Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዲህ ነው እንጂ መታደስ!

ሰላም! ሰላም! የቁልምጫ ስሜ ደሌክስ! የሥራ ስሜ ደላላው፡፡ የመዝገብ ስሜ አምበርብር ምንተስኖት ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ደላላዎች መካከል አንቱ የምባል ነኝ፡፡ መቼም ጠላት ይህን ሲያነብ፣ ‹‹አንተ?›› ማለቱ አይቀርም፡፡ እኔን ግን አንቱ በሉኝ፡፡ ይህንን ስል ይህን ማዕረግ ያጎናፀፈኝ ሥራዬ እንደሆነ ልብ በሉልኝ እንጂ፣ ዕድሜ ከተጠየቅኩ ገና ሮጬ ያልጠገብኩ አንድ ፍሬ ሰውዬ ነኝ፡፡ የዕድሜ ጉዳይ ሲነሳ ሁሌም ሆድ የሚብሳቸው ባሻዬ ናቸው፡፡ ያው ወደ ማገባደጃው ተጠጋግተዋል፡፡ ሰው መቼም መኖር በቃኝ አይልም፡፡ አንዳንዱ ሰው ምድር ላይ ዘለዓለም ቢኖር አይቆጨውም፡፡

ወዳጆቼ ይህንን ስል በምንም መንገድ ከባሻዬ ጋር እንዳታገናኙብኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በሚስጥር ከጠየቃችሁኝ ግን በሻዬም ቢሆኑ ለዘለዓለም ቢኖሩ የሚቆጫቸው አይመስለኝም፡፡ ዳሩ ግን የባሻዬ ልጅ እንደሚለው ብዙ ዘመን እንደ ማቱሳላ ኖሮ ምንም ሳይሠራ ኖረ ሞተ መባል ሳይሆን፣ በኖርንባት ጥቂት ዘመን ውስጥ ትውልድን የሚሻገር ሥራ ሠርተው፣ በወጣትነት አንቱ ተብለው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችንና እንደ እኔ (እኔ ስል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተጠጋጋሁ እንደሆነ እንዳታስቡ) ዳሩ ግን በሙያዬ ለማለት ፈልጌ ነው፡፡

እናማ 900 ዓመታት ምድር ላይ ተመላልሰው ምንም ነገር ሳይሠሩ በብላሽ ወደ መቃብር ከመውረድ ፈጣሪ ይጠብቀን፡፡ ባይሆን በተሰጠችን እንደ ጤዛ ታይታ በምትጠፋዋ ብኩን ዘመን ላይ ፈጽሞ የማይጠፋ ታላቅን ነገር ሠርተን እንድናልፍ እመኛለሁ፡፡ ሌላም ምርቃት ባሻዬ መርቀውኝ ያውቃሉ፡፡ ‹‹በሽምግልና ወራት እንደ ሕፃን ከመታየት ይሰውርህ፤›› ነበር ያሉኝ፡፡ የባሻዬ ውስጠ ወይራ ምክር መቼ ይጠፋኝና? ሰው በትንሽነቱ ታላቅ ነገር እያከናወነ አንቱታን ሲያከማች አንተ ደግሞ በሽምግልናህ ወራት የተሻለ ነገር መሰብሰብ ጠበቅብኃል የሚል አንድምታ ያዘለ ነው፡፡

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንቱ ሊባሉ ይገባቸዋል፣ የዓለምም ሆነ የአገር ውስጥ ሚዲያ ብዙ አልዘመረላቸውም፤›› በማለት ሲማረር ነበር፡፡ እሳቸው በነገራችን ላይ አንቱ ነው የሚላቸው፣ ‹‹ድርጊታቸው አንቱታ ያሰጣቸዋል፤›› ባይ ነው፡፡ ‹‹መቼም መንበረ ሥልጣናቸውን አልለቅም፣ ሞቼ እገኛለሁ፣ ለኢትየጵያ ከእኔ ውጪ መፍትሔ ላሳር ብለው ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባት እምዬ ኢትዮጵያን ምን ጉድጓድ ልትገባ እንደምትችል ትንሽ መለስ ብለህ አሰላስለው . . . ›› ብሎ ነበር የቤት ሥራ የሰጠኝ፡፡ ‹‹ሥልጣናቸውን አልለቅም ብለው ቢሆን ኖሩ እነ ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጄዚራ፣ ወዘተ በፊት ገጾቻቸው ላይ የሚያቀርቡት ዋና ጮማ ዜናቸው ሆኖ በሰነበተላቸው ነበር፡፡ እውነቱን ስናወራ፣ ወደኋላ ተመልሰን ታሪክን ብናገላብጥ፣ እንደዚህ ያለ የሥልጣን ሽግግር ተደርጎ ያውቃል ለማለት እቸገራለሁ፤›› ነበር ያለኝ፡፡

‹‹ይህም ሳያንስ . . . ›› አለ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ . . . አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም ቢሆኑ ከተመረጡበት ማግሥት ጀምረው የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ወዲህ ወዲያ እየኳተኑ ይገኛሉ፤›› በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥራ አሞካሹ፡፡ አንድ ደላላ የቀለደው ግን ትንሽ አስፈግጎኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ባህላዊ ልብስ አምረውና አሸብርቀው ሲመለከታቸው፣ ቀጣይ ጉዞዋቸው ያው ወደ ደቡብ እንደሚሆን ጠርጥሮ፣ ‹‹ሐመር ሄደው እስከማይ ቸኩያለሁ . . . ›› አለ፡፡ በጎንደር ያሳዩትን ሕዝቡን ለማክበር ልብሱን የመልበሳቸውን ጅማሮ በሐመር እንዲቀጥሉት በመመኘት ነው፡፡ ሐመሮችን መምሰል ያቅታቸዋል ብሎ ይሆን? እኔን ግን አልመሰለኝም፡፡

ወይ ደላላ! ሌላ ጊዜ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወዲያ ወዲህ ማለት ያልተዋጠለት አንድ ሰው፣ ‹‹እንዲያው ይኼ ዙረት አልበዛም? እንዲያው ምን አለ አረፍ ብለው ተቀምጠው የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ቢሞክሩ?›› በማለት ላቀረበው ጥያቄ፣ ሌላው ሲመልስ፣ ‹‹በቃ አንተ ‹የፎር ፕሌይ› ጥቅም አልገባህም? ማለት ዝም ብለህ እንዳገኘህ ድርግም ማድረግ ለምደህ አሁንም እሳቸው እየሠሩ ያለው ሊገለጥልህ አይችልም፡፡ ጊዜ ደጉ ጊዜ ዳኛው ሁሉንም ያሳየናል፤›› በማለት መለሰለት፡፡

‹‹ገና ከአሁኑ አንቱታውን እያከማቹ ያሉ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በቀጣይ ዓመታት በእያንዳንዳችን ልብ እያሠረፁ የጠፉትን ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት አግዝፈው፣ ሁሉም ሰው አካፋና ዶማውን አንስቶ ኢትዮጵያውን ለማልማት የሚነሳበትን አዲስ ዘመን እንደሚያበስሩን አንጠራጠርም፤›› በማለት ሌላው ወዳጄ ተናገረ፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ዋናው አዕምሮአችን ውስጥ ያለው ጥቀርሻ ከተወገደልን ቀስ በቀስ ሌላውን የማንቀይርበትና የኢትዮጵያን ትንሳዔ የማናበስርበት ምንም ዓይነት ተግዳሮት አይኖርብንም፤›› በማለት ሲያብራራ ነበር፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ለሥራ ብሎ ሆ ብሎ ከመነሳት በፊት በመጀመርያ ሁሉም ነገር ከሐሳብ መጀመር አለበት፡፡ አዕምሮ ውስጥ የተሰገሰጉ አልባሌ ነገሮችን በመሸኘት፣ በአዲስ ኢትዮጵያዊ ሐሳብ መተካት ያስፈልጋል፤›› በማለት አከለ፡፡ አዎን ከውስጥ ወደ ውጭ የሆነን ልማት ማንም ሊያስቆመው አይችልም፡፡ ምክንያቱም በአዕምሮ መታደስ፣ በልማት ውስጥ አገሬው እንዲሳተፍ ማንም ቀስቃሽና ሞጋች አያስፈልገውም፡፡ ምክንያቱም ግዴታ መር የሆነ ሥራ ውስጥ ሳይሆን፣ ፍላጎትና ፈቃድ መር የሆነ ንቅናቄ ውስጥ፣ አገር ሁሉ ሆ ብሎ ስለሚገባ፡፡ ለዚህ ነበር የባሻዬ ልጅ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በተለያዩ ክልሎች ያደረጉዋቸውን ጉብኝቶች ያደነቀው፡፡ ሕዝቡ አገሩን የራሱ ካደረጋት ማን ይሆን አገርን ከሕዝብ እጅ ፈልቅቆ ሊወስድ የሚችለው? መልሱ ማንም ነው፡፡

‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞና ጉብኝት አሁንም እንዲቀጥል እንፈልጋለን፤›› ብላ ያሳቀችን ማንጠግቦሽ ናት፡፡ ውዴ ማንጠግቦሽ ካለች ደግሞ ያው እንደምታውቁት ነው፡፡ እየዞሩ የሚሰጡት መልስ እጅግ አስገርሟታል፡፡ እንዲያውም ሁለተኛ ዙር ጉዞ ወደ ጎንደር፣ ወደ አምቦ፣ ሁለተኛ ዙር ጉዞ ወደ ሐዋሳ ቢያደርጉ ሁሉ ደስታዬ ነው ስትለኝ ሳቅኩላት፡፡ ማንጠግቦሽም ብትሆን በመጀመርያ በየሰው አዕምሮ ውስጥ የተሰገሰጉ የማይጠቅሙ ነገሮችን ለማርከስ የሄዱበትን መንገድ አክብራለች፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ባልታደሰ አሮጌ አስተሳሰብ የታደሰች አዲስ ኢትዮጵያን መፍጠር አይቻልም፤›› በማለት የአዕምሮ መታደስን አስፈላጊነት አበክሮ ይናገራል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለራሳችን ለአኅጉራችን የምንበቃ መሆናችንን የምናሳይበት ዘመን እነሆ በደጅ ነው፡፡ ‹‹ከአንድ ሁለት ይሻላል፣ በሦስት የተገመደ ደግሞ ፈጥኖ አይበጠስም፤›› እንደሚባለው እኛ ደግሞ መቶ ሚሊዮን ሆነን ስንገመድ ማንም እሳት ማንም ጀግና ሊበጣጥሰን የማይችል፣ የፈለግነውን የምናስርና የምንፈታ ታላቅ ሕዝብ እንሆናለን ማለት ነው፡፡

እዚሁ ሠርተን መለወጥ አያቅተንም፡፡ የፈጀውን ይፍጅ እያሉ በአገራቸው ለመሠራት የቆረጡ ሰዎችም እንደ አሸን እየፈሉ ይገኛሉ፡፡ አሁን አሁን እኔ ደላላው አምበርብር ምንተስኖት ከተውኳቸው ሥራዎች መካከል፣ ዓረብ አገር ለሥራ የቤት አገልጋዮችን መላክ እንደ ድሮ መስያቸው ‹ደሌክስ እባክህን ላከን . . . › እያሉ በእጅ መንሻቸው ሊያባብሉኝ ይሞክራሉ፡፡ እኔ ግን ከዚህ በኋላ እህቶቼን ዓረብ አገር በመላክ የማገኘው ገንዘብ እርም ይሁንብኝ ብያለሁ፡፡ እንዲያውም የሄዱት ሁሉ እንዲመለሱ ጥረት ከሚያደርጉ በጎ አድራጊዎች ጋር በጎ ፈቃደኛ ሆኜ ማገልገል ለመጀመር ወስኛለሁ፡፡ አሁንም ካልሄድን እያሉ ለሚነዘንዙኝ ደግሞ መሬት ጠብ የማይል በልምድ የዳበረ ምክሬን አደርሳቸዋለሁ፡፡

ይኼኔ ስንቶች ሐሳባቸውን ቀይረው ግማሾቹ የጀበና ቡና ጀምረው፣ ግማሾቹ ትምህርት ቤት መሄድ ጀምረው ስመለከታቸው፣ ይህች አርጅታ ምንም ነገር ከዚህ በኋላ አትፈጥርም የተባለችው የእኔዋ አዕምሮ በመታደስ መንገድ ውስጥ አልፋ፣ በበርካቶችን እየጠቀመች አንዳለች ይገለጥልኛል፡፡ ይህች ጭንቅላትማ ትንሽ ማበረታቻ ማግኘት አለባት በማለት እንዲያው ለመክበር ሳይሆን፣ በጎ ተፅዕኖ እየፈጠረች ያለችውን አዕምሮዬን ለማነቃቃት ያህል አንድ ሁለት ቢራ ለማለት ወደ ተለመደችው ግሮሰሪ ጎራ አልኩ፡፡ እዚያ ስደርስ ከቧልት ይልቅ ቁም ነገር፣ ከጭቅጭቅ ይልቅ የሰከነ ውይይት፣ ከሐሜት ይልቅ ምክር፣ . . . ደርቶ ሳገኝ እንዲህ ነው እንጂ መታደስ አልኩ! መልካም ሰንበት!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት