Thursday, April 18, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሁለት ዓመታት በፊት መስከረም 24 ቀን 2008 ዓ.ም. የፀደቀው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ አዋጅ መግቢያ፣ የልማታዊ መንግሥት መርሆዎችን የተከተለ ጥብቅ ትስስርና ቅንጅታዊ አሠራርን መፍጠር፣ ጠንካራና ውጤታማ የአስፈጻሚ ተቋማት መዋቅርን መፍጠር፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተገቢ ሁኔታ መጠቀም ለሚያስችል አደረጃጀት ትኩረት መስጠትና በውድድር ውስጥ ተፎካካሪ መሆንን ታሳቢ ያደረገ መዋቅር መመሥረት በማስፈለጉ አዋጁ መዘጋጀቱን ይገልጻል፡፡

በዚህ መሠረት በወቅቱ የመዋቅር ማሻሻያ ከተደረገበት የመንግሥት ተቋም ዋነኛው የግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሁሉንም የግብርና ዘርፎች በሰብል ምርት፣ በእንስሳት ልማት፣ በአፈር የተፈጥሮ ይዘት ጥበቃና በመሳሰሉት ሰፋፊ ተግባሮች በአንድ ተቋም ውስጥ ያጨቀ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም ተገቢውን ትስስር በግብርናውና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መፍጠር አለመቻሉ በጥናት መረጋገጡን፣ በወቅቱ አዲስ የመንግሥት መዋቅር ያቀረቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለፓርላማው አስረድተው ነበር፡፡

‹‹ይህንን ውስብስብ ሥራ በአንድ ተቋም ውስጥ ከማጨቅ ግብርና ሚኒስቴርን ለሁለት እንዲከፈል ተደርጓል፤›› ሲሉ በወቅቱ ለፓርላማው አስተዋውቀዋል፡፡ እነዚህም የእርሻና የተጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሆነው በአዋጅ እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡

አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት በገጠማት ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የተገኙት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በ2008 ዓ.ም. በፀደቀው የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር በሚወስነው አዋጅ ላይ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ይዘው ቀርበዋል፡፡

እሳቸው ይዘው የቀረቡት ማሻሻያም ትኩረት ያደረገው በዚሁ የግብርና ዘርፍ ተቋም ላይ ነው፡፡ ‹‹የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴር በአብዛኛው ተመሳሳይነት ያላቸውና በቅንጅት በአንድ ሚኒስቴር ሥር ሊዋቀሩ የሚችሉ ናቸው፤›› በማለት የማሻሻያ አዋጁ አባሪ ማብራሪያ ሰነድ ያስረዳል፡፡

ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለየብቻቸው ሲንቀሳቀሱ የሰው ሀብታቸውና የፋይናንስ አቅርቦታቸው ባለመቀናጀቱ ምክንያት በውጤታማነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ የሚገልጸው አባሪ ሰነዱ፣ ተመሳሳይና ተመጋጋቢ ተግባርና ኃላፊነት ያላቸው ተቋማት በመሆናቸው መሥሪያ ቤቶቹን በማዋሀድ አንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በማድረግ ቅልጥፍናን፣ ውጤታማነትንና የሥራ አፈጻጸማቸውን ማሳደግ እንደሚቻል የታመነበት መሆኑን ይገልጻል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፓርላማው ከተሰየሙ በኋላ ባደረጉት የመጀመርያ የሥራ ውሎ ይዘውት ከቀረቡት የመዋቅር ማሻሻያ ጋር በተገናኘ፣ በመጀመርያው ዕለት የመጀመርያ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡

በርከት ያሉ የምክር ቤቱ አባላት ሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከሁለት ዓመታት በፊት እንዲቋቋሙ ሲወሰን፣ አንዱ በአንዱ እንዳይጨፈለቅና አገሪቷ ያሏትን የተጥሮ ሀብቶች የበለጠ በመጠቀም ከፍተኛ ትስስር ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጋር ለመፍጠር ዕቅድ እንደነበረው፣ አሁን ግን ተመልሰው ይቀላቀሉና አንዱ አንዱን ይደፍጥጠው እንደ ማለት መሆኑን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን፣ እንዲሁም ለተቃውሞ አስተያየታቸው ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ከመደጋገፍ ይልቅ የሀብት ሽሚያ ውስጥ መግባታቸው ከሆነ ችግሩ፣ ይህንን ችግር መቅረፍ የሚቻልበትን ሥልት ማበጀት ተገቢ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለቀረቡላቸው ተመሳሳይ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ሁለቱ ተቋማት እንዲዋሀዱ መንግሥት ከውሳኔ ላይ የደረሰው በጥናት ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መዋሀዳቸው አንዱ አንዱን የሚጨፈልቅበት ሁኔታ እንደማይፈጥር፣ ሁለቱም በአንድ ተቋም ውስጥ የተለያዩ ዘርፎች ሆነው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት የፋይናንስና የሰው ኃይል ሽሚያ ውስጥ በመግባታቸው እስካሁን ማደራጀት የቻሉት 56 በመቶ የሚሆን የሰው ኃይል በመሆኑ፣ ለአንድ ዓላማ መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የምክር ቤቱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጣቸው ምላሽ የተደሰቱ አይመስሉም፡፡ በዙህ ሁኔታ ውስጥ ወደ ድምፅ መስጠት የተገባ ሲሆን ማሻሻያ አዋጁ በሦስት ተቃውሞና በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

አዲሱ ካቢኔ

የመንግሥት መዋቅር ማሻሻያው ከቀረበ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በከፊል ያደራጁትን ካቢኔያቸውን ለፓርላማው አቅርበዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት ከነባሮቹ 31 ሚኒስትሮች ውስጥ አሥር ሚኒስትሮች በአዲስ እንዲተኩ፣ ሌሎች ስድስት ሚኒስትሮች ደግሞ ከነበሩበት ወደ ሌላ ተቋም እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት በአካውንቲንግ እንዲሁም በተቋማዊ አመራር የተመረቁት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እንደገና ለሚዋቀረው የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትርነት፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በስታትስቲክስ በኋላም በተቋማዊ አመራርና በደኅንነት ዘርፍ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙትን አቶ ሲራጅ ፈጌሳን ደግሞ፣ ከመከላከያ ሚኒስትርነት ወደ ትራንስፖርት ሚኒስትርነት አዘዋውረዋል፡፡

ረዥም ዓመታትን በዲፕሎማሲ ዘርፍ ያገለገሉትን በስታትስቲክስ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ በኋላም በዓለም አቀፍ አስተዳደርና ዴቨሎፕመንት ፖሊሲ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙትን አምባሳደር ተሾመ ቶጋን በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትርነት፣ የደቡብ ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ በኋላም የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩትን አቶ መለሰ ዓለሙ በማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትርነት መድበዋል፡፡ አቶ መለሰ ዓለሙ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በልማትና በመልካም አስተዳደር ይዘዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ላለፉት ሁለት ዓመታት ያገለገሉት ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) ወደ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተዘዋውረዋል፡፡ እሳቸው ሦስቱንም ዲግሪዎቻቸውን ያገኙት በሥነ ልሳን ነው፡፡

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ በኋላም በተቋማዊ ለውጥ አመራር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆነው የተመደቡ ሲሆን፣ አቶ ብርሃኑ በዚሁ ተቋም ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩና ከተመረቁበት ሙያ ጋር በተገናኘ ለረዥም ጊዜ የሠሩ ናቸው፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አሚን አማን (ዶ/ር) በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ ሌላው ከአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ናቸው፡፡ አቶ ጃንጥራር የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በከተማ ፕላን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአርክቴክቸርና በሥነ ሕንፃ በከተማ ዲዛይንና ልማት ያገኙ ናቸው፡፡

ሌላው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩትና ቀደም ብሎም የኦሮሚያ ክልል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ እንዲሁም የክልሉ የሥራና ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ኡመር ሁሴን በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል፡፡

አቶ ኡመር የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ በመቀጠልም በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር የነበሩት አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ወደ ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነት ተመድበዋል፡፡ ዶ/ር አምባቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውንም ሆነ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተማሩት በተመሳሳይ ዘርፍ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ካቢኔ አዲስ ሆነው ከተቀላቀሉት መካከል ወ/ሮ ኡባ አህመድ አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ኡባ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያገኙ ሲሆን፣ በተማሩበት ሙያ ያገለገሉና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የሴቶችና ሕፃናት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ወ/ሮ ኡባ የኢሶዴፓ አባል መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የሕወሓት ታሪክ ዝርዝር ያስረዳል፡፡

ዋና እንባ ጠባቂ በመሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያገለገሉት የኦሕዴድና የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባል የሆኑት ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ወደ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርነት ተመድበዋል፡፡ ወ/ሮ ፎዚያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋማዊ አመራር ያገኙ ሲሆን፣ የሕዝብ ዋና እንባ ጠባቂ ከመሆናቸው አስቀድሞ የኦሮሚያ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽነር ነበሩ፡፡

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ እንዲሁም በሕዝብ ተሳትፎ ልማትና ማኅበራዊ ለውጥ ያገኙት አቶ አህመድ ሺዴ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያገለግሉበት ከቆዩበት የትራንስፖርት ሚኒስትር ወደ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡

የመጀመርያና ሁለተኛ ደግሪያቸውን በስታትስቲክስ የሠሩት አቶ ሞቱማ መቃሳ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲገለገሉበት የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትርነት ተነስተው በመከላከያ ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በዕፅዋት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ያገኙትና በአማራ ክልል የንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ የነበሩት አቶ መላኩ አለበል፣ በንግድ ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ደግሞ እስከ ሹመት ጊዜያቸው ድረስ የትግራይ ክልል የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ያለም ፀጋዬ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ያለም ፀጋዬ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኅብረተሰብ ጤና ውስንነት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በተመሳሳይ ዘርፍ አግኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ከሚሾሙትም ሆነ ባሉበት ከሚቀጥሉ ሚኒስትሮች የሚጠብቁትን በግልጽ ይፋ አድረገዋል፡፡ ‹‹እንዲገነዘቡ የምፈልገው አንደኛ የአቅም ውስንነት ካለ ለመማር ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ በመደጋገፍ ያንን ክፍተት መሙላት ይቻላል ወይም መታገስ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

      ነገር ግን በፍፁም የማያልፏቸው ሁለት ቀይ መስመሮች ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብበት አገልግሎት አሰጣጥ  ጉዳይና ሙስና፣ እንዲሁም የሀብትና የጊዜ ብክነትን እንደማይታገሱ ተናግረዋል፡፡ ያቀረቡት የካቢኔ ሹም ሽርና ሽግሽግም በፓርላማው በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

አዲሱ ካቢኔ የፈጠረው ስሜት

ሪፖርተር ያነጋገረቸው በውጭ ተቋም ውስጥ የሚያገለግሉ የፖለቲካና የደኅንነት ተንታኝ፣ ‹‹ዶ/ር ዓብይ ርፎርሚስት ሆነው ነው የመጡት፡፡ በካቢኔው ላይ ግን ዕቅዱን መተግባር የሚችሉ አመራሮችን አላየሁም፡፡ ሪፎርሙን ለመተግበር ከሚያስፈልጉት የመዋቅር እንቅስቃሴዎች ይልቅ፣ ስለሪፎርም ብዙ መወራቱን ነው ያረጋገጠልኝ፤›› ሲሉ የተደበላለቀ ስሜት እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡

      በአንድ በኩል አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመጣ ለሥልጣኑ ጠቃሚ የሚባሉ የመንግሥት መዋቅሮችን እምነት በሚጥልባቸው የራሱ ሰዎች እንደሚይዘው፣ ዶ/ር ዓብይም የመከላከያ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣናትን እምነት በሚጥሉባቸው ሰዎች በመያዝ ጠቃሚ የሚባሉ ቦታዎችን ወደ ራሳቸው ማሰባሰባቸውን ያሳያል ይላሉ፡፡ ከዚህ የካቢኔ ሹመት በኋላ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳን የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማድረጋቸው፣ ወ/ሮ ደመቱ አምቢሳን የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ማድረጋቸው የዚሁ እንቅስቃሴ አካል እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

      በመሆኑም ወደ ሥልጣን ከወጡ በኋላ በደኅንነት ተቋማት ላይ አሰርፃለሁ ያሉትን ሪፎርም መጀመራቸውን ያሳያል ብለው ያምናሉ፡፡ ለምሳሌ በኮማንድ ፖስት ውስጥ በአንድ አባል ብቻ ተወክሎ የነበረው ኦሕዴድ አሁን አምስትና ምናልባትም ከዚያ በላይ የኦሕዴድ አባላት መወከሉን ማየት ይቻላል የሚሉት እኚሁ ተንታኝ፣ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉና ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮማንድ ፖስቱ አባል በመሆን የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አምጥተውታል ይላሉ፡፡

ከዚህ ውጪ ያለው አመዳደብ ሁለት ዓይነት ገጽታ ያለው እንደሆነ ተንታኙ ይናገራሉ፡፡ አንደኛው በክልል ተቋማት ውስጥ የነበሩ አመራሮችን ወደ ፌዴራል ማምጣት ሲሆን፣ በፌዴራል ተቋማት መካከል ሽግሽግ ነው የተደረገው፡፡ ‹‹ይህ አካሄድ ተመሳሳይ ወታደር ተጠቅመህ ለማሸነፍ እንደሚደረግ ጦርነት ነው፤›› ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ የተካተቱት ‹‹ቴክኖክራቶች›› (ባለሙያዎች) አንድ ዓመት ከጥቂት ወራት ብቻ አገልግለው እንዲወጡ መደረጋቸው፣ ሪፎርም እንዴት ነው የሚመጣው? ወይስ ሪፎርሙ ተረስቷል? የሚል ጥያቄን እንደሚያጭር ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ጨለምተኛ መሆን ተገቢ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ሰውየው ጊዜ ያስፈልጋቸዋል በደኅንነት ተቋማት ላይ የጀመሩትን ሪፎርም ካጠናቀቁ በኋላ ወዴት እንደሚሄዱ እናያለን፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ባለሙያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወጣቶችን ሰብስበው በሚሊኒየም አዳራሽ ባደረጉት ንግግር በሥነ ምክር የታነፀ፣ በዕውቀት፣ በክህሎትና በችሎታ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ እንዲሰማራ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን በማስታወስ፣ ካቢኔያቸው የቃላቸውን እንደማይመስል ይገልጻሉ፡፡ የተሰየሙት አመራሮች የትምህርት ዝግጅትና የተግባር ልምድ ከተመደቡበት ቦታ አይጣጣምም ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -