Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን ሥራ እያወከ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ የተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችንና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ላይም ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ታኅሳስ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የአንዳንድ ኤምባሲዎች የፕሮጀክት አተገባበር ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት ኤምባሲዎች ከተመደበላቸው በጀት ውስጥ ከ94 እስከ 98 በመቶ ብቻ እንደሚጠቀሙ በመካተቱ፣ ለምን መቶ በመቶ እንዳላደረጉት ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲያብራሩ፣ ‹‹የበጀት አጠቃቀማችንን መቶ በመቶ ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚለቀቅልን በጀት በንግድ ባንክ በኩል የውጭ ምንዛሪን በሚፈለገው ጊዜ ስለማይደርስ በሥራዎቻችን ላይ መዘግየት እያጋጠመን ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከባንኩ ጋር በሚያደርጉት ተመሳሳይ ጉዳይ እንዲያግዟቸው ዶ/ር ቴድሮስ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ምንም እንኳ ከባንኩ ጋር ተቀራርበን የምንወያይና የምንሠራ ቢሆንም፣ እናንተ ያላችሁን ሥልጣን ተጠቅማችሁ ችግራችን እንዲፈታ እንድታግዙን እጠይቃለሁ፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በውጭ አገሮች ባሉ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ቢሮዎች ለሚከናወኑ ተግባራት የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በሪፖርታቸው ከተካተቱት ውስጥ በዋሽንግተንና በናይሮቢ ያሉ ኤምባሲዎች የሕንፃ ጥገናና ተጨማሪ ቢሮዎችን ግንባታ አውስተዋል፡፡ በተጨማሪ በቤጂንግ፣ በሞስኮና በተወሰኑ አገሮች የቢሮ ጥገናና ተጨማሪ ግንባታ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ ከዲፕሎማቲክ ተልዕኮ ጋር በተገናኘ አዳዲስ ሦስት ኤምባሲዎችን ለመክፈት መታቀዱን ሚኒስቴሩ አመልክተዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ይከፈታሉ ተብለው የሚጠበቁት ኤምባሲዎች በሞሮኮ፣ በአልጀርስና በጃካርታ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ዜናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዕጩ ሆና መቅረቧን በይፋ የገለጹ ሲሆን፣ በምርጫውም ቦታውን እንደምታገኝ ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ ብቸኛ ተፎካካሪ መሆኗን ገልጸዋል፡፡ ሲሸልስ ራሷን አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ከሲሸልስ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት ራሷን ከውድድሩ ማግለሏን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከቅርብ ወራት በፊት ኢትዮጵያ ለተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመረጧን ያወሱት ዶ/ር ቴድሮስ፣ ‹‹ያገኘነው ልምድ አሁንም ኢትዮጵያ የብዙ አገሮችን ድጋፍ እንደምታገኝ እምነት አሳድሮብናል፤›› ብለዋል፡፡ በተለይም ለኮሚሽኑ አባልነት ኢትዮጵያ ከ190 አባል አገሮች የ186 አገሮች ድጋፍ ማግኘቷን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ‹‹አራት አገሮች ብቻ ነበሩ ያልመረጡን፡፡ እነሱም የምናውቃቸው ናቸው፤›› በማለት በስም ግን ሳይዘረዝሩ አልፈውታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች