እንዳለባት ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ያህል ቤት ተዘግቶባት ትኖር ነበር፡፡ ራሷን መንከባከብም ሆነ መመገብ የማትችል በመሆኗ በሰው ላይ ጥገኛም ነበረች፡፡ ወደ ትምህርት ቤት በተላከችበት በመጀመርያው ሰሞን ሰውና የፀሐይ ብርሃን ለመልመድ ብዙ ተቸግራ ነበር፡፡ ስትንቀሳቀስም ፊቷን በእጇ እየሸፈነች እንደ ነበር አስተማሪዋ ታስታውሳለች፡፡ በነዚህ መምህሮች ታግዛ ዛሬ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ለመሆን በቅታለች፡፡
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ገብሬ ሲያብራሩ ትምህርት ቤቱ በሦስት ፈረቃ ከአራት ሺሕ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ገልጸዋል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎችም በከተማው ዝቅተኛ ኑሮ ከሚኖሩ ቤተሰቦች የተገኙ ናቸው፡፡ 700 ለሚሆኑ የደሃ ደሃ ተማሪዎች ምገባም እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ አቶ ገብሬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዓመት ዓመት የተማሪ ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በተለይ በአካቶ ትምህርት ዘርፍ ለመግባት የመጡት ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በቦታ ጥበት ምክንያት ዘንድሮ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከፍተኛ የላብራቶሪ የላይብረሪ፣ የአይሲቲ ማዕከል አለመኖር ከአጋጠሙት ችግሮች ባስ ያለው ነው፡፡
ሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያለበትን የመማሪያ ክፍሎች ጥረት ለመቅረፍ ታስቦ በአማራ አቀፍ ልማት ማኅበር (አልማ) አስተባባሪነት በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ካምፓኒ የተሠሩትን አምስት የመማሪያ ክፍሎችን ለትምህርት ቤቱ ሠርቶ አስረክቧል፡፡ እነዚህ የመማሪያ ክፍሎች እያንዳንዳቸው 42 ዴስኮችን የሚይዙ ሲሆን በአጠቃላይ እስከ 600 የሚደርሱ ተማሪዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ ግንባታው በአንድ ዓመት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሦስት ሚሊዮን ብርም ወጪ እንደተደረገበት የኩባንያው የሕግ አማካሪ አቶ ንጉሡ ዓለሙ በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የመማሪያ ክፍሎች ትምህርት ቤቱ ያለበትን የክፍል ጥበት በጥቂቱም ቢሆን የሚቀርፉ ናቸው፡፡
ለሽምብጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጨማሪና ተመሳሳይ የመማሪያ ክፍሎችን በድጋሚ ለመገንባት ኩባንያው የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡