Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ የማንቂያ ደወል

ሌሎች ቅርሶችን ለማስመለስ የማንቂያ ደወል

ቀን:

በአሜሪካ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከ40 ዓመታት በላይ የተቀመጠውና ንብረትነቱ የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሆነ የብራና ጥራዝ መሰንበቻውን ወደ ቦታ ተመልሷል፡፡ የሁለት ቅዱሳንን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና የሰማእቱ ቅዱስ ሰራባሞን ገድሎች (ታሪኮች) በአንድነት የያዘው ጥራዝ (ብራና) የተጻፈው በ15ኛው ክፍለ ዘመን መሆኑ ተወስቷል፡፡

 የሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ ዲቪኒቲ (የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት) ተወካዮች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መጻሕፍቱን ለደብረ ሊባኖስ ገዳም አስረክበዋል፡፡ ብራናው ኤምኤስ 150 በሚል መጠሪያ በተቋሙ የቆየ ሲሆን፣ አሜሪካ ውስጥ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ቅዱሳን መጻሕፍት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በድረ ገጹ እንዳስታወቀው ብራናው ለዩኒቨርሲቲው በስጦታነት የተበረከቱት እ.ኤ.አ. በ1993 ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩት ዕውቅ ሳይካትሪስት ዶ/ር አንድሬ ትዊድ ነበር፡፡ ብራናው ስለቀደምቱ የክርስትና እምነትና በአፍሪካና አይሁድ ባህል መካከል ስላለው ትስስር ያስረዳል፡፡

የተቋሙ የብሉይ ኪዳንና ሐዲስ ኪዳን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ዲን ዶ/ር ጌይ ኤል ባይረን እንደተናገሩት፣ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ላሉ ባህላዊ ሀብቶች ክብር በመስጠት ለሌሎች ትምህርት ቤቶችና ሙዚየሞች ተምሳሌት መሆን ይሻሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹በተለያዩ አገሮች ባሉ ተቋሞችና በዓለምም ውድና የማይገኙ ብራናዎች በትክክለኛ ባለቤቶቻቸው እጅ መሆናቸው ያለውን ትልቅ ቦታ እገልጻለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ዶክተሩ ብራናው ላይ ጥናት ከሠሩ ቀደምት ተመራማሪዎች አንዱ ናቸው፡፡

የዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ፕሮፌሰር ዶ/ር አሊስ ኦጋዴን ቤሊስ በበኩላቸው፣ ብራናውን ዲጂታይዝ ለማድረግ በተደጋጋሚ ቢሞክሩም የተሳካላቸው በስተመጨረሻ ባገኙት ድጎማ ነው፡፡ ብራናው የደብረ ሊባኖስ ገዳም መሆኑን የተገነዘቡትም ዲጂታይዝ አድርገው ካጠናቀቁ በኋላ፣ ካታሎግ ሲያሲዙ ነው፡፡ ከዛም በሕጋዊ መንገድ ብራናው ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስበትን መንገድ ማፈላለግ ጀመሩ፡፡

በዋሽንግተን ዲሲ የደብረገነት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር ዶ/ር ዘበነ ለማ፣ የብራናው መመለስ ስለ አፍሪካ ባህልና ታሪክ አጠባበቅን ለዓለም የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ብራናው የተጻፈው በኢትዮጵያውያን ነው፤ መመለሱ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ጋርም ጥሩ ግንኙነት ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

ብራናው የተመለሰበት ጊዜ በኢትዮጵያ ልደትና ጥምቀት የሚከበርበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም ተገልጿል፡፡ በተለይም በእንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጀርመን የሚገኙ በርካታ የጥንት ቅዱሳን መጻሕፍት፣ መስቀሎችና የከበሩ ቁሳቁሶች እንዲመለሱ ማንቂያ ደወል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቡድን አባላት ብራናውን ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ባደረጉት ጉዞ እንደተደሰቱ ተናግረዋል፡፡ ጥንታውያን ቤተክርስቲያኖች ወደሚገኙባት አገር በመጓዛቸው የተሰማቸውን ሐሴትም አክለዋል፡፡

ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ብራና (መጽሐፍ) መመለስ አስመልክቶ የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ከጀርመን በድረ ገጻቸው እንደገለጹት፣ ገድለ ሰራባሞን በመጀመሪያ የተጻፈው በቅብጢ (ኮፕቲክ) ቋንቋ ሲሆን የጻፈውም  የእስክንድርያ ፓትርያርክ የነበረው እለእስክንድሮስ (ከ313-326 ዓ.ም.) ነው።
የቅብጢ ቋንቋ እየተዳከመ ሲመጣና በዐረብኛ ሲተካ እንደ አብዛኞቹ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ይኸው ገድለ ሰራባሞንም ወደ ልሳነ ዐረቢ ተመለሰ።
ገድሉ ወደ ኢትዮጵያ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር መጥቶ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በደብረ ሊባኖስ ገዳም አበምኔት በነበሩት አባ መርሐ ክርስቶስ ዘመን (1401 እስከ1490 ዓ.ም.) ወደ ግእዝ ቋንቋ የተተረጐመ ሲሆን ይዘቱም የሰማዕቱን ዜና ሕይወት እና ዜና ተጋድሎ በሁለት ክፍሎች የተዘረዘረበት ነው፡፡   

በአሁኑ ወቅት በግብጽ ሙሉው ገድሉ ተሟልቶ አይገኝም። የተወሰነ ክፍል በቅብጢ፣ የተወሰነው ደግሞ በዐረብኛ ነው። ሙሉው ገድሉ ከነተአምራቱ በግእዙ ነው። ይህም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ጠብቀው ማቆየታቸው የሚያስመሰግናቸው ሲሆን፤ እስካሁን በነበረው የአጠቃላይ  ቤተክርስቲያን  ታሪክ (በተለይ የጥንቱ እስከ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ያለውን) ላይ ብዙ ነጥብ ይጨምርልናል፤ ብዙ ነጥቦችን ግልጥ ያደርጋል።  ለጥናትና ለምርምር ሥራ በእጅጉ ይረዳል። በግእዙ ገድለ ሰራባሞን ላይ የሚገኙ የቅብጥ፣ የጽርእ፣ የዐረብኛ ቃላትና ስያሜዎች በብዛት ስለሚገኙበት ለጥናት ይጋብዛል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...