Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሕዝብና ቤት ቆጠራን ለማራዘም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ሊወስኑ ነው

የሕዝብና ቤት ቆጠራን ለማራዘም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ሊወስኑ ነው

ቀን:

– ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባዔ እንደሚመረጥ ታውቋል

ዘንድሮ መካሔድ የነበረበትን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለማራዘም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የጋራ ጉባዔ እንደሚያካሂዱ ታወቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሪፖርተር በላከው ጥቆማ፣ የአምስተኛው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ ልዩ የጋራ ስብሰባ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጋራ ጉባዔው አጀንዳም አራተኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ለማራዘም በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ እንደሚሆን ተገልጿል። በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተናጠል በሚያካሂደው ጉባዔ በሥራ ላይ በሚገኙት አፈ ጉባዔ አቶ ያለው አባተ ምትክ አዲስ አፈ ጉባዔ እንደሚመርጥ ተጠቁሟል።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሄዳል። በውጤቱም መሠረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስናል፤›› በማለት ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተመሳሳይ ዓመት ከተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ጋር በመገጣጠሙና ሁለቱንም ኃላፊነቶች በአንድ ዓመት ማካሄድ ከፍተኛ በጀት በመጠየቁ፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ ቆጠራው የሚካሄድበት የጊዜ ገደብ የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ በከፊል እንዲሻሻል መደረጉን የሪፖርተር መረጃዎች ያመለክታሉ።

በወቅቱ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች እንዲሁም የሁሉም ክልሎች ምክር ቤቶች በተናጥል ባካሄዱት ስብሰባ የቀረበላቸውን የውሳኔ ሐሳብ በማጽደቅ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚካሄድበት የጊዜ ወሰንን በተመለከተ የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) እንዲሻሻል አድርገዋል።

በወቅቱ በተወሰነው መሠረት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103(5) ይዘት ላይ ‹‹የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየአሥር ዓመቱ ይካሔዳል፤›› ከሚለው ቀጥሎ ‹‹ሆኖም ቆጠራውን ለማካሄድ ከአቅም በላይ ችግር ስለመኖሩ የተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ካረጋገጡ የቆጠራው ዘመን እንደ ሁኔታው ሊራዘም ይችላል፤›› የሚል ድንጋጌ በማሻሻያነት የአንቀጹ አካል እንዲሆን ተወስኗል።

በዚህም ምክንያት በ1997 ዓ.ም. መካሄድ የነበረበት ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. እንዲካሄድ ሁለቱ ምክር ቤቶች ወስነዋል፡፡

በወቅቱ የተደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሕግ መንግሥቱን የተከተለ አለመሆኑንና በዚህም የተነሳ ማሻሻያው ሕጋዊ ተቀባይነት አለው ብለው እንደማያምኑ የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሒጅራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ የተደረገው ማሻሻያ ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ሕገ መንግሥታዊ መስፈርት ተከትሎ አለመሆኑንና ተሻሻለ የተባለው አንቀጽ እስከዛሬ ድረስ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ አለመውጣቱ፣ በሕግ ቅቡል የሆነ ማሻሻያ ተደርጓል ለማለት እንደሚቸገሩ አቶ አብዱ ይከራከራሉ።

ክርክራቸውን ለማጠናከርም በ2008 ዓ.ም. ተሻሻሎ በድጋሚ የታወጀውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008ን ይጠቅሳሉ።

በዚህ ደንብ አንቀጽ 59 ላይ ‹‹የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚኖርበት ጊዜ እያንዳንዱ ማሻሻያ ቁጥር ተሰጥቶት በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተም ይኖርበታል፤›› የሚል ድንጋጌ መያዙን፤ በቀጣዩ ንዑስ አንቀጽ ሥር ደግሞ ‹‹እያንዳንዱ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ በሚታተመው ሕገ መንግሥት መጨረሻ ላይ ‹ማሻሻያ› የሚል ርዕስ ተሰጥቶት ይካተታል፤›› የሚል ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ከ13 ዓመት በፊት ተሻሻለ የተባለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽን በተመለከተ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሠረት የታተመ ሕገ መንግሥት ወይም ነጋሪት ጋዜጣ አለመኖሩን ይጠቅሳሉ።

በሕግ ተቀባይነት ያለው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጓል ብለው እንደማያምኑ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው፣ ለጊዜው ለግንዛቤ እንዲረዳ ማሻሻያውን በመቀበል ክርክራቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ተደረገ በተባለው ማሻሻያ መሠረት ቢሰላ እንኳን ቆጠራው መካሄድ የነበረበት ወይም በተባለው ማሻሻያ መሠረት መራዘም የነበረበት በ2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ምክንያቱም በ1999 ዓ.ም. የተደረገው ቆጠራ አሥረኛ ዓመት የሞላው 2009 ዓ.ም. ላይ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2008 ዓ.ም. በድጋሚ ያወጀው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 7 ሥር ስለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ሥልጣንና ተግባር ባስቀመጣቸው ድንጋጌዎች፣ የሕዝብ ቆጠራን ስለማራዘም የሚጠቅስ አንቀጽ አለመኖሩን ያስረዳሉ።

እርሳቸው የጠቀሱት የሁለቱ ምክር ቤቶችን የጋራ ሥልጣንና ተግባር የሚዘረዝረው ደንብ፣ የምክር ቤቶቹ የጋራ ተግባር ‹‹የሪፐብሊኩን ፕሬዚዳንት መምረጥ፣ ፕሬዚዳንቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የሚያደርጉትን ንግግር ማዳመጥ፣ በማንኛውም ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ድርጊቱን ክልሉ ማስቆም ሳይችል ሲቀር ሊወሰድ የሚገባውን ዕርምጃ መወሰን፣ ለፌዴራልና ለክልሎች ተለይተው ባልተሰጡ ታክስና ግብር የመጣል ሥልጣንን መወሰን፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 105(2) መሠረት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል፤›› መሆናቸውን ይዘረዝራል።

ስለሕዝብ ቆጠራ የሚደነግገው አንቀጽ በትክክልም ተሻሻሎ ከሆነ፣ ከአሥር ዓመት በኋላ በተደነገገው የፓርላማው የአሠራር ደንብ ላይ ይካተት እንደነበረ አቶ አብዱ ይጠቅሳሉ።

የቆጠራ ውጤት በአገር አቀፍ ደረጃ በምርጫ ጣቢያዎች አከላለል ላይ ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም፣ እሰካሁን ድረስ ያለው የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀት የተሠራው በ1987 ዓ.ም. የተደረገውን የሕዝብ ቆጠራ መሠረት በማድረግ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መረጃ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ወይም አገልግሎቶች ጠቃሚ ቢሆንም፣ በሕገ መንግሥቱ እንደተጠቀሰው የሕዝብ ቆጠራ ዋነኛ ፋይዳ የሕዝቦችን የሥልጣን ውክልና ማረጋገጥ እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶች ሥልጣን የሚያገኙበት መሠረት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

‹‹በመሆኑም መንግሥት በጀት የለኝም፣ ዘንድሮ ደክሞኛል፣›› የሚሉ ምክንያቶችን እየዘረዘረ የሕዝብ ቆጠራ የሚካሄድበትን ጊዜ እንዳያራዝም የማያወላዳ የሕግ ማሰሪያ ሊበጅለት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...