Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በድራማ የታጀበው የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ምሥረታ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን አሠሪዎች ይወክላሉ የተባሉ ስድስት ፌዴሬሽኖች በሕግ ፊት ዕውቅና አግኝተውና ተመዝገበው እየንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ፌዴሬሽኖኑም የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎት አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የኢትየጵያ ከተሞች ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአማራ ክልል አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አሠሪዎች ፌዴሬሽን የሚባሉት ናቸው፡፡

ከእነዚህ ፌዴሬሽኖች ውስጥ በምሥረታ ቀዳሚው እንደሆነ የሚነገርለት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የዚህን ፌዴሬሽን ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሦስት የአሠሪዎች ፌዴሬሽኖች በምሥረታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በየዘርፉ አሠሪዎችን እንዲወክሉ የተቋቋሙት ፌዴሬሽኖች፣ በተናጠል ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም፣ በሁሉም የሥራ ዘርፍ ያሉትን አሠሪዎች በአንድ ጥላ ሥር ለማሰባሰብ የሚችል ጠንካራ ኮንፌዴሬሽን ለመመሥረት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ሁሉንም ፌዴሬሽኖች በአባልነት አካቶ እንዲፈጠር የተፈለገውን ኮንፌዴሬሽን ለመመሥረት በተደራጀ አግባብ መንቀሳቀስ የተጀመረው ግን ከአሥር ወራት ጀምሮ እንደሆነ ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምስት ፌዴሬሽኖች አማካይነት የተቋቋመውን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን አደራጅ ኮሚቴ በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ጌታቸው ኃይሌ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ምሥረታ ቀደም ብሎ ቢታቀድም፣ ለወራት የዘገየው ካሉት ስድስት የአሠሪዎች ፌዴሬሽኖች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ወደ ኮንፌዴሬሽኑ እንዲገባ ለቀረበለት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠበቅ በመቆየት የተፈጠረ መዘግየት ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የቦርድ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በአዲሱ ኮንፌዴሬሽን ውስጥ እንዲካተት ለቀረበለት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ኮንፌዴሬሽኑን እንዲመሠረት ከተያዘለት ጊዜ ቢዘገይም፣ የተቀሩት አምስቱ ፌዴሬሽኖች በስምምነት ኮንፌዴሬሽኑን ሊመሠርቱት ችለዋል፡፡

ላለፉት አሥር ወራት በምሥረታው ሒደት ላይ ሲንቀሳቀስ የቆየው አደራጅ ኮሚቴ፣ የአደራጅ ምክር ቤት በማቋቋም፣ የአደራጅ ምክር ቤቱን ዓላማና ተግባራትም በተለያዩ አካላት እንዲታወቅ በማድረግና በማወያየት፣ የኮንፌዴሬሽኑን ረቂቅ ሕገ ደንብ  በማዘጋጀት እንዳሳለፈ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ውስጥ እንዲሳተፍና መሥራች እንዲሆን ለኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በደብዳቤ፣ በአካልና በሦስተኛ ወገን የተደረጉ የጥሪ ሙከራዎች አልተሳኩም ተብሏል፡፡

ሌሎቹ ፌዴሬሽኖች ተሰባስበው ኮንፌዴሬሽን መመሥረታቸው ግን ትልቅ ውጤት እንደሚያስገኝ ተገልጿል፡፡ አደራጅ ምክር ቤቱ የባንክ ሒሳብ ከመክፈቱም በተጨማሪ፣ ለምሥረታው የሚያግዙ የፋይናንስ ምንጮችን በማፈላለግ ከምሥረታው በኋላ የሚኖረውን ሒደት ምቹ ለማድረግ መቻሉን የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን የአሠሪዎችን መብትና ጥቅም ከማስክበር ቀዳሚ ተልዕኮው ትይዩ፣ የኢንዱስትሪ ሰላም ሰፍኖ ልማት እንዲፋጠን የሚመከርበት የጋራ መድረክ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አሠሪዎች መብትና ጥቅም በማስከበር በኩል ተደማጭና ተመራጭ መሆን›› የሚል መሪ ዓላማ የያዘው ኮንፌዴሬሽን፣ በይዘቱ የአሠሪና ሠራተኛ ጥቅም ሳይከበር ልማት፣ ልማትም ሳይኖር መብትና ጥቅም እንደሌለ በማመን በሥራ መስክ እንዲህ ያለው ጥምር ጉዳይ ተሳስሮ መጓዝ እንደሚሻ የቦርድ ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከአገራችን ልማት ጋር ተያይዞ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ባለው አደረጃጀት መያዝ እንዳለበት የሥራው ዓለም ቤተሰቦች ሁሉ እምነት ነው፤›› ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ሊመሠረት እንደቻለ ጠቅሰዋል፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ የአጭር ጊዜ ዕቅዶቹን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሁሉን ያሳተፈ (አሠሪው፣ መንግሥት፣ ሠራተኛው፣ ምሁራን፣ የዓለም የሥራ ድርጅት (አይአሌልኦ) እና ሌሎችም) የአሠሪውን መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች የሚቃኙበት አገር አቀፍ የለውጥ ኮንፈረንስ ማዘጋጀት የሚለው ከቀዳሚዎቹ ሥራዎቹ ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ አሠሪዎች በማደራጀትና በፌዴሬሽንነት እንዲሰባሰቡ ማድረግም በአጭር ጊዜ ዕቅዱ ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን፣ የጤና፣ የሚዲያ፣ የትራንስፖርትና መገናኛ ዘርፎች ላይ የሚንቀሳቀሱ አሠሪዎችን በማደራጀት ወደ ፌዴሬሽንነት ማብቃትም ዓላማው ነው፡፡ የግብርናና የአበባ አምራቾች አሠሪዎችን፣ በጥበቃና በሰው ኃይል አቅርቦት መስክ ያሉትን አሠሪዎችም ወደ ፌዴሬሽንነት ለማምጣት ፌዴሬሽኑ የራሱ ቢሮና ማሠልጠኛ ማዕከል እንዲኖረው ማስቻል የሚሉትም በአጭር ጊዜ የሚተገበሩ ናቸው ተብሏል፡፡  

በዚሁ የኮንፌዴሬሽን ምሥረታ ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የዓለም ሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተወካዮች የኮንፌዴሬሽኑን ምሥረታ በማስመልከት አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከምሥረታው ጎን ለጎን በተደረገ ውይይት ወቅት ከቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ውስጥ፣ በተለይ በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ለምን አልተካተተም? የሚለው ጥያቄ አንዱ ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከአደራጆቹ በተሰጠው ምላሽ፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ እንዲሳተፍ መጠየቁ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን በሽምግልና ጭምር ወደ ኮንፌዴሬሽኑ እንዲገባ ብዙ ጥረት መደረጉንም አደራጆቹ አስረድተዋል፡፡ የመንግሥት አካላት ጭምር እንዲያውቁት በማድረግ ኮንፌዴሬሽኑን እንዲቀላቀል ተጠይቆ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ በማለት ለወራት ሲጠበቅ እንደቆየ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ከዛሬ ነገ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ ምንም ምላሽ በመታጣቱ እንጂ፣ ኮንፌዴሬሽኑን እንዲቀላቀል ብዙ ጥረቶች አድርገናል፤››ያሉት የአሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን አደራጆች፣ ፌዴሬሽኑ እንቢተኛ በመሆኑ ምክንያት ሳይካተት እንደቀረ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮንፌዴሬሽኑን እንቢተኛ ስለመሆኑ ስሞታ የቀረበበት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ የተመሠረተበትን 65ኛ ዓመት በማስመልከት በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹ወደ ኮንፌዴሬሽን ለመግባት ጊዜው ሲደርስ ምላሽ እሰጣለሁ›› ብሎ ነበር፡፡ ይሁንና ይህን መግለጫ ባወጣ በቀናት ልዩነት ውስጥ፣ በድጋሚ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ፣ በኮንፌዴሬሽኑ ምሥረታ ዙሪያ መግለጫ ለመስጠት መዘጋጀቱን የሚገልጽ ጥሪ በማስተላለፉ ጋዜጠኞችም መግለጫው ይሰጥበታል ወደ ተባለው ጌትፋም ሆቴል በማቅናት ይሰጣል የተባለውን መግለጫ ቢጠባበቁም የውኃ ሽታ ሆኖባቸዋል፡፡

የተባለው መግለጫ ሊሰጥ ያልቻለው ‹‹ስብሰባችሁ ፈቃድ አልተሰጠውም ተብለናል፤›› በሚል ምክንያት መሆኑ ተገልጾ እድምተኛው ዘጋቢ እንዲበተን ቢደረግም    ብዙዎችን ግር ያሰኘ አንድ ጉዳይ ግን መከሰቱ አልቀረም፡፡ ሰፊ የግድግዳ ጽሑፍ የተጻፈበት ንጣፍ በሆቴሉ አዳራሽ ውስጥ እንዲሰቀል ተደርጎ፣ የፌዴሬሽኑ አባላትና ፕሬዚዳንቱ በዚያው ፖስተር ሥር ፎቶ እንዲነሱ ተደረገ፡፡ በፖስተሩ የሸፈረው ጽሑፍ ‹‹የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን ምሥረታ፤›› የሚል ነበር፡፡ ነገርየው በቦታው የነበሩትን የፌዴሬሽኑን አባላት ጭምር ግር ያሰኘ ሲሆን፣ የምን ኮንፌዴሬሽን ምሥረታ ነው በማለት ሲጠይቁ የነበሩም አልታጡም፡፡

ከፎቶ መነሳቱ ፕሮግራም በኋላ ስብሰባውን ማካሄድ ስለማንችል ነገ ጠዋት እንድትገኙ በመባሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ይተላለፋል የተባለው መልዕክትም በዚያው ይቀራል፡፡ ሆኖም ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አምስቱ ፌዴሬሽኖች በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል ተገናኝተው የኮንፌዴሬሽን ምሥረታ እያካሄዱ በነበሩበት ወቅት፣ አቶ ታደለ ይመር የሚመሩት የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ ከዛሬ ጀምሮ ኮንፌዴሬሽን መሥርቻለሁ ብሎ መነሳቱ ግርታ ፈጥሯል፡፡

አምስቱ ፌዴሬሽኖች የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንን በይፋ ካቋቋሙ በኋላ በአቶ ታደለ ይመር የሚመራው ፌዴሬሽን ግን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን በሚል ስያሜ መመሥረቱን አስታውቋል፡፡

ይህ የተወነባበደ አካሄድ እንዴት ተፈጠረ የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ 65ኛ ዓመቱን ለማክበር በጠራው መግለጫ ወቅትም ስለኮንፌዴሬሽን ምሥረታው የገለጸው ነገር ባለመኖሩ አካሄዱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በአገሪቱ ስድስት ፌዴሬሽኖች መኖራቸው ቢታወቅም፣ አምስቱ ተጣምረው ኮንፌዴሬሽን እንደመሠረቱ ቀደም ብለው አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ታደለ የትኞቹን ፌዴሬሽኖች ይዘው ነው ኮንፌዴሬሽ የመሠረቱት አሰኝቷል፡፡

የአዲሱ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጌታሁን (ኢንጂነር) ግን ‹‹ይህ አውቀው ለማደናቀፍ ያደረጉት ነው፤›› በማለት ወርፈዋቸዋል፡፡ ‹‹እኛ ኮንፌዴሬሽኑን ለመመሥረት ቀን ስንቆጥር የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በጎን በኩል አስቸኳይ ጉባዔ ጠርቶ ኮንፌዴሬሽን መሥርቻለሁ ማለቱ እኛን ለማደነቃቀፍ የታሰበ ቢሆንም የተሠራው ሥራ ሕጋዊ መሠረት የለውም፤›› በማለትም አጣጥለውታል፡፡ ኮንፌዴሬሽን የሚፈጠረው በፌዴሬሽኖች ጥምረት በመሆኑ ‹‹የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን መሠረትኩ የትኞቹን ፌዴሬሽኖችን ይዞ እንደሆነ ግራ ያጋባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በሕግ የተመዘገቡትና ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው አምስቱ ኮንፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽኖችን መሥርተዋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን መሠረትኩ ያለው ኮንፌዴሬሽን ሕጋዊ አይደለም፡፡ አምስቱ ፌዴሬሽኖች የፈጠሩት ጥምረት የተቋቋመው ኮንፌዴሬሽን በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳ ሚኒስትር ታውቆ በምሥረታው ወቅትም የሚኒስቴሩ ተወካይ ተገኝተው ለኮንፌዴሬሽኑ ምሥረታ ዕውቅና ሰጥተዋል፤›› በማለት የይገባናል ጥያቄውንና ተቃውሞውን አጠናክረዋል፡፡

የዓለም የሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተወካዮች አረጋግጠውታል በተባለውና የአምስቱ ፌዴሬሽኖች ጥምረት መሠረት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽንን እንዲመሩ አቶ ጌታሁን ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፣ አንድ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ ስድስት የቦርድ አመራር አባላት ተመርጠዋል፡፡

ይህ በሆነ በማግሥቱ ግን የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን የተመሠረተበትን 65ኛ ዓመቱን በሸራተን አዲስ ባከበረበት ወቅት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ሲናገሩ፣ ኮንፌዴሬሽን ባቋቋምን ማግሥት ይህንን በዓል ማክበራችን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የፌዴሬሽኑን እንቅስቃሴ አወድሰው፣ ወደፊት ለሚያደርገው እንቅስቃሴም የመንግሥት ዕገዛ አይለየውም ብለዋል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይና በኢትዮጵያ የዓለም ሥራ ድርጅት ተወካይ የአጋርነት ንግግር አሰምተዋል፡፡ 65 ዓመታት ያስቆጠረው ይህ ፌዴሬሽን ለአፍሪካውያን ምሳሌ ስለመሆኑም ታውሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች