Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምለዓለም ሥጋት የሆነው የቻይና ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል

ለዓለም ሥጋት የሆነው የቻይና ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል

ቀን:

በዓለም ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው አገሮች በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው ቻይና፣ እ.ኤ.አ. የ2015 የኢኮኖሚ ዕድገቷ ማሽቆልቆሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

በጠንካራ ኢኮኖሚዋና በወጪ ንግዷ የዓለምን አብዛኛውን ክፍል የተቆጣጠረችው ቻይና፣ ባለፉት 25 ዓመታት ተመዝግቦ በማያውቅ ሁኔታ ኢኮኖሚዋ ያዘቀዘቀ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2015 ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት 6.9 በመቶ ሆኗል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው አኃዙ ባለፉት 25 ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛው ነው፡፡ የቻይና የ2015 የኢኮኖሚ ዕድገት ዕቅድ ሰባት በመቶ የነበረ ሲሆን፣ የተመዘገበው ግን 6.9 በመቶ ነው፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. በ2014 ከነበረው የኢኮኖሚ ዕድገት በ0.4 በመቶ ቀንሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እ.ኤ.አ. በ2014 ብቻ 7.3 በመቶ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በ2015 ወደ 6.9 በመቶ ያሽቆለቆለው፣ በቻይና የወጪ ንግድና ኢንቨስትመንት በመቀዛቀዙና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በራስ አቅም ለመገንባት አዲስ አቅጣጫ በመቀየሱ መሆኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

የአገሪቱ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት እ.ኤ.አ. በ2015 በሦስተኛው ሩብ ዓመት 1.8 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ ይህ በአራተኛው ሩብ ዓመት ወደ 1.6 በመቶ ቀንሷል፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር ትልቅ የሚባል ባይሆንም፣ መረጋጋት ላቃተው የዓለም ኢኮኖሚ ግን ሥጋት ነው፡፡ በዓለም ያለውን የገበያ ሥርዓትም ያዛባዋል፡፡ የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ ከታወቀ በኋላ በእስያ ያለው የገበያ ሥርዓት መዋዠቅ ጀምሯል፡፡

ላለፉት ሦስት አሥር ዓመታት የቻይና ኢኮኖሚ በዓመት በአማካይ አሥር በመቶ አድጓል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በአገሪቱ የደመወዝ ክፍያ በዓመት በአማካይ 15 በመቶ አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1990 ቤት የገዙ ቻይናውያን 17 በመቶ ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ. በ2005 ወደ 85 በመቶ አድገዋል፡፡ በቻይና የቁጠባ ባህል ያደገ ሲሆን፣ የቁጠባ መጠኑ ከአጠቃላይ ገቢ እ.ኤ.አ. በ1995 ከነበረው 17 በመቶ እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ 25 በመቶ አድጓል፡፡ አገሪቱም ለሕዝቧ የብድር ማበረታቻ አድርጋለች፡፡

የቻይና ባለሀብቶች ዓይናቸውን ወደ ሪል ስቴት ልማት በማዞር ወደ ሥራው የገቡ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ከሚመረተው ሲሚንቶ 60 በመቶ የሚሆነው በቻይና ለሪል ስቴት ግንባታ እንዲውል አድርጓል፡፡ 43 በመቶ ያህል የግንባታ መርጃ ቁሳቁሶች (ቡልዶዘርና ትላልቅ ማሽኖች) ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ የግንባታ ዘርፉ በቻይና ውስጥ ከሚመረተው ብረት 40 በመቶ ያህሉን ማለትም ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 12 በመቶ የተጠቀመ ሲሆን፣ በቻይና ለሥራ ደርሷል ከሚባለው ሕዝብ 14 በመቶ ያህሉም በዘርፉ ተቀጥሮ ይሠራል፡፡ በቻይና የሪል ስቴት ዘርፍ ቢንሰራፋም፣ በአገሪቱ ለንግድና ለመኖሪያ የሚሆኑና 64 ሚሊዮን የሚጠጉ አፓርትመንቶች ፈላጊ አጥተዋል፡፡

ከግንባታ ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ብረት፣ ሲሚንቶ፣ መስታወትና የቤት ቁሳቁስ አምራቾችና አቅራቢዎች፣ እንዲሁም ሠራተኞቻቸው በሪል ስቴቶች ላይ በደረሰው ኪሳራ ተጐጂ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ጥሬ ዕቃዎችን ለቻይና የሚያቀርቡ አገሮች በቻይና በሚኖረው ዝቅተኛ ፍላጐት የተነሳ ኢኮኖሚያቸው ይጎዳል፡፡

በቻይና የተመዘገበው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት እ.ኤ.አ. በ2016 እንደሚቀጥል፣ ይህም በኢንዱስትሪ ልማቷ ከፍተኛ ነዳጅ ዘይት ትጠቀም የነበረችው ቻይና ፍላጐቷ እንዲቀንስ እንደሚያደርግና በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ የባሰ ቅናሽ እንደሚያመጣ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ለቻይና ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የመግዛት አቅም መቀነስ ለቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት አንዱ እንቅፋት ነው፡፡

ከቻይና ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ 59 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ ይህ በሙሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ ከቻይና ጋር ባላቸው የንግድ ግንኙነት ትልቁን ሥፍራ የሚይዙት የአውሮፓ አገሮች፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ደግሞ የመግዛት ፍላጐታቸው ቀንሷል፡፡ ይህም የቻይና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያመረተውን ያህል እንዳይሸጥ አድርጐታል፡፡

በቻይና የቤት ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ከቻይና ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከ25 በመቶ እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የሪል ስቴት ዘርፍ ነው፡፡ በሪል ስቴት ዘርፍ ውስጥ ብረት፣ ሲሚንቶ፣ መስታወት፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ይካተታሉ፡፡ በቻይና የቤት ዋጋ እያሽቆለቆለ መሄዱ የሚጐዳው በዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎት ፈላጊውንና ለባለሀብቶቹ ያበደሩ የገንዘብ ተቋማትንም ነው፡፡

በዓለም ትልቋ የብረት አምራች አገር ቻይና ናት፡፡ በብረት ምርት በሁለተኛነት ከምትከተለው ጃፓን፣ ቻይና ሰባት እጥፍ ታመርታለች፡፡ ሆኖም ብዙ የብረት ምርት የሚፈልጉት የግንባታና የተሽከርካሪ ኢንዱስትሪ ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍላጐታቸው እያሽቆለቆለ ነው፡፡ ይህም  ቻይና ካላት የተትረፈረፈ የብረት ምርትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የፍላጐት መቀነስ አንፃር የቻይናን ኢኮኖሚ ፈትኖታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 የነበረው የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት መቀነሱና እ.ኤ.አ. በ2016ም እንዲሁ ይቀጥላል ተብሎ መተንበዩ፣ በእስያም ሆነ በሌሎች አገሮች አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ለቻይና የምርት ግብዓቶች እንደ መዳብ፣ ነዳጅ ዘይትና ማዕድናት የመሳሰሉት ጥሬ ዕቃዎች የሚያቀርቡ አገሮች ከአሁኑ ለውጥ ማየት እየጀመሩ ነው፡፡ የቻይና ኢንዱስትሪዎች መቀዛቀዝ ሲያሳዩ፣ አገሮቹ የሚያመርቷቸው ጥሬ ዕቃዎች ላይ የፍላጐት መቀነስ ታይቷል፡፡ ኢኮኖሚያቸውን በእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የበለጠ ትኩረት አድርገው እየሠሩ ያሉት ካዛኪስታንና ቺሊ በቻይና የተከሰተው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ተጐጂዎች ያደርጋቸዋል፡፡

ጃፓን የኤሌክትሪክ ዕቃዎችንና ክፍሎችን ለቻይና ስትልክ፣ ቻይና ገጣጥማ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ፍጆታ ታውላለች፡፡ አብዛኞቹ የጃፓን ክፍልፋይ የኤሌክትሪክ ምርቶች ለዓለም ገበያ የሚቀርቡትም በቻይና ተገጣጥመው በመሆኑ ጃፓን የችግሩ ሰለባ ትሆናለች፡፡

በሌላ በኩል በቻይና ካለው ከፍተኛ የጉልበት ዋጋ በቀነሰ ዋጋ የሚያሠሩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች አምራች አገሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ቬትናም የስማርት ፎኖችን ምርት በማብዛትና ወደ ውጭ በመላክ ቻይና ተቆጣጥራ የነበረውን ገበያ መያዝ ትችላለች፡፡ ህንድና ኢንዶኔዥያም ይህንን ዕድል መጠቀም ይችላሉ፡፡ ለዚህ ግን አገሮቹ የፖሊሲ ማሻሻያና የውጭ ገበያ ኢንቨስትመንትን ማበረታቻ በማድረግ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከቻይና ጋር ይወዳደሩ የነበሩ አገሮች፣ ገበያውን ሰብረው ለመግባት ዕድል ያገኛሉ፡፡ በቻይና የጉልበት ዋጋ በመቶ ፐርሰንት መጨመሩም፣ የሕዝብ ብዛት ላላቸው ባንግላዴሽ፣ ማይናማርና ሌሎች አገሮችም አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ በአውቶሞቢል የበለፀገችው ጀርመን እንዲሁም በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የመጠቀችው አሜሪካ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ትንበያ አለ፡፡

የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት የቀነሰው መሠረታዊ የተባለው የሠራተኛ ቁጥር መቀነስና የጉልበት ዋጋ መጨመር ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ቢሆን የቻይና ኢኮኖሚ ትልቅ ነው፡፡ የቻይና ስድስት በመቶ ዕድገት ለዓለም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ዓለም በኢኮኖሚ ቀውስ ከተመታችበት እ.ኤ.አ. 2007/08 በፊት አገሪቷ ከነበራት አሥር በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዛሬ ያስመዘገበችው ስድስት በመቶ ዕድገት ለዓለም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ምክንያቱም ብዙ አገሮች በተለይም በአውሮፓ ያሉት ከኢኮኖሚ ቀውሱ መውጣት አቅቷቸዋል፡፡ በድጐማና ፍላጐቶችን በመሸራረፍ መኖርም ጀምረዋል፡፡

በሌላ በኩል የቻይና ኢንቨስትመንት ከደሃ እስከ ሀብታም አገሮች የተሳሰረ ነው፡፡ በዓለም በኢኮኖሚ ዕድገቷ በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘውና በጨርቃ ጨርቅ፣ በኮንስትራክሽን፣ በኤሌክትሮኒክስና በተለያዩ ዘርፎች ከዓለም የተሳሰረችው ቻይና ኢኮኖሚዋ ሲነካ በሌሎች አገሮች ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...