Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ ጠንክሮ መገኘት የግድ ይላል!

  በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቁ ችግር የመወዳደሪያ ሜዳው እንደነበር ብዙ ተብሎለታል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳር በመባል የሚታወቀው የመወዳደሪያ ሜዳ አባጣና ጎርባጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ፈታኝ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ ያለፉት 27 ዓመታት ውጣ ውረዶች ብዙ የሚናገሩት አላቸው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ለመገዳደር ብርቱ ጥረት ያደረጉ ፓርቲዎች ያሉትን ያህል፣ ዓላማቸውና መድረሻ ግባቸው የማይታወቅ አጃቢዎችም ሞልተዋል፡፡ በግለሰቦች ቁጥጥር ሥር ውለው ፋይዳ ሳይኖራቸው ዕድሜ ያስቆጠሩም እንደዚሁ፡፡ ከሕገወጥ ግንባታ የማይተናነሱትን ትተን በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረጉት ላይ ስናተኩር፣ የነበሩ ጫናዎችንና መከራዎችን ተቀብለው በፅናት የቀጠሉትንና ከመንገድ የቀሩትን ስናስብ በርካታ አሳዛኝ ትውስታዎች ይገጥሙናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውስጣዊ ችግሮቻቸው ጀምሮ በገዥው ፓርቲ የደረሰባቸው በደል፣ ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ምን ያህል እንደ ጎዳው ግልጽ ነው፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲን የሚያህል ነገር መምራት ከባድ ነው፡፡ አስቸጋሪና ፈታኝ ትግል ተቋቁሞ በፅናት መገኘት ያስመሠግናል፡፡ ለዓላማ መቆም የሚቻለው ፅናት ሲኖር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ትግሉ አሰልቺና ከባድ ቢሆንም ጠንክሮ መገኘት መቻል በራሱ እንደ ድል ሊቆጠር ይገባል፡፡ ድሉ አድማሱን እያሰፋ ሲሄድ ደግሞ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ ትልቅ ዕድል ይሰጣል፡፡ ዋናው ጉዳይ ተስፋ አለመቁረጥ ነው፡፡

  ሰሞኑን ባህር ዳር የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሐሳብ ያለው ተደራጅቶ አማራጭ ሆኖ ይቅረብ…›› በማለት ያቀረቡት ሐሳብ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ‹‹…ከተሸነፍን በደስታ እናስረክባለን…›› ማለታቸውም እንዲሁ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የጎደለው ይኼ ዓይነቱ ቀና ሐሳብ ነው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ የፈለገውን በነፃነት መርጦ ለሥልጣን የሚያበቃበት ፍትሐዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዕውን እንዲሆን፣ እንዲህ ዓይነቱን በአደባባይ በግልጽ የተነገረ እውነታ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች በዚህች ታሪካዊት አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ጠንክረው መገኘት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ (ተፎካካሪ) ፓርቲዎች የአኩራፊዎች መሰባሰቢያ ብቻ ሳይሆኑ፣ የአገር ፍቅርና የዓላማ ፅናት ያላቸው ዴሞክራት መሆናቸውን በተግባር ማሳየት የሚችሉት፣ መራጩ ሕዝብ ዘንድ ሊያደርሱት የሚችሉት ጥራት ያለው ሐሳብ አፍላቂ ሲሆኑ ነው፡፡ ‹‹ሜዳውም ያው ፈረሱም ያው›› ማለት የሚቻለው እንደተባለው የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲከፈት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ እንዲከፈትና ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ዋስትና እንዲያገኝ የራስንም ልብ መክፈት ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይወቀስ የነበረው ምኅዳሩን በማጥበቡ ወይም በማዳፈኑ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ከቁዘማ ውጡ…›› ሲሉ፣ ትልቅ ሆኖ መገኘትና መጠንከር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጥንካሬ የሚመጣው ግን ትልቅ ሐሳብ ወይም አጀንዳ ይዞ ለመቅረብ የሚያስችል ቁመና ላይ ለመገኘት በሚደረግ የራስ ትግል ነው፡፡ ያኔ ብርቱ አማራጭ መሆን ይቻላል፡፡

  የፖለቲካ ትግል እንደ ጤና ቡድን ወይም እንደ ማስ ስፖርት በትርፍ ጊዜ የሚሠራ ሳይሆን፣ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የሚብራራ ሁለገብ ዝግጅት የሚያስፈልገው ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያለ አባላትና ደጋፊዎችን ከመያዝ በተጨማሪ፣ በሐሳብና በማቴሪያል የሚደግፉ ወገኖችን ጭምር ማሳመን የሚችሉ አንደበተ ርቱኦችን ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመደራጀትና ሐሳብን ለመግለጽ እንቅፋት የሆኑ ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ በሕግ ዋስትና የተሰጣቸው መብቶችና ነፃነቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ፣ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩልነታቸው እንዲረጋገጥና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ በፍትሐዊነት እንዲከናወን ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ግንባር ቀደም መሆን በቸልታ ሊታለፍ አይገባም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን ተረክበው አገር ለማረጋጋትና የሕዝብ አስተያየቶችን ለመስማት በየቦታው ሲዞሩ፣ በዚያው ልክ ራስን ከለውጡ እኩል ማንቀሳቀስ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ሥራ መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተከፍቶ ለሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መደላድል ማመቻቸት የሚቻለው ዳር ቆሞ በመታዘብ፣ ወይም ከንግግሮች መሀል ቃላት እየሰነጠቁ በመተቸት አይደለም፡፡ ሕዝብ መልካም አንደበትና ተግባር እንደሚፈልግ በግልጽ እየተሰማ ነውና፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ተግባር የሚጀምረው ከሐሳብ ስለሆነ፣ ጠንካራ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ ጥራት ያለው ሐሳብ ይዞ መነሳት የግድ ነው፡፡ ከተግባር በፊት ሐሳብ ይቀድማልና፡፡

  ሥልጡን ፖለቲካ የሚያምነው በሰጥቶ መቀበል መርህ እንደ መሆኑ መጠን፣ ይኼንን መርህ ማሳካት የሚቻለው ለውይይትና ለድርድር ዝግጁ መሆን ሲቻልም ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ መነጋገርና መደማመጥ በተሳነው የአገሪቱ የ50 ዓመታት የፖለቲካ ታሪክ፣ ትልቁን ሥፍራ የያዘው ቂም በቀልና ጥላቻ ነው፡፡ ይኼንን ዓይነቱን አሳዛኝ ምዕራፍ መሻገር የሚቻለው ደግሞ በቀናነት ነገን አሸጋግሮ በማየት ነው፡፡ ጠባሳዎችን እያከኩ ቁስል በማመርቀዝ ለውጥ አይገኝም፡፡ ከእልህና ከግትርነት በመላቀቅ በሆደ ሰፊነት ራስን ማዘጋጀት ይገባል፡፡ አገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ስሜት ተነሳስተው ወደፊት መራመድ ሲቻል፣ ከሰላማዊ ፖለቲካ አፈንግጠው ወደ ሌላ አማራጭ የገቡም ሐሳባቸውን የማይቀይሩበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ሁሉንም ወገን አሳታፊ የሚሆን ድርድር ለማምጣት የሚቻለው በትግሥትና በጥበብ ነው፡፡ መነጋገሩና መደማመጡ እየሰፋ ሲሄድም አሁን የሚታየው ቅራኔ ረግቦ፣ ለጋራ አገር ሲባል የማይደረግ ነገር አይኖርም፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው ግን በእልህና በፉከራ ሳይሆን፣ ብልኃት በታከለበት አቀራረብና በብዙ የሐሳብ ልውውጦች ነው፡፡ ድርድር ማድረግም ሆነ በሰላማዊ ፖለቲካ ውስጥ መፎካከር የሚቻለው አንዱ እያስገደደ፣ ሌላው እየተገደደ ነው ብሎ ለመንቀሳቀስ መሞከር ውጤቱ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ፖለቲካ የብልኃተኞች መጫወቻ መሆን ሲገባው የግትሮች መሻኮቻ ከሆነ ውጤቱ የዜሮ ድምር ይሆናል፡፡ በሳል መሆን ከስሜታዊነትና ከግብታዊነት ይታደጋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት እንዲያስተናግድ ከተፈለገ ከጀብደኝነት መላቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ለመነጋገርም ሆነ ለመደማመጥ የሚቻለው ከዚህ ዓይነቱ አባዜ ውስጥ መውጣት ሲቻል ነው፡፡ የዴሞክራሲ ንድፈ ሐሳብን እያነበነቡ በድል አጥቢያ አርበኝነት ስሜት ግብዝ መሆን ሞኝነት ነው፡፡ የሐሳብ የበላይነት ይዞ ማሸነፍ የሚቻለው ከጀብደኝነት ስካር ውስጥ በመውጣት ነው፡፡ ቂምና ጥላቻን ተሸክሞ መዞር አኩራፊነትን ያባብሳል እንጂ ዴሞክራት አያደርግም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ዙሪያ ገብ ችግር ማወቅ በራሱ ለመፍትሔ ቅርብ ነው፡፡ የመፍትሔ መንገዱ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው አዙሪት ውስጥ ከመውጣት ይጀምራል፡፡ ለዚህ ሲባል ራስን በሚገባ መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተፎካካሪ እንዲሆን ሲፈለግ፣ ተገዳዳሪዎቹም ከዚያ ባልተናነሰ ለፉክክር የሚዘጋጁበት ምኅዳር እንዲፈጠር እንቅልፍ አጥተው መሥራት አለባቸው፡፡ አሁን እንደሚታዩት ደካማና ጎስቋላ ሆነው ሳይሆን ተጠናክረው መውጣት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከርዕዮተ ዓለማቸው ጀምሮ እስከ አጀንዳቸው ድረስ ለጥራት ትልቅ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል፡፡ የሌላውን ድክመት ብቻ እያነፈነፉ መዝለቅ አይቻልም፡፡ ጠንካራ አማራጭ ለመሆን የሚያስችለቸውን ብቃትና ታታሪነት ሊጎናፀፉ ይገባል፡፡

  መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናት አገሩን ማዕከል በማድረግ ለውጥ እንደሚፈልግ በግልጽ እየተናገረ ነው፡፡ የዚህ ለውጥ ታዛቢ ከመሆን ይልቅ በርትቶና ጠንክሮ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ልብና ቀልብ መግዛት የሚቻለው ደግሞ በስሜት ኮርኳሪ ንግግሮች ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ሕዝብ መልካም አንደበት እንደሚፈልገው ሁሉ፣ ከንግግር በኋላ ጠብ የሚል ነገር ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝብ ውስጥ ሰርፆ መግባት የግድ ይላል፡፡ አሉ የተባሉ ችግሮችን እየዘረዘሩ ማሰልቸት ሳይሆን ለችግሮቹ መፍትሔ ሐሳቦች ይዞ መቅረብ ተገቢ ነው፡፡ የትናንት በደሎችን እያላዘኑ የነገን ተስፋ ማመላከት አለመቻል ጥቅም የለውም፡፡ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ትውልድ የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት የሆኑ ፖለቲከኞችን ነው የሚፈልገው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ፖለቲከኞች ደግሞ ከስሜት ይልቅ ምክንያትን ያስቀድማሉ፡፡ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ወደ ብርሃን ያመለክታሉ፡፡ የነጠሩ ሐሳቦችን እያቀረቡ ሕዝብን ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ለዓመታት ያንቀላፋው ፖለቲካ መታደስ የሚችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አማራጭ ይዞ መቅረብ የሚቻለው ተጠናክሮ በመውጣት ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...