Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለብሔራዊ መግባባት የማይጠቅሙ አፍራሽ ድርጊቶች ይምከኑ!

ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን በትጥቅ ትግል አስወግዶ ሥልጣን ከያዘ 27 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እነዚህ 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ክስተቶችን አስተናግደዋል፡፡ ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራላዊ ሥርዓት በመሸጋገር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች በርካታ ጉዳዮች ተከናውነዋል፡፡ በፖለቲካው መስክ አሁንም አወዛጋቢ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች ከችግሮች ጋር ተሁኖም በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሮ ፖለቲካዊ ችግሮች መፈታት ከቻሉ ደግሞ ወደፊት አንፀባራቂ ስኬቶች መመዝገባቸው አይቀሬ ነው፡፡ የኢሕአዴግ 27 ዓመታት በሚዛናዊ ዓይን ከታዩ ሰላምና ዴሞክራሲ ማስፈን ከተቻለ፣ ኢትዮጵያን ለዘመናት ከነበረችበት አረንቋ ለማውጣት ይቻላል፡፡ ትልቁ ቁልፍ ግን ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ለሚረዱ ተግባራት ራስን በቁርጠኝነት ማዘጋጀት ነው፡፡ ሰላም የሚኖረው የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በፍትሐዊ መንገድ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ምኅዳር ሲኖር ነው፡፡ ልማት የሚኖረው በኢትዮጵያዊያን ሙሉ ስምምነት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መቀየስ ሲቻል ነው፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት እንደ ጎዶሎ ይታይ የነበረው በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መግባባት አለመቻሉ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረቱን፣ ጭቆና ተወግዶ ዴሞክራሲና እኩልነት ማበቡን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ፍትሐዊ ተጠቃሚ የሆኑበት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መመዝገቡን፣ የቡድንና የግል መብቶች እንዲከበሩ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን፣ የአገሪቱ ገጽታ እንዲለወጥ መደረጉን፣ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፈጠሩን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጎልበቱን፣ የዲፕሎማሲ ስኬት ማግኘት መቻሉን፣ ወዘተ የግንቦት ሃያ ስኬት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ምንም እንኳ በብዙ ጉዳዮች ላይ መስማማት ባይቻልም፣ ባለፉት 27 ዓመታት በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ለውጦች መታየታቸውን መቼም ቢሆን መካድ አይቻልም፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን በእነዚህ ተገኙ በተባሉ ውጤቶች ላይ ምን ያህል ስምምነት አለ? ከሌለስ ምክንያቱ ምንድነው? በማለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የደርግ መንግሥት ተወግዶ የሽግግሩ መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በተቃውሞ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ ግለሰቦች፣ ኢሕአዴግ የተገኘውን ወርቃማ አጋጣሚ አበላሽቶታል ይላሉ፡፡ ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ተጠራቅመው ባለፉት ሦስት ዓመታት የተከሰቱት አመፆችና ተቃውሞዎች በአገር ላይ የፈጠሩት ቀውስ ከባድ ነበር፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሕይወት መስዋዕትነትና የንብረት ውድመት ሊደርስ የቻለው ብሔራዊ መግባባት በመጥፋቱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንዳመነው የችግሮች ሁሉ ባለቤት ራሱ ነበር፡፡ በውስጡም መሰነጣጠቅ ተፈጥሮ ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩ አይዘነጋም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በቃኝ ብለው አዲሱ የተተኩት ግለቱ ከባድ ስለነበር ነው፡፡

ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንቅፋት ከሆኑት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የኢሕአዴግ የጠቅላይነት ባህሪ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት የተፈጠረው ትርምስና ከጊዜ በኋላ የተወሰዱት ዕርምጃዎች፣ ተስፋ የተጣለበትን ዴሞክራሲ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርገውታል፡፡ በተለይ ከምርጫው በኋላ የወጡት የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕግ፣ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕግ የአገሪቱን መልካም አጋጣሚ አጨልመውታል፡፡ በፖለቲካውና በሚዲያ ውስጥ የነበሩ በርካታ ወገኖች ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ የሐሳብ ልዩነት ያላቸው እንደ ጠላት እየታዩ ብዙዎች እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች ተጥሰዋል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ዕምቅ አቅም የነበራቸው ወገኖች ‹ጎመን በጤና› እንዲሉ ተገደዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ አደገኛ በመሆኑ ቅራኔዎችና ብሶቶች እንዲደራረቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሥርዓቱን ለጥቅም ሲሉ የተጠጉ ደግሞ ሙሉ ትኩረታቸው ዘረፋ ላይ በማተኮሩ ፍትሕ ጠፍቷል፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌለበት ግለሰቦች ራሳቸውን ሕግ እስከ ማድረግ ደርሰዋል፡፡ የአገር ሀብት እየተዘረፈ ጥቂቶች እንደፈለጉ ሲሆኑበት ጠያቂ በመጥፋቱ፣ አገር የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ተጠራቅመው ነው የአገርን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጥ ቀውስ የተፈጠረው፡፡

የፌዴራል ሥርዓቱ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በእርግጥም ክልሎች የራሳቸውን መስተዳድር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ዳኝነት፣ ወዘተ በሚፈልጉት መንገድ የሚጠቀሙበት ሥርዓት ተመሥርቷል፡፡ ይህ ሥርዓት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ በማተኮሩ ኅብረ ብሔራዊ አገር ለመገንባት አላስቻለም፡፡ በሐሳብ ደረጃ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መገንባቱ ቢነገርም፣ አሁንም ይኼንን ምኞት የሚይሳይ ተጨባጭ ነገር የለም፡፡ በመላ አገሪቱ ተዘዋውሮ መሥራት፣ ሀብት ማፍራትና የመሳሰሉት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እየተጣሱ ነው፡፡ ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ በግድ ከመፈናቀል ጀምሮ እስከ ሕይወት ማጣት ድረስ አሁንም አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን እንደ ባዕድ የሚያዩ ሹማምንትና መሰሎቻቸው ዛሬም ዜጎችን ያፈናቅላሉ፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ እንቅፋት የሆኑበትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለኢትዮጵያዊያን የሚመች አኗኗር ማምጣት የሚቻለው፣ ከእልህና ከቂም በመላቀቅ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን የሚቻለው ተቀምጦ መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት የሚደረገውን ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚቻለው የዘመናት ቁርሾን አስወግዶ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር ፈቃደኝነቱ ሲኖር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይህ ዓይነቱ ቀና መንገድ እንዲጀመር ተግባራዊ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ቃል መግባታቸው ያፅናናል፡፡ ጅምሮችም ይታያሉ፡፡ ይህ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድና ሕዝብም የሚረዳበት አግባብ ለየቅል መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቅርቡ ዕድገቱ ለሕዝቡ የፈየደው ምንድነው የሚለው ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በድህነት ውስጥ የሚማቅቅ ሕዝብ አገሪቱ እያደገች ነው ሲባል፣ ይኼንን ዕድገት የሚረዳው ጥቂቶች እንደሚቀማጠሉበት አድርጎ ነው፡፡ ከኖሩበት ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ከተማ ውስጥ የተገጠገጡ ሕንፃዎችን እየተመለከቱ የጥቂቶች መክበሪያ መሆናቸውን ካመኑ፣ ልማቱም ሆነ ዕድገቱ ለእነሱ ባዕድ ነው፡፡ የከተሞች ዕድገት ቁሳዊ ነገሮች ላይ አተኩሮ ሰብዓዊው ጉዳይ ሲዘነጋ ሕዝብና መንግሥት እንዴት ይግባባሉ? ከነባር ይዞታቸው በልማት ስም የተነሱ ከእነ ቤተሰቦቻቸው ተሽቀንጥረው ሲጣሉና እዚህ ግባ የሚባል ካሳ ሳያገኙ ሲቀሩ ልማት የሚባለው ነገር ይጎመዝዛቸዋል፡፡ የአገር አንጡራ ሀብት የግለሰቦች ሲሳይ ሲሆንና ፕሮጀክቶች ሲመክኑ በምን ተዓምር ነው ሕዝብ ለልማቱ የባለቤትነት ስሜት የሚሰማው?  የአገር ብልፅግና ባለቤት ሕዝብ መሆን ሲገባው ተሳትፎው በመገደቡ ብቻ በርካታ ጥፋቶች ደርሰዋል፡፡ ለዓመታት ሲንተከተኩ የነበሩ ብሶቶች ገንፍለው ደግሞ አገር ተተራምሳለች፡፡ ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው የተረጋጋችና ለሁሉም እኩል የሆነች አገር ለመፍጠር ነው፡፡

ያለፉት 27 ዓመታት ጉዞን አሁንም ከስኬት ጋር ብቻ ለማያያዝ የሚፈልጉ አሉ፡፡ ይኼ ራስን ማታለል ነው፡፡ የወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታም እየተናገረ ያለው በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሉ እየዞሩ ከሕዝብ ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች የተሰሙት ድምፆች ይኼንን ያረጋግጣሉ፡፡ አንድ ተስፋ ግን አለ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር አሁንም ለአገሩ ካለው ጥልቅ ፍቅር አኳያ፣ በአንድነት የመኖርን ፍላጎት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንፀባረቀ ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ይኼንን የሕዝብ ፍላጎት መሠረት በማድረግ የዓመታት ጥላቻቸውን  ያስወግዱ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ እንዲከፈትና እነዚያ ያመለጡ ወርቃማ ዕድሎች እንደገና እንዲያቆጠቁጡ ተግተው ይሥሩ፡፡ በቅድመ ሁኔታ የታጠሩ የሸርና የሴራ ብልጣ ብልጥነቶች ይብቃቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ የምትችለው በአንድ ጎራ የበላይነት ሥር እንዳልሆነ ከበቂ በላይ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ እንቅስቃሴዎች ፋይዳ ስለሌላቸው ቀልብን በመሰብሰብ ለውይይትና ለድርድር መቀመጥ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ካሁን በኋላ እስር ቤት መሆኗ ይቁም፡፡ የታሰሩ ተፈተው ሰላም ይስፈን፡፡ ሳይወዱ በግድ ከአገራቸው ተሰደው የወጡ ወገኖች በሰላም ተመልሰው ከወገኖቻቸው ጋር ይቀላቀሉ፡፡ ለቂም፣ ለበቀልና ለጥፋት የሚያሰፈስፉ አንደበቶችና እጆች ይታቀቡ፡፡ ለብሔራዊ መግባባት የማይጠቅሙ አፍራሽ ድርጊቶች ይምከኑ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...