Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከመስማት እክል የመታደግ ጅማሮ

ከመስማት እክል የመታደግ ጅማሮ

ቀን:

አፎሚያ ዳንኤል የ12 ዓመት ታዳጊ ነች፡፡ የመስማት ችግር ያጋጠማት በአንድ ዓመት ከሁለት ወር ዕድሜዋ ቤት ውስጥ ድክ ድክ ስትል በወደቀችበት አጋጣሚ ነበር፡፡ መውደቋን ተከትሎ ቀስ በቀስ የቅርብ እንጂ የርቀት ድምፅ መስማት ተሳናት፡፡ አንደበቷም ይይዛት፣ ትኮላተፍ ጀመረ፡፡

ቤተሰቦቿም ለሕክምና ወደ ተለያዩ ተቋማት ከመሄድ አይቦዝኑም ነበር፡፡ ዕድሜዋ እየጨመረ ሲመጣ ችግሩ ይለቃታል በማለት በመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ትምህርቷን እንድትቀጥል ገፏፏት፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳየችም ነበርና በትምህርቷም ኋላ ቀረች፡፡ ይህን ጊዜ ነበር ወላጆቿ ከባድ ያለ የሕክምና ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋት ያመኑበት፡፡ በቅርቡም ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ በተደረገላት ቀዶ ሕክምና ‹‹ኮክላይር ኢንፕላንት›› የተባለ መሣሪያ ጆሮዋ ላይ እንዲተከልላት ጤናዋም መሻሻል እንዲያሳይ ሆኗል፡፡

መሣሪያው የተተከለላት ክፉኛ የተጎዳውን የጆሮዋን ነርቭ ተክቶ እንዲሠራ ለማድረግ ነው፡፡ መሣሪያውን የሚያመርቱ ድርጅቶች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን፣ የመሣሪያ ግዢ 300ሺሕ ብር ነበር የፈጀው፡፡ የቀዶ ሕክምናውን ወጪ የሸፈኑላት  ወላጆቿ ሲሆኑ፣ መሣሪያውን ኦስትሪያ ከሚገኘው ሜድኢል ሜዲካል ኤሌክትሮኒክስ ከሚባለው የኮክላይር ኢንፕላንት አምራች ድርጅት ገዝቶ ያቀረበው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው ኢስት አፍሪካ ሒሪንግ ኤይድ ሴንተር ነው፡፡ ለሴንተሩ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገለት ደግሞ በጣሊያን የሚገኘው አኩዛ የተባለ የዕርዳታ ድርጅት ነው፡፡

እኗቷ ወ/ሮ አሰገደች ከተማ እንደገለጹት፣ አፎሚያ እንደ ትምህርት አጀማመሯ ቢሆን ኖሮ ዘንድሮ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ትሆን ነበር፡፡ ነገር ግን የመስማት ችግሯና መኮላተፏ በትምህርቷ ብዙም ውጤታማ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡ ውጤቷም ከክፍል ጓደኞቹ አንፃር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነበር፡፡ ይህም ከአምስተኛ ክፍል ወደ ሁለተኛ ክፍል ዝቅ ብላ እንድትማር አድርጓታል፡፡

ኮክላይር ኢንፕላንት የተባለው መሣሪያ ከተተከለላት በኋላ ግን የሩቁን የቅርቡን ሳትል ድምፅ መስማት ችላለች፡፡ መኮለታተፍም አቁማ በደንብ መናገር ችላለች፡፡  አስጠኚም ተቀጥሮላት ትምህርቷን በጥሩ ሁኔታ በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚተላለፉትን የልጆች መዝሙር ሳይቀር እንደምታዳምጥ፣ አብራም እንደምትዘምርና ከእኩዮቿ ጋር ያላትም ትስስር እየተሻሻለ እንደመጣ ወ/ሮ አሰገጀች ተናግረዋል፡፡

የኢስት አፍሪካ ሒሪንግ ኤይድ ሴንተር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ነጋ እንደገለጹት፣ ለመለየት ወይም ለመናገር የሚያስቸግሩ አንዳንድ ቃላት ሲያጋጥማት ወደ ሴንተሩ እየሄደች አስቸጋሪ ቃላቱ ጆሮዋ ላይ ከተተከለው የመሣሪያው ፕሮግራም ጋር እንዲስተካከልላት ይደረጋል፡፡ ይኼንንም የማስተካከል ሥራ የሚያከናውኑት የሴንተሩ የሥነ ልሳን ባለሙያ ናቸው፡፡

ይኼው ድርጅት በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሥፍራዎች በተቋቋሙ ሦስት መዋለ ሕፃናት ለሚገኙና ዕድሜያቸው ከአራት እስከ ዘጠኝ ዓመት የሆኑ 150 ሕፃናትን የመስማት መጠናቸውን ለክቶ 32ቱ ችግር እንዳለባቸው አረጋግጧል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሕፃናቱ የኮክላይር ኢንፕላንት ያስፈልጋቸዋል ማለት ሳይሆን በቀላል ሕክምና የሚረዱ ናቸው፡፡ ሆስፒታል ሄደው ክትትል ካልተደረገላቸውና ካልተመረመሩ ግን በቀጣይ ከፍተኛ ችግር ሊያመጣባቸው እንደሚችል አቶ አበራ አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ነቢያት ተፈሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአንገት በላይ እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ስፔሻሊስቱ እንዳሉት የመስማት ችግር 40 ከመቶ የሆነው በዘር፣ 60 በመቶ ደግሞ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች አማካይነት ይከሰታል፡፡ መከላከል በሚቻል በሽታዎች ለሚከሰተው 60 ከመቶ ያህሉ የመስማት ችግር ዋናው ምክንያት ኢንፌክሽን እንደሆነም ይናገራሉ፡፡

ለመስማት ችግር የሚያጋልጠው ኢንፌክሽን በሁለት መንገዶች ሕፃኑ በማሕፀን ውስጥ እያለና በወሊድ ወቅት በሚያጋጥም ችግር ይከሰታል፡፡ ነገር ግን ሕፃኑ በእናቱ ማሕፀን ውስጥ እያለ እናትየው ትክክለኛ የሆነ የቅድመ ወሊድ ክትትል ካደረገች፣ ክትባቶች ከወሰደችና ልዩ ልዩ ኢንፌክሽኖችን በመከላከል የመስማት ችግር እንዳይመጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሌላው ደግሞ በወሊድ ወቅት ሕፃኑ የመታፈን አደጋ ሲያጋጥመው የሚከሰተው የመስማት ችግር ሲሆን፣ ልጁ ካደገም በኋላ እንደ ኩፍኝ፣ ጆሮ ደግፍ፣ ማጅራት ገትር የመሳሰሉ በሽታዎች ሲይዘው የመስማት ችግር ሊያመጣ፣ ከፍተኛ ድምፆችም ለመስማት ሊቸገር እንደሚችልና ይህም በወሊድ ወቅት በሚደረግ ጥንቃቄ መከላከል እንደሚቻል ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

የመስማት ችግር ከብዙ ነገር ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤትና ከኅብረተሰቡ ራስን ማግለል ሲያስከትል ይታያል፡፡ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ይፈጥራል፣ ሥራ መቀጠር አለመቻል፣ ድብርት፣ ትዕግስት ማጣት፣ ከሰው ጋር አለመቀራረብ፣ ዕረፍት ማጣትና የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት አለመቻል የመስማት ችግር ከሚያስከትላቸው እንቅፋቶች ተጠቃሽ እንደሆኑ ዶ/ር ነቢያት ተናግረዋል፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ከሆነ በዓለም ከ360 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የመስማት ችግር አለባቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ ከሰሃራ በታች የሚገኙ በአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ሕፃናት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያም 850 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት የመስማት ችግር አለባቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...