Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረብኩ ስለሆነ እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ›› ዋና ኦዲተር...

‹‹ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረብኩ ስለሆነ እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ›› ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ

ቀን:

ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የኦዲት ችግር የያዘ ሪፖርት አቅርበዋል

ከተሾሙ አንስቶ ለዘጠነኛ ዓመታት ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ያቀረቡት ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ፣ ለዘጠነኛ ዓመት ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረቡ መሆኑን በመጥቀስ የፓርላማ አባላት እንዲሰሟቸውና ግፊት እንዲያደርጉ ጠየቁ፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ሐሙስ ግንቦት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በ59 ገጾች ተጨምቆ የተጠናቀረ የ2009 ዓ.ም. የኦዲት ግኝት ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ተስፋ የቆረጡ የሚመስሉ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በታብሌት ኮምፒዩተራቸው ቪዲዮዎችን በኢንተርኔት ሲመለከቱ ለማየት ተችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በተለያዩ የኦዲት ዘርፎች የደረሰባቸው የኦዲት ግኝት በድምሩ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ያልተሰበሰቡ ውዝፍ ገቢዎች፣ ያልተወራረዱና ደረሰኝ ያልተገኘላቸው ወጪዎች፣ ለማን እንደሚከፈሉ ያልታወቁና ለረጅም ዓመታት የተወዘፉ ተከፋይ ሒሳቦች፣ ሕግን ያልተከተሉ ግዥዎችና ከበጀት በላይ መጠቀምን ያመለክታል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ያቀረቡት ሪፖርት በ173 የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የኦዲት ምርመራ ግኝትን ያካተተ ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ አያያዝና አጠባበቅ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት፣ ከአምስት መሥሪያ ቤቶች 927,522 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

የሒሳብ ሰነድ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ በ116 መሥሪያ ቤቶች 5.8 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱን፣ ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ በሌሎች አሥር መሥሪያ ቤቶች 1.3 ቢሊዮን ብር ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተያዘ፣ ከማን እንደሚሰበሰብ በቂ ማስረጃ ባለመኖሩ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች መሠረት የመንግሥት ገቢ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በሌሎች ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 1.5 ቢሊዮን ብር አለመሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰቡን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት 6.2 ቢሊዮን ብር በወቅቱ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መገኘቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ግብር ከፋዮች ያቀረቡት ቅሬታ በፍጥነት መፍታት ባለመቻሉ 1.6 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሰበሰብ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

የተሟላ ማስረጃ መቅረቡን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት በ68 መሥሪያ ቤቶች የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 5.6 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ ደግሞ 98 መሥሪያ ቤቶች ከ190 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጋቸውን ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው ጠቁመዋል፡፡

የግዥ ደንብና መመርያ ሳይከተሉ 97 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 487.9 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን፣ ሌሎች ዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች ደግሞ ያለ ንብረት ገቢ ደረሰኝ 1.8 ቢሊዮን ብር መክፈላቸውን ገልጸዋል፡፡ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ ሒሳብ ላይ 110 ሚሊዮን ብር በ19 መሥሪያ ቤቶች ተመዝግቦ መገኘቱንም ዋና ኦዲተሩ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ በሌሎች 74 መሥሪያ ቤቶች በተከፋይ ሒሳብ ሥር 789.6 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ተከፋይ መገኘቱን፣ ከዚህ ውስጥ 177 ሚሊዮን ብር ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅና 580 ሚሊዮን ብር የቆይታ ጊዜው የማይታወቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት 41 መሥሪያ ቤቶች 898 ሚሊዮን ብር ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ተጠቅመው መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ አቶ ገመቹ ሪፖርቱን ካረቀቡ በኋላ በምክር ቤቱ አባላት ተጠያቂነት ማስከበርን በተመለከተ ተጠይቀው፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ ዘጠነኛ ሪፖርቴ ነው፣ ተመሳሳይ ሪፖርት እያቀረብኩ ነው ያለሁት፤›› ያሉት ዋና ኦዲተሩ፣ ዕርምጃ ቢወሰድና መቅጣት ቢጀመር ኖሮ አንድ ቦታ ይቆም እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹እንድትሰሙኝ እፈልጋለሁ›› ያሉት አቶ ገመቹ፣ ‹‹ችግሮቹ አንድ ቦታ የሚቆሙበት መፍትሔ ተሰጥቶ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሻገር ይኖርብናል፤›› ሲሉ ተስፋ መቁረጥን የቀላቀለ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

አሁን የተሾሙት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በራሳቸው ተነሳሽነት እንዳናገሯቸው የጠቆሙት ዋና ኦዲተር ገመቹ፣ ይህንኑ ሪፖርት መሠረት በማድረግ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚያስተላልፉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...