Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አሸጋግረን እናስብ!

ሰላም! ሰላም! ያቺ አያሌ የሥራ ዓይነቶችን ሁሉ ንቄ ደላላ ለመሆን የወሰንኩባት ሌሊት የተባረከች ናት፡፡ ደላላነትን ወጌና ማዕረጌ አድርጌ የተቀበልኩባት ናት፡፡ አቻ ጓደኞቼ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? ሲባሉ ግማሾቹ ዶክተር፣ ግማሾቹ ኢንጂነር፣ ሌሎቹም ፓይለት እያሉ ምክንያታቸውን ሲደረድሩ፣ በማናቸውም ምርጫና ውሳኔ ‘ሳልወሰወስ’ በራሴ መተማመን እየተነዳሁ ከአስተማሪዬ ለቀረበልኝ፣ ‹‹ስታድግ ምንድነው መሆን የምትፈልገው?›› ለሚለው ጥያቄ ስመልስ፣ ‹‹ደላላ ነው መሆን የምፈልገው!›› ብዬ በልጅነት ብሩህ አዕምሮዬ ዛሬን ዓይቼ፣ ስለዛሬዬ ደላላ መሆን ነው የምፈልገው ብዬ ትንቢት የተናገርኩባት ቀን የተቀደሰች ናት፡፡

ደላላነቴን የማወድስባቸው ሺሕ ምክንያቶች በአዕምሮዬ አስቀምጬ፣ የተዋወቅኳቸውን ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚወክሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎች ሳስብ፣ የእኔ የገቢ ምንጭ መሆኑን ሳስብ፣ ዞሬ ዞሬ ደላላ መሆኔን አመሰግናለሁ፡፡ የማንደልለው አንዳች ነገር የለንም፡፡ መሬት፣ ቤት፣ መኪና፣ አሁን ደግሞ ከዚህም እልፍ ብለን ሐሳብ ማሻሻጥ ጀምረናል፡፡ ዋናው ጠቃሚ የሆነ ሥጋ መልበስ የሚችል ሐሳብ ማምጣት ብቻ ነው፡፡ ዘመናዊው የድለላ ሰንሰለት ሐሳባችሁን ሳይቀር ይቸበችብልዎታል፡፡

የባሻዬ ልጅ እንደሚለው የሁሉ ነገር መጀመርያው ሐሳብ ነው፡፡ እንዲያውም የሐሳብን መሠረታዊነት ሲያብራራ፣ ‹‹ሥራ ጀምሮ ከማሰብ ፈጣሪ ይጠብቅህ፤›› ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እሱ እንደሚለው ምንም ነገር በአቦ ሰጡኝ መሥራት የለበትም፡፡ ‹‹መጀመርያ ለሥራ ከመንቀሳቀሳችን በፊት ጉዳዩን ሙሉ ለሙሉ አስበን መጨረስ ይኖርብናል፡፡ አስበን፣ አውጥተንና አውርደን የጨረስነውን ነገር ሥጋ ማልበስ የዚያን ያህል አስቸጋሪ የቤት ሥራ አይደለም፤›› በማለት ያብራራል፡፡ ‹‹ዘጠኝ ጊዜ ለካ፣ አንድ ጊዜ ቁረጥ›› አይደል የሚባለው?

እንግዲህ ወዳጄ እኔ ባደግኩበት ባህል ውስጥ ሐሳብ ቀድሞ የሚመጣበት አጋጣሚ ጥቂት ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ሥራው መሀል ነው መታሰብ የሚጀመረው፡፡ እንዲህ ቢሆንስ? እንዲያ ቢሆንስ? እየተባለ ወይም በሌላ አነጋገር ሳንደርስ እናየዋለን ይባላል እንጂ፣ መጀመርያ በሐሳብ መርምረን፣ አውጥተንና አውርደን ስናበቃ ሥጋ ወደ ማልበሱ ከመምጣት ይልቅ፣ ገና ለገና አንድ ሐሳብ መጣ ሲባል ወዲያው ተነስቶ እዚያው በዚያው ያዝ፣ ለካ፣ ቁረጥ የምንልበትና ብዙ ዋጋ የምንከፍልበት ባህል ውስጥ ነው ያደግኩላችሁ፡፡

የባሻዬ ልጅ አሜሪካ ስለሚገኘው ‹ዳዝኒ ወርልድ› ስለሚባለው በዓለማችን ላይ እጅግ ውብ ስለሚባለው ሰው ሠራሽ ቦታ ያጫወተኝን ሳልነግራችሁ ማለፍ አይሆንልኝም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ አንቱ የሚባሉ ዓይናማ ሰው ገነት ሊሆን መላዕክት ብቻ የቀሩት አንድ ምድራዊ ገነት ሊባል የሚችል ቦታን በምናባቸው ያያሉ፡፡ እኚህ ሰው ያዩትን ነገር ለማድረግ ወዲያው መዶሻና ሚስማር ከማንሳታቸው በፊት እያንዳንዷን ነገር አስበውና አሰላስለው ጨረሱ፡፡ በምናባቸው ሰማይ ላይ የጨረሱትንም ዋና ነገር መሬት ለማውረድ ያመቻቸው ዘንድ፣ ያዩትን ነገር ወረቀት ላይ አሰፈሩት፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደሚለው ‹‹ጨርሰው ጀመሩት››፡፡ በዚህም መሠረት ሥራቸውን ወደ ግብ ለማድረስ ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ፡፡ በዚህ መሀል ነበር እኚህ ታላቅ ዓይናማ ሰው በድንገት ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ ይህንን የሰሙ በሙሉ ታላቅ ጅማሬያቸውን ዓይተው አዘኑላቸው፣ አለቀሱላቸው፡፡

እሳቸው የጀመሩትንም ታላቅ ነገር አገሬው ሁሉ ተረባርቦ ጨረሰው፡፡ በባሻዬ ልጅ አባባል ሥጋ አለበሰው፡፡ የሚገርመው በዚህ ታላቅ መዝናኛ መንደር የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ አያሌ ታላላቅ ሰዎች ተገኙ፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙ አንድ ሰው እንዲህ በማለት ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፣ ‹‹በዚህ ታላቅ ምርቃት ላይ የዚህ ታላቅ ሐሳብ ጠንሳሽና ጀማሪው ኖረው ቢሆንና ይህንን ድል ዓይተው ቢያልፉ ኖሮ ደስታችንን እንዴት ሙሉ ያደርግልን ነበር?›› በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ፡፡ ታዳሚዎችም ‘እውነት ነው’ በሚል ስሜት በጭብጨባ አጅቧቸው፡፡ ሰውዬውም የተለያዩ ነገሮችን ጨምረው ሐሳባቸውን አሳረጉ፡፡

በመቀጠልም የዚህ ሐሳብ መሥራች የነበሩት አሁን ግን በሕይወት የሌሉት ሰው ባለቤት ትናገር ዘንድ ዕድል ተሰጣት፡፡ እሷም እንዲህ በማለት ንግግሯን ጀመረች፣ ‹‹ባለቤቴ ይህንን ታላቅ መንደር ሳያየው ሞተ በሚለው ሐሳብ አልስማማም፡፡ ምክንያቱም እሱ መጀመርያ ከማናችንም በፊት ቀድሞ ተመልክቶት ነበር፡፡ የእሱ ጥረትና ምጥ የነበረው እሱ ቀድሞ ጨርሶ የጀመረውን ነገር እናንተን ማሳየት ነበር፡፡ ስለዚህ ይህች ቀን እርሱ ለዘመናት ሲመኛት የነበረች ቀን ናት፡፡ እሱ እንዳመለከተው እንዲሁ እናንተን ሥጋ አልብሶ የማሳየት ይህ ህልሙ ዛሬ ተፈጽሞለታል፡፡ ማየት ይፈልግ የነበረው ይህ ሥራ መጠናቀቁን ሳይሆን፣ እርሱ ቀድሞ የተመለከተውን ለእናንተ ማሳየት ነው፤›› ስትል፣ ቅድም ከነበረው ጭብጨባ በላይ የሚያስተጋባ ሆታ ተሰማ፡፡

ባሻዬ፣ ‹‹እኛን የሰለቸን እነሱ ያላዩትን ነገር እኛን እዩ ብለው የሚያስጨንቁንን መሪዎች ማየት ነው፤›› በማለት የተናገሩት ነገር አዝናንቶኛል፡፡ ባሻዬ ሲቀጥሉ፣ ‹‹መሪ ማለት ዓይቶ የሚያሳይ ነው፡፡ አለቱን ፈንቅሎ ውኃ የሚያፈልቅ ነው…›› እያሉ ስለልባም መሪዎች ፀሎት መቆማቸውን ገፍተውበታል፡፡

ማንጠግቦሽም አሁን አሁን ቤቷን እንኳን ለማስተካከል ስትነሳ መጀመርያ ምን ማድረግ እንዳለብን ትነግረኛለች፡፡ ‹‹መጀመርያ ሶፋውን ውጪ እናወጣዋለን፡፡ ከዚያ ፍሪጁን የሶፋው ቦታ ላይ እናመጣዋለን፡፡ ከዚያ ሌላውን ዕቃ ለማንቀሳቀስ ቦታ አገኘን ማለት አይደለም?›› ትለኛለች፡፡ እኔም፣ ‹‹እውነትሽን እኮ ነው፣ ከዚያስ?›› እላታለሁ፡፡ እሷም እያንዳንዷን ነገር ማብራራት ትጀምራለች፡፡ ይህንን ሁሉ የምናደርገው ሶፋው ላይ ተቀምጠን ነው፡፡ ሶፋ ለማንቀሳቀስ ምንም ኃይል ሳይባክን ሁሉንም ነገር ቁጭ ብለን ካበሰልን በኋላ ስንጨርስ እንጀምራለን፡፡ ይኼኔ ምንም የምናስተናግድው ሰበር ሐሳብ አይኖረንም፡፡ ይኼው ታዲያ ጨርሶ መጀመር በሚል ሐሳብ እየተብነሸነሽኩ እገኛለሁ፡፡

የባሻዬ ልጅ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን የተመኘላቸው ነገር ይህንኑ ነበር፡፡ ‹‹ወዴት መድረስ እንደሚያስቡና ኢትዮጵያን ምን ላይ ማስቀመጥ እንደሚፈልጉ ግልጽ ግብ አስቀምጠው መንገዳቸውን ቢጀምሩ፣ ምናልባትም እሳቸው እንኳን በማይኖሩበት ዘመን መልካቸውን በሥራዎቻቸው ላይ መመልከት ያስችለናል፡፡ በሌሉበት በሥራቸው ላይ አሻራቸውን እያየን እናጨበጭብላቸዋለን፤›› በማለት ነግሮኛል፡፡

አንድ ደላላ ወዳጄ ደግሞ፣ ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ ቢያደርጉኝ ምን እንደማደርግበት አውቅ ነበር…›› ሲለኝ ደስ ብሎኝ፣ ‹‹ምን ዓይነት ልዩ ደላላ ነው የሚሠራውን የሚያውቅ?›› ብዬ ብጠይቀው ምን ብሎ ቢመልስልኝ ጥሩ ነው? ‹‹ኢትየጵያ ውስጥ ያሉትን ስታዲዮሞች በሙሉ ለኢንቨስተሮች ሸንሽኜ እሸጥላቸው ነበር፤›› ቢለኝ ፈገግ ብዬ ማለፍ አልፈለግኩም፡፡ ይልቁንም፣ ‹‹መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል›› የሚለው አገርኛ ብሒል ትዝ እያለኝ፣ ‹‹በአጭሩ እያሰብህ ዘላቂውን ጉዳይ ዕድሜውን አታሳጥረው፤›› አልኩት፡፡ አርቆ አሳቢዎች ያቆዩዋትን አገር አቋራጭ ፈላጊዎች እንዳይፈነጩባት መላ ይመታ እንጂ፡፡ ‘አርቆ ማሰቢያ እያለን አዕምሮ…’ እንዳለው ድምፃዊው፣ እኛም አሸጋግረን እናስብ! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት