Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትፌዴሬሽኑና የዳኞቹ ማኅበር በስብሰባ ቀነ ቀጠሮ አልተስማሙም

ፌዴሬሽኑና የዳኞቹ ማኅበር በስብሰባ ቀነ ቀጠሮ አልተስማሙም

ቀን:

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ እየጠና የመጣውን የስፖርታዊ ጨዋነት መደፍረስ ተከትሎ ዳኛዎቹ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የአቋም መግለጫ በማውጣት ከብሔራዊ ፌደሬሽኑ ጋር ሊያከናውኑት የነበረውን የስብሰባ ቀነ ቀጠሮ ላይ መስማማት አልቻሉም፡፡

ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. መከላከያ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት 22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኛው ኢያሱ ፈንቴ ላይ የደረሰውን ደብደባ ተከትሎ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ የጠራው የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር ሊስተካከሉ ይገባል ያላቸውን ስምንት የአቋም ነጥቦች አስቀምጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዳኞች ማኅበር የጠራውን ጠቅላላ ጉባዔ ተከትሎ ከዳኞቹ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠትና ለመወያየት ቀጠሮ ቢያዝም ሁለቱ አካላት የተለያየ አቋም ይዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር ጉባዔ የቀረቡትን ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ለሚያዝያ 25 ቀጠሮ ይዞ ነበር፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ያሰናዳው የስፖርታዊ ጨዋነትን መድረክ ተከትሎ ወደ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀነ ቀጠሮ መያዙን የዳኞቹ ማኅበር ለፌዴሬሽኑ የላከው ደብዳቤ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁለተኛ ጊዜ ቀጠሮውን ቀደም ብሎ እንደሚያዘጋጅ ቢያስረዳም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ የኢትዮጵያ ዳኛዎችና ታዛቢዎች ማኅበር ግን ለግንቦት 4 ቀን ቀጠሮ መያዙንና ምንም ዓይነት የፕሮግራም ለውጥ አለመኖሩን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ሚካኤል አርአያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በውዝግብ የታጀበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ የዳኞች ማኅበር ይሟሉልን ያላቸውን ነገሮች ካልተሟሉ ምንም ዓይነት ጨዋታ ማድረግ እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ውሳኔያቸው ተከትሎ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለተነሱት ጥያቄዎች ቀስ በቀስ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ሐሙስ ሚያዝያ 25 ቀን ከሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራሮች ጋር የተወያየው ፌዴሬሽኑ ዳኞች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም፣ ውድድር ማቆም መፍትሔ እንደማይሆን ክለቦች አንስተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙ የክለብ አመራሮችም ‹‹ዳኛ ከውጭ አስመጥተን ውድድሩን እናስቀጥላለን›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የእግር ኳስ ሜዳው ወደ ጦር ዓውድማ እየተለወጠ መምጣትና እየተሰሙ ያሉት ውዝግቦች ፌዴሬሽኑ ተጠያቂ እንደሆነ በሁለቱም አስቸኳይ ጉባዔዎች ላይ ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ዳኛዎችና ታዛቢዎች ማኅበር በጠራው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በአቋም መግለጫው ስምንት ነጥቦችን አስቀምጧል፡፡ ከነዚህም በዘንድሮው ውድድር የተጎዱት ዳኞች ካሳ ይከፈላቸው፣ ለዳኞቹ የኢንሹራንስ ክፍያ ይከናወን፣ በወልድያ ጨዋታ ላይ ጉዳት የደረሰበት ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ከፍተኛ ሕክምና ያግኝ፣ በክልሎች በቂ ጥበቃና ለዳኞች የሕግ ከለላ ይደረግ፣ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አሠራሩን ያሻሽል፣ በኢንተርናሽናል የመሀል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ላይ የደረሰውን ድብደባ በሕግ አግባብ እንዲጠየቅ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የተቀመጡት የአቋም መግለጫዎች በፌዴሬሽኑ መሟላት ካልቻሉ ለሦስት ሳምንት ማንኛውንም ጨዋታ እንደማያደርጉና አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡

በፌዴሬሽንና በዳኞች ማኅበር መካከል በውይይት ይፈታል ተብሎ የሚጠበቀው ውሳኔ ውድድሩን ለማስቀጠል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሒደት የተለያየ ችግር በመንፀባረቁ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) አማካይነት ሁለት የአጣሪ ኮሚቴ አባላት በመላክ አዲስ አስመራጭ ኮሚቴና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ዳግም እንዲመረጥ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን በካፒታል ሆቴል በተደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ መሠረት አዲስ አምስት አባላት ያሉት የምርጫ አስፈጻሚና ሦስት ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡ ተመራጮቹ የምርጫውን ቀንና ቦታ በዚህ ሳምንት ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ ዕጩ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጻሚ አባላት እንዲልኩ ይደረጋል ተብሏል፡፡ አዲስ ከሚላኩት ዕጩዎች በተጨማሪም ነባር ዕጩዎችን የሚልኩ ክልሎችም እንደሚኖሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡

በመጀመሪያ የምርጫ ሒደት ዕጩ የሆኑትን አካላት ሙሉ በሙሉ መቀየር ካልተቻለና አዲስ የእግር ኳስ መንፈስ መፍጠር ካልተቻለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› መሆኑ አይቀሬ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አልታጡም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...