Wednesday, June 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከብዙ ንትርክ በኋላ ውድድሩ እንዲቀጥል የተወሰነበት የፌዴሬሽኑና የእግር ኳስ ዳኞች ፍጥጫ

ከብዙ ንትርክ በኋላ ውድድሩ እንዲቀጥል የተወሰነበት የፌዴሬሽኑና የእግር ኳስ ዳኞች ፍጥጫ

ቀን:

  • የወልዋሎ ቡድን መሪ የዕድሜ ልክ እገዳ ተጣለበት

የውዝግቡ መነሻ ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በመከላከያና ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦች መካከል የተካሄደው 22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነው፡፡ ዋናው ዳኛ በወልዋሎ ክለብ ቡድን መሪና ተጫዋቾች መደብደባቸው ተከትሎ የእግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች እስከ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ምንም ዓይነት ጨዋታ እንደማይዳኙ አስታውቀው ነበር፡፡ በወጣቶች ስፖርት አካዴሚ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የጠራው የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማኅበር አሥር የአቋም መግለጫ ማውጣቱም ይታወሳል፡፡

ውድድሩ ከተቋረጠበት ጊዜ አንስቶ የመላው የእግር ኳስ ቤተሰብ ልብ ገዝቶ የሰነበተው ይኼ የዳኝነት ጉዳይ፣ ተሰምተው የማያውቁ የዳኝነት በደሎች የተሰሙበት፣ እግር ኳስ ያለዳኛ አንድ ዕርምጃ እንደማይራመድ የታየበትና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በግልጽ መመልከት የተቻለበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡

በተለይ በክልል ከተሞች ላይ ጨዋታ ሲከናወን በጨዋታ ዳኞች ላይ የሚደርሱት አደጋዎች ከፍተኛ መሆናቸው፣ ዳኞች በክልል ክለብ ጫና ውስጥ እንዲገቡ መደረጉ ችግሩን የበለጠ እንዳሰፋው ተስተውሏል፡፡ ውድድሮችን ያለመዳኘት አድማው ከተሰማ በኋላም፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦችን በመሰብሰብ ውይይት እንዲያደርግ ከማስገደዱም በላይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በመጥራት አዳማ ላይ ጠንከር ያለ ውይይት እንዲያደርግ ማስገደዱ አይዘነጋም፡፡ በዳኞቹ ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ተከትሎ ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር የስፖርት ቤተሰቡን ሲያነጋገር ሰንብቷል፡፡

የዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማኅበር ያስቀመጣቸው ባለ አሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ እናሟላለን ያለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ግንቦት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጠራው የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ክፍተቶቹን ለመሙላት ተስማምቷል፡፡

የእግር ኳስ ዳኞች ያቀረቡትን የአቋም መግለጫ ተከትሎ በጁፒተር ሆቴል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ሙያ ማኅበር የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ባደረጉት ውይይትም ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ እልባት የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎችን ተቀብሎ፣ ቀሪዎቹን ደግሞ በሒደት እንደሚያስተካክላቸው ቃል ገብቷል፡፡

የዳኞች የሕይወት ዋስትናን በተመለከተ ልዩ ጥያቄዎችን ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ ፌዴሬሽኑም ከሦስት ኢንሹራንስ ድርጅቶች ጋር እየተነጋገረ ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡ በሌላ በኩል ወልድያ ከፋሲል ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪን ሙሉ የሕክምና ወጪ ፌዴሬሽኑ እንደሚሸፍን፣ እስካሁን ለሕክምናው ያወጣውን ወጪ ፌዴሬሽኑ እንደሚሸፍን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ተናግረዋል፡፡

በወልዋሎና መከላከያ ጨዋታ ላይ ድብደባ የደረሰበትን ፌዴራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴን በተመለከተ፣ የፌዴሬሽኑ የሕግ ባለሙያ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በክለቦች ላይ የተጠጣለውን ውሳኔ በመሻር ፍትሐዊ ያልሆነ ቅጣት ቅነሳ በማድረግ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ለጊዜው እንዲበተን ስለመደረጉም ተነግሯል፡፡

የክልል የፀጥታ ኃይሎችን በተመለከተም፣ ፌዴሬሽኑ በቀሪ ቀናት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ ችግሩን እንደሚፈታ አስታውቋል፡፡ በዳኞች ማኅበር የተነሱት ጥያቄዎች ካልተመለሱ እስከ ግንቦት 20 ድረስ ምንም ዓይነት ውድድር እንደማይዳኙ ገልጸው የነበሩት የማኅበሩ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት፣ ፌዴሬሽኑ የጠየቀውን ጥያቄ በአግባቡ አልመለሰም በማለት ተቃውሞ ያቀረቡ አልጠፉም ነበር፡፡

ለዚህም አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰሎሞን ገብረሥላሴ የውድድር ዓመቱ ሲጠናቀቅ፣ አዲስ የሚተካው አመራር የተባሉትን ጉዳዮች ይተግብር አይተግብር ምን ማረጋገጫ አለን ሲሉ ዳኞቹ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ የጠየቃቸውን ጥያቄዎች በ2010 ዓ.ም. እንዲመለሱ እንጂ፣ በ2011 ዓ.ም. የውድድር ዘመን አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ ውድድሩ ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ፌዴሬሽኑ ማኅበሩ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ተከትሎ ክለቦች ዳኛ ከታንዛኒያ አስመጥተን ውድድሩን እናስቀጥላለን ማለታቸውና የአቋም መግለጫው በኋላ ከፍተኛ ሊግ ለመዳኘት ወደ ክልል ያመሩ ዳኞች ላይ ማስፈራሪያ መድረሱ በማኅበሩ ተቃውሞና ቅሬታ አስነስቶም ነበር፡፡

ባለፉት ጊዜያት የተከሰቱትን የስፖርታዊ ጨዋነት ተከትሎ በተለይ ወልድያ ከወልዋሎ ያደረገው ጨዋታ በተመለከተ ካፍና ፊፋ ውሳኔውን እንድናሳውቅ በደብዳቤ መጠየቃቸውን የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የዳኞች ታዛቢዎች ማኅበር ባካሄዱት የድምፅ አሰጣጥ መሠረት ከተሳተፉት አሥር ክልልና ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ በልዩነት ተይዞ፣ አማራ ክልል ባለመገኘቱ በስምንት ድምፅ ውድድሩ ይቀጥል የሚለው አሸናፊ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በቀሪዎቹ ቀናት ውስጥም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በወረቀት ላይ የሰፈረ ማረጋገጫ በማውጣት መሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች እንዲያሟላ የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየት ከጨዋታ ዳኞች ተነስቷል፡፡

ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንዲሁም ሌሎች የእግር ኳስ ውድድሮች ከሰኞ ጀምሮ በወጣላቸው መርሐ ግብር መሠረት የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ ተቋርጦ የነበረው የወልዋሎና መቐለ ከተማ ጨዋታ ሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም.  ሽሬ ላይ እንዲከናወን ተወስኗል፡፡ በተመሳሳይ አዳማ ከወላይታ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤሌክትሪክ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ዓርብ ግንቦት 10 ቀን ድሬዳዋ ከወላይታ፣ መቐለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡  

በተያያዘ ዜና፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከመከላከያ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ በፈፀመው ጥፋት ቡድን መሪው፣ ተጫዋቾቹና ክለቡ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡ ግጥሚያውን በዋና ዳኛነት የመራውን ኢያሱ ፈንቴን የመታው የቡድን መሪ ማሩ ገብረፃድቅ ከእግር ኳስ ለዕድሜ ልክ ሲታገድ፣ የወልዋሎ ስምንት ተጫዋቾች ከሁለት ዓመት እስከ ስድስት ወራት ዕገዳና ከ15 ሺ እስከ 10ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡  ክለቡ በፎርፌ 3ለ0 እንዲሸነፍና የሩብ ሚሊዮን ብር ቅጣት መወሰኑም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ገዳ ቢዝነስ ግሩፕ በቅርቡ ለሚጀምረው እርሻ ከ500 ሔክታር በላይ መሬት አዘጋጅቻለሁ አለ

ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ አስጀምራለሁ ላለው...

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...