Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅ‹‹እኔም ወግ ይድረሰኝ!›› (ፎቶ ከድረ ገጽ)

‹‹እኔም ወግ ይድረሰኝ!›› (ፎቶ ከድረ ገጽ)

ቀን:

እኔ እወድሻለሁ

ብዙ ሺሕ ዘመናት

እልፍ ኣእላፍ ሌሊት

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሚሊዮን መሰለኝ

ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ፡፡

እኔ እወድሻለሁ

የሰማይ መሬቱን

የባህር ስፋቱን

የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል

እንደ ፅጌረዳ

እንደ አደይ አበባ

እንደሎሚ ሽታ፡፡

እንደእጣን ጢስ እንጨት፣ እንደከርቤ ብርጉድ፣

እኔ እወድሻለሁ፣

            አበባ እንዳየ ንብ፡፡

እንደ ቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው

ፍቅርሽን በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው

ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኩዋር

አማርኛ አይበቃ፤

            ወይ ጉድ!

                  ባለም ቁዋንቁዋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር፤

እኔ እወድሻለሁ

            እንደማታ ጀንበር፡፡

እንደ ጨረቃ ጌጥ፣

            እንደንጋት ኮከብ፣

እኔ እማልጠግብሽ

ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፡፡

ጡት እንዳየ ሕፃን ወተት እንዳማረው

ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ሕይወቴ ነው፡፡

ጣይ እንዳየ ቅቤ

       ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፣

አፈር መሬት ትቢያ ውኃ እንደሚበላው፤

ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ

       ብዙ ሺሕ ዘመናት

እልፍ አእላፍ ሌሊት

እኔ እወድሻለሁ፤

አይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ

ስወድሽ ስወድሽ

       እኔ እወድሻለሁ፡፡

  •  16/9/1960 የኢትዮጵያ ጋዜጣ ድምፅ

****************************

እባብ ለመሣም የሞከረች ቱሪስት አፍንጫዋን ተነደፈች

የታይላንድ የእንስሳት ፓርክ ስትጐበኝ የነበረች ቱሪስት እባብ ለመሣም ሞክራ፣ አፍንጫዋን ተነደፈች፡፡

ባንኮክ ፖስት እንዳሰፈረው፣ የ29 ዓመቷ ጂን ጂንግ፣ እባቡን ለመሳም ስትጠጋ ሁለት ጥርሶቹን አፍንጫዋ ላይ ሰክቶ አለቅም ይላል፡፡ የእባቡን ጥርሶች ከአፍንጫዋ ለማላቀቅ በተደረገ ጥረት የተጐዳችው ጂንግ፣ ፐኬት ኢንተርናሽናል ሆስፒታል የአፍንጫ ቀዶ ሕክምና ተሠርቶላታል፡፡

በፐኬት ባዮ ቴክኖሎጂ ሜድስናል ኸርብ ኩባንያ አዘጋጅነት የቀረበውን ‹‹ዘ ፍሪ ስኔክ ሾው›› የእባብ ትርዒት፣ ለመከታተል ከስፍራው ተገኝታ በእባቡ ጉዳት የደረሰባት ጂንግ፣ ከአዘጋጆቹ የ3,700 ዶላር ካሳ ተከፍሏታል፡፡ እባቡ መርዛማ አልነበረም፡፡

****************************

ለይፈለጋል የተለጠፈው ፎቶግራፉ እንዲቀየርለት የጠየቀ ተጠርጣሪ ታሰረ

በአሜሪካ ኦሃዮ ነዋሪ የሆነው የ45 ዓመቱ ዶናልድ፣ ጠጥቶ በመንዳት ወንጀል ተጠርጥሮ እየተፈለገ ነበር፡፡ የፍሎሪዳ ፖሊስ ዶናልድን ለማግኘት ይረዳው ዘንድ ፎቶውን በፖሊስ ዲፓርትመንቱ የፌስቡክ ገጽ ይለጥፋል፡፡ ዶናልድ ግን ፖሊስ በተጠቀመው ፎቶ ደስተኛ ስላልነበረ የተሻለና ቆንጆ ያለውን የፀሐይ መነፅር አድርጐና መኪና ውስጥ ሆኖ የተነሳውን ፎቶ፣ የእጅ ስልኩን በመጠቀም በፌስቡክ ድረ ገፁ ይለጥፋል፡፡ ከስሩም ‹‹ይህ ጥሩ ፎቶ ነው፣ ያኛው ያስቀይማል›› የሚል ጽሑፍ ያሰፍራል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ዶናልድ በማኅበረሰብ ድረገፁ የለጠፈው ፎቶ ሰዎች በቀላሉ እንዲያውቁት የፍሎሪዳ ፖሊስ ዲፓርትመንትም ያለብዙ ውጣ ውረድ እንዲይዘው ረድቷል፡፡

***************************

ቭላድሚር ፑቲን የሚገለጹበት ‹‹ሊደርስ ነምበር ዋን›› ሽቶ

‹‹ሊደርስ ነምበር ዋን›› የሚለውና የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማንነት በብልቃጡ ላይ ያሰፈረው የሽቶ ዓይነት ባሳለፍነው ሳምንት በሩሲያ መሸጥ ጀመረ፡፡

የቤላሩስ ተወላጅ በሆነው የሽቶ መቀመም ባለሙያ ቫላድስላቭ ሪኩኖቭ የተሠራው ሽቶ፣ በ95 ዶላር ነው ለሽያጭ የቀረበው፡፡

ሪኩኖቭን ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ሽቶውን ለመቀመምና የፑቲንን ማንነት እንዲሁም ቅርፅ በብልቃጡ ላይ ለማስፈር የተነሳሳው የፑቲን አድናቂ በመሆኑ ነው፡፡

***************************

ግማሽ ሺ ዓመት ያስቆጠረው ደብዳቤ

አፄ ልብነ ድንግል በ16ኛው ምእት ዓመት የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ነበሩ፡፡ በ1520ዎቹ አጋማሽ ለፖርቱጋል ንጉሥ አማኑኤል ከጻፉላቸው ደብዳቤ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡ የታሪክ ጸሐፊው አቶ ተክለ ጻድቅ መኩርያ ‹‹ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዲህ ጽፈውታል፡፡ ደብዳቤው የኢትዮጵያን መልክአ ምድር ዘርዘር አድርጎ አመልክቶታል፡፡

‹‹ስሜ ዕጣነ ድንግል፣ በኢትዮጵያ ቋንቋ ድንግል ያበራችለት፣ ይኸው ስም የተሰጠኝ ቅድስት ጥምቀትን በተቀበልሁበት ቀን ነው፡፡ በነገሥሁ ጊዜ ዳዊት ተባልሁ፡፡ ዳዊት ፍቁረ እግዚእ ዘእምነገድ ይሁዳ የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ልጅ፣ … የዘርዓ ያዕቆብ ልጅ በሥጋ የናሁ (ናዖድ) ልጅ፡፡ የላይኛውና የታችኛው ኢትዮጵያ የትልልቆቹም የነጋሢ ግዛቶች የክሶአ ንጉሥ የካፋታ (ከፋ)፣ የፈጠጋር፣ የአንጎት፣ የባሩ፣ የበአሊንግዝ፣ የአድአ የሻንግ (ወንጅ)፣ ዓባይ የሚፈልቅበት የጐዣም የአማራ የባጋሚድሪ (ቤጌምድር)፣ የአምቢያ (ደምቢያ)፣ የዋኝ የትግሬ መሆም (ትግሬ መኰንን ወይም ትግሬ መሆኔ)፣ ንግሥተ ሳባ የወጣችበት የሳበይም (ሳባ)፣ የባርናጋስ፣ ንጉሠ ነገሥት በመጨረሻ እስከ ኑብያ ያለው ግዛት ጌታ እርሱም ከግብጽ የሚዋሰን . . . ደጉ ንጉሥ አማኑኤል ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን፡፡

አሁንም ሰላም ላንተ ይሁን፤ ለንግሥቲቱም ለውዲቱ ጓደኛህ ክርስቶስ ጸጋውን የሰጣት የድንግል ማርያም አገልጋይ ለወንዶች ልጆችህም ሁሉ ሰላም ይሁን፤ ከነርሱም ጋር መዓዛው በሚጣፍጥ የጽጌረዳ አበባ በሞላበት አትክልት እንደተቀመጥህ ሁሉ፣ ደስታህን የምታይ፣ ለሴቶች ልጆችህም ሰላም ይሁን፤ ሥጋጃው በተነጠፈበት የመሳፍንቶችና ያለቆች አዳራሽ በጥሩ ልብስ አጊጠው ለሚታዩት … ለዳኞችህና ለአማካሪዎችህ ለጦር አለቆችህም ሰላም ይሁን፡፡››

******************

ፕላቶን

ፕላቶን የሶቅራጥስ ደቀ መዝሙር ነው፡፡ ተወላጅነቱም ጽርአዊ ነው፡፡ እንዲሁም የተወለደውና ያደገው እንደ ሶቅራጥስ በአቴን ከተማ ነው፡፡ ይህም የጽርአ ፈላስፋ የተወለደው ከክርስቶስ ልደት በፊት ይኸውም ወደ 427 ዓመት አቅራቢያ ነው፡፡ ያረፈበትም ዘመን ከዚሁ ከልደተ ክርስቶስ በፊት 347 ዓመት ላይ ነው፡፡ ይኸውም ያረፈው በ80 ዓመቱ ነው ማለት ነው፡፡ የዚህ ፈላስፋ አባቱ አሪስቶን ይባላል፡፡ እናቱም ፔሪክቲዮኒስ ትባላለች፡፡

ፕላቶን የመጀመሪያ ስሙ አሪስቶክሊስ ነበር፡፡ በኋላ ግን አያቱ ፕላቶን የሚለውን ስም ሰጠው ይባላል፡፡ አያቱም ይህን ዓይነት ስም የሰጠው ግንባረ ሰፊ ወይም ጐበዝ ሲለው ነው ብለው ብዙዎች ይህን ሐሳብ ይደግፋሉ፡፡ ይህ ፈላስፋ በሕፃንነቱ ዘመን ግጥም መጻፍ በጣም አድርጎ ይወድ ነበር፡፡ ለዚህም ከፍ ያለ ልዩ ስጦታ ነበረው አንድ ዓመት ሲሞላው ለትምህርት ወደ ሶቅራጥስ ዘንድ ሄዶ ከዚያም ብዙ ዓመታት የርሱ ደቀ መዝሙር ኾኖ ተቀምጦዋል፡፡ ፕላቶን እጅግ ከፍ ያለ ስመ ጥሩ ፈላስፋ ነው፡፡ ፍልስፍናውንም የምንረዳባቸው በቂ መጻሕፍት ትቶልናል፡፡

  • የማነ ገብረ ማርያም ‹‹የፍልስፍና ትምህርት ፩ኛ መጽሐፍ›› (1954)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...