Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከአጉል ልማድ ጋር መኖር ከእውነታ ጋር ያጋጫል!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚኮራባቸውና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የተለያዩ ባህሎች፣ ወጎችና ልማዶች አሉት፡፡ የማኅበረሰብ ህልውናን የሚያጎለብቱና አብሮ መኖርን የሚያጠናክሩ እነዚህ እሴቶች፣ ዘመናትን እየተሸጋገሩ በትውልዶች ቅብብሎሽ እዚህ ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ጎጂ ተብለው የሚታወቁ ልማዶች ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ኖረዋል፡፡ በዚህ የሠለጠነ ዘመን ጎጂ ልማዶችን በሒደት ለማስወገድ፣ ጠቃሚ የሆኑትን ደግሞ ለማስቀጠል ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎች ይታያሉ፡፡ በሕዝባችን ውስጥ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ልማዶችን በማስወገድ፣ ጠቃሚውን የማስቀጠል ፍላጎት በፖለቲካው አካባቢ አልታይ በማለቱ አገሪቱን ወደ ኋላ እየጎተታት ነው፡፡ ከአጉል ልማድ ጋር ተጣብቆ የመኖር አባዜ ፖለቲካው ውስጥ በመንሠራፋቱ አድሮ ቃሪያ መሆን የተለመደ አመል ሆኗል፡፡ ፖለቲካው አገርንና ሕዝብን ማዕከል እስካላደረገ ድረስ፣ ከዚህ ዓይነቱ አዙሪት ውስጥ መውጣት አዳጋች ይሆናል፡፡ በአንድ በኩል ራዕይ አልባነት፣ በሌላ በኩል ራስ ወዳድነት የተጠናወተው የሴራ ፖለቲካ ብዙ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ መላ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ ከአጉል ልማድ ጋር መኖር በዝቷል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ተደራጅተው በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ሁሉንም ወገን ማስማማት አለበት፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲደራጁ ዓላማቸውን ካላወቁ፣ የሚመሩበትን ፕሮግራምና ደንብ ካልቀረፁ፣ ሕዝብን ከጎናቸው ለማሠለፍ የሚያስችል አጀንዳ ካልያዙና ዘመኑ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ ካልመጠኑ መኖራቸው ምን ይፈይዳል? በዙሪያቸው የሚኮለኮሉ አባላትና ደጋፊዎች በጭፍን ከመመራት ወጥተው ጠያቂና ሞጋች ካልሆኑ ፓርቲዎቹ ዘንድ ምን ይሠራሉ? አመራር እንሰጣለን የሚሉትም ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ከተሳናቸው ምን ይፈይዳሉ? በሌላ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ሕጉ ከለላ ካልሰጣቸው? ሕጉን የሚያስፈጽሙት አካላት ዋስትና ካልገቡላቸው? የሚመለከታቸው አካላትም ትብብር ካላደረጉላቸው ስለሕግ የበላይነት መነጋገር አይቻልም፡፡ መላው ሕዝብም መብቱና ነፃነቱ ተጠብቆለት ድጋፉን እንዲቸራቸው ካልተደፋፈረ፣ እንዴት ስለሕግ ማክበርና ኃላፊነት መነጋገር ይቻላል? በዚህ በኩል መንግሥት ከፍተኛ  ኃላፊነት ያለበት ሲሆን፣ በየደረጃው ያሉ መዋቅሮችም ተጠያቂነት ሊኖርባቸው ይገባል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ በፊት የነበረውን አሳዛኝ ድርጊት ፈር የማስያዝ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ጎጂ ልማዶች አገርን ያበላሻሉ እንጂ ፋይዳ የላቸውም፡፡

ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸው በሕግ ዋስትና ያገኘ ቢሆንም፣ በተግባር ሲታይ ግን በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ መንግሥት ለዚህ መብት የሰጠው የተዛባ ትርጉም ብዙዎች አንደበታቸውን እንዲሸብቡ አድርጓል፡፡ ብዕራቸውን አንስተው የሞገቱ ወደ አፎቱ እንዲከቱ ተገደዋል፡፡ ወይም በእስር መከራ አይተዋል፡፡ አገር ጥለው የኮበለሉም ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ሰቆቃ በሕግ ዋስትና ያገኘ መብት ባለመከበሩ ብቻ የደረሰ ነው፡፡ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ለየት ያለ መነቃቃት እየታየ ቢሆንም፣ በስፋትና በምልዓት ተግባራዊ የመሆኑ ጉዳይ አሁንም የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ ከመንግሥት ባልተናነሰ ይኼንን መብት የሚጋፉ ወገኖች በብዛት እየታዩ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ጉዳይ የመሰላቸውን ሐሳብ ሲያራምዱ፣ ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብት የሌላቸው ይመስል የስድብ ናዳ ይወርድባቸዋል፡፡ ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና መስጠት በማይፈልጉ ወገኖች ምክንያት የአደባባይ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ ጫናውን ተቋቁመው የመሰላቸውን ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ የጎራ ፖለቲካ ወጥመድ ይጠብቃቸዋል፡፡ በጎጂ ልማዶች ምክንያት ተሸማቀው የሚኖሩ ወገኖችን ቤት ይቁጠራቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው ትልቁ በሽታ መረጃን የማግኘት መብት ጥሰት ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ሕጉ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ቢወጣም፣ ዜጎች ዛሬም መረጃ ለማግኘት አሳራቸውን ያያሉ፡፡ በተለይ በመንግሥት እጅ የሚገኝ መረጃ ለማግኘት የሚታየው መከራ ከሚናገሩት በላይ ነው፡፡ ለትምህርት፣ ለምርምርና ለተለያዩ ጉዳዮች መረጃ የሚፈልጉ ወገኖች ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ያለ ውጤት ይባክናሉ፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ትኩስና ወቅታዊ ዘገባዎችን ለመሥራት ካለመቻላቸውም በላይ፣ በመረጃ አለቃቀቅ የሚታየው አድሏዊነት ከመጠን በላይ ያበሳጫል፡፡ የአገርን ጥቅምና ብሔራዊ ደኅንነት ከሚነኩ ጉዳዮች ውጪ ያሉ በቀላሉ መገኝት ያለባቸው መረጃዎች፣ በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ነው የሚሠራጩት፡፡ ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት ባቃታቸው ሹማምንት ምክንያት አገር ስትጎዳ ጠያቂ የለም፡፡ ከገዛ ቤቱ ጓሮ ቀጥፎ እንደሚያመጣው ጎመን፣ የመንግሥትን መረጃ እንደ ግል ንብረቱ የሚቀልድበት ተሿሚ የበዛበት አገር ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ በሕግ ዕውቅና የተሰጠው መብት የግለሰቦች መጫወቻ እየሆነ ከአጉል ልማድ ጋር መኖር የዜጎች ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን ከጨበጡበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር መነጋገር በጣም ጠቃሚ ስለሆነ በርካታ ሐሳቦችን ማቆር እንደተቻለ ይታመናል፡፡ ተሿሚዎቻቸውም ከሚመሩዋቸው ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር በግልጽ በመነጋገር እንደ መርግ የከበዱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ካላደረጉ፣ ውጤቱ ‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ ነው› የሚሆነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ አመራሮች የፖሊሲ ሐሳቦችን በማመንጨት ጎጂ ልማዶች እንዲወገዱ ዕገዛ ካላደረጉ፣ በየአዳራሹ የሚደረገው ዲስኩር መና ሆኖ ይቀራል፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ ምን መደረግ እንዳለበት ማሳሰቢያ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ አፈጻጸሙ የተሻለ እንዲሆን የሚረዱ ምክረ ሐሳቦችንና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መጠቆም ጭምር መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ አመራር የሚሰጥ አካል ከላይ ወደታች ማንቆርቆር ሳይሆን፣ በአርዓያነት ለመምራት የሚያስችለውን ምክክር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ‹አመራር ሰጪ መሆን ከኋላ ሆኖ መንዳት ሳይሆን፣ አርዓያ ሆኖ መምራት› ነው እንደሚባለው፣ ከላይ እስከ ታች ከነባሩ ጎጂ ልማድ መላቀቅ ይገባል፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርቶች ማወናበድ የተነቃበት የሰነፎች አጉል ድርጊት ነው፡፡ በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ አመራር መስጠት የሚቻለው ከላይ ወደ ታች፣ እንዲሁም ከታች ወደ ላይ ሐሳቦችን በማንሸራሸር ብቻ ነው፡፡

ሁሌም እንደምንለው ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ሕዝቧም የተከበረ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ ነው፡፡ ይኼ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ በአራቱም ማዕዘናት በተለያዩ መልክዓ ምድሮች ውስጥ ቢኖርም፣ የሚጋራቸው አኩሪ የሆኑ የጋራ እሴቶች አሉት፡፡ የተለያዩ ባህሎች፣ ወጎች፣ ልማዶች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ወዘተ ቢኖሩትም ለአገሩ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በሰላምና በመከባበር ዘመናትን አሳልፏል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ልዩነቶች ሳይገድቡት ተጋብቶና ተዋልዶ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን ጠብቆ ኖሯል፡፡ አልፎ አልፎ ችግሮች ቢያጋጥሙም አስደማሚ በሆነው የሽምግልና ሥርዓቱ የተበደለን እየካሰ፣ የበደለን ደግሞ እየገሰፀ መኖር ይችልበታል፡፡ እንዲህ ዓይነት በሥርዓት መኖር የሚችል አስተዋይ ሕዝብን በቅጡ መምራት ያልተቻለው ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ስለበዙ ነው፡፡ በተለይ ተምሬያለሁ የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል ቂም፣ ጥላቻ፣ ክፋትና ሴራ ውስጥ በመዘፈቅ አገርንና ሕዝብን በመርሳቱ ነው፡፡ ለተቆመለት የፖለቲካ ዓላማና ጎራ ብቻ በማቀንቀን በሕዝብ ስም መነገድ ስለበዛ ነው፡፡ ለዚህ የሠለጠነ ዘመን የማይመጥን አጉል ድርጊት እንዲያበቃ መደረግ አለበት፡፡ ከአጉል ልማድ ጋር አብሮ መኖር ከእውነታ ጋር እያጋጨ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...