Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢኮኖሚው ሁለተኛ እግር ያስፈልገዋል›› ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ

ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሚኒስትር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በፓርቲያቸው በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በኩል ባለፉት ሁለት አሥርት ውስጥ በኢሕአዴግ መንግሥት ውስጥ እያገገሉ ካሉ ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር አርከበ በአዲስ አበባ ታዋቂነት ያተረፉበት ወቅት የተፈጠረው ለአምስት ዓመታት ከተማውን በከንቲባነት በመሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በቅፅል ስማቸው ‹‹አርከበ ሱቅ›› የተሰኙ ትንንሽ የኮንቴይነር ሱቆች ለከተማው የተዋወቁበት ጊዜ የአርከበ የከንቲባነት ዘመን ነው፡፡ ከከንቲባነት በኋላ በሚኒስትር ዴኤታነት የቀድሞውን የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴርንም መርተዋል፡፡ በዚህ ወቅት በከተማ ማኔጅመንትና በመሠረተ ልማት መስክ ሰፊ ትኩረት አድርገዋል፡፡ በዘጠነኛው የሕወሓት ጉባዔ ወቅት ግን / አርከበን ጨምሮ ነባር አመራሮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ ኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ይፋ አደረጉ፡፡ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ተራ አባል ሆነው ለመቀጠል ወሰኑ፡፡ በዚህ ጊዜም ነበር / አርከበ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን ‹‹ደቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ›› መስክ ለመከታተል ወደ ለንደን ያቀኑትና የመመረቂያ ጥናታቸውንም ‹‹ሜድ ኢን አፍሪካ፡- ኢንዱስትሪያል ፖሊሲ ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ ለማሳተም የበቁት፡፡ በመጽሐፋቸውም በአግባቡ የኢንዱስትሪ ፖሊሲን በመቅረፅ መንግሥት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገሮች ውስጥ መሪነቱን በመያዝ ኢንዱስትሪያዊ ልማትን ለማምጣት የሚችልባቸውን ቁልፍ ተግባራት በመተንተን ይከራከራሉ፡፡ በጠቅላላው መጽሐፋቸው የአበባ፣ የሲሚንቶና የቆዳ ዘርፎችን በመንተራስ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ስኬቶችና ውድቀቶች ገምግሟል፡፡ አሁንም በፖሊሲ አውጪው ክበብ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው / አርከበ፣ በቅርቡ በፀደቀው የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይም ትልቅ ተሳትፎ ነበራቸው፡፡ ዕቅዱ በአገሪቱ የመዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የተዘጋጀ ከመሆን አልፎ አገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ ለማንደርደርና የአምራች ኢንዱስትሪ መሠረት ለመፍጠር የተወጠነ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው የአገሪቱን የቆየ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለማቃለል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማልማት ተልዕኮ የተሰጣቸው / አርከበ ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ስለአምራች ኢንዱስትሪው (ማኑፋክቸሪንግ) እ ከዚያም ባሻገር ስላለው የዕድገት ሒደት / አርከበ ከአሥራት ሥዩም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አብዛኛውን ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመንደርደር ላይ ያለ ኢኮኖሚ ነው ሲሉ ይደመጣል፡፡ ከኢኮኖሚ መገለጫዎች አኳያ በመንደርደር ላይ ያለ ኢኮኖሚ ማለት ምን ማለት ነው? መንደርደሩስ እስከ ምን ያህል ጊዜ የሚቆይ ነው?

ዶ/ር አርከበ፡- በመንደርደር ላይ ያለ ኢኮኖሚ በምንልበት ጊዜ በደርግ ወቅት የነበረውን የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል የማስቆምና የማንሰራራትን ሒደት ለማመልከት ነው፡፡ በደርግ ውድቀት ማግሥት የመጀመርያው ትኩረት የነበረው በጦርነት የተጎዳውን አገር እንዲያገግም ለማድረግ መሥራት ላይ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ኢኮኖሚው ወደ ፈጣን ዕድገት እንዲሸጋገር ለማድረግ በተለይ በግብርናና በገጠር ልማት ያተኮረ ሰፊ ሥራ ሲሠራ ነበር፡፡ ይህንን በማድረጋችን ባለፉት 12 ዓመታት የድርብ አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ይሁን እንጂ የአንድ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ በዚህ አይገደብም፡፡ ያለንበት የኢኮኖሚ ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ደረጃ ለመሸጋገር ከኢኮኖሚ መንደርደር በመጀመሪያው ምዕራፍ የነበረው ለየት ያለ ስትራቴጂና ለየት ያሉ ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢኮኖሚው መንደርደር ሒደት ቆይቷል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያሳለፋቸው ዓመታት ኢኮኖሚው መነሳት የነበረበት ነው፡፡ ይሁንና ይህ ሒደት አልረዘመም ወይ? ገደቡስ እስከ ምን ድረስ ነው? ልምዱስ ከየት የተገኘ ነው?

ዶ/ር አርከበ፡- አሁን ያለንበትን የዕድገት ደረጃ ማየት ተገቢ ነው፡፡ አገሪቱ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች አሠላለፍ ውስጥ የምትገኝ ናት፡፡ አንድ ኢኮኖሚ አድጓል የምንለው ወደ መካከለኛ ገቢ፣ ከዚያም ሲያልፍ ወደ ከፍተኛ ገቢ ሲያድግ ነው፡፡ የነበረውን የማሽቆልቆል ጉዞ የማስቆም ሥራ መሠራቱን ማዕከል በማድረግ ነው የኢኮኖሚ መንደርደር የምንለው እንጂ፣ በቀጣይ ምዕራፎች ወደ አዲስ ምዕራፍ የመሸጋገርና ተመሳሳይ የሆኑ እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ አሁን ግብርናው መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ ኢኮኖሚውም መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው (ማኑፋክቸሪንግ) ግን ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ ከአምስት በመቶ ያለፈ ድርሻ የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ኢኮኖሚ ማዕከል ከወሰድን በሚፈልገው ደረጃ ወይም ቁመና ላይ የሚገኝ ኢኮኖሚ ነው ማለት ስለሚያስቸግረን ዋቢ የምናደርገውን ነገር መለየት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር በተያያዘ በግልጽ እየተለመደ የመጣው ነገር፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የአገልግሎት ዘርፉ ከግብርናው ቀድሞ ለኢኮኖሚው
(ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑ ነው፡፡ መንግሥትዎ ግን በተደጋጋሚ እንደታየው የአገልግሎት ዘርፍ ኢኮኖሚውን ስለመቆጣጠሩ በይፋ ሲቀበል አይታይም ነበር፡፡ ይህ ለምንድነው? እርስዎ በመጽሐፍዎ እንዳሰፈሩት ንቁ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መኖር እንዳለበት ይደግፋሉ፡፡ ይኼ መንግሥትም ይህንን ያደርጋል፡፡ ሆኖም የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴና ምንጮች የሚቆጣጠረው መንግሥት ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንዲያመራ ማስቻል ሲገባው፣ ወደ አገልግሎት በማምራቱ ይህ እንዴት ሊያመልጠው ቻለ?

ዶ/ር አርከበ፡- የአገልግሎት ዘርፉ ለምን ቀድሞ አደገ ካልን የፈጣን ኢኮኖሚ ውጤት ነው ማለት አይደለም፡፡ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ጉዞ ካየነው አገሮች ከግብርና ነው የሚጀምሩት፡፡ ከዚያ አምራች ኢንዱስትሪው ያድጋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ የአገልግሎት ዘርፉም እንዲሁ ይቀጥላል፡፡ ይኼ በኢኮኖሚ ታሪክ ብዙዎች አገሮች የተጓዙበት ተመሳሳይ ሒደት እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛው የአፍሪካ አገሮች በምናይበት ጊዜ የአገልግሎት ዘርፍ የምንለው በተለያዩ ሕጋዊ ያልሆኑ ዘርፎች የሚሳተፈውንም ጨምሮ ነው፡፡ የበለፀጉ አገሮች የአገልግሎት ዘርፍ በሚያድግበት ጊዜ ከማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ጋር የተያያዙ የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው የሚያድጉት፡፡ ለምሳሌ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪ እንደ አንድ አገልግሎት ዘርፍ ብንወስደው ይህ ኢንዱስትሪ በተጠናከረ መልኩ ማደግ የሚችለው ጠንካራ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሲኖር ነው፡፡ ስለሆነም የአገልግሎት ዘርፍ በምንልበት ጊዜ ቀደም ሲልም ካየነው ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ሰፊ ድርሻ ይዞ ቆይቷል፡፡ ይኼንን ግን የዕድገት ውጤት አድርገን ማየት የለብንም፡፡ አንዱ ትልቁ የልማት ጥያቄ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ለመሸጋገር ምንም እንቅስቃሴ ባናደርግ እንኳ የአገልግሎት ዘርፍ ያድጋል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንኳ ባላደገበት ጊዜ ማለት ነው፡፡ ነግር ግን እንደ እኛ ባሉ አገሮች ውስጥ ልማታዊ ጉዞ ይኑራቸው ካልን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አስቀድሞ የማጠናከሩ ሥራ ከሁሉም በላይ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ቀላል ምሳሌ ብናይ፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች አንዷ ናይጄሪያ ነች፡፡ ሦስት ሺሕ ዶላር አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ አላት፡፡ ይሁን እንጂ ከ55 በመቶ በላይ ኢኮኖሚው የተያዘው በአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አላደገም፡፡ ነዳጅ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው ግን ምንም አላደገም፡፡ በሌላ በኩል እንደ ቬትናም ያሉ አገሮች አሉ፡፡ ከ2,000 ዶላር ያልበለጠ የነፍስ ወከፍ ገቢ አላቸው፡፡ ይሁንና ማኑፋክቸሪንግ ጠንካራ መሠረት አለው፡፡ ቻይናም፣ ደቡብ ኮሪያም፣ ታይዋንና ጃፓንም በተመሳሳይ መንገድ ሄደዋል፡፡ ስለዚህ አንድ ኢኮኖሚ ያለማቋረጥ በፍጥነት ማደግና መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የሚችለው፣ ማኑፋክቸሪንግ በፈጣን ደረጃ ሲያድግና የአገልግሎት ዘርፉም ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጋር አብሮ የሚያድግበትን ዕድል በሚያገኝበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ባለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፋችን በጣም አነስተኛ በመሆኑ አብዛኛዎቹ የኢንዲስትሪ ምርቶች አገር ውስጥ አይመረቱም፡፡ ከውጭ እየገቡ ነው፡፡ ኤክስፖርት የምናደርገውና የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፋችንም ከ12 በመቶ ያልበለጠ ትንሽ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ወሳኙ ጉዳይ ይህንን ሁኔታ መለወጥ እንደሆነ መመልከት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ የተሠራው ሥራ የዘገየ በመሆኑ ነው የአገልግሎት ዘርፉ ያደገው ማለት ነው?

ዶ/ር አርከበ፡- የመዘግየት ጉዳይም አይደለም፡፡ ኢኮኖሚ በምኞት አያድግም፡፡ አንድ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ከተጨባጭ ሁኔታህ ነው የምትነሳው፡፡ ስለዚህ ከተጨባጭ ሁኔታችን ስንነሳ ከአርሶ አደሩ መጀመር ነበረብን፡፡ ከግብርና መጀመር ነበረብን፡፡ እርሻ ወይም ግብርና መንቀሳቀስ ሲጀምር ለጊዜው ለውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እንጠቀምበታለን፡፡ የኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች የሚያስፈልጋቸውን ዕቃ ለመግዛት እንጠቀምበታለን፡፡ እንደዚሁም የሰውን የምግብ ፍላጎት ማሟላት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ ነው የምትጀምረው፡፡ ቢያንስ ኢትዮጵያ በተከተለችው ትክክለኛ መንገድ በዚህ መልኩ ነው ለመነሳት የተሞከረው፡፡ ምክንያቱም ግብርናን ማንቀሳቀስ ሳትጀምር ኢንዱስትሪን ለማጠናከር ብትሞክር የሚፈለገው መዋዕለ ንዋይ የሚገኘው ከግብርና በመሆኑ፣ መነሻችን ግብርና ነው ማለት ነው፡፡ ዋናው ግን ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ ከጀመርን በኋላ እንዴት ወደ ፈጣኑ የዕድገት አቅጣጫ መሄድ እንችላለን? እንዴት ነው ማኑፋክቸሪንግ በተጠናከረ መልክ የሚመራውና ኢኮኖሚ የሚፈጠረው? የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ያለው ባለሀብት ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገባ በመንግሥት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደጋግሞ በሚያካሂዳቸው ዘመቻዎችና ቅስቀሳዎች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ ለመጠየቅ የምሞከረው ምንድነው በአጠቃላይ የማበረታቻ መዋቅሩ በራሱ ባለሀብቱን ሳይስበው በዘመቻ እንዲሳብ ማድረጉ ዘላቂነት የሚኖረው ትክክለኛ አካሄድ ነው?

ዶ/ር አርከበ፡- መንግሥት ኢኮኖሚውን የሚመራው በተለይም የግል ዘርፉን ሲያንቀሳቅስ ባህሪውን ለማስተካከል የተለያዩ ማበረታቻዎችንና ድጋፎችን በመጠቀም ነው፡፡ እንዲሁም መበረታታት የሌለባቸውን ዘርፎችና እንደ ልብ ትርፍ የሚገኝባቸውን ዕድሎች በመዝጋት ነው ይህንን ማድረግ የምትችለው፡፡ ስለዚህ ከተለያዩ ባለሀብቶች ጋር የምንገናኝበት መድረክ ካለ ዋና ዓላማው የሚሆነው ስለመንግሥት አጠቃላይ ዕቅድና አቅጣጫ እንዲያውቁ፣ ምን ዓይነት ዕድሎች እንዳሏቸው እንዲያውቁ ለመረዳት ያግዛቸዋል፡፡ ስለዚህ የኢንቨስትመንት ውሳኔያቸውን ከዚህ አኳያ እንዲያዩት ይረዳቸዋል፡፡ በዚህ መልክ ግን ኢንዱስትሪ አይገነባም፡፡ ኢንዱስትሪ የሚገነባው የተመረጡ ዘርፎችን ለማሳደግ የሚያስችል የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ፣ የተሟላ የማበረታቻ ማዕቀፍ፣ የተሟላ የድጋፍ ማዕቀፍ፣ ማነቆዎችን የሚፈቱ ተጨባጭ መፍትሔዎችን ይዞና ተግባራዊ በማድረግም ወደ ሥራ እንዲገቡና የገቡትም ትርፋማ እንዲሆኑ በማድረግ ነው፡፡ ቀዳሚዎቹ ትርፋማ ካልሆኑ ሌሎች አይከተሏቸውም፡፡ የባለሀብቱ አንዱ ዋና ዓላማ ትርፍ ማግኘት ነው፡፡ ትርፍ በማያገኝበት ዘርፍ ውስጥ አይገባም፡፡ ለፅድቅ ብሎ የሚሠራ ማንም ባለሀብት የለም፡፡ የመንግሥት አካሄድም ቢሆን በተለያዩ ዘርፎች ካየን ለምሳሌ በአበባ፣ በቆዳና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች ውስጥ ባለሀብቶቹ ለመሠማራት የሚስፈልጓቸው ድጋፎች ምንድናቸው? ማነቆዎቹስ? ማነቆዎቹን ለመፍታት መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎችና ድጋፎች ምንድን ናቸው? ከሚለው በመነሳት ነው እንቅስቃሴ የሚያደርገው፡፡ ትክክለኛ አካሄዱም ይኼው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተወሰኑ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የማበረታቻ ሥርዓት ዘርግቶ መደገፍ አንድ ነገር ነው፡፡ ወደ አገልግሎቱ ዘርፍ የሄደውን ባለሀብት አሸንፎ ማምጣት ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው የማበረታቻ ድጋፍ ሥርዓት ወደ አገልግሎት የሄደውን ባለሀብት ለመሳብ በቂ ነው?

ዶ/ር አርከበ፡- እስካሁን የነበሩን ማበረታቻዎች በቂ ናቸው አልልም፡፡ ምክንያቱም በተጨባጭ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከመግባት ይልቅ በንግድና በአገልግሎት ውስጥ በመግባት የተሻለ ትርፍ የሚገኝ ከሆነ የውድድሩን ሜዳ አልቀየርነውም ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ መንግሥት የሚያያቸው ማሻሻያዎች አሉ፡፡ ባለሀብቶች የሚፈልጉት ማበረታቻ ስንል ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ወይም ከታክስ ዕፎይታ ማግኘት አድርገን ባናየው ጥሩ ይሆናል፡፡ ባለሀብቶች ወደ አምራችነት ለመግባት የሚፈልጓቸው ሌሎች ማበረታቻዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ፋይናንስ ይፈልጋሉ፡፡ ያለ ፋይናንስ ኢንቨስትመንት ማካሄድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ፋይናንስ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ ኢንቨስተር ወደ ልማት ለመግባት መሬት ያስፈልገዋል፡፡ ከመሬት አልፎ ሕንፃ ያስፈልገዋል፡፡ ከሕንፃ አልፎም መሠረተ ልማት ያስፈልገዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ቴሌኮምና ውኃ ወዘተ. ከዚህም አልፎ ጥሬ ዕቃ ሲያስገባም ሆነ ምርቱን ወደ ውጭ ሲልክ የሎጂስቲክስ ማነቆዎች እንዲያጋጥሙት አይፈልግም፡፡ ዋናው ማየት የሚኖርብን ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስንል በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ውድድር አኳያ የሚመጥን እንቅስቃሴ ሲኖርህ ብቻ ማሸነፍ እንደምትችል ነው፡፡ ለምሳሌ አልባሳት እንዲመረቱ ትዕዛዝ ተሰጥቶ በ30 ቀናት ውስጥ መቅረብ እያለባቸው፣ በ30 ቀናት ውስጥ ማቅረብ የሚችል አምራች ካልሆነ ከውጭ ያሉ ደንበኞችን ትዕዛዝ ማግኘት አይችልም፡፡ ስለዚህ ይህንን የሚመጥንና ማነቆዎችን የሚፈታ አካሄድ መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን የሠራናቸው ሥራዎች በቂ አይደሉም፡፡ በመንግሥት በርካታ ድጋፍ የተሰጠባቸው በርካታ ዘርፎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሲሚንቶን ዘርፍ ብናይ መንግሥት ብድር አመቻችቷል፡፡ የተለያዩ የማዕድን ቦታዎችን አዘጋጅቷል፡፡ ገበያው ራሱ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በጨርቃ ጨርቅም በሌሎችም ዘርፎች ተመሳሳዩ ተደርጓል፡፡ እስካሁን እንዳየነው ግን በቂ አይደሉም፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያየነው ምንድንነው ካልን አንዱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት በርካታ ማነቆዎችን እንዲፈታ ለማስቻል ነው፡፡ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በየፓርኮቹ ውስጥ በማመቻቸትና የጉምሩክ አገልግሎት በፓርኩ ውስጥ ብቻ እንዲሰጥ በማድረግ፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ማነቆዎች የሚፈቱበት፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይልና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ድጋፎች ተመቻችቶላቸው የሚያገኙበት ነው፡፡ መሬት ወስደው፣ ገንብተው ወደ ሥራ እስኪገቡ ድረስ ሦስት አራት ዓመት የሚፈጅ አድካሚ ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች በማመቻቸት አሁን ያሉትን ማነቆዎች የበለጠ ማቃለል ይቻላል በሚል ነው መንግሥት አዳዲስ ዕርምጃዎችን እየወሰደ የሚገኘው፡፡ እስካሁን የነበሩት የድጋፍ ማዕቀፎች በቂ አይደሉም፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያስችሉ ቁልፍ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ሁሉንም ማነቆዎች ሙሉ በሙሉ እንፈታለን ባንልም፣ ዋነኞቹ ላይ በማተኮር መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የምንችልበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንዱስትሪ ዘርፍ ካሉ ማነቆዎች ውስጥ መንግሥት በመጀመርያው ዕቅድም ተስፋ የጣለባቸው የቆዳና የጨርቃ ጨርቅ ዘርፎች ላይ የሚታዩ አሉ፡፡ በተለይ ቆዳ ላይ በግብዓት ገበያ ሰንሰለት ላይ በትልልቅ ቆዳ ፋብሪካዎችና በቆዳ አቅራቢዎች መካከል ባለው ግንኙነት ላይ የሚወጡ ተደጋጋሚ መረጃዎች ችግሩን ያሳያሉ፡፡ ጥጥ ላይም እንዲሁ ነው፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ ዘመን እንዲህ ያሉት ችግሮች እንዴት ይፈታሉ? 

ዶ/ር አርከበ፡- የግብዓት ችግሮችን ካየን በእንስሳት ሀብት ዙሪያ ለውጥ ማምጣት አለብን፡፡ ቆዳ የሚገኘው ከእንስሳት ነው፡፡ ቆዳ ተረፈ ምርት ሲሆን ሥጋ ዋናው ምርት ነው፡፡ ስለዚህ ጤንነቱ የተጠበቀ ቆዳ፣ ከበሽታ ነፃ የሆነ ቆዳ ለፋብሪካዎች መቅረብ አለበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ከውጭም ቢሆን ማስገባት ይችላሉ፡፡ ጥሬ ዕቃ ከውጭ አስገብተህ ሙሉ የፋብሪካ ምርት አድርጎ ማውጣት ራሱን የቻለ ዕድገት ነው፡፡ ጥሬ ዕቃው የግድ ከአገር ውስጥ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ይሁን እንጂ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆንበት ሰፊ የእንስሳት ሀብት ስላለን ጤናማ ቆዳ እንዳይኖር ማነቆ የሆኑትን ጉዳዮች መፍታት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የእንስሳት ሀብትን አስመልክተው የወጡ መፍትሔዎች አሉ፡፡ በዘመናዊ መንገድ እንስሳትን ማርባት የሚፈልጉ ካሉም የሚሳተፉበት መንገድም አንዱ የመፍትሔ አካል ነው፡፡ እያንዳንዱ ዘርፍ በጨርቃ ጨርቅም፣ በቆዳም ሆነ በሌላው መስክ ዘርፎችን በልዩ መልክ በማየትና ማነቆውን በመለየት ሥራውን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ካለፈው ልምድ በመነሳት በርካታ ማሻሻያዎች በአሁኑ ዕቅድ ተካተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪ ዕድገት ታሪኮች አኳያ በመጽሐፍዎ የጠቀሱትን የምሥራቅ እስያ አገሮችን ብንመለከት ለተቋማዊ ለውጥ ትልቅ ቦታ ሰጥተው አትተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ቆዳ፣ ጨርቃ ጨርቅና ኬሚካል ዘርፍ ላሉት ድጋፍ የሚሰጡ ኢንስቲትዩቶች ቢቋቋሙም በርካቶቹ ለውጥ እንዳላመጡ ተገምግመዋል፡፡ ችግራቸው ምን ነበር? እርስዎ እነዚህ ተቋማት ኢንዱስትሪውን አገልግለዋል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር አርከበ፡- በእኔ እምነት ተቋማቱ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በበቂ ደረጃ ድጋፍ አድርገዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ በአበባ ዘርፍ ያለውን የሆልቲካልቸር ኤጀንሲ፣ በቆዳ ዘርፍ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍም ያለው መፍትሔውን በመተግበር ረገድ መሄድ የቻሉት ርቀት አለ፡፡ ይኼንን መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ባለሀብቱም ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ወደ እነዚህ ተቋማት በማምራት ችግሮቹን ለመፍታት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡ ተቋማቱ አካባቢ የተሟላ የላቦራቶሪ ድጋፍና ሥልጠናም ይሰጣሉ፡፡ ዋና ችግሮች ምንድን ናቸው ብንል ግን ከቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ከዕውቀትና ከክህሎት ሽግግር ጋር በተያያዘ የእኛ ባለሙያዎች ብዛት በቂ አይደለም፡፡ መንግሥት መፍትሔ አድርጎ የወሰደው ጥሩ አቅም አላቸው ከሚባሉ የውጭ ተመሳሳይ ኢንስቱትዩቶች ጋር በቁርኝት እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ልምድ ይወስዳሉ፣ ይማራሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት ዕድገት በኢንስቲትዩቶች ብቻ የሚመጣ ለውጥ ባለመኖሩ ባለሀብቶቻችን እንዲማሩ የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡  ባለሀብቶችን በሁለት መንገድ መለየቱ ጥሩ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ጫማ አምራቾች ወይም ጓንት የሚያመርቱ የውጭ ድርጅቶች ከሆኑ ከመንግሥት የሚፈልጉት የቴክኖሎጂ ድጋፍ የለም፡፡ ገበያው አላቸው፡፡ የማኔጅመንት ክህሎት አላቸው፡፡ የቴክኖሎጂና ሥራውን ለማስተባበር የሚችሉ ሰዎችም በበቂ አላቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን አስመልክቶ የምናደርገው ሌሎች የሚያጋጥሟቸውን አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ ማነቆዎችን መፍታት ነው፡፡ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን ማስቀረትና ሌሎች ድጋፎችን ማሟላት ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ባየን ጊዜ ግን ተጨማሪ ድጋፍና ሥልጠና ይፈልጋሉ፡፡ ተጨማሪ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ በመንግሥት ኢንስቲትዩት ከሚደረገው ድጋፍ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ቀዳሚ የሆኑ ድርጅቶች እንዲመጡና ኢትዮጵያውያን ተቋማትም ከእነሱ የሚማሩበትን ዕድል መፍጠር መቻል ነው፡፡ ይህንን መፍጠር ከቻልን፣ ፈጣን የክህሎት ሽግግር በዚህ መንገድ ማምጣት ይቻላል ማለት ነው፡፡ የአበባ ዘርፍን በምሳሌ በምናይበት ጊዜ አንዱ የውጭ ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ የቆዩ ሰዎች ኢትዮጵያውያን የሚመሩት ድርጅት ጋ በሚሄዱበት ጊዜ የዕውቀት ሽግግር ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዕውቀት ሽግግር ፈጣን እንዲሆን ሁሉን ነገር ከኢንስቲትዩት ከመጠበቅ ይልቅ በክህሎትም፣ በችሎታም፣ በዘመናዊ ማኔጅመንትና በገበያ ትስስር ቀዳሚ የሚባሉ ድርጅቶችን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማድረግ፣ ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር በመሆን ተቋም ከተቋም ጋር ትስስር እንዲኖር ማድረግም አንዱ የመፍትሔ አድርገን ማየት ይኖርብናል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል በምንልበት ጊዜ የካፒታል እጥረትን ለማቃለል አይደለም፡፡ ዋናው የቴክኖሎጂ፣ የገበያና የማኔጅመንት ክህሎትን ማሻሻል አንዱ ቁልፍ የመፍትሔ አካል ብለን ስለምንወስደው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪ ዕድገት አኳያ እስካሁን ተመሥርተው የነበሩትን ተቋማት መልሶ የማዋቀር አካሄድ ባለፉት አምስት ዓመታት ሲሠራበት ነበር፡፡ የነበሩትን የማለያየት፣ የተለያዩትን የማዋሀድና አዳዲሶችን የማምጣት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የተቋማት ዘለቄታዊነት ጉዳይ እዚህ ላይ ሊነሳ ይችላል፡፡ በርካቶች ሥጋታቸው ቀደምት ተቋማት ሲጠፉ ይዘዋቸው የነበሩ ነገሮች እንዳይጠፉ ነው፡፡ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ይደረጋል? ስለዚህ ጉዳይ ታስባላችሁ?

ዶ/ር አርከበ፡- የተቋም አቅም ግንባታን አስመልክቶ በፈጣን ጉዞ ላይ ያሉ አገሮች ከመነሻው የተሟላ አቅም ይዘው አይደለም የሚጀምሩት፡፡ አቅም ከገነባህ በኋላ አይደለም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የምትገባው፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት ለማከናወን በምታደርገው ጥረትና ሒደት ነው ተቋማት የሚፈጠሩት፡፡ ሁሉንም ቢሮክራሲያችንን ከወሰድን እንደ ተቋማት አድርገን መውሰድ እንችላለን፡፡ ይኼንን መለወጥ ግን የማይቻል ነው፡፡ በበርካታ አገሮች ውስጥም ተመሳሳይ ማነቆዎች አሉ፡፡ ዋናው ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ልማትን በማፋጠን ቁልፍ ድርሻ ያካቸው አካላት የትኞቹ ናቸው ብለን በመለየት፣ እነዚህን ለመለወጥ መጣር ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ የታክስ አስተዳደር ተቋም ቁልፍ ተቋም ነው፡፡ በኢንቨስትመንትም በኢንዱስትሪ ልማትም በጣም ይፈለጋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ቁልፍ ተቋም ነው፡፡ ፓርኮችን እናልማ ካልን የፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በጣም ቁልፍ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ከተቋማቱ መለየትና እነዚህ ላይ ያተኮረ፣ ሰፊ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ መሠራት አለበት፡፡ አቅም ማጠናከር በምንልበት ጊዜ አሁንም ማየት የሚኖርብን በሥልጠና ብቻ እንለውጣለን ማለት አይደለም፡፡ ጠንከር ካሉ የውጭ ተቋማት ጋር አብረው እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ የውጭ ባለሙያዎችን በሚገባ መጠቀም ይገባል፡፡ በቂ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከባለሀብቱ በሚገኘው ግብዓት መሠረት አሠራራቸውን ለማሻሻል መሞከሩን ማየት አለብን፡፡ በእኔ ዕምነት ሁሉንም ተቋማት መቀየር የምንችል አይመስለኝም፡፡ ሌሎች አገሮችም ሁሉንም ተቋም በመቀየር አይደለም ለውጥ ያመጡት፡፡ የማይተካ ሚናና ቁልፍ ድርሻ ያላቸውን ተቋማት ለይተን እነሱ ላይ አጥብቀን መሥራቱን መቀጠል ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተቋማት ላይ የመልሶ ማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው የሚል ምልከታ ሊኖረን አይገባም፡፡ የትኞቹ ናቸው አሁን ለያዝናቸው ቁልፍ ሥራዎች ቁልፍ ሚና ያላቸው ብለን ማየት ይኖርብናል፡፡ የተቋማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ሁሌም ቢሆን በጣም ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  እርስዎን ጨምሮ መንግሥትም የአምራች ኢንዱስትሪውን ዕድገት ለማምጣት በኢንዱስትሪ ዞኖችና በኤክስፖርት ዞኖች ግንባታ ሥራ ላይ አተኩራችኋል፡፡  የዚህ አካሄድ ጥሩ ጎን ምንድነው? አንዳንዶች እንደሚሉት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ሲባል የመጣ ነው? ወይስ የራሱ አወንታዊ ጎኖች አሉት?

ዶ/ር አርከበ፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወይም በሌላ አገላለጽ የኢንዱስትሪ ዞኖችን የኢኮኖሚ ዞኖች ይሏቸዋል፡፡ ለምን አስፈለጉ በምንልበት ጊዜ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ማምጣት ካለብን ምንድን ነው ማድረግ ያለብን የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ ፈጣን የኢንዱስትሪ ልማት ካስፈለገ በማኑፋክቸሪንግ ዙሪያ የተሰማሩ ምርጥ ድርጅቶችን መሳብ ይኖርብናል፡፡ ሁሉም ለማጅ መሆን አይችልም፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ገና ጀማሪዎች ነን ካልን ልምድ ያላቸው የውጭዎቹ መሆናቸው ምንም የሚያወላዳ ነገር የለውም፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደ ጠላት ማየት የለብንም፡፡ ጠላት አይደለም፡፡ ሁሉም አገሮች ይፈልጉታል፡፡ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና ሁሉም የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ይፈልጋል፡፡ ዋናው እዚህ ማንሳት ያለብን የውጭ ኢንቨስትመንትን ለምን እንደምንፈልግ ነው፡፡ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛ የገበያ ትስስር እንፈልጋለን፡፡ እዚህ ለምሳሌ ልብስ ሰፍተህ ኒውዮርክ ሄጄ እሸጣለሁ ብትል አትችልም፡፡ ስለዚህ አንደኛ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማምጣት ነው፡፡ ሦስተኛ የማኔጅመንት አመራር ሥልትን ለመቅሰም ነው፡፡ እነዚህ በኢንዱስትሪ ልማት በስፋት ልምድ ማካበትን ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ በምንመርጣቸው ዘርፎች ቀዳሚ የሚባሉ ድርጅቶችን መሳብ በጣም ያስፈልገናል፡፡ ቀዳሚ የሚባሉትን ድርጅቶች ለመሳብ በምንሞክርበት ጊዜ ኢትዮጵያ መምጣት ከፈለጉ ወደ ሥራ ፈጥነው የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን፡፡ ፈጥነው የሚገቡበትን ዕድል መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ቶሎ ወደ ሥራ ሲገቡ አንደኛ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ኤክስፖርት በምናደርግበት ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እናገኛለን፡፡ የውጭ ምንዛሪ ችግራችንን ለመቅረፍ ይረዳናል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለብን ይታወቃል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የአገር ውስጥ ተጨማሪ የምርት አቅምና የልማት ትስስር ይጠናከራል፡፡ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሲኖር ጥጥ ማምረት ይቻላል፡፡ ጥጥ የመዳመጥ አቅም ያድጋል፡፡ ስለዚህ በርካታ አብረው የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ በፓርኮቻችን በመረጥናቸው መስኮች ላይ ምርጥ የሚባሉ ድርጅቶችን ስንስብ ወደ ምርት ቶሎ እንዲገቡ ያስችላቸዋል፡፡ ቀላል ምሳሌ ለመስጠት ቦሌ ለሚ ላይ አንድ የኮሪያ ድርጅት አለ፡፡ ይህ ድርጅት በሦስት ወራት ውስጥ ነው ምርት የጀመረው፡፡ ሲጀምር 1,000 ሠራተኞችን ቀጥሮ፣ አሠልጥኖ፣ መሣሪያዎችን ተክሎ ወደ ጀርመንና ወደ ጣሊያን በሦስት ወራት ውስጥ ኤክስፖርት አድርጓል፡፡ ስለዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ ከፈለግን ይህንን ማድረግ ያስፈልገናል፡፡ ፋብሪካዎች በስፋት የሚስፋፉ ከሆነ አካባቢ የመበከል ሁኔታ ይኖራል፡፡ ስለዚህ በየቦታው እንዲበተኑ አንፈልግም፡፡ የሚያወጡት ፍሳሽም ሆነ ደረቅ ቆሻሻ በሚገባ መከላከል ይኖርብናል፡፡ ይህንን ለማድረግም ፋብሪካዎችን አንድ አካባቢ ማሰባሰብ ያስፈልገናል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ በጣም ቁልፍ ሥራ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ እየጎላ መጥቷል፡፡ የአገር ውስጥ አምራች በበኩሉ ወደ ሥራ ይግባ ካልን አሁን ባለው አካሄድ ወደ ምርት መግባት አይችልም፡፡ መሬት ጠይቀው፣ ብድር ጠይቀው፣ ሕንፃ ገንብተው፣ እንደገና መሠረተ ልማት አሟልተው እንዲሄዱ ካልን ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሉበት ሕንፃውን ለመረጡት ዘርፍ ተከራይተው ለዚህ የካፒታል ወጭ ሳያደርጉ፣ መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ከሄዱ፣ ከእነሱ የሚጠበቀው ሠራተኛ መምረጥ፣ መቅጠርና ማሠልጠን፣ እንዲሁም ለመሣሪያና ለሥራ ማስኬጃ የባንክ ብድር ማግኘት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሁሉንም አገልግሎት እዚያው ያገኛሉ፡፡

ስለዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአገር ውስጥ ባለሀብት እንዲጠናከር የሚያደርግ ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ሌላው ተጨማሪ ምክንያት ፋብሪካዎች በባህሪያቸው ትስስር፣ መሰባሰብ ይፈልጋሉ፡፡ መርካቶን እንደ ምሳሌ ብንወስድ፣ በርካታ ሱቆች ያሉበት በመሆኑ ሸማቹ የሚፈልገውን ዕቃ እዚያ ቢሄድ እንደሚያገኝ ያውቃል፡፡ ሻጩም ዕቃውን እዚያ ቢወስድ ሸማች እንደሚያገኝ ያውቃል፡፡ በፋብሪካም ይኼ የመሰባሰብ ባህሪይ በጣም የተጠናከረ ነው፡፡ ከግብርናም የሚለየው ይኼው ነው፡፡ ፋብሪካዎችን እንደ እርሻ ማሳ በየቦታው መበተን አትችልም፡፡ ከፍተኛ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ በመሰባሰብ የክህሎት ሽግግር እንዲኖርና የምርት ትስስር እንዲኖር ይረዳል፡፡ ስለዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የምናስበውን ፈጣን የኢንስትሪ ልማት ለማከናወን የምንችልባቸው ናቸው፡፡ የሌሎችንም ልምድ ብናይ ተመሳሳይ ነው፡፡ ቀድመው ካደጉት እንደ አሜሪካና እንግሊዝ ላሉት ግን የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ማስፋፋት ብዙም አስፈላጊያቸው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በመቶ ዓመት ውስጥ ነው ያደጉት፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1960 ጀምሮ በተለይ በእስያ አካባቢ ያደጉ አገሮች እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ማሌዥያ፣ ቻይና ያሉትን በምናይበት ጊዜ ፈጣን ልማትን ለማምጣት የተጠቀሙበት ዋነኛው መሣሪያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ጋር በተያያዘ ግልጽ መሆን ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሲባል አንዳንድ ሰው የሚመስለው የፋብሪካ ሕንፃ መገንባት ነው፡፡ ይኼ ግን አይደለም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ የተሟላ ሥርዓት ነው፡፡ ተቋም ነው፡፡ መሠረተ ልማቱ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ከፍተኛ ደረጃ ያለው መሆን ካልቻለ ተጠቃሚዎቹ ምርታማ ሆነው ማምረት አይችሉም፡፡ መጠበቅና መከተል የሚገባቸው ዓለም አቀፍ ደረጃዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከባንግላዴሽ ቃጠሎ ወዲህ የተቀመጡ፣ በተለይ ዋናዎቹ ገዥዎች የሚባሉት ያስቀመጧቸው ደረጃዎች አሉ፡፡ የበር ደረጃ ምን ያህል መሆን እንዳለበት፣ አጥሩ፣ የአሜሪካ የሴፕተምበር 9/11 ከሚባለው ጥቃት ወዲህ ያስቀመጧቸው በርካታ የጥራት ደረጃዎች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ኤክስፖርት ለማድረግ ሲያስፈልግ ለምሳሌ ዕቃው ሲጫን በቪዲዮ መቀረፅ አለበት፡፡ እነዚህን ደረጃዎች ሁሉ ማሟላት ይኖርብሃል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የአካባቢ ጥበቃ መኖር አለበት፡፡ ሕንፃው መገንባቱ፣ መሠረተ ልማቱ መሟላቱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በዚያ የሚሠሩ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሙያዎች የሚፈልጓቸውን ድጋፎች ማግኘት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ አሁን በሰፊው እየሠራችሁት ያለው የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከገቡ በኋላ ምርታቸውን ኤክስፖርት እንዲያደርጉና የውጭ ምንዛሪ እንዲያስገኙ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ሆኖም ግን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ይዞታ በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ጥሬ ዕቃ እንኳ ለማስገባት እየተቸገሩ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ ጥሬ ዕቃ አምጥተው መሥራት ካልቻሉ ዶላር ማምጣት አይችሉም፡፡ የዚህ ችግር አዙሪት ቀለበት እንዴት ነው የሚፈታው?

ዶ/ር አርከበ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ ወይ ካልክ ምንም የሚደበቅ ሚስጥር የለውም፡፡ አዎ እጥረት አለብን፡፡ በአንድ በኩል የዕድገት ደረጃችን ውጤት ነው፡፡ አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ለምን ተግባር እየዋለ ነው ብለን ካየን፣ ለማሽነሪዎችና ተያያዥ ለሆኑ ጥሬ ዕቃዎች ግዥ የውጭ ምንዛሪ እየተጠቀምን በመሆኑ ነው፡፡ አሁን ክፍተቱ ለምን ሰፋ ካልንም የኤክስፖርት ገበያችን ባለማደጉም ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የታየው የኤክስፖርት ገቢ ዕድገት በጣም ዝግመታዊ ነበር፡፡ በአሁኑ አምስት ዓመት የወጪ ንግድ ዕድገት 30 በመቶ ይሆናል ብለናል፡፡ ባለፈው የአምስት ዓመት ዕቅድ ያስቀመጥነው የወጪ ንግድ ግብ በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያ ልክ ማሳካት አልቻልንም፡፡ ለምንድን ነው ካልን በወጪ ንግድ ዘርፍ ትልቅ ድርሻ ሊኖረው የሚገባው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባለማደጉ ገቢው ቀንሷል፡፡ የግብርና ምርት በዓለም ገበያ የመውደቅ አዝማሚያ አለው፡፡ የፋብሪካ ምርት በሚሆንበት ጊዜ፣ በሚቀነባበርበት ጊዜ ግን ዋጋ ይጨምራል፡፡ በቁም እንስሳት መልክ ኤክስፖርት ስታደርግና ሥጋ ከቄራዎች ታሽጎ ወደ ውጭ ሲላክ የሚገኘው ገንዘብ ለየብቻው ነው፡፡ የለፋ ቆዳ ስትልክና በጫማ መልክ ስትልከው የሚገኘው ገቢ ለየብቻው ነው፡፡ ስለዚህ ኤክስፖርትን የሚመለከቱ ማነቆዎችን በወቅቱ ስላልፈታናቸው፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ያሉ አምራቾች በሚገባ ዘርፉን ማወቅ ስላልቻሉ፣ የግብርና ምርታማነትን በሚመለከትም የዓለም ገበያ የሚጠይቀውን ወጪ መሠረት ባደረገና ጥራትን መሠረት ባደረገ መልኩ በከፍተኛ መጠን ማሳደግ ስላልቻልን የመጣ ነው፡፡ ከዚህ አዙሪት የምንወጣው እንዴት ነው ስንል አንደኛ ፈጥነን በርካታ ፋብሪካዎችን በማልማት ነው፡፡ ፋብሪካዎችን ማስፋፋት የሞት የሽረት ጉዳይ ነው የምንልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ድርቅ በየጊዜው ያጋጥመናል፡፡ ከእንግዲህ በኋላም ያጋጥመናል፡፡ ምክንያቱም በመስኖ ላይ የተመሠረተ ግብርና እስኪሆን ድረስ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ ግብርና ብቻ ግን ኢኮኖሚውን ከተሸከመ በየጊዜው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሲደጋገሙ ከዚህ አዙሪት የማንወጣበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚው ሁለተኛ እግር ያስፈልገዋል፡፡ ግብርናውን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን በማጠናከር ስንደግፈው የግብርና ምርት በፋብሪካ ምርት ያልፋል፣ ጥሩ ዋጋ ያወጣል፣ ገቢም እናገኛለን፡፡ ማኑፋክቸሪንግ እያደገ ሲሄድ የሚፈልጋቸው የግብርና ግብዓቶች ይኖራሉ፡፡ ጥጥና ሌሎችም በስፋት ከግብርና እንዲቀርቡ የሚያስገድድ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ወደ ውጭ የምንልከበትን ዕድል በማስፋትና አሁን በገፍ የሚገቡትን የገቢ ዕቃዎች አገር ውስጥ የሚመረቱበትን ዕድል በምንፈጥርበት ጊዜ ደግሞ፣ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማጠናከር ማለት ሲሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እየተቃለለ ይሄዳል፡፡ አሁን ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተፈጠረ አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ቻይና ወደ ፈጣን ዕድገት ስትገባ ተመሳሳይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነበረባት፡፡ በርካታ በፈጣን ልማት ያለፉ አገሮች በዚህ ችግር ውስጥ አልፈዋል፡፡ ስለዚህ አሁንም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው፣ የኤክስፖርት ዘርፍ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው ካልን፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በስፋት ማስፋፋት የምንችለው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ስናስፋፋ ነው፡፡ እየደጋገምኩ የማነሳው ለዚህ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለውድቀት በር በማይከፍት መንገድ በወቅቱ እንዲለሙ ካደረግን የውጭ ምንዛሪ ችግርን የምናቃልልበት መንገድ ይፈጠራል፡፡ በአንድ ዓመት ያልቅ የነበረ ሥራ በአምስት ዓመት ካለቀ፣ ኤክስፖርት የማድረግ አቅማችንን ገድበነዋል ማለት ነው፡፡ የሐዋሳ ፓርክ ሥራው ሲጠናቀቅ ኤክስፖርት ማድረግ ይጀምራል፡፡ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሙሉ አቅሙ ማምረት በሚጀምርበት ጊዜ የራሱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ከማሟላት አልፎ የተወሰነ ትርፍ ለኢኮኖሚው ያበረክታል፡፡ በአዳማ፣ በመቀሌ፣ በኮምቦልቻ፣ በባህር ዳር ከሚመጀመሩት ኢንዱስትሪ ፓርኮችም እንዲሁ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ማጠንጠኛው ምንድነው ስንል ፈጥነት ከዚህ አዙሪት መውጣት የምንችለው ማኑፋክቸሪንግን በማጠናከር ነው፡፡ እዚያው አዙሪት ውስጥ ሆነን ሳይሆን ከአዙሪት በመውጣት ችግሩን የምንፈታው፡፡ ይህንን ስናደርግ የተለመደውን አካሄድ በመከተል ሳይሆን፣ ወጣ ባለ መንገድ ስንሠራ ነው ከዚህ ችግር የምንወጣው፡፡

ሪፖርተር፡- የኤሌክትሪክ ኃይልን እናንሳ፡፡ ከተሞችና ኩባንያዎች የኃይል ሽሚያ እያካሄዱ ለመጠቀም ተደገደዋል፡፡ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሰሞኑን ያጋጠሙት ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ከኢንዱስትሪው አኳያ ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ እንዴት ነው መፍትሔ የሚሰጣቸው? 

ዶ/ር አርከበ፡- ማኑፋክቸሪንግ እናስፋፋ ካልን አንዱ ቅድመ ሁኔታ ጎን ለጎን ማድረግ የሚገባን የኢነርጂና የኃይል አቅርቦትን ማነቆ ወደ ማይሆንበት ደረጃ ማውረድ ነው፡፡ በጣም ቁልፍ ጥያቄ ነው፡፡ ፋብሪካዎቹ ለምንድን ነው ለኪሳራ የሚዳረጉት ብለን ብናይ በወር ውስጥ ለአምስት ቀናት ሳያመርቱ ከቀሩ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ያለው የትርፍ ህዳግ በጣም ትንሽ በመሆኑ፣ አምስት ቀናት ሳያመርቱ ካለፉ ወደ 15 በመቶ የምርት ጊዜያቸውን ስለሚያጡ በምንም ሁኔታ ትርፋማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የማምረት አቅማቸው ተገድቧል፡፡ ነገር ግን ኢነርጂ በወቅቱ ሳያገኙ ሲቀሩ ከውጭ እንዲያመርቱና በአራት ወይም በአምስት ሳምንት እንዲያደርሱ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ማድረስ አይችሉም፡፡ አንዳንዶቹ ፋብሪካዎች በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት ምርታቸው በመስተጓጎሉ በመርከብ መላክ የነበረባቸውን በአውሮፕላን በመላካቸው፣ ገዥው ቀጣይ አዲስ ትዕዛዝ የሰረዘባቸውን ፋብሪካዎች አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ የኢነርጂ አቅርቦት በጣም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ የብዙዎች አገሮችም ማነቆ ይኼው ነው፡፡ ቻይናም የኃይል አቅርቦት ትልቅ ማነቆዋ ነው፡፡ የኃይል መቆራረጥ ችግር ባይኖርባቸውም እጥረት ግን አለባቸው፡፡ አብዛኛው የኃይል ምንጫቸው ከከሰል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለኢንዱስትሪያቸው መቆም ትልቁ ምክንያት ከኃይል ማመንጨት አቅማቸው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ ኃይል የመማንጨት አቅማችንን ችግር መፍታት ብቻም ሳይሆን፣ ኃይል የሚያመነጨውን ዘርፍ እንደ ትልቅ ኢንዱስትሪና ትልቅ የገቢ ምንጭ አድርጎ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ በአሥር ዓመት ዕቅዳችን ውስጥ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ብለን ከለየናቸው የኢነርጂ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ይህንን ዘርፍ ትልቅ ማድረግ አለብን፡፡ ኤክስፖርት ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ በኃይል ማመንጨት ቴክኖሎጂ ማሳደግ፣ በበቂ ደረጃ የኃይል ማመንጨት አቅማችንን ማዳበሩ ላይ ማሰብ አለብን፡፡ ከእጥረት አልፈን እንዴት ወደ ትልቅ አቅም እንደምንቀይረው ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን የሠራነው ሥራ በቂ ነው አይባልም፡፡ አሁንም ከችግሩ አልወጣንም፡፡ መንግሥት ግን የኃይል ማመንጫ ደካማ ቋጠሮአችን እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ በሚቀጥሉት አምስትና አሥር ዓመታትም እስካሁን ከያዝናቸው በተጨማሪነት ለምሳሌ የግሉ ዘርፍ በኃይል ማመንጨት ዘርፍ መሠማራት ይችላል፡፡ ፖሊሲው ይፈቅድለታል፡፡ ይሁን እንጂ ያመነጨውን ለኤሌክትሪክ ኃይል መሸጥ አለበት፡፡ በመሆኑም የኃይል ማመንጨት አቅማችን በጣም ሰፊ ነው፡፡ በንፋስ ላይ የተመሠረተው አቅማችን ሰፊ ነው፡፡ ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት ይቻላል፡፡ ከጂኦተርማል እንዲሁ ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት ይቻላል፡፡ ሌሎችም አማራጮች እንዲሁ፡፡ የኃይል ዘርፍ መንግሥትን የሚፈታተን ትልቅ ዘርፍ ነው፡፡ ያለ ኢነርጂ የፋብሪካ ምርት የሚባል ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ዓላማችን የአሥር ዓመት ራዕያችን ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከሚባሉት የማኑፋክቸሪንግ አገሮች የላቀች ማዕከል እናድርጋት ለሚለው ትልቅ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ምን ያህል ኃይል ማመንጨት እንደሚያስፈልግ በዕቅዳችን ተቀምጧል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብክለትን ለመቀነስ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንደሚሠራ ጠቅሰውልናል፡፡ በቀደሞው አሠራር በአዲስ አበባ ዳርቻ የኢንዱስትሪ መንደር ተብለው የሚሰጡ ቦታዎች ነበሩ፡፡ በርካታ ኢንዱስትሪዎችም አሉ፡፡ ሆኖም በእነዚህ አካባቢዎች የአካባቢ ብክለት ትልቅ ችግር ነው፡፡ የአዋሽ ወንዝን ብናይ ብክለት አሳሳቢ እየሆነበት ነው፡፡ ስለዚህ በፓርኮቹ አካባቢ ብክለት እንዴት ነው ቁጥጥር የሚደረግበት?

ዶ/ር አርከበ፡- መንግሥት የአካባቢ ጥበቃንና የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት እ.ኤ.አ. እስከ 2030 ተግባራዊ የሚያደርገው ስትራቴጂ ቀይሷል፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህ በግብርና፣ በከተሞች፣ በኢንዱስትሪ ዙሪያና በሌሎችም ላይ የሚፈጸም በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦችን የያዘ ነው፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ስንመጣ በተለይ በእስያም እንደታየው ኢንዱስትሪዎች አካባቢ የመበከል ባህሪ አላቸው፡፡ ይህንን ለመቆጣጠር ምንድነው የምናደርገው ለሚለው በመንግሥት የተቀመጡ መፍትሔዎች አሉ፡፡ አንደኛ እኛ ጋ የሚጠቀሙት የኃይል ምንጭ ታዳሽ ነው፡፡ በከሰልና በናፍጣ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ስለዚህ በመንግሥት የታዳሽ ኃይሎችን አቅም ማሳደግ በዕቅድ የተያዘ ነው፡፡ ሁለተኛው ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህም በከተማና በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን፣ መንግሥት እዚህ ላይ ከሚከተላቸው አካሄዶች መካከል ለምሳሌ የቀላል ባቡር ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀስ በመሆኑ የከተማ ብክለትን ለመቀነስ ይረዳናል፡፡ የባቡሩ ኔትወርክ ወደፊት እየሰፋ ሲመጣ የተሽከርካሪ ፍላጎትን ይቀንስልናል፡፡ አገር አቀፉን ካየነው ደግሞ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ የተዘረጋው ባቡር ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚታገዝ ነው፡፡ ስለዚህ ብከላ እየቀነስን ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አረንጓዴ ማድረግ ነው፡፡ ከመጀመሪያውም በፓርኮች አካባቢ ምንም ዓይነት ፍሳሽ እንዳይለቀቅ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ እንጠቀማለን፡፡ ብዙውን ጊዜ ከፋብሪካዎች የተጣራ ፍሳሽ ይወጣል፡፡ በእስያም ኢንዱስትሪዎች የተጣራ ፍሳሽ ይለቃሉ፡፡ የተጣራ ቢባልም የመበከል አቅም አለው፡፡ በእኛ ሁኔታ እያልን ያለነው ግን የተጣራ ፈሳሽም ቢሆን እንዳይወጣ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ነው፡፡ አሁን ያሉት ፋብሪካዎች በተለያዩ አከባቢዎች የሠፈሩ ናቸው፡፡ አከባቢን እየበከሉም ነው፡፡ ለምሳሌ በአቃቂ መስመር ያሉ፣ ሞጆ አካባቢ ያሉ የቆዳ ፋብሪካዎች ይጠቀሳሉ፡፡ በሞጆ አካባቢ በርካታ የቆዳ ፋብሪካዎች ስለሚገኙ ማዕከላዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት በዚያ ላሉትና ወደፊት ለሚመጡትም የሚያገለግል የብክለት መከላከያ ተቋም ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ፋብሪካዎች የራሳቸው ፍሳሽ ማጣሪያ ቢኖራቸውም ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ ይኼም የሌላቸው አሉ፡፡ ስለዚህ ለሁሉም የሚያገለግል የፍሳሽ ማጣሪያ ለመገንባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በዕቅዱ የያዘው ተግባር ነው፡፡ ተጨባጭ የሆነ የአከባቢ ብክለትን የሚቀንስ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ ከዚህ ወጣ ባለ መልኩ ያረጁ ፋብሪካዎች ካሉ ምርታቸውን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲያሸጋግሩ ዕገዛ ይደረጋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ገና ዝርዝር ሥራ አልተሠራም፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንዴት እንደሚያስቆም መንግሥት በሚገባ አስቦበት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ የጠቀሱት እስካሁን ያለው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ልማት ፖሊሲ ማትጊያዎች በመስጠት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ተከታትሎ ማትጊያ መስጠት ብቻም ሳይሆን የመቅጣትም ስትራቴጂ መውጣት አለበት ብለው የሚመክሩ አሉ፡፡ እስካሁን ከማትጊያ ስትራቴጂው ጎን ለጎን ቅጣትና መሰል ይዘቶች አብረው መጓዝ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነበር? ወደፊትስ ምን ታስቧል?

ዶ/ር አርከበ፡- ማበረታቻ መስጠትና መቅጣት አንደኛ የማበረታቻዎችን የማስተዳደር ብቃትን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ኤክስፖርተር ነው እንበል፡፡ ለኤክስፖርተሮች የሚሰጥ ማበረታቻ አለ፡፡ ለኤክስፖርት ተብሎ ያስገቡት ወይም የሚሰጣቸውን ማበረታቻ ለተባለለት ዓላማ ስለመዋሉ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለመቆጣጠር ብለህ አንቀህ ብትይዘው ሥራው ይቆማል፡፡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ብቃት ያለው ቢሮክራሲም ያስፈልግሃል፡፡ ሌሎች አገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢሮክራሲያቸውን በከፍተኛ ደረጃ አቅሙ እንዲያድግ በማድረግና ማበረታቻዎችን የማስተዳደር አቅም ገንብተዋል፡፡ እኛ ገና ጀማሪዎች ነን፡፡ ኢንዱስትሪ መገንባት አልጀመርንም፡፡ ስለዚህ እስካሁን ድረስ የሄድንባቸው ካሉም በትንሽ ደረጃ ነው፡፡ አሁን ከምንገባበት ሰፊ የዕድገት ደረጃ ሲታይ በትንሹ ነው የተንቀሳቀስነው ማለት እንችላለን፡፡ በትንሹም ቢሆን ግን ተግባራዊ ለማድረግ የተደረገው ጥረት ጥሩ ነው ብዬ እወስዳለሁ፡፡ ለምሳሌ ሆቴሎች ማበረታቻ ይሰጣቸዋል፡፡ አልጋ ያስገባሉ፡፡ የሕንፃ ዕቃዎችን በነፃ ያስገባሉ፡፡ ከሦስት ወይም አራት ዓመት በፊት እንዳየነው ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች መርካቶ ይሸጡ ነበር፡፡ ይኼ የመቆጣጠር ብቃትን ይጠይቃል፡፡ እንቆጣጠር ብለን ሁሉን ቀዳዳ ለመድፈን ስንሞክር ደግሞ ሥራው ይቆማል፡፡ ሁለቱን አጣጥመን መሄድ እስከተቻለ ድረስ በአስተዳደራዊ መንገድ የምትቆጣጠርበትን መንገድ መቀነስ ጥሩ ይሆናል፡፡ ጥሩ ምሳሌ መሬት ነው፡፡ መሬት ትልቁ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የሚታይበት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ብቻ ነው መሬት የሚያቀርበው፡፡ ሁሉም ሥራ ደግሞ መሬት ይፈልጋል፡፡ ለግብርና መሬት ይጠየቃል፡፡ ፋብሪካው መሬት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ እስካሁን ባለው ሁኔታ ካየን ፋብሪካ ወይም ሆቴል የሚገነባ ሰው መሬት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ ይገጥመዋል፡፡ በጨረታም ሲባል ውስብስቡ ብዙ ነው፡፡ የወሰድነውን አማራጭ እንይ፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚገቡ በሙሉ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ መሬት ማግኘት ይችላሉ፡፡ በዚያ የገነባናቸውን ሕንፃዎች ዋጋቸውን ከፍለው መግዛት ይችላሉ፡፡  መሬቱን ተከራይተውም ሕንፃ መገንባት ይችላሉ፡፡ አሊያም የፋብሪካውን ሕንፃ መከራየት ይችላሉ፡፡ ሦስት አማራጭ አላቸው፡፡ ይኼ ምንድነው አንድምታው ስንል በከተሞች ከፋብሪካ መሬት ጋር በተያያዘ ያለውን ኪራይ ሰብሳቢነት ወደ ዜሮ ያወርደዋል፡፡ ለፋብሪካ መሬት መስጠት አንዱ ማበረታቻ ነው፡፡ ሆኖም የሚሰጡ ማበረታቻዎችን በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ውጤታማነታቸውን መገምገም ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን ጅምር ልምድ ብቻ ነው ያለን፡፡ ይሁን እንጂ ካለው ጅምር ልምዳችን በላቀ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ አሠራሮችን እያስገባን ነው፡፡ የውጭ ኢንዱስትሪዎችን ካየን የውጭ ኢንቨስተሮችን መሳብ የሚለውን አቅጣጫ አሁን ትተነዋል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንት ነው የምንሰበው ብለናል፡፡ በማኑፋክቸሪንግና በዘመናዊ ግብርና ላይ አተኩረናል፡፡ ቁልፍ በሚባሉ በተመረጡ ዘርፎች ላይ እናተኩራለን፡፡ ከሁሉም አገር የሚመጣ ኢንቨስተር ሳይሆን እኛ በመረጥናቸው ዘርፎች ላይ ጠንካራ ከሚባሉ አገሮች ራሳችን እየሄድን ኢንቨስተሮችን የመመልመል ሥራ እንሥራ እያልን ነው፡፡ ምርጥ የሚባሉትን ፋብሪካዎች እንስባለን፡፡ ምርጥ የሚባሉ ድርጅቶች ዋናው ትኩረታቸው ማበረቻዎችን ላልተገባ ጥቅም ማዋል ሳይሆን፣ ምርታማነትን በማሻሻል የሽያጭ መጠናቸናቸውንና ኤክስፖርታቸውን ማሳደግ ነው፡፡ እኛም እንዲህ እያደረግን ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...