Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየነዳጅ ፖለቲካውና ውዝግቡ

የነዳጅ ፖለቲካውና ውዝግቡ

ቀን:

እ.ኤ.አ. 2015 ሲገባደድ አብዛኞቹ የዓለም ነዳጅ አምራች አገሮች የነዳጅ ዋጋ ከወደቀበት ይነሳል የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡ ሆኖም 2016 ብሩህ ተስፋ ይዞ ብቅ አላለም፡፡ ይልቁንም የነደጅ ዋጋ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ ወይም ከዚህ ጊዜ በኋላም፣ ከዚህ ቀደም የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 115 ዶላር ደርሶ እንደነበረው መልሶ እንደማያሻቅብ የኦይል ፕራይስ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የኃይል ሚዛን ያናጋዋል ነው የተባለው፡፡

በተለይ ከሳዑዲ ዓረቢያ እስከ ሩሲያ እንዲሁም ሌሎቹ የነዳጅ ሀብት ያላቸው አገሮች፣ በነዳጅ አቅራቢነታቸውም ሆነ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ያላቸው ጫና የመፍጠር አቅም ይላሽቃል ተብሏል፡፡

የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 115 ዶላር በተሸጠበት እ.ኤ.አ. በሰኔ 2014 የኢኮኖሚ ተንታኞች የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር እንደማይወርድ፣ ከ115 ዶላር በላይ ሆኖም ለረዥም ጊዜ እንደሚቆይ ተናግረው ነበር፡፡ ሆኖም የኢኮኖሚስቶቹ ትንበያ የነዳጅ ክምችታቸውን ጠብቀው የቆዩት ካናዳና አሜሪካ ተጨማሪ ነዳጅ ወደ ማውጣቱ እንዲገቡ ነበር የመራቸው፡፡ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 50 ዶላር ዝቅ ያለውና የገነነው የነዳጅ ዋጋ ለብዙ ዓመታት ሳይዘልቅም ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከ15 ቀናት በፊት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 33 ዶላር ወርዷል፡፡ አሁን ደግሞ ከ30 ዶላር በታች፡፡ ይህ ከ18 ወራት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በሁለት ሦስተኛ ቀንሷል፡፡ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ እንደሚለው፣ የነዳጅ ዋጋ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ50 ዶላር እስከ 60 ዶላር፣ እስከ 2040 ድረስ ደግሞ ከ85 ዶላር በላይ አይወጣም፡፡ ይህ የሚያሳየው የዓለም ነዳጅ ዋጋ መውደቅን ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚውንም መንኮትኮት ነው፡፡

አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ለትልልቆቹ የነዳጅ አምራቾች፣ እንዲሁም ከነዳጅ ማውጣት ጋር ትስስር ያላቸው ሌሎች ንግዶች ላይ የሚያደርሰው ውድቀት ቀላል አይደለም፡፡

የነዳጅ ሀብት ካላቸው አገሮች በተጨማሪ ነዳጁን ለማውጣት ከባድ ማሽነሪዎችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎችና የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ከነዳጅ ዋጋ ውድቀቱ ጋር አብረው የሚሽመደመዱ ናቸው፡፡

የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ የነዳጅ ሀብት ያላቸው አገሮችም በንፋሱ ይመታሉ፡፡ ናይጄሪያ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ሩሲያና ቬንዙዌላ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውዝግቡ ውስጥ ከገቡ ነዳጅ አቅራቢ አገሮች ተርታ ይጠቀሳሉ፡፡

የነዳጅ ዋጋ ሊጨምር የሚችለው በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ኢኮኖሚ መሻሻል ሲያሳይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍላጐት ሲጨምር፣ አቅራቢዎች በከፍተኛ አቅማቸው ማቅረብ ሲጀምሩና በማከማቻ ሥፍራዎች ያሉ ቁሳቁሶች ሲመናመኑ የነዳጅ ዋጋ ከኢኮኖሚው ጋር አብሮ ያድጋል፡፡ ሆኖም የዓለም ኢኮኖሚ እያሽቆለቆለ ወይም ባለበት እየረገጠ ባለበት ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም ያለውን የኃይል ሚዛን ያዛባል፡፡

የነዳጅ ዋጋው መቀነስ ነዳጅ ወደ ውጭ የሚልኩ አገሮች ገንዘባቸውን ተጠቅመው ያቆዩት የበላይነት ላይ ጥላ እያጠላ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ማብቂያ የናይጄሪያ መንግሥት 75 በመቶ፣ ሩሲያ 50 በመቶ፣ ቬንዙዌላ 40 በመቶ ያህሉን ገቢ ያገኙት ከነዳጅ ሽያጭ ነበር፡፡

በናይጄሪያ ከተንሰራፋው ሙስና በተጨማሪ የነዳጅ ዋጋ መውደቁ፣ የጉድላክ ጆናታን መንግሥት በምርጫ እንዲሸነፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁን አገሪቱን እየመሩ ያሉት ሙሐሙዳ ቡሃሪ ለምርጫ ሲቀሰቅሱም የናይጄሪያን ኢኮኖሚ በነዳጅ ላይ ብቻ ከመንተራስ አውጥተው በሌሎች ዘርፎችም እንዲደገፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውም ለመመረጣቸው ምክንያት ሆኗል፡፡

ቬንዙዌላ ተመሳሳይ የፖለቲካ ቀውስ ገጥሟታል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ቬንዙዌላን ይመሩ የነበሩት ሟቹ ሁጐ ሻቬዝ ለደሃውና ተቀጥሮ ለሚሠራው ማኅበረሰብ ቤት በመገንባትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በመስጠት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም አድርገዋል፡፡ ከቬንዙዌላ ጋር አጋር የሆኑት ኩባ፣ ኒካራጓና ቦሊቪያ ደግሞ የነዳጅ ድጐማ ያገኙ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2013 በሞት የተለዩትን ሻቬዝ የተኩት ኒኮላስ ማዱሮ የሻቬዝን ስትራቴጂ ቢከተሉም፣ ነዳጅ ላይ የነበረውን ድጐማ አላካተቱም ነበር፡፡ በመሆኑም ፓርቲያቸው ተሽመድምዷል፡፡

በሩሲያ ያለው ሁኔታ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናናነታቸው ተንሰራፍቷል፡፡ በዩክሬንና በሶሪያ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ናቸው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ቢወድቅም፣ የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በሩሲያ ላይ ቢጥሉም፣ የሩሲያ ኢኮኖሚ እ.ኤ.አ. በ2016 እንደነበረው ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በሌላ በኩል ፑቲን በሶሪያ ያደረጉት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትና በሶሪያ ያለውን ግጭት በሰላም ድርድር ለመፍታት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማሳካት ሩሲያ ጉልህ ሚና አላት፡፡ በመሆኑም በሶሪያ የሰላም ድርድር ለማስጀመር ብሎም ለማሳካት ሩሲያ በአውሮፓና በአሜሪካ የተጣለባትን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደ መደራደሪያ ልታቀርብ ትችላለች፡፡ ይህም በነዳጅ ዋጋ መውደቅ ሊደርስባቸው የሚችለውን ኪሳራ ያካክስላቸዋል፡፡

ለዓለም ከፍተኛውን ነዳጅ የምታቀርበው ሳዑዲ ዓረቢያም፣ በነዳጅ ዋጋ መውደቅ ምክንያት በቅርቡ በጉልህ አትጐዳም፡፡ ለተወሰኑ ዓመታት ተረጋግታ መዝለቅ ትችላለች፡፡

ሆኖም የሳዑዲ ዓረቢያ ዜጐች የለመዱትን የተትረፈረፈ የአኗኗር ዘይቤ ሊቀጥሉበት አይችሉም፡፡ የሳዑዲ መንግሥትም አንዳንድ ወጪዎች ላይ ቅነሳ አድርጓል፡፡

አልጄሪያና አንጐላም የፖለቲካ መዋዠቅ ይገጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ዳካ ትሪቢዩን እንደ ዘገበው፣ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ነዳጅ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ አገሮችን የሚያሽመደምድ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ ያለውን ፖለቲካም የሚያናጋ ነው፡፡

የዎል ስትሪት ተንታኞች፣ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ30 ዶላር በታች ምናልባትም 20 ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ተንብየዋል፡፡ ሆኖም በሳዑዲ ዓረቢያና በኢራን መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል የሚል ትንበያም እየተሰነዘረ ነው፡፡    

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...