Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹እንጫወት እንጂ ገሩን ገራገሩን . . .!›

ሰላም!  ሰላም! የተወደዳችሁ ወዳጆቼ እንደምን ከርማችኋል? እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እኔ እንዳማረብኝ፣ ጠላቴም እንደቀናብኝ አለሁ፡፡ ባሻዬ ‹ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም› ብሎ ሰለሞን ጠቢቡ ቀድሞ ተናግሮታል ያሉትን ነገር መጠራጠር ጀምሬያለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የማየውና የምሰማው ሁሉ አዲስ እየሆነብኝ ነው፡፡

የባሻዬ ልጅም ቢሆን ‹‹አዲስ ነገር ማየት ጀምረናል›› በማለት ከእኔ ሐሳብ ጋር ሲተባበር ነበር፡፡ ‹‹የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እየተመሰጥኩበት ነው፤›› ያለኝ ግን ትንሽ አስፈግጎኛል፡፡ ‹‹አሁን ከቤተ መንግሥት አካባቢ የሚወጡት ዜናዎች በናፍቆት የምጠብቃቸው ሆነዋል፡፡ ያውም ደግሞ ድንቁ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ምን የመሳሰሉ ጎሎችን እያስቆጠሩልን በደስታ እያስጨበጨቡን ይገኛሉ፤›› ብሎ ብቻም አላበቃም፡፡

‹‹ፍፁም ልንገምታቸው አልቻልንም እኮ? በታሰሩት ሲገርመን በግፍ ተገድለው የሞቱትን የወንድሞቻችንን አስከሬን አስመጣለሁ በማለታቸው፣ የኢትጵያዊነት ስሜቴን አንድ ዕርከን ወደ ላይ ከፍ አድርገውልኛል፤›› በማለት አብራራልኝ፡፡ እኔም ቀበል አድርጌ፣ ‹‹በዚህ አካሄድ ቁፋሮ ከቀጠለ ወርቅ የለ፣ አልማዝ የለ፣ በመላው አገሪቱ ውስጥ የተሰወሩ የከበሩ ማዕድናት ሁሉ እየወጡ፣ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚውሉበት ጊዜ እነሆ በደጅ ነው የሚል ሐሳብ ቢጤ ወደ አዕምሮዬ መጣብኝ፡፡

ባሻዬም ፈገግ ብለው፣ ‹‹በዚህ አካሄዳቸው የታሰረውን ከእስር ቤት፣ የሞተውን ከመቃብር ካወጡ ወደፊት ማዕድኑን ከምድር ሆድ፣ አመፀኝነትና ዘረኝነትን ደግሞ ከሰው ሆድ ውስጥ አውጥተው እንደሚያስወግዱ እናምናለን፤›› አሉ፡፡ ባሻዬ ዘመንን ወደኋላ አሸጋግረው በምናብ እያዩ ይመሰጣሉ፡፡ ‹‹ልጅ አንበርብር በሁለት ወራት ውስጥ ይህንን ያሳየን አምላክ በሁለት ዓመታት ምን ሊያሳየን እንደሚችል ይታሰብሃል? እኔማ በህልሜ ነው በውኔ እያልኩ እደነቃለሁ፡፡ ቸርነቱ የማያልቅበት አምላክ እንዲህ እያስደነቀን በሰላም ያስቀጥለን . . . ›› እያሉም ይፀልያሉ፡፡   

ማንጠግቦሽ እንኳን በአቅሟ ዋና ኮሚክ ሆናልኝ አርፋዋለች፡፡ እንዲህም እያለች ስትኮምክ ሰምቻት ፈገግ አልኩ፣ ‹‹ወደፊት ሄድ መጣ የምትለው ቧንቧችን ትዝታ ሆና፣ ባለአምስት ጡት ቧንቧ በየቤታችን ተገጥሞልን የፈለግነውን እየተጫንን እንጠጣለን፤›› ስትለኝ እየሳቅሁ፣ ‹‹ደግሞ ምን የሚሉት ቧንቧ ነው አምስት ጡት ያለው?›› በማለት ጥያቄ ሰነዘርኩላት፡፡ እሷም እየሳቀች እንዲህ በማለት አስረዳችኝ፣ ‹‹ወደፊት በቧንቧ የሚመጣልህ ውኃ ብቻ አይደለም፡፡ ስትፈልግ ወተት የሚለውን ቁልፍ ስትጫን ወተት ከተፍ ይልልኃል፡፡ ቡና የሚለውን ቁልፍ ስትጫን ደግሞ ሌላ ምርጫ ይሰጥኃል፡፡ ይርጋ ጨፌ፣ ሲዳማ፣ ኮቸሬ፣ ወዘተ እያልክ አንተም የምትፈልገውን ቁልፍ ትጫናለህ፡፡ እርጎም ብትፈልግ ወይ ደግሞ የምትወደው ቢራ ሲያምርህ ቁልፉን ብቻ መጫን ነው፡፡ እቤትህ ድረስ በቧንቧህ ይመጣልኃል፡፡ ይህንን ሳናይማ አንሞትም የእኔ ውድ  . . . ›› ብትለኝ አንቺን ነበር የግብዓቶች ሚኒስትር ማድረግ ብዬ አቅፌ ሳምኳት፡፡

የማንጠግቦች ቅዠት ህልም ሆኖ ህልሟ ደግሞ ዕውን ሆኖ የምናይበት ኢትዮጵያ ትፈጠር ይሆን? ባሻዬ እንደሚሉት ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፡፡ ቤታችን ቁጭ ብለን ዘመናዊውን ከባለ አምስት ጡት ቧንቧ ቁልፍ መካከል ወተት የሚለውን ቁልፍ ሲጫኑት ወዲያው ከዝርዝር ውስጥ የላም፣ የፍየል፣ የግመል፣ የዱቄት ወተት ብሎ ምርጫ ሲቀርብ ይታሰባችኋል? በምርጫችን መሠረት የግመል ወተት የሚለውን ቁልፍ ስንጫን፣ ከዚያ ለበርካታ በሽታዎች መድኃኒት ነው የተባለውን የግመል ወተት ሲናጣጥም፣ መቼ ይኼ ብቻ መብራት መጥፋት የሚለው ተረት ተረስቶ በርካታ አምፖሎች በቤታችን ተሰቅለው፣ በኅብረ ቀለም ደምቀው በብርሃን ሲያንቆጠቁጡን ማየት፣ አገራችን በአፍሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ሆና ብትሸጥ፣ ታላቅ አገር ሆኖ ከምናገኘው ሀብት ብዛት ውኃ፣ መብራት፣ ወተት፣ በነፃ በየቤታችን ሲመጣልን የምናይበት ዘመን አይመጣም ብልን መፍራት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ባሻዬ ሁሉንም ብለውታል፡፡ ለሚያምን ሁሉም ይቻላል በማለት፡፡

ታላቁ አትሌት ይቻላል በሚለው መፈክሩ የማይቻለውን ችሎ በተግባር አሳይቶናል፡፡ የእርሱ ጥረት ላይ ባሻዬ ያሉትን እምነት ቢጤ ጣል አድርገንበት ለሚያምን ሁሉ ይቻላል በማለት ወደ ግባችን የምንነጉድበት ጊዜ ነው፡፡ በጥረት ላይ እምነት ያስፈለገበት ዋነኛው ምክንያት፣ ተረት ብቻውን የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ሰው ማመን አለበት፡፡ ማሸነፍ እችላለሁ ብሎ ማመን አለበት፡፡ መለወጥ እችላለሁ ብሎም ማመን አለበት፡፡ በዚህ መሠረት የተለወጠችና የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት ይቻላል በማለት ማመን ነው፡፡

ምሁሩ የባሻዬ ልጅም ቢሆን፣ ‹‹እንግዲህ አባቴ እንዳልከው ልስማማና ልመን፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን ሳተላይት ስታመጥቅ፣ ለኃይል የሚሆን የኑክሌር ጣቢያ ስትገነባ፣ በቴክኖሎጂ ከቀደሙት አገሮች ተርታ ተሠልፋ የአገሬ ድምፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ሲያገኝ፣ ደሃ የሚለው ስማችን ተፍቆ በምትኩ ከሀብታሞች ተርታ ሆነን አፋችንን ሞልተን ጮክ ብለን ስንናገር፣ አባቴ ሆይ እኔም አምናለሁ ይቻላል፤›› በማለት የማይቻለው ይቻላል ብለው ከሚያምኑት ተርታ ተደረደረ፡፡

ባሻዬ የሁልጊዜም ፀሎታችን ይኼው ነበር፡፡ አገራችን በሩጫው መድረክ ያገኘችውን ድል በእግር ኳስ ደግማው መመልከት፡፡ የባሻዬ ልጅ ሕዝቡ ሁሉ ከየቤቱ ወጥቶ የኢትዮጵያን ብሔራዊ መዝሙር እየዘመረ፣ የዓለም ዋንጫን ይዘው ለመጡት ኢትየጵያውያን አቀባበል ሲያደርግ ማየት የምንችልበት ዘመን መቼም ሩቅ አይሆንም በማለት ሲናገር ነበር፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ? አሁንም መልሱ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል የሚል ይሆናል፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ጽፎ ጮክ ብሎ አነበበልኝ፡፡ ‹‹ግልጽ ማሳሰቢያ ለዓለም ዋንጫ! ሰላምታችን ባለሽበት ሩሲያ ይድረስሽ፡፡ የሩሲያን ቅዝቃዜ ተቋቁመሽ ሊያሞቁሽ ከመላው ዓለም የሚመጡትን ሰዎች እየተጠባበቅሽ እንደምትገኚ እናውቃለን፡፡ እንዲያው እንዳለመገጣጠም ሆኖ እኛ መጥተን ልንወስድሽ በዚህኛው ዙር ባይቻለንም እንኳን፣ በውስጣችን ታላቅ እምነት ሰንቀናል፡፡ ልጆቻችን የገባሽበት ገብተው ታላላቆቹን የእግር ኳስ ኃያላን ረትተው ወደ ምድራችን ይዘውሽ እንደሚመጡ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ቤትሽ ናት፡፡ ማነው ብራዚል ብቻ ነው ቤትሽ ያለው? ማነው ጀርመን ብቻ ነው ቤትሽ ያለው? ማነው እንግሊዝ ብቻ ነው ማደሪያሽ ያለው? ኢትዮጵያም ቤትሽ ነው፡፡ መኖሪያሽ መክረሚያሽ እነሆ! የእኛ ሆነሽ የምንጨፍርበትን ጊዜ እንደምናየው ሙሉ እምነቴ ነው፤›› ሲል ባሻዬ ካሉት አንዳች እንኳን ቃል መሬት ጠብ እንደማይል ማረጋገጫ የሆነ መሰለኝ፡፡

እነሆ የዓለም ዋንጫን ለጉብኝት ብቻ ሳይሆን ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት ተጋድሎ አሸንፈን እንደምናመጣ እናምናለን፣ አምነንም እንናገራለን፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን አልፈን የዓለም ዋንጫ ላይ ቂብ የምንለበት ዘመን ገስግሶ እየመጣ ነው፡፡ እነሆ ሩሲያ በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ማጠራቀም ጀምሬያለሁ፡፡ ወጪዋን ቀነስ ገቢዋን ጨመር እያደረኩኝ እገኛለሁ፡፡ ምንም እንኳን ቀዳዳው ሺሕ ምንጩ አንድ ቢሆንም፡፡ አሁን በቀየስኩት ስትራቴጂ እየተመራሁ ቀዳዳዎችን በመድፈን ምንጮችን ማብዛት የዕለት ተዕለት ተግባሬ አድርጌያለሁ፡፡

ማን ያውቃል ሩሲያ ድረስ ዘልቄ አንዱን ባለሀብት ጎትቼ ላመጣው ነው ያሰብኩት፡፡ ምን ዓይነት ባለሀብት ካላችሁኝ ልክ እንደ ቼልሲ ሩሲያ ባለሀብት ሮማን አብራሞቪች ዓይነቱን፡፡ እዚህ መጥቶ አንድ ሁለት ቡድኖችን ቢገዛ ሊፈጠር የሚችለውን ተሃድሶ መገመት አያዳግትም፡፡ እግር ኳሳችን ላይ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች ጠምተውኛል፡፡ የዚያኔ አርሰን ቬንገር ሳይቀሩ ‹በልጆች ላይ መሥራት እፈልጋለሁ ብለው ትኬታቸውን ቆርጠው ወደ አዲስ አበባ ከች ይሉልናል› ማለት ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ መልሱ አንድ ነው ‹‹ለሚያምን ሁሉ ይቻላል››፡፡ በሌላ ኳስ ከመደባደብና የአገር ስም ከማጥፋት እንዲህ መመኘትና ለሥራ ታጥቆ መነሳት አይሻልም? ‹እንጫወት እንጂ ገሩን ገራገሩን አሁን ምን ያደርጋል የምሩን የምሩን› ያለው ማን ነበር? መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት