Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዱ ፈተና የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ነው!

ሐሙስ ሚያዝያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን በምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ሲዘከር የዘንድሮ መሪ ቃሉ ‹‹ሥልጣን ከልኩ እንዳያልፍ መጠበቅና በዓይነ ቁራኛ መቆጣጠር…›› የሚል አንድምታ አለው፡፡ ጋና ይኼንን ዓለም አቀፍ በዓል የምታስተናግደው የፕሬስ ነፃነትን ተቋማዊ ለማድረግ ባሳየችው ግስጋሴ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2017 የዓለም የፕሬስ ነፃነት መመዘኛ ከ180 አገሮች 20ኛ ደረጃ በማግኘት ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆኗ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መለስ ስንል ግን ለ25ኛ ጊዜ የፕሬስ ነፃነት ቀን ቢዘከርም፣ እንዲያው ‹ተከድኖ ይብሰል› ከማለት ወጣ ብሎ ብዙ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የፕሬስ ነፃነት የፖለቲካ መድረኮች ዥንጉርጉር ሆነው የተለያዩ ሐሳቦችን ከማፍራት፣ ከመፈለግና ከማብላላት ጋር እንዲተዋወቁ፣ ከራሳችን የተለየ ሐሳብ ለመስማት ቻይ የምንሆንበት፣ ሐሳባችን ሲተች ኩርፊያን፣ ሐሜትንና ጉልበትን መሣሪያ የማድረግ ልማድን ለማስቀረትና በነፃነት የመነጋገር ባህልን ለማዳበር ይረዳል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ በዚህ ወቅት ልዩ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ከሕዝብ ጋር በተነጋገሩባቸው መድረኮች ካደረጓቸው ንግግሮች ጋር በማዛመድ፣ መሠረታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ጠቃሚ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለ25ኛ ጊዜ የሚዘከረው የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚውለው jጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) 31ኛ የሥልጣን ቀናቸው ላይ መሆኑን እያስታወስን፣ በፓርላማ ከተሰየሙበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ንግግራቸው በመጀመር፣ ከዚያም በጅግጅጋ፣ በአምቦ፣ በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ (ሚሊኒየም አዳራሽ)፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በሐዋሳና በጂቡቲ ያደረጉዋቸው ንግግሮች ተስፋ ማለምለማቸውንና ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ጉጉት መፍጠራቸውን እንቃኛለን፡፡ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች በተለይ የንግግር ነፃነት አስፈላጊነትን አንግሠዋል፣ ለንግግር ነፃነት ልዩ ቦታ ሰጥተዋል፣ እኔ ብቻ ልክ ባይነትን አሟሸዋል፣ የእኔ ሐሳብ ብቻ ካላሸነፈ ሞቼ እገኛለሁና ከእኔ ሌላ አማራጭ የለም ባይነትን አስተንፍሰዋል፣ እኔ ከሌለሁ አገር ትጠፋለች የሚለውን ስሜት ጭምር አደብዝዘዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ፓርቲ መስመር የመመራት ጉዳይ ከተለያዩ ሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ የመርታት ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት እንዳለበት፣ ይኼንንም በሕዝብ ነፃ ድምፅ ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑን ለገዥውም፣ ለተቃዋሚ ፓርቲም፣ ለሕዝብም አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ጎልቶ የማይታወቀውን መንግሥት ሁሉንም እኩል የሚሰማ ጆሮ፣ ለሁሉም በእኩልነት የሚመልስ ቀና አንደበት፣ ሁሉንም በእኩል የሚያይ ዓይን ለመጎናፀፍ ጥረት እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡ ስለቃልና ስለተግባቦት ከፍተኛነት ለሕዝብ በሚገባ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ‹ወሬ ብቻ፣ ቃል ብቻ› ስለተባለው ሲያስረዱ ማለት ነው፡፡ እነዚህና ሌሎችም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ያዘሉዋቸው ቁም ነገሮች፣ የፕሬስ ወይም የሚዲያንና በሕገ መንግሥቱ የሠፈረውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አንቀጽ 29 ፋይዳን ያመላክታሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮችና የፕሬስ ነፃነትን በአንዳንድ ምሳሌዎች እንይ፡፡ በባህር ዳርም ሆነ በሐዋሳ ንግግሮቻቸው ስለ ‹‹መቆንጠጥ›› አውስተዋል፡፡ ‹‹የጎንደር ሕዝብ ስለተጣላህ እዚያ አትሂድ›› ሲባሉ፣ ‹‹የጎንደር ሕዝብ አይጣላኝም፣ ግፋ ቢል ቆንጥጦ ያስተምረኛል›› ማለታቸውን ተናግረዋል፡፡ በሐዋሳም፣ ‹‹…ስንባልግ በጨዋ ደንብ ቆንጠጥ እያደረጋችሁ ወደ መስመር ማስገባት አላባችሁ›› ብለዋል፡፡ አነጋገራቸው ጨዋነት ቢበዛበትም፣ ይህ የመቆንጠጥ ተግባር ከዘንድሮው የፕሬስ ቀን መሪ ቃል ጋር ይዛመዳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን በጎ ምኞት ተፈጻሚነት ያለው ሕግ ያድርጉት፡፡ ሚዲያ ሲባልጉ የሚቆነጥጥ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳይባልጉም ነቅቶ ዘብ በመቆም የሚጠብቅ መሣሪያ ይሆን ዘንድ መንግሥት ለሕግ የበላይነት ይገብር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሐዋሳ ከሕዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ መጀመርያ ላይ የሲዳማን ባህል ከልብ ባደነቁበት አንደበት፣ ለካ ኢትዮጵያዊያን መልዕክቶቻቸውን ድንጋይ ሳያነሱና ጥይት ሳይተኩሱ እየዘፈኑና እያስደሰቱ፣ ሠልፋቸው ሳይበላሽ ሐሳባቸውን ማስተላለፍ ይችላሉ ሲሉ ተሰምቷል፡፡ እንግዲህ ወደ ኋላ ሄደን ስናጠነጥን መንግሥት የዘጋው ይኼንን ሐሳብን በነፃ መግለጫ ባህላዊ መንገድ ጭምር ነው ለማለት እንገደዳለን፡፡ የፕሬስ ነፃነትን ማክበርና ተግባራዊ ማድረግ የዴሞክራሲን መሠረት ማንጠፍና በእሱ ላይ መገንባት ማለት ነው፡፡ ተቃውሞን የመግለጽ መብትና ጨዋነት በተግባር ተግባብተው የሚከናወኑበት፣ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እየተነጋገሩ፣ እየተደራደሩ፣ እየተስማሙ፣ ዴሞክራሲያዊ እልባት እየሰጡ ሳይዋከቡ የመኖር ፀጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ብርቅ የሆነው ፕሬስ ነፃ ባለመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ያለው ሁኔታ ያስተማረን ቤት የሚያጠፋውና አገር የሚያተረማምሰው እንደ ልብ መናገር ወይም መጻፍ፣ መተንፈሻና መመለሻ ያለው ተቃውሞና ቅሬታ አይደለም፡፡ ታምቆ የሚኖር ሐሳብ እንጂ፡፡

በተደጋጋሚ እንደሰማነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሙስና (ሌብነት) ያላቸውን ጥላቻ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ሌብነት የአገር ጠላት እንደሆነም አስጠንቅቀዋል፡፡ ይህ የእሳቸው ማስጠንቀቂያ ባዶ ስብከት ሆኖ እንዳይቀር በፕሬስ ነፃነትና በሕግ የበላይነት ውስጥ መኖር ያዋጣል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የዝርፊያ ማዕድ መሆኑ እንዲቀር፣ መንግሥታዊ ተቋማት የምዝበራ፣ የሌብነትና የቅሚያ ጎሬ መሆናቸው እንዲቆም፣ የዘራፊዎች ክንብንብ እንዲገፈፍና መሽለኩለኪያቸው እንዲጋለጥ፣ የሌብነት ዳስና ምሽግ እንዲፈርስ ከመንግሥት ቢሮክራሲ ውጪ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሚሆን ነፃ ሚዲያ መኖር አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የፀጥታና የደኅንነት፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዱ እንዲሆኑ መንግሥታቸው እንደሚሠራ በሚሊኒየም አዳራሽ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡ በሐዋሳው ንግግራቸውም ከሌሎች መካከል ዋና መሥሪያ ቤታቸውን ውጭ አገር ላደረጉ የሚዲያ ተቋማት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽንና የመንግሥት ሚዲያን ልዩነትም ‹‹ስማ! ላልሰማህ አሰማ!›› በማለት ያውጁ፡፡ የመንግሥት ሚዲያ በመንግሥት ይዞታነት እስከቀጠለ ድረስ፣ የአንቀጽ 29(5) ነፃነት ከስም ጌጥነትና ከክርክር በላይ ‹‹የብዝኃነት ድምፅ›› ዕውን እንዲሆን ያረጋግጡ፡፡ ሳይጠየቁ መቅረትን እዋጋለሁ ይበሉ፡፡

የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካላትና ተሿሚዎች ዋና ችግር ገለልተኛ አለመሆናቸው ነው፡፡ ለማንኛውም ፓርቲም ሆነ ለብሔርተኛ አስተሳሰብ የማይበገሩና የሁሉም የጋራ አለኝታ ተደርገው ለመታየት የበቁ አይደሉም፡፡ በተለይ ተሿሚዎች በገለልተኝነታቸው፣ በሙያ ብቃታቸውና ለተሰጣቸው አደራ በመታመን ጥንካሬያቸው የተመረጡ አይደሉም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ድኅረ 2010 ዓ.ም. የፕሬስ ነፃነት ቀን አጣዳፊ ሥራ መሆን ያለበት ይኼንን መዋቅራዊ ለውጥ ማስተዋወቅ ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነትን የሚታገሉ ሕጎች፣ የሌሎችም ማለትም የኢንቨስትመንት፣ የታክስና የጉምሩክ፣ እንዲሁም የማስታወቂያ ሕጎች ወዘተ አወጣጥ፣ ቅኝትና አፈጻጸም አቅጣጫ የተቀየሰው ‹‹ከእኔ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም›› ባይነት ላይ በመሆኑ፣ በዚህ በኩል ከፍተኛ ህዳሴ ማረጋገጥ ይጠበቃል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከየትኛውም ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን አካል (ፍርድ ቤቶች፣ ፓርላማ) የባሰ የተደራሽነት ችግር አለባቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ ካቢኔ፣ የአውሮፕላን ጉዞና የመሳሰሉት በታወቁ የግልጽነት መርሆዎች መሠረት ግልጽና ተደራሽ ማድረግ ይገባል፡፡ በሚዲያዎች መካከል የኖረውን የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ‹‹የእምነት ድጋፍ›› ያለውን አድልኦ ማውገዝና ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን በመጋፋት በፕሬሱ ላይ የሚደረገው ጫና አለፍ ሲልም ጭርገዳ ካሁን በኋላ ሊቆም ይገባል፡፡ በዚህ መስክ ሕጉ ተከብሮ ሁሉም ለሕግ የበላይነት እጁን ይስጥ፡፡ ያላግባብ ጣልቃ እየገቡ የሚፈተፍቱ እጆችም በሕግ ይባሉ፡፡ የመንግሥትንና የገዥውን ፓርቲ የራሳቸውን አስተሳሰብና ፍላጎት ከውይይትና ከንግግር በላይ የማድረግ አባዜ በማውገዝ፣ መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረግ ለፕሬስ ነፃነት ታላቅ ድል ነው፡፡ ፈተናው ቢከብድም ይኼንን ነፃነት ማረጋገጥ ፈፅሞ ጊዜ የማይሰጠው የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...