Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የፍትሕ አካላት ነፃነትና ገለልተኝነት ከፍተኛ ትግል ያስፈልገዋል!

የፍትሕ መለያ የሆነችው ዓርማ ዓይኗ በጨርቅ መሸፈኗ የገለልተኝነት ተምሳሌት ነው፡፡ ይህ ተምሳሌት የፍትሕ አካላትን ነፃነትና ገለልተኝነት ይወክላል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ኢትዮጵያ የጎደላት ከየትኛውም የተቋም ግንባታ ይበልጥ፣ ከየትኛውም ፓርቲ ወይም ቡድን ርዕዮተ ዓለም ጭምር ገለልተኛ የሆነ የፍትሕ ተቋም ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፍትሕ ተቋማት ቋንቋ፣ አደረጃጀትና መፈክር ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለፓርቲ ‹‹መስመር›› ይበልጥ የገበረ ነው፡፡ ስለዚህም የፍትሕ አካላት በአንድ ድምፅ ስለ ‹‹ሕዝብ ክንፍ››፣ ስለ ‹‹አንድ ለአምስት›› አደረጃጀት፣ ስለ ‹‹ተባብሮ›› መሥራት ሲናገሩ ወይም ሲነጋገሩ ይሰማሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ብሏል፡፡ የፖሊስን ምርመራና የዓቃቤ ሕግን ክስ መርምሮ በሕጉ መሠረት ፍርድ ወይም ውሳኔ የመስጠት ብቸኛ ሥልጣን ለፍርድ ቤት ሰጥቷል፡፡ በዚህ ረገድ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት ‹‹ተስማምታችሁ›› ሥሩ፣ ‹‹አንድ ሁኑ›› የሚባልበት መሠረት የለም፡፡ የሕጉ ትርጉም ይኼ ነው ብሎ የመወሰን ብቸኛ ሥልጣን የፍርድ ቤት መሆኑን ለድርድር የሚያቀርብ የፍትሕ አካላት ‹‹ትብብር›› አይኖርም ማለት ነው፡፡ ‹‹የፍትሕ አካላት ሳምንት›› በማለት የሚታወቀው በዓል አከባበር መሠረታዊ ችግር የሚነሳው ከዚህ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፌዴራል የፍትሕ አካላት በመባል የሚታወቁት ፍርድ ቤት፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች ላይ ሁሌም የሚነሱ የነፃነትና የገለልተኝነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ የዘንድሮው የፍትሕ ሳምንት ክብረ በዓል መሪ ቃል ‹‹ጠንካራ የፍትሕ ተቋማት ለአስተማማኝ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት›› የሚል ነው፡፡ የሚከበረውም ለስምንተኛ ጊዜ ነው፡፡ ቃልና ተግባር ቢሰምሩ ኖሮ እንደ ዓይን ብሌን የሚታየው ፍትሕ የብዙዎች እሮሮ አይሆንም ነበር፡፡ የሚከበረውና የሚወራው አልጣጣም እያሉ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አደረጃጀትና ሥምሪት በጥሩ ጎኑ ቢወሳም፣ የነፃነቱና የገለልተኝነቱ ጉዳይ ግን ብዙ ያነጋግራል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ሙስናን መዋጋትና የሕግ የበላይነትን ማስፈን የሚቻለው የፍትሕ አካላት በገለልተኝነትና በነፃነት እንዲሠሩ ሲደረግ ነው፡፡ ካለፉት አሳዛኝ ስህተቶችና ሆን ተብሎ ከተፈጸሙ ድርጊቶች በመማር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር መገንባት የሚቻለው፣ በሕገ የበላይነት ሥር ፍትሕ ማስፈን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በገዛ አገራቸው ነፃነት የሚሰማቸው፣ ሐሳባቸውን በነፃነት እየገለጹ ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ የሚኖሩትና ሰላማዊው የፖለቲካ ምኅዳር ተከፍቶ ብርቱ ፉክክር የሚኖረው፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ሕግን ብቻ ተከትሎ ሥራውን በገለልተኝነትና በነፃነት ሲያከናውን ነው፡፡ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል እንደፈለገ የሚዘውረው የፍትሕ ሥርዓት አገር ከማመሰቃቀል ውጪ ፋይዳ ስለሌለው ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ፍርድ ቤቶች በነፃነትና በገለልተኝነት እንዳይሠሩ ሲደረግ ይዳከማሉ፡፡ ዳኞች በሕጉና በህሊናቸው እየተመሩ መፍረድ ሲያቅታቸው ፍርድ ቤቶች ይልፈሰፈሳሉ፡፡ የዳኞች አሿሿም ከምልመላው ጀምሮ ብቃት ላይ ካልተመሠረተና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ጋር ከተቆራኘ ፍትሕ አይኖርም፡፡ አስፈጻሚው አካል በዳኝነት ምልመላና አሿሿም ላይ በሕግ ቢገደብም፣ በፍርድ ቤቶች ከሚታየው ተግባራዊ እንቅስቃሴ አንፃር ነፃነቱና ገለልተኝነቱ በእርግጥ አለ ወይ ቢባል እንዴት አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል? ዳኞች ሕጉና ህሊናቸው በመራቸው መሠረት ይወስናሉ ወይ? የነፃነታቸውና የተጠያቂነታቸው ጉዳይ በሕግ የተወሰነ ቢሆንም፣ ነፃነታቸው አስተማማኝ ባለመሆኑ ጥያቄ የሚነሳባቸውና አቤቱታ የሚቀርብባቸው ዳኞች አሉ እኮ? ችሎት ላይ የተፈጠሩ አምባጓሮዎችም ይታወቃሉ፡፡ የዳኞች ምልመላ ሥርዓት በሕግ የተደነገገ ቢሆንም፣ ይህም በርካታ አቤቱታዎች ይሰሙበታል፡፡ የፌዴራል ዳኝነት አካሉ ከአስፈጻሚው ነፃ ሆኖ ከተለያዩ አካላት በተወከሉ ቢደራጅም ነፃ ነው ተብሎ መደምደም ይቻላል እንዴ? በርካታ አቤቱታዎችና ጥያቄዎች እየጎረፉ የነፃነትና የገለልተኝነት ጉዳይን እንደ ዋዛ ለማየት መሞከር ፈፅሞ አያዋጣም፡፡ የዳኝነት አካሉ ገለልተኝነትና ነፃነት መቼም ቢሆን የሚታለፍ አይደለም፡፡

ዓቃቤ ሕግ በመባል የሚታወቀው ተቋም ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ይህ ተቋም የነፃነቱና የገለልተኝነቱ ጉዳይ ሲወሳ በርካታ እሮሮዎች ይሰማሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ በትዕዛዝ ክስ ሲመሠርት ወይም ክስ ሲያቋርጥ፣ ሐሰተኛ ምስክሮችን በማደራጀት ንፁኃን ተብለው የሚታሰቡ ወገኖችን ሲወነጅልና የፍትሕን ልዕልና እየተጋፋ ዜጎች በሕግ የበላይነት ላይ ተስፋ ሲቆርጡ ነበር፡፡ ‹‹አንድ ንፁህ ሰው ከሚታሰር ይልቀ አንድ ሺሕ ወንጀለኞች ቢፈቱ ይመረጣል›› በመባል የሚታወቀውን የፍትሕ መርህ የሚፃረሩ ድርጊቶች ሲፈጽም እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሕግን የመሰለ የፍትሕ መሣሪያ ንፁኃንን ለማጥቂያነት በመዋሉ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በርካቶች ተንገላተዋል፡፡ ሳይወዱ በግድ ከአገራቸው ተሰደዋል፡፡ ዜጎች በሕግ መተማመን አቅቷቸው ‹‹ፍትሕ እንደ ሸቀጥ እየተቸበቸበ ነው›› ለማለት ተገደዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ሕግን የማጥቂያ መሣሪያ ያደረጉ ጥራት የሌላቸው፣ የዜጎችን መብቶች ለመጨፍለቅ የሚያግዙ፣ ለትርጉም የተጋለጡና በክፍተቶች የተሞሉ የፍትሕ ሥርዓቱን ጭምር ገንዘው የሚቀብሩ ሕጎች እየወጡ በርካቶች አሳራቸውን ዓይተዋል፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ሕገ መንግሥት የሚጋፉ ሕጎች ያተረፉት ቢኖር አገሪቱን ቀውስ ውስጥ መክተት ነው፡፡ ይኼንን አሳዛኝ ምዕራፍ በፍጥነት ማስቆም የወቅቱ ዋነኛ ሥራ መሆን አለበት፡፡

በፖሊስና በማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ ድርጊቶች ብዙ የተባለባቸው ናቸው፡፡ ፖሊስ በምርመራ ስም ተጠርጣሪዎችን በተጨማሪ ቀጠሮዎች ማንገላታት፣ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ሰዎችን መደብደብ፣ ሰብዓዊ ክብራቸውን ማዋረድ፣ ወዘተ ብቻ ሳይሆን ከሕግ መሠረታዊ መርህ በማፈንገጥ በሚፈጽማቸው ድርጊቶች አቤቱታዎች ይሰሙበታል፡፡ ምንም እንኳ ብዙኃኑን የፖሊስ አባላት ባይወክሉም እነዚህ ድርጊቶች የዘወትር እሮሮ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሳይቀር ሪፖርት የቀረበበት በማረሚያ ቤቶች ይፈጸማሉ የተባሉ ድብደባዎችና ማሰቃየቶች ነፃነትንና ገለልተኝኝነትን ገደል የሚከቱ ናቸው፡፡ ታራሚዎችን ከጠያቂ ጀምሮ እስከ ሕክምና መንፈግ ድረስ ያሉ ፀረ ሕገ መንግሥት ድርጊቶች የሰዎችን ብቻ ሳይሆን የፍትሕን ሥቃይ ያጋልጣሉ፡፡ ማዕከላዊ ምርመራ የሚባለው ተቋም ተዘግቶ ወደ ሙዚየምነት እንዲቀየር መወሰኑ እንዳለ ሆኖ፣ አስተሳሰብ በፍጥነት ካልተቀየረ ድርጊቶቹ ለመቆማቸው መተማመኛ ማግኘት አይቻልም፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው እንግዲህ የነፃነቱና የገለልተኝነቱ ጉዳይ አንድ መላ ይበጅለት የሚባለው፡፡ ሰብዓዊ መብት እየተጣሰ በሐሰት ስለነፃነትና ገለልተኝነት መነጋገር አይቻልም፡፡

ፍትሕ ዓይኗን የሸፈነችበት ጨርቅ የገለልተኝነቷ ተምሳሌት ነው እየተባለ ዓለም በሚግባበት በዚህ ዘመን፣ የዓለም ጭራ ሆኖ ፍትሕን እየደረመሱ አገር መገንባት አይቻልም፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በሕግ ዋስትና ተሰጥቶት፣ በተግባር ግን ፍትሕ እንደ ውኃ ሲጠማቸው ጦሱ ለአገር ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን እየተዳፈሩ ስለፍትሕ መደስኮር አይቻልም፡፡ ዳኞች ነፃነታቸውን በተጠያቂነት መርህ ካላጣጣሙት፣ ዓቃቢያነ ሕግ በነፃነት ሥራቸውን ካላከናወኑ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤት ሕጉን ብቻ መሠረት አድርገው በገለልተኝነት ካልሠሩ ስለፍትሕ መነጋገር ቀልድ ነው፡፡ ጉልበተኛው ፍትሕን በገንዘብ እየተጫወተበት አቅመ ቢሱ የሚጠቃ ከሆነ አገር ከቀውስ አዙሪት አትወጣም፡፡ ሕገወጥነት የበላይነቱን የሚይዘው በሕግ የበላይነት ላይ ከሆነ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት በሌለበት አገር አደጋ ውስጥ ትገባለች፡፡ የፍትሕ አካላት ነፃነትና ገለልተኝነት ከፍተኛ ትግል ያስፈልገዋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...