Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎችን ፈተዋል የተባለ ዳኛ በኮማንድ ፖስቱ ለአራት ቀናት ታሰሩ

በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎችን ፈተዋል የተባለ ዳኛ በኮማንድ ፖስቱ ለአራት ቀናት ታሰሩ

ቀን:

በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎችን ፈተዋል የተባሉ ዳኛ በኮማንድ ፖስቱ ለአራት ቀናት ታስረው ተፈቱ፡፡

ከዳኛው በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ይዘው ያቀረቡ አንድ ዓቃቤ ሕግም፣ ለአንድ ቀን ከታሰሩ በኋላ መፈታታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን በደኖ ወረዳ የመጀመርያ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት አቶ አብነት ታደሰ ተጠርጣሪዎች ናቸው የተባሉ ሦስት ግለሰቦችን በነፃ በማሰናበታቸው፣ ዓርብ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በወረዳው የኮማንድ ፖስት ዕዝ እንዲቀርቡ ተጠርተው በዚያው መታሰራቸውን ዳኛው አቶ አብነት ታደሰ ለሪፖርተር በስልክ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እርሳቸው ለሚመሩት ችሎት ተጠርጣሪዎቹን ግለሰቦች ይዘው የቀረቡት የወረዳው ዓቃቤ ሕግ አቶ ተርፋ ደሴም አብረዋቸው ታስረው የነበሩ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕጉ በማግሥቱ ቅዳሜ መለቀቃቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተጠርጠሪዎቹ እንዲለቀቁ ውሳኔ ያስተላለፉት ስለተጠረጠሩበት ወንጀል የሚያብራራም ሆነ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ኮማንድ ፖስቱ ይሁን መደበኛ ፖሊስ ማረጋገጥ ባለመቻሉ፣ ተጠርጣሪ የተባሉትን ግለሰቦች ቃል አድምጠው በነፃ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ማሳለፋቸውን አስረድተዋል፡፡

ዓርብ ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በወረዳው የኮማንድ ፖስት ዕዝ ጽሕፈት ቤት እንደሚፈለጉ ጥሪ እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ አብነት፣ ‹‹የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ውክልና ሰጥተውኝ ለፕሬዚዳንትነትም እያገለገልኩ በመሆኑ፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ፈልገውኝ ይሆናል ብዬ ብሄድም ጉዳዩ ተጠርጣሪዎቹን በተመለከተ ሆኖ በቁጥጥር ሥር አውለውኛል፤›› ብለዋል፡፡

አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ይሆናል ብለው በመገመታቸው እንጂ፣ በዳኝነት ኃላፊነታቸው በሰጡት ውሳኔ ያለመከሰስ መብት ያላቸው ስለሆኑ ላይሄዱ ይችሉ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ከሄዱ በኋላ ግን ይህንን የሕግ ከለላቸውን ሊረዳ የሚችል የፀጥታ ኃላፊ እንዳላገኙ ገልጸዋል፡፡

ሰኞ ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምርያ ይዘዋቸው እንደሄዱ፣ በወቅቱም የመምርያው ፖሊስ አዛዥ ደንግጠው፣ ‹‹ዳኛ እንዴት ሊታሰር ቻለ?›› ብለው እንደጠየቁ አቶ አብነት ተናግረዋል፡፡

የፖሊስ መምርያ ኃላፊውም ጉዳዩ የጀመረው ይጨርሰው ብለው እጃቸውን በማውጣታቸው፣ ተመልሰው ወደ ወረዳው የኮማንድ ፖስት ዕዝ ጽሕፈት ቤት እንደተወሰዱ ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ ጽሕፈት ቤትም አንድ የመከላከያ ሠራዊት ሻምበል፣ የወረዳው ፖሊስ አዛዥና የወረዳው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊ እንደጠበቁዋቸው ገልጸዋል፡፡

በኋላም የተፈጠረውን ነገር ተረጋግተው ለፀጥታ ኃላፊዎች እንዳስረዷቸው የሚናገሩት አቶ አብነት፣ ‹‹በመጨረሻም ይቅርታ ጠይቀውኝ ሰኞ ከቀትር በኋላ ተፈትቻለሁ፤›› ሲሉ የገጠማቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የወረዳውን ፖሊስ፣ እንዲሁም የኮማንድ ፖስቱ ዕዝ ተጠሪን ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸምን የሚከታተለው መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ ስለጉዳዩ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ መረጃ እንደሌላቸው የገለጹ ቢሆንም፣ በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ ገነት ታደሰ የሚመራ ቡድን በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኝ በመሆኑ የተፈጸመውን ድርጊት እንደሚያጣራ ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...