Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አይበርደን አይሞቀን!

የታክሲ ተሳፋሪዎች ጉዞ ዛሬም አልተገታም፡፡ የሰው ልጅ የመጨረሻዋን እስትንፋስ እስከሚያደርግበት ቀን ድረስ ይጓዛል፡፡ ካሰበበት መድረስ የማይፈልግ ማንም ሰው የለም፡፡ ሁሉም ከቤቱ ሲወጣ ታላቁን የመድረስ ተስፋ ሰንቆ ነው፡፡ እኛም ይኼው ከአያት ተነስተን ሜክሲኮ የመድረስ ተስፋ ሰንቀን ባቡር ውስጥ ተሰግስገናል፡፡ ዘወትር ጠዋት ከሰሚት እስከ መገናኛ ያለው መንገድ እጅግ የተጨናነቀ ነው፡፡  በተለይ የሥራ ሰዓት ማሳለፍ የማይችሉ ሰዎች በባቡር መሄድ ግድ ይሆንባቸውና የተፋፈነ ጉዞ ይደረጋል፡፡

ባቡሩ እጅግ መጨናነቁ እንዳለ ሆኖ ቢያንስ ሰው ባሰበው ሰዓት ያሰበበት ይውላል፡፡ ዳሩ ግን ጥያቄው እንዴት ተብሎ ወደ ባቡር ውስጥ መግባት ይቻላል ነው፡፡ ፈርጣማ በስፖርት የዳበረ ሰውነት የሚያስፈልግበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡ ማለዳ ላይ ያለውን የባቡር ጭንቅንቅ ለመግለጽ ያስቸግራል፡፡ ሰው በሰው ላይ ተለጥፎ ነው የሚሄደው፡፡ አንዲት ሴት መናገር ጀመረች እንደ መቆጣት ብላለች፡፡ ‹‹ባቡር የወሲባዊ ትንኮሳ ማካሄጃ ቦታ እየሆነ መጥቷል፤›› በማለት በምሬት ተናገረች፡፡ የእሷን ሐሳብ የሳባቸውም ያልሳባቸውም ማድመጣቸውን ቀጥለዋል፡፡

‹‹ምንድነው ሰው ላይ እንደ መዥገር መለጠፍ? ራስህን ችለህ ቁም፤›› በማለት አጠገቧ ቆሞ ሲተሻሻት የነበረውን ሰው አሳፈረችው፡፡ የሰውን ሁሉ ትኩረት በመውሰዷ፣ ሰውዬው እሳት ላይ እንደወደቀ ላስቲክ ኩምትር ብሎ ቆመ፡፡ በዚያ ጠባብ ሥፍራ ውስጥ ከእሷ ሲሸሽ በመካከላቸው ክፍተት ተፈጠረ፡፡ ሌላ ሴት መናገር ጀመረች፣ ‹‹ወንዶቹን ግን ምን ነክቶአቸዋል . . . ሴት ባዩ ቁጥር የሚያቅበጠብጣቸውን ነገር ቢያቆሙት መልካም ነው፤›› በማለት ሐሳቧን ሰነዘረች፡፡ ይኼኔ በሐሳባቸው ያልተስማማው ወጣት፣ ‹‹ምን ወንድ፣ ወንድ ትላላችሁ? በእናንተ ነው የባሰው፡፡ በመጀመርያ ራሳችሁን ግዙ፡፡ ቢቻላችሁ ራሳችሁን ተቆጣጠሩ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ በወንድ ላይ ከመፍረዳችሁ በፊት ልብስ ልበሱ፤›› በማለት ምሬቱን ተናዘዘ፡፡ ሰውየው ‹ራቁታችሁን ነው የምትንቀሳቀሱት› ለማለት የፈለገ ይመስላል፡፡

ሁሉም ሴቶች በአንድ ድምፅ ሲናገሩ ‹ዛሬ የሴቶች ቀን ነው እንዴ?› ያሰኛል፡፡ ሌላኛዋ ሴት መናገር ጀመረች፣ ‹‹የፈለግነውን ዓይነት ልብስ ብንለብስ ምንም አይመለከታችሁም፡፡ ነገር ግን ሴትን ልጅ የወሲብ አሻንጉሊት አድርጋችሁ ማየታችሁን አቁሙ፤›› በማለት ብሶቷን ተነፈሰች፡፡ በዚህ ንግግር ያልተስማማው ሌላ ሰው መናገር ጀመረ፣ ‹‹ሁሉም ነገር አግባብና ደንብ አለው፡፡ የአመጋገብ ሥርዓት አለ፡፡ እንዲሁም የአለባበስ ሥርዓትም አለ እኮ፡፡ በተለይ አለባበሳችን ለሰው የሚታይ ስለሆነ መጠንቀቅ አለብን፤›› በማለት ትንሽ ማብራሪያ ሰጠን፡፡ እኛ በዚህ መሀል ስንት ሠፈር አልፈን፣ ጥቁር ዓባይ የሚባል በሚካኤልና በሲኤምሲ መካከል ያለው ሠፈር ደርሰናል፡፡ ባቡራችን አሁንም እየቆመ የመግባት አቅም ያላቸውን ሁሉ እያሳፈረ ነው፡፡

ጨዋታውም በዚያም መጠን ቀጥሏል፡፡ ሴቶች የፈለግነውን የመልበስ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለን ሲሉ፣ ወንዶች ደግሞ አግባብ አይደለም ለእኛም ሊታሰብልን ይገባል እያሉ ነው፡፡ ሰውየው ወጣቷን በመተሻሸቱ የተጀመረው ወሬ እነሆ የሴቶች መብት ዘንድ ደርሷል፡፡ በመሀል አንዲት ሴት፣ ‹‹ወይኔ ስልኬን›› በማለት ባቡሩን አደበላለቀችው፡፡ እስቲ ይደወልበት ቁጥርሽ ስንት ነው ተባለ፡፡ አንዳንዶቻችን ምናልባት ብለን ኪሶቻችንን ዳበስን፡፡ ምናልባት ሰርቀን እንዳይሆን ብለን ይሆን ወይም ምናልባት ሌባው ኪሳችን ውስጥ አስቀምጦት እንዳይሆን በሚል ሥጋት፡፡ እውነታው ግን ስልኩ ሌባም አልሰረቀው፡፡ ሴትየዋ በግፊያው ሰበብ ጥላው ሊሆን በሚመስል ሁኔታ ከአንድ ወገን ድምፅ ማስተጋባት ጀመረ፡፡ ይኼን ጊዜ ነበር በስልኩ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ጥርጣሬው ወደ እነርሱ እንዳይሆን በሚል ሥጋት ሁሉም ሲሸሹ፣ ስልኩ ብቻውን መሀል ላይ ቁጭ ብሎ ታየ፡፡ ለአየር ቦታ ያልነበረበት ባቡር ሌባ ላለመባል ሰው ሁሉ ስልኩን ሲሸሽ መሀል ላይ ክፍተት ተፈጠረ፡፡ ይኼን ጊዜ የስልኩ ባለቤት ካለችበት ቦታ እየተጣደፈች ሄዳ ስልኳን አነሳች፡፡ እዚያው ስልኩ የተገኘበት ቦታ ቆም ብላ ማብራራት ጀመረች፡፡

‹‹ሌባው ጥሎት ነው እዚህ ጋ፡፡ እስቲ እንዲያው እግዜር ያሳያችሁ የሰው ንብረት ምን ያደርጋል?›› በማለት ደስታ በተቀላቀለበት ቁጣ አንባረቀች፡፡ ሌላ ሴት ተቀበለቻት፣ ‹‹ሠርቶ መብላት ሲቻል ምን ዓይነት አስነዋሪ ነገር ነው የሰውን ንብረት መዝረፍ?›› በማለት ከፆታ አቻዋ ጋር ተባበረች፡፡ ወንዶች ሁሉ ፀጥ ብለው ሴቶች ተራ በተራ ሐሳባቸውን እያንሸራሸሩ ነው፡፡ ሌላ ሴት ወሬውን ተቀላቀለች፣ ‹‹ደግሞ በዚህ ዘመን ሞባይል ይሰረቃል እንዴ? ምን ዓይነት ሞኝ ሌባ ነው ሞባይሉን ባለቤቱ ቴሌ ሄዶ ሊያዘጋው እንደሚችል ያላወቀ፡፡ ከዕውቀት ነፃ የሆነ ሰው ነው፤›› በማለት ቀለደች፡፡ ይኼኔ ሴቶች ብቻ በሳቅ አወኩ፡፡ ወንዶች ቅር የተሰኙባቸው ይመስላል፡፡

የሴቶቹ ድርጊት ያልተመቻት በርካታ ወንዶች ቢኖሩም፣ ደፍሮ የእነሱን ሐሳብ የሚሞግት አንድ ሰው ለማግኘት ትንሽ ጊዜ ወስዶ ነበር፡፡ በመጨረሻ አንድ ጎልማሳ መናገር ጀመረ፡፡ ይኼን ጊዜ ወንዶች ደስ ያላቸው መሰሉ፡፡ ባቡር ውስጥ ሴቶች እየጨቆኑ ያለ ይመስል ነበር፡፡ ሰውዬው መናገር ሲጀምር ወንዶች ሁሉ ‹አፌ ቁርጥ ይበልልህ . . . ንገራቸው . . .› በማለት አንደበቱን ማራሻ ውኃ ሳይቀር ቀድተው ቢሰጡት ደስታቸው ነበር፡፡ ዳሩ ግን የታሰበው እንዳልታሰበው ሆነና ነገሩ ተገለባበጠ፡፡ ወንዶችን ይወክላል የተባለው ሰው የሴቶች መብት ተሟጋች ሆኖ አረፈው፡፡

‹‹ሌባ ከምድሪቱ ላይ ይወገድ ዘንድ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሴት እህቶቻችን ላይ የሚሰርቅ ልዩ ቅጣት ሊከናነብ ይገባል፡፡ በእህቶቻችን ቀልድ የለም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ የተዘረፉት፣ እስከ ዛሬ ድረስ የተበደሉት፣ እስከ ዛሬ የተደፈሩት ይበቃል፡፡ አሁን በውርደታቸው ፈንታ የሚከብሩበት፣ በተበደሉበት ፈንታ የሚካሱበት፣ በተረገሙበት ፈንታ ደግሞ የሚሞከሹበት ዘመን ላይ ነው ያለነው . . . ›› በማለት ረዘም ያለ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ ከእሱ በተቃራኒ የሚናገር አንድም ጀግና ነኝ ባይ ጠፍቶ ሁሉም ፀጥ ብለው ባቡር ውስጥ የሌሉ እስኪመስል ድረስ፣ ግማሹ በመስኮት አሻግሮ ወደ ውጪ ሲመለከት፣ ሌላው ደግሞ ጣሪያ ጣሪያውን እየተመለከተ የለሁም ዓይነት ስሜት ሲያንፀባርቅ ቆ፡፡

ስለመብቱ የሚናገር አንድ ወንድ ነኝ ባይ ሳይኖር በጠፋው ስልክ ሰበብ አብዛኛዎቹ ወንዶች ሌቦች ናቸው ወደሚል ጅምላ ፍረጃ ውስጥ በመሆኑ ጉዞው ቀጥሏል፡፡ አሁን ደግሞ አዲስ ተናጋሪ ተነስታለች፡፡ እሷ ደግሞ ምን ልትል ይሆን የሚለው የብዙዎች ሥጋት ነበር፡፡ የባቡሩን ውጥረት ለተመለከተው ‹ወንድ መሆን ከባድ ነው› ያሰኛል፡፡ ለዘመናት በሴቶች ላይ ሲፈነጩ የነበሩ ወንዶች አሁን ልጓም ተበጅቶላቸው ሴቶቹ ጮክ ብለው እየተናገሩ ሲገስጿቸው ማየት እንግዳ ነገር የሆነባቸው በርካታ ይመስላሉ፡፡ ዛሬም ባቡር ውስጥ በሴቶች ተከበናል፡፡ ረዳቷም ብትሆን ሴት ናት፡፡ በየመሀሉ እየመጣች፣ ‹‹የሚቀጣጠል ነገር ይዞ ወደ ባቡር መግባት ክልክል ነ፤›› ትለናለች፡፡

ይህች ወሬውን የተቀላቀለች ሴት እንዲህ በማለት ጀመረች፣ ‹‹ወንድ ሁሉ ሌባ አይደለም፣ ሌባ ሴቶችም አሉ፤›› ከማለቷ በርካታ ሴቶች አጉረመረሙ፡፡ ወንዶችም ተደርበው አጉተመተሙ ሴትየዋ የተናገረችው ይወክለኛል በሚል ስሜት፡፡ እሷ ግን ሴቶቹ ተቃውሞ ሳይበርዳት፣ የወንዶቹም ሙገሳ ሳይሞቃት ንግግሯን ቀጠለች፣ ‹‹ወንዶችን በክፉ ነገር ሁሉ ልንወነጅላቸው አይገባም፡፡ ስንት እሳት ሞጭላፋ ሴቶች አሉ፡፡ በፆታ መወነጃጀል አግባብ አይደለም፡፡ ዳሩ ግን ወንድም ሰረቀ ሴት በድርጊታቸው ነው ሊጠየቁ የሚገባቸው፤›› በማለት ሐሳቧን አጠናከረች፡፡ አሁንም ሐሳቧን አላሳረገችም ነበር፡፡ ‹‹እንዲያው እናውራ ከተባለ በየመሥሪያ ቤቱ ደጅ የሚስጠኑን እነ ማን ሆኑና ነው? ሴቶች አይደሉም እንዴ?›› በማለት ጥያቄውን ወደኛ ስትሰነዝር አብላጫዎቹ ወንዶች ‹እውነት ነው› የሚል ዓይነት ጉምጉምታ አሰሙ፡፡ ዳሩ ግን አንደበቱን አፍታቶ የተናገረ ወንድ አልነበረም፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ወደ ሜክሲኮ ደርሰናል፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር ሜክሲኮ መድረሳችንን ያበሰረችን አቅጣጫ የምትጠቁመው የባቡሩ ረዳት ናት፡፡ ከባቡሩ ወርደን ወደ ጉዳያችን ስንገሰግስ የእዚያች ትንታግ ሴት ድምፅ ነበር በጆሮአችን ላይ ያቃጭል የነበረው፡፡ ምናለበት ተቃውሞ ሳይበርደን ሙገሳ ሳይሞቀን ሥራችንን ብናከናውን? መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት