Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹ማን ነህ ባለ ተራ?›

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከረማችሁ የተወደዳችሁ ወዳጆቼ? ‹‹እየታገልን አለን፡፡ እየተሯሯጥን አለን፡፡ እያሸነፍን አለን፡፡ ከማሸነፍ ውጪ ምንም አማራጭ የለንም ብለን አምነን፡፡ ከመቅደም ውጪ መቀደም ፍፁም አማራጭ ሊሆነን አይችልም ብለን፡፡ ከመግዛት ውጪ መገዛት ለእኛ አልተሰጠንም፡፡ ከአባቶቻችንም አልተማርንም ብለን፡፡ እያሸነፍን፣ እየገዛንና እየቀደምን እነሆ አለን፤›› እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ወደ የትኛውም ሜዳ ስትገባ እንደምታሸንፍ አምነህ ግባ፤›› እያለ ያበረታታኛል፡፡ ታዲያ እኔስ ምኔ ሞኝ? የትኛውም ዓይነት የድለላ ሥራ ውስጥ ስገባ፣ ተፎካካሪ ደላላዎችን በከፍተኛ ብልጫ እንደምዘርራቸው አምኜ ነው የምገባው፡፡ ወዳጆቼ ታዲያ ይህንን አስተሳሰቤን ‹መብላቷን ሳታውቅ እጇን ታጠበች› እንዳይሆንብኝ አትሥጉ፡፡ መብላቴን አውቄ ነው ታጥቤ የምገባበት፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሁሉ ነገር አዕምሮህ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የሽንፈትም፣ የአሸናፊነትም ቁልፍ በእጅህ ይገኛል፡፡ የትኛውን መክፈት እንዳለብህም የምትወስነው ራስህ ነህ፤› ባለኝ ሐሳብ ስብሰለሰል ቆይቼ፣ በመጨረሻ የማሸነፊያውን ቁልፍ ብቻ ነው መያዝ ያለብኝ ብዬ በመወሰን ይኼው አሁን ከማሸነፍ ውጪ ‹‹ሜኑዬ›› ውስጥ መሸነፍ የሚል አማራጭ ከተወገደ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ‹ይሞታል ወይ ታዲያ?› ያለው ማን ነበር?

ያንን ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬት ለእነዚያ ትጉሃን ኢንቨስተሮች ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ይጨርስላቸዋል ብሎ ያሰበ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ማንጠግቦሽ እንኳን ስታበረታታኝ፣ ‹‹ስንቱን ባለሀብት፣ ስንቱን የተማረ ሰው አሸንፈህ ነው በፍቅርህ ድል ነስተህ የራስህ ያደረግከኝ፤›› ስትለኝ አንዳች የጀግንነት ስሜት ከእግር ጥፍሬ እስከ ራስ ፀጉሬ ሲወረኝ ይታወቀኛል፡፡ ባለ በሌለ ኃይሌ ከተቀመጠችበት አንከብክቤ አንስቻት ወደ መኝታ ቤት እነጉዳለሁ፡፡ ይኼኔ እሷም፣ ‹‹አንተ ተው . . . ሥራ አለብኝ ተው . . . ›› ትለኛለች፡፡ እንደ ጀመርነው እንጨርሰው እንጂ፡፡ የምን ተው ነው? እሷም አይከፋትም፡፡

ባሻዬ ሰሞኑን በእስራኤልና በፍልጤም መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ተመልክተው ሐዘን ሲያጎብጣቸው ነው የከረሙት፡፡ ‹‹መቼ ይሆን እነዚህ ወንድማማቾች በሰላም ተከባብረው ቡና ተጠራርተው የሚያድሩት? መቼ ይሆን ጋዛና ቴላቪብ ቦምብ መወራዋራቸውን አቁመው፣ ልጆቿም ድንጋይ መወራወራቸውን ትተው፣ ደም መቃባታቸውን አቁመው በሰላም የሚያድሩት?›› እያሉ ባሻዬ በርካታ መልስ የሌላቸውን ጥያቄዎቻቸውን ያነሳሉ፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ መልስ የሚገኘው ተደጋግሞ ሲጠየቅ ነው፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ ሁለቱን ወገኖች ደም የሚያፋስሰው ግጭት ማቆም አለመቻሉ ያናድዳል፡፡ በተለይ የዓለም መንግሥታት ጎራ ለይተው ሁለቱ ሲባሉ ዝም ብለው ማየታቸው የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፤›› ይላል፡፡ ባሻዬ ሁልጊዜም ሕመም የሚሆንባቸው የአንድ አባት ልጆች መተላለቃቸው ነው፡፡ ‹‹የእስማኤልም የይስሐቅም አባት የሆነው አብርሃም ልጆቹ እንዲህ ለዘመናት ሲበጣበጡ ቢመለከት ምን ይል ይሆን?›› እያሉ በሐሳብ ይመሰጣሉ፡፡ ወደ ፈጣሪያቸው ሲነጉዱ አካባቢያቸውን ይረሳሉ፡፡

‹‹አወዛጋቢው ትራምፕ የእስራኤልን ዋና ከተማ እየሩሳሌም እንድትሆን ከወሰነ በኋላ የተፈጠረው ግጭት እንዲህ በቀላሉ የሚያቆም አይደለም፤›› ይላል ልጃቸው፡፡  ‹‹ይህም ብቻ አይደለም አሜሪካ የአንድ ወገን ደጋፊ ሆና በአካባቢው የምትፈጽመው የትንኮሳ ድርጊት ለዓለም ሰላም ጠንቅ ነው፤›› ካለን በኋላ፣ ‹‹ዓለም የሚያስከፍለውን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ ሰላም ለማስፈን ጥረት ካላደረገ የበለጠ ዕልቂት እንደሚኖር ጥርጥር የለኝም፤›› በማለት ሲነግረን ነበር፡፡ እውነት ነው፡፡ ይኼ ችግር ጦሱ የት እንደሚደርስ አለመረዳት ሞኝነት ነው፡፡

ባሻዬም የልጃቸውን ሐሳብ ሲያጠናክሩ፣ ‹‹በዘመናት መካከል የደረሰው ግፍና መከራ አሁን አሁን አካባቢውን የበለጠ ያተረማምሰዋል፤›› አሉ፡፡ ልክ ናቸው ወንድማማቾችን እያፋጁ መቀጠል ጠንቁ ለዓለም ነው፡፡ የሰው ልጅ በፈጣሪ አምላክ አምሳያ እንደ መፈጠሩ ከፈጣሪው ፈቃድ ውጪ ሲሆን ብርቱ መከራ ይገጥመዋል፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሰላም የማስፈን ዕድሉ ቢሰጠኝ፣ እነዚህን ሁለት ወንድማማቾች ዋሽቼም ቢሆን ማስታረቅ አያቅተኝም፡፡ የበደለ እየተካሰ፣ ያጠፋ እየተገሰፀ ማስታረቅ እንደሆነ የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ወግ ነበር፡፡ ወይ ነዶ?

ባሻዬ፣ ‹‹ለዘመናት አልሽር ያለው ቁስል እያመረቀዘ ነው፡፡ አፀፋዊ ዕርምጃዎች ሁሉ ትናንትናቸውንና ነጋቸውን ከግምት አስገብተው ነው የሚወሰዱት፤›› ይላሉ፡፡ ዳሩ ግን የዕብድ ገላጋይ በበዛባት ዓለም ውስጥ የማንም ጉልበተኛ እንደ ልቡ እየሆነ ሕፃናት፣ አረጋውያንን፣ ነፍሰ ጡሮችንና አቅመ ደካሞችን ጭምር ፍዳቸውን ሲያሳይ ለምን ካልተባለ እንዴት ሰው መሆን ይቻላል? ሰው መሆን እያቃተን መሰለኝ በረባ ባልረባው ስንባላ የምንውለው፡፡  

ባሻዬ እንዳሉት በእርግጥም የወንድማማቾች ፀብ ከባድ ነው፡፡ ‹‹ፀቡም ቢሆን የዘመናት ነው፡፡ ለትውልድ የሚተላለፍ ነው፡፡ ስለሆነም በፍጥነት ሊቋጭ ይገባዋል፤›› ያሉት ልቤን ነክቶኛል፡፡ ይህንንም ሐሳብ የባሻዬ ልጅ እንዲህ ሲል አጠናክሮልኛል፡፡ ‹‹ትንንሽ የሚባሉ በብሔሮች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶች ሳይውሉ ሳያድሩ መፍትሔ ይበጅላቸው፡፡ በወሰን ይገባኛል የሚነሱ ጭቅጭቆች ትክክለኛውን መድኃኒት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ወንድማማቾች በመሬትና በመሳሰሉት ምክንያት በምንም ምክንያት መጣላት የለባቸውም፤›› እያለ ያብራራል፡፡ በዚህ ብቻ መቼ ሊያበቃ? ‹‹የተለያዩ ማዕድናትን ሊያወጡ የሚመጡ ምርቱን አውጥተው ሲያበቁ ለትውልድ ነቀርሳ የሚሆን ነገር ትተውብን መሄድ የለባቸውም፤›› ይላል፡፡ በየደረሱበት ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ቦምብ ቀብረው የሚሄዱት ፈረንጆች ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ሴረኞች ናቸው እያስቸገሩን ያሉት፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ በምሬት ሲናገር፣ ‹‹የገዛ ሀብቱን የሰጠ ማኅበረሰብ ወይም መንደር እንዴት በምላሹ የማይፈልገው ነገር ይደረግበታል? እያለ ሲጠይቅ፣ ባሻዬ የልጃቸው ሐሳብ መስጧቸው፣ ‹‹እውነት ብለሃል፡፡ ባይሆን ትምህርት ቤት ይከፈትለታል እንጂ፣ ባይሆን ሆስፒታል ይገነባለታል እንጂ፣ ባይሆን ንፁህ የመጠጥ ውኃና መንገድ ይሠራለታል እንጂ፣ እንዴት ሀብት የታፈሰበት ሕዝብ መከራ ይደርስበታል?›› በማለት አማረሩ፡፡ ከምሬት ይሰውረን እንጂ የምንሰማው ሁሉ ያቃጥላል እኮ?

ሰሞነኛውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን እንቅስቃሴ እንዴት አገኛችሁት? ሥራ ትተው ይዞራሉ ሲባሉ በጥናት የተደገፈ መመርያ እያወጡና ትንታኔ እየሰጡ በሉ ሥሩ ይላሉ፡፡ ‹ጉልቻ ቢቀያየር . . . ›› ሲባሉ እነሆ አያሌ ቀደምት ሰዎችን እሸኙ ይገኛሉ፡፡ መቼም አገር ያማረረውን ስብሰባ ከሥራ ቀናት ውስጥ ሸኝተው ወደ ቅዳሜ እንደወሰዱት የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አንጋፋዎችን መሸኘታቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኔማ ቀጣይ ተሸኚ ማን እንደሚሆን ለማየት ጓጉቻለሁ፤›› ያለኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አገርኛውን አባባል ተውሼ ‹ማን ነህ ባለ ተራ?› ብል ምን ይጎለኛል? ‹ተው ማነህ? ተው ማነህ . . . › የሚለውንም ጨምሩበት፡፡ መልካም ሰንበት!      

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት