Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢንቨስተሮችን የሚያስደነግጡ ድርጊቶች በፍጥነት ይቁሙ!

ከሰሞኑ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና በሁለት ሠራተኞች ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት ያህል ከዘለቀው የፖለቲካ ቀውስ በማገገም አንፃራዊ መረጋጋት በተፈጠረላት በዚህ ወቅት ግድያው መጸፈሙ፣ አሁንም ለሥጋት የሚጋብዙ መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች እንዳሉ ያመላክታል፡፡ ሰሞኑን የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የሚመለከተው አካል አጣርቶ ውጤቱን እንደሚያቀርብ ቢጠበቅም፣ በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተጋረጠውን ችግር ለመፍታት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በፍጥነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ ክልላዊ መንግሥታትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተናበቡ እየሠሩ ባለመሆናቸው፣ ለኢንቨስትመንት መሰናክል የሆኑ አላስፈላጊ ድርጊቶች በስፋት ይታያሉ፡፡ የአገር የጋራ መጠቀሚያ መሆናቸው በሕግ ዕውቅና የተሰጣቸው የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማልማት የሚሰማሩ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ኢንቨስተሮች የመንግሥት ከለላ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ በሕጋዊ መንገድ ስምምነት ፈጽመው ሥራ የጀመሩ ኢንቨስተሮች ሲዋከቡ፣ በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ከለላ ካልሰጡዋቸው የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የአገር ገጽታ በረባ ባልረባው እየተበላሸ ችግር ከሚፈጠር፣ መስተካከል ያለባቸውን በሕጋዊ መንገድ ፈር ማስያዝ መቅደም አለበት፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን አሳዛኝ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ ለአገር አይጠቅሙም፡፡

በሁሉም መስኮች የኢትዮጵያውያን ተጠቃሚነት መቅደሙ ሁሌም የሚደገፍና የሚበረታታ ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን የተከለሉ የሥራ ዘርፎች ውስጥ በሕገወጥ መንገድ የውጭ ሰዎች እንዳይገቡ ነቅቶ መከላከልም ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች በግላቸውም ሆነ ተደራጅተው እንዲሠሩ ዕድሉን የማመቻቸት ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ይህ ፍላጎት ሊሳካ የሚችለው በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ሥራቸውን ግልጽነትና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ሲያከናውኑ ነው፡፡ እጃቸው ንፁህ የሆነ ተሿሚዎች ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑበት ዓውድ እንዲፈጠርና ወጣቶችም በሥርዓት ታንፀው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን የተቀደሰ ተግባር ማስፈጸም ያቃታቸው ግድየለሾች በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት አገር መበደል የለባትም፡፡ በስንት ማግባባትና ልመና ወደ አምራችነት የሚገቡ አገር በቀል ኢንቨስተሮችን ጨምሮ፣ የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያስበረግጉ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንዳላዩ መሆን አያዋጣም፡፡ ኢንቨስተሮች ባልተመቻቸ ከባቢ ውስጥ መሥራት እንደማይፈልጉ የታወቀ ነው፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ደግሞ የሚከተለው ግልጽ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል መብቶችን በሚያብራራበት አንቀጽ 41፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው ይላል፡፡ ይህ እንግዲህ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት ውስጥ የሠፈረና ዋስትናው የተረጋገጠ መብት ነው፡፡ ይህ መብት እየተገፋ ዜጎች እንደ ልብ ተዘዋውረው ለመሥራት የማይችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡ እንደ ባዕድ ከኖሩበት ቀዬ የተሰደዱ ሞልተዋል፡፡ አሁንም ድርጊቱ አለ፡፡ በሌላ በኩል ልምዳቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን አቀናጅተው በተለያዩ አካባቢዎች ኢንቨስት የሚያደርጉ ወገኖች እንደ መጤ እየታዩ ንብረታቸው ሲዘረፍና ሲወድም ታይቷል፡፡ በሚሠሩባቸው አካባቢዎች ከመስተዳድሮችና ከፀጥታ አካላት ድጋፍና ከለላ ሲጠይቁ ጆሮ ዳባ ልበስ የተባሉ አሉ፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ጉቦ እየተጠየቁ አንሰጥም በማለታቸው ብቻ ለጥቃት የሚጋለጡም አሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተደራጁ ሰዎች ሲያጠቋቸው የሚደርስላቸው በማጣታቸው ዝርፊያም ያጋጠማቸው ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን የተገፉ ሰዎች ያዩ ሌሎች ባለሀብቶች ምን ለማግኘት ነው ለልማት የሚነሱት? በማንስ ተማምነው ነው ወደ አካባቢዎቹ የሚዘልቁት? ይኼንን ሥጋት በመጋራት ለመፍትሔው መነሳት ካልተቻለ መጪው ጊዜ ያሠጋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን አሳምኖ ወደ አገር ለማምጣት ያለውን ሥቃይ የሚረዳ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ቁምነገሮችን ማንሳት ይችላል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉት ውስጥ ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሰላማዊ አገር መሆኗን፣ ተስፋ  የሚጣልበት የኢኮኖሚ ዕድገት እየታየ እንደሆነ፣ ጠንካራ የሆነ ዋስትናና ከለላ መኖሩን፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል እንደሚገኝ፣ ኢትዮጵያ የክፍለ አኅጉሩ የንግድ እምብርት መሆኗን፣ መሠረተ ልማቶች መስፋፋታቸውን፣ የሚያማልል የማበረታቻ ሥርዓት እንዳለ፣ ወዘተ በመግለጽ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተቻለ አቅም ጥረት ይደረጋል፡፡ በሌላ በኩል ማንም የማይክደው ቀርፋፋና ለምላሽ ዳተኛ የሆነው ቢሮክራሲ፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ለሥራ ከማይመቹ አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ ያደርጋታል፡፡ አልፎ አልፎ ኢንቨስተሮችን በማወያየት ችግራቸውን ለመረዳት ጥረት ቢደረግም፣ የማስፈጸም ብቃት ባለመኖሩ ምክንያት ከዓመት ዓመት ተደጋጋሚ ችግሮች ይሰማሉ፡፡ በዚህ ላይ ነውጥ በተፈጠረ ቁጥር የውጭ ኢንቨስትመንቶች የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ፡፡ ይኼ ማንን ይጠቅማል? ለአገር ገጽታስ ፋይዳው ምን ይሆን? ብዙ ያነጋግራል፡፡

ችግሮች ሲያጋጥሙ በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ወደ ኃይል የሚያዘነብሉ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ መብትን በአግባቡ ጠይቆ የሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲሰጥበት ዕድሉን ከመስጠት ይልቅ፣ ኃይል ላይ ማተኮር ከጥፋት በስተቀር የሚፈይደው የለም፡፡ ሕዝብን ለማስተዳደር በየደረጃው ያሉ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ተሿሚዎችም፣ እነሱ በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት አገር መሰቃየት የለባትም፡፡ ወጣቶችም ሆኑ በኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ወገኖች ጥያቄ ሲኖራቸው በተቻለ መጠን አግባብ የሆኑ መልሶች እንዲያገኙ፣ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲያጋጥሙም የበላይ አካላት መረጃው ደርሶዋቸው የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስዱ ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ አስተዳደራዊ ችግሮች ተለጥጠው ቀውስ እንዳይፈጠር መትጋት ይገባል፡፡ ሠራተኞች ተበድለናል ሲሉ በቅንነትና በኃላፊነት ስሜት በመነሳሳት ለመፍትሔ መጣደፍ የሰው ሕይወት ለአደጋ እንዳይጋለጥ፣ ንብረትም እንዳይወድም ይጠቅማል፡፡ ኢንቨስተሮችም ከአካባቢ ማኅበረሰቦች ጋር ተቀራርበው ይመካከሩ፡፡ በዚህ መንገድ መነጋገር ካልተቻለ ቅሬታዎች ተጠራቅመው ብሶት ሲፈነዳ ለመቆጣጠር ያዳግታል፡፡  በተቻለ መጠን የጋራ መግባባት እንዲፈጠር ዕድሉ ይመቻች፡፡ ዳተኝነት ትርፉ አደጋ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለአገር ትልቁ የራስ ምታት እየሆነ ያለው አንዱና ዋነኛው ችግር የቅንነት መጥፋት ነው፡፡ አገርን ማዕከል አድርጎ ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ፣ ለግልና ለቡድን ጥቅማ ጥቅም የሚደረገው ትንቅንቅ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ አንድ ችግር ሲያጋጥም የጋራ ጉዳይ ከማድረግ ይልቅ፣ ብሔረሰባዊ ገጽታ በማላበስ ትርምስ ለመፍጠር የሚደረገው መሯሯጥ በዝቷል፡፡ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤት እየተረሳች ግላዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ሲበዛ፣ እንኳን ስለኢንቨስትመንት ስለህልውናም ለመነጋገር ያዳግታል፡፡ ቅንነት እየጠፋ አገር መገንባት ስለማይቻል ወደ ቀልብ መመለስ ይገባል፡፡ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር የሚቻለው፣ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት በመሠለፍ ለአገር የሚጠቅመውን ለማበርከት ቅንነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በአደባባይ ስለአንድነት እየሰበኩ አንድነትን የሚሸረሽር ፀረ ኢትዮጵያዊነት ድርጊት መፈጸም መወገዝ አለበት፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የጋራ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዱ ድርጊቶችን ማስቆም ይገባል፡፡ አሁን ባለው አያያዝ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ኢንቨስተሮችን የሚያስደነግጡ ድርጊቶች በፍጥነት ይቁሙ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...