Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

ዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

ቀን:

እሑድ ሚያዚያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ቴል አቪቭ በሚገኘው የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ በተደቀኑ የቪዲዮ ካሜራዎች ፊት ቆመው፣ ‹‹እንደምን አመሻችሁ? ዛሬ ዓለም ዓይቶት የማያውቀውን እውነታ እነግራችኋለሁ፡፡ ዛሬ ኢራን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በድብቅ ይዛ የቆየችውንና በድብቅ የኑክሌር ማኅደር ውስጥ ያደረገቻቸውን ሚስጥሮች እገልጻለሁ፤›› ሲሉ በእብራይስጥ ቋንቋ የጀመሩትን ንግግር ወደ እንግሊዝኛ በመቀየር፣ አገኘሁ ያሉትን ሰነድ ለ20 ደቂቃዎች አቀረቡ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 አሜሪካን ጨምሮ ቻይና፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሣይ ጀርመንና ሩሲያ የፈረሙት የኢራን የኑክሌር ስምምነት ዕርባና የለሽ እንደሆነ ያሳያሉ ያሏቸውን መረጃዎች አቀረቡ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በእስራኤል የደኅንነት አካላት የተገኙ ኮምፒዩተሮች ላይ የተጠራቀሙ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ተቀናጀ ባሉት ገላጻ (Presentation)፣ ኢራን ምን ያህል ለራሷ በሚበጃት መንገድ የኑክሌር የጦር መሣሪያዎች ስምምነት ለማድረግ እንደዋሸች ሲያስረዱ ፎቶግራፎችን ጨምሮ ሌሎች ምሥሎችን፣ ብሎም የኢራን ሚሳይሎች ምን ያህል ርቀት መጓዝ ይችላሉ የሚሉ ዝርዝሮችን የያዙ ገጾችን ተጠቅመው ነበር፡፡

ሆኖም የተገኙት መረጃዎች ምንም እንኳን ተቺዎች አዲስ ነገር አላሳዩም ቢሏቸውም፣ ከአንድ ቀን በፊት በእስራኤል የደኅንነት አገልግሎት ሞሳድ አማካይነት ከኢራን የተሰረቁ ናቸው የሚሉ አሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

 

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በዋናነት ኢራን የኑክሌር ስምምነቱ ባልተገባ ሁኔታ እንዲፈጸም ዋሽታለች፣ የኑክሌር ማበልፀግ ሥራዋንም አላቆመችም፣ ተዘግቷል የተባለው የአማድ ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ በተግባር ላይ ይገኛል የሚሉ ነጥቦችን አንስተዋል፡፡

‹‹የአማድ ፕሮጀክት ዋነኛ ዓላማ የኑክሌር መሣሪያዎችን ማምረት ነው፡፡ እነዚህም እያንዳንዳቸው አሥር ኪሎ ሜትር የመምዘግዘግ አቅም ያላቸው አምስት የሚሳይል ጫፍ አረሮችን ዲዛይን ማድረግ፣ መሥራትና መሞከር ናቸው፣›› ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ፕሮግራም የለኝም ባለች ጊዜ ስትዋሽ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ተውኔታዊ አቀራረባቸው መሀል ላይ እውነተኛ የኢራን ሰነዶች ቅጂ ናቸው ያሏቸውን በማኅደር የተያዙና በሲዲ የተገለበጡ ሰነዶችን ድርድሮች ለካሜራዎቹ እየገለጡ ሲያሳዩ ነበር፡፡ እነዚህም ሰነዶች ኢራን እ.ኤ.አ. ከ1999 እስከ 2003 ድረስ የነበሯትን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ፕሮጀክቶች የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

ኔታንያሁ ይኼንን በማለታቸው ግን ኢራን የኑክሌር ስምምነቱን ጥሳለች ለማለት አያስችልም የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ኢራን ይኼንን ሰነድ ይዛ በመገኘቷ ከኑክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የሆኑ አገሮች ቡድን ስምምነትን መጣሷ እየወራ ነው፡፡

ዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

 

ይህ የኔታንያሁ ገለጻ ግን በብዙዎቹ ችላ ቢባልም አንድ ዋና አድማጭ ግን አግኝቷል፡፡ እርሱም ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ ስምምነቱን ሲያጣጥሉ የነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ናቸው፡፡ የኦባማን ሥራዎች በማጣጣልና በመሻር የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ፣ ይኼንን የኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ስምምነት ‹‹እጅግ አስቀያሚው ስምምነት›› እያሉ ሲተቹትም ተደምጠዋል፡፡

የኋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ፣ ‹‹ስምምነቱ የተደረገው ሙሉ በሙሉ ውሸት በሆነ ነገር ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ኢራን በስምምነቱ ወቅት ዋሽታለች፡፡ ኢተዓማኒም ነበረች፡፡ የተደረገው ሁሉ ትክክል ባልሆኑ ሁነቶች ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእኛ እጅግ አሳሳቢ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት ለመውጣት ወይም ለመቆየት የሚያደርጉት ውሳኔ የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ሲቀረው የኔታንያሁ ግኝት መምጣቱ፣ በውሳኔያቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግምቶች ፕሬዚዳንቱ ከዚህም የጊዜ ቀጠሮ ቀደም ብለው የአገራቸውን ውሳኔ ያሳውቃሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

ምናልባትም ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ስምምነት ሊወጡ ይችላሉ ብላ ያሰበችው ኢራን ደግሞ፣ ማስጠንቀቂያ እየሰጠች ትገኛለች፡፡

አሜሪካ ከዚህ ስምምነት ከወጣች ከፍተኛ ችግር ውስጥ ትወድቃለች ሲሉ የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሩሃኒ ማሳሰቢያ ከመስጠት አልፈው፣ ኢራን የሚመጣባትን ፈተና ሁሉ ለመቋቋም ዝግጁ ሆና ቆማለች ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

 

ሩሃኒ አክለውም፣ ‹‹እንዲያውም የኑክሌር ስምምነቱ አሜሪካ ባትኖርበት ይበልጡን ውጤታማ ይሆናል፣›› ብለዋል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ከኑክሌር ስምምነቱ ሊወጡ ይችላሉ በሚል ሥጋት ያደረባቸው የአውሮፓ አገሮች መሪዎች፣ ካሁኑ አሜሪካ ከፓሪሱ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት ለመውጣት ስትንደረደር ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ፣ አሜሪካን ተረጋግተሽ አስቢ እያሏት ነው፡፡

አሜሪካ ተፅዕኖ በማሳደር አገሮች እንዲከተሏት ለማድረግ ስትል የምትወስዳቸው ዕርምጃዎችም እንደማያዋጧት እያሳሰቡም ይገኛሉ፡፡

የአውሮፓ ፓርላማ አባላትን አሜሪካ ከኑክሌር ስምምነቱ እንዳትወጣ ለማሳሰብ የቀደማቸው አልነበረም፡፡ በተለይ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና ጀርመን አሜሪካ ከኢራን የኑክሌር ስምምነት ከወጣች ሩቅ ምሥራቅ ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል፣ በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች መካከል ያለውን የአትላንቲክ ተሸጋሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነት ሊጎዳ እንደሚችል እያሳሰቡ ነው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. ሜይ 12 ቀን 2018 የኢራን የኑክሌር ስምምነት እንዲስተካከል፣ አለበለዚያ ግን አሜሪካ ያለ ኢራን ስምምነት ማዕቀብ ለመጣል እንደምትገደድም አሳስበዋል፡፡

‹‹በሜይ 12 ምን ላደርግ እንደምችል ማንም አያውቅም፣›› ሲሉም ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይኼንን ለማድረግ እንዲመቻቸው የኔታንያሁ የገለጻ መረጃዎች ጥንቅር ላይ የአሜሪካ እጅ ረጅም እንደሆነ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በኢራን የኑክሌር ስምምነት ላይ ምን ሊወስኑ እንደሚችሉ ባልታወቀበት በዚህ ጊዜ፣ የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአራት ዓመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ ከፍተኛ በሆነ ዋጋ እየተሸጠ ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ከ70 ዶላር በልጦ የማያውቀው የነዳጅ ዋጋ፣ አሁን እስከ 75.5 ዶላር በበርሜል እየተሸጠ ነው፡፡ 

ዓለምን ሥጋት ውስጥ የጣለው የኢራን የኑክሌር  ስምምነትና የዶናልድ ትራምፕ አቋም

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...