Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በልማዳዊ አሠራሮች የትም መድረስ አይቻልም!

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች በየዕለቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በአመርቂ ውጤት ማለፍ የሚቻለው ከልማዳዊ አሠራር በተላቀቁ ሳይንሳዊ ሥነ ዘዴዎች ነው፡፡ ማንኛውም ነገር የሚከናወነውና አፈጻጸሙም የሚለካው በሳይንሳዊ መንገድ በተዘጋጁ መሥፈርቶች ሲሆን ውጤቱ አጥጋቢ ይሆናል፡፡ ይህ ያለንበት ዘመን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ከመራቀቁ የተነሳ፣ በማናቸውም የውድድር መስክ በመፎካከር ማሸነፍ የሚቻለው በቂ ዝግጅት ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ዝግጅት ደግሞ በሚገባ እየተፈተሸ አጥጋቢ ከሆነ ሁሌም የተፎካካሪነትን ጥንካሬ ያጎናፅፋል፡፡ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን ስንዳስስ ግን በርካታ ነገሮች ይቀሩናል፡፡ በፖለቲካው መስክ አሁንም ከኋለኞቹ ተርታ ተሠልፈን እንገኛለን፡፡ በኢኮኖሚው ተስፋ ሰጪ ነገሮች መታየት ቢጀምሩም፣ አሰቃቂው ድህነት ትልቁን ድርሻ ይዟል፡፡ በማኅበራዊው መስክ ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ለዘመናት በልማዳዊ አሠራሮች በተተበተበች አገር ውስጥ የተሻሉትን ብቻ በመምረጥ፣ ስኬት እያስመዘገብን ነው እያልን ብንኩራራ የምናታልለው ራሳችንን ነው፡፡ ራስን እያታለሉ ለመቀጠል የማይቻልበት ጊዜ ላይ መሆናችንን በመረዳት በፍጥነት መንቀሳቀስ ይሻላል፡፡

ልማዳዊ አሠራሮች ከመንግሥት ትልልቅ ተቋማት ጀምሮ እስከ ቤተሰብ ጎጆ ድረስ ተንሠራፍተዋል፡፡ ለውጥ ለሚያፈልቁ ሐሳቦችና ለፈጠራዎች ዕድል በማይሰጥበት አገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሀብት እየባከነ ነው፡፡ የመጀመርያው የሰው ሀብት ብክነት ነው፡፡ የአገሪቱን በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች በመጠቀም የምድር ገነት መፍጠር የሚችለው የሰው ኃይል የሚያንቀሳቅሰው በማጣቱ በድህነት ማጥ ውስጥ ይዳክራል፡፡ መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማውጣት፣ ግብርናውን ማዘመንና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር በመስነፉ፣ የአገሪቱን ዕምቅ ሀብቶች ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት 25 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ አሁንም ከድህነት ወለል በታች ሲገኝ፣ ከእዚህ እጥፍ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት አሳር ሆኖበታል፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ውኃ፣ ተስማሚ የአየር ፀባዮችና የመሳሰሉ ፀጋዎችን ይዞ በየዓመቱ በትንሹ አምስት ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይፈልጋል፡፡ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምፅዋት ይለመናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ስንዴ በከፍተኛ ወጪ ከባህር ማዶ ይገዛል፡፡ ልማዳዊ አሠራሮች በመንገሳቸው ድህነት አገሪቱ ላይ ጎጆውን ቀልሷል፡፡

ትምህርት ለአገር ዕድገት ያለውን ፋይዳ ለመናገር መሞከር ‹ለቀባሪው ማርዳት› ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለትምህርት ተደራሽነት ትልቅ ዕድል በተመቻቸበት አገር ውስጥ፣ ለጥራት የተሰጠው ግምት የወረደ በመሆኑ አገር እየከሰረች ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዕውቀትና ክህሎትን ከማስረፅ አኳያ ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም፣ ለጥናትና ለምርምር ቸልተኛ በመሆናቸው አገር እየተጎዳች ነው፡፡ በአካባቢያቸው በምግብ ዋስትናም ሆነ በሥራ ፈጠራ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ማኅበረሰቡን ለማንቀሳቀስ ሲተጉ አይታዩም፡፡ ከሥር ጀምሮ ተማሪዎች ጥራት ባለው ትምህርት ተኮትኩተው ለከፍተኛ ደረጃ እንዲበቁ ሲያግዙ አይስተዋሉም፡፡ ሌላው ቀርቶ ዙሪያቸውን በመጠጥና በጫት መሸጫዎች ተከበው ተማሪዎቻቸው ሲሰነካከሉ ሲታደጉ አይታወቁም፡፡ የዕውቀት መቋደሻ ማዕድ መሆናቸው ተረስቶ እነሱም በልማዳዊ አሠራሮች ከተበተቡ ችግሩ የአገር ነው፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚመሩ በሙሉ ተጨንቀውና ተጠበው ተቋማቱን ካሉበት ድንዛዜ ማላቀቅ ካልቻሉ፣ ኃላፊነቱን ሠርተው ለሚያሠሩ ቢተው ይመረጣል፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካዴሚያዊ ነፃነታቸውን አስከብረው በኃላፊነት ስሜት ተልዕኮዋቸውን መወጣት የሚችሉት፣ ከልማድ ባርነት ሲገላገሉ ብቻ ነው፡፡

የአገሪቱ ፖለቲካ የልማድ እስረኛ መሆኑን ለማሳየት ርቀት መሄድ አይገባም፡፡ ከተፎካካሪነት ይልቅ ለጠላትነት የሚሽቀዳደም፣ ለድርድርና ለሰጥቶ መቀበል መርህ ከመገዛት ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን አጥፍቶ ለመደላደል የሚመርጥ፣ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ፣ ለአምባገነንነት የሚያመቻቹ ቅራኔዎችን የሚያባብስ፣ ለሕዝብ ፍላጎት ከመታዘዝ ይልቅ፣ የሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመስፈር የሚራኮት፣ በምክንያታዊነት ዓላማን ከማስረዳት ይልቅ፣ በስሜታዊነትና በግብታዊነት የሚነዳ፣ ወዘተ ኃይል የሚተራመስበት ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎቹ ከምድረ ገጽ ቢጠፉለት የሚፈልገውን ያህል፣ በተቃራኒው ጎራ ያሉትም ይኼንን ይመኛሉ፡፡ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ምስቅልቅሉ ወጥቶ የአንድ ፓርቲ የበላይነት ተንሠራፍቷል፡፡ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ቢኖሩም ባይኖሩም ፋይዳ የሌላቸውም በየስርቻው ተወሽቀው አሉ፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባለባት አገር ውስጥ ፖለቲካው ውጥንጥቅጡ ወጥቶ የት ነው መድረስ የሚቻለው? እንዲህ ዓይነቱ ልማዳዊ ድርጊትስ እስከ መቼ ይቀጥላል? አገር ከዚህ አሳሪና አፋኝ ችግር ውስጥ በፍጥነት መውጣት አለባት፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ባሉባት አገር ውስጥ ፖለቲካው ከልማዳዊ ድርጊቶች መላቀቅ አለበት፡፡

የዜጎች መሠረታዊ መብቶች ጉዳይ ሲነሳ ከዴሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብቶች ባልተናነሰ የእናቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች አኗኗርም ትኩረት ይሻል፡፡ እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ እስከ ወሊድ ድረስ አስፈላጊውን የጤና ክብካቤ ባለማግኘታቸው፣ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ከሆነው የኑሮ ውጣ ውረድ ጋር  የሚያንገሸግሽ ትግል ስለሚገጥማቸው፣ ከአቅማቸው በላይ በሚያንዣብባቸው ድህነት ምክንያት ትልቅ ፈተና ውስጥ ናቸው፡፡ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ከመሠረታዊ አቅርቦቶች ጀምሮ የሚገጥሟቸው ፈተናዎች ለማመን የሚከብዱ ናቸው፡፡ እነዚህን ወገኖች የሚፈትኗቸው ችግሮች ከልማዳዊ አሠራሮች የሚመነጩ ናቸው፡፡ ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት፣ የጤና ክብካቤና የመሳሰሉት መሠረታዊ ፍላጎቶች በቀላሉ አይገኙም፡፡ እናቶች ካቅማቸው በላይ የማገዶ እንጨት እየተሸከሙ ለአካላዊ ሥቃይና ለውስጥ ደዌ ይዳረጋሉ፡፡ ሕፃናት በድህነት ምክንያት የተመጣጠነ ምግብ ስለማያገኙ ይቀነጭራሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ተርፈው ለውስብስብ የጤና እክሎች ይዳረጋሉ፡፡ የአረጋውያንና የአቅም ደካሞች ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው፡፡ አገር በልማዳዊ አሠራሮች በመተብተቧ ምክንያት እንዲህ ዓይነት ችግሮች ለዘመናት ሕዝብ ላይ ያናጥራሉ፡፡

ልማዳዊ አሠራሮች በጣም ከመለመዳቸው የተነሳ ለውጥ እንደ አባት ገዳይ ይጠላል፡፡ የለውጥ ሐሳቦችን ይዘው የሚቀርቡ እንደ ጠላት ይታያሉ፡፡ ደፈር ብለው ሐሳቦቻቸውን ማቅረብ ሲጀምሩ በሐሜትና በአሉባልታ ይከበባሉ፡፡ አገር የምታድገው በአዳዲስ አስተሳሰቦችና ጊዜውን በሚመጥኑ የድርጊት መርሐ ግብሮች ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ቢሮክራሲ እንዳለ ማለት ይቻላል ልማዳዊ አሠራሮች ሰፍነውበታል፡፡ ተቋማቱን የሚመሩት ደግሞ ለአዳዲስ አስተሳሰቦች ዕውቅና እንሰጣለን ቢሉም ከልባቸው አይደለም፡፡ ያቀዱት ሳይሳካ ሲቀር በአፈጻጸም ድክመት ያሳብባሉ፡፡ የአፈጻጸም ድክመት የሚመጣው እኮ ሥራቸው በሳይንሳዊ መሥፈርቶች ስለማይገመገም ነው፡፡ ከልማድ እስረኝነት ስለማይላቀቁ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ተቋም ለለውጥ ለመነሳት ዝግጁ መሆን የሚቻለው፣ ከልማድ እስረኝነት ራስን ለማላቀቅ ቁርጠኝነት ሲኖር ነው፡፡ በኋላቀር አሠራሮች ተተብትቦ ስለለውጥ ማውራት በፍፁም አይቻልም፡፡ አገሪቱ አሁን የሚያስፈልጋት መሠረታዊ ለውጥ ነው ከተባለ፣ ከልማዳዊ አሠራሮች በፍጥነት መላቀቅ ይገባል! አሁን ባለው ሁኔታ የትም መድረስ አይቻልም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...