Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከግራካሱ ተራራ ግርጌ የከተመ የኢንቨስትመንት ውጤት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አላማጣ ከተማ ከአዲስ አበባ በ619 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ከ55 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች እንደሚገኙባትም ይገመታል፡፡ የአየር ፀባይዋም ወይና ደጋ ነው፡፡ ከተማዋ በብዛት የፍራፍሬና የእንስሳት ተዋፅኦ ታመርታለች፡፡

አቶ ኢሳያስ ተሾመ ትኩዬም በአላማጣ ከተማ ልዩ ስሟ ገዳ ሐኪም በምትባል ቦታ ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእርሻ፣ በሆቴልና በቱሪዝም ሥራዎች ውስጥ ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ የአቶ ኢሳያስ ቤተሰቦች በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ቢሆኑም፣ እሳቸው ግን ከልጅነታቸው ጀምረው ወደ ንግዱ ያደሉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

በትውልድ ቦታቸው አካባቢ ከደርግ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅትም በወጣትነታቸው ጦርነቱን ለመቀላቀል በረሃ በመግባታቸው የተነሳ፣ እርሻውንም ንግዱንም በደንብ ለማወቅ ዕድል እንዳልነበራቸው ገልጸዋል፡፡ ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ ምንም ስላልነበረኝ ምን እንደምሠራ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ውጭ በመውጣት ለሁለት ዓመታት በአሜሪካ ቆይታዬን በማድረግ ጥቂት ጥሪት ቋጥረው ወደ አገር ቤት በመመለስ አዲስ አበባ ውስጥ ትንሽ ካፊቴሪያ በመክፈት ሥራ እንደጀመሩም ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ኢሳያስ በ1990 ዓ.ም. አካባቢ ባታቸውን ተስካር ለማውጣት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው አላማጣ ባቀኑበት ወቅት፣ የከተማዋ አስተዳደር ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደጋበዟቸውና መሬት እንደሰጧቸውም ገልጸዋል፡፡ በተሰጣቸው መሬት ላይ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ፖም (አፕል)፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ቡና፣ እንዲሁም ለቡና ከለላ የሚሰጡ በርካታ የዋንዛ ዛፎች፣ ከ300 በላይ የንብ ቀፎዎች፣ እንዲሁም አምስት የወተት ላሞችን በማርባት በጀመሩት ሥራ ቀስ በቀስ ወደ እርሻው በስፋት እንደገቡበት ያብራራሉ፡፡

‹‹ሥራው በጥሩ ሁኔታ በመሄዱ አካባቢውን ከመለወጥ በላይ ከማንጎው ብቻ በዓመት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ማግኘት ቻልኩ፡፡ በአካባቢው ለሚኖሩ 120 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ፡፡ ከዚህ ጋር ሊሄድ የሚችል ሥራ ሆቴልና ሪዞርት እንደሆነ አሰብኩ፡፡ በከተማዋም ቱሪስቶች ከላሊበላ ወጥተው በቀጥታ ወደ መቀሌ ይሄዳሉ፡፡ በሆቴል ዙሪያ በከተማዋ ያለውን እጥረት እመለከት ስለነበር፣ ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪው ገባሁ፤›› በማለት እየተስፋፋ ስለመጣው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴያቸው ገልጸዋል፡፡

በአቶ ኢሳያስ ኢንቨስትመንት ሥር ከሚጠቃለሉት አንዱ ራያ ግራንድ ሪዞርት ሆቴል ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሆቴል ከ250 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት በሰባት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የተገነባ ነው፡፡ ሆቴሉ ከአዲስ አበባ የሚዘረጋውና የአላማጣ ከተማን ለሁለት ከፍሎ መቀሌ በሚገባው መንገድ በኩል ወደ አላማጣ እንደተገባ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስተቀኝ በኩል ይገኛል፡፡

ባለ ሦስት ወለል ሕንፃ ያለው ይህ ሆቴል፣ በውስጡ ዘመናዊ ሬስቶራንት፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎችን የሚያስተናግድ አዳራሽ፣ የሆቴሉ ግንባታ በሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም 120 አልጋዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጠት በጀመረው ሕንፃ ውስጥ 45 የመኝታ ክፍሎች ሥራ ጀምረዋል፡፡ ከሕንፃው ጋር ግንባታቸው የተጠናቀቀ ዘመናዊ የሕፃናት መዋኛም አለው፡፡ በአንድ ጊዜ ከ70 በላይ ተሽከርካሪችን ለማቆም የሚችሉ አምስት የመኪና ማቆሚያዎች ያሉት ሲሆን፣ በግንባታ ላይ የሚገኘው የሆቴሉ ጅምናዚየም በሁሉም የመኝታ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ቁሳቁሶች አልጋውን ጨምሮ በአገር ውስጥ ከእንጨት ተፈልፍለው የተሠሩ ናቸው፡፡ የመታጠቢያ ክፍሎቹም በአካባቢው ከሚበቅል የማሽላ አገዳ ዝርያ በተቀዳ የቀለም ዓይነት ያጌጡ ናቸው፡፡ ከሕንፃው አናት ላይ ሲወጣም፣ በአቅራቢያ የሚገኘው የግራካሱ ተራራ በሆቴሉ ያለውን ሰው ቁልቁል የሚያይ ይመስላል፡፡ ከመኝታ ክፍሎቹ በረንዳ ትይዩም የሆቴሉ አካል የሆኑት የፍራፍሬ ማሳዎች በተንጣለለው ሜዳ ላይ ተንሠራፍተው ሲታዩ ዓይንም መንፈስም ያጠግባሉ፡፡

በዓመት ሁለት ጊዜ 200 ኩንታል ፍራፍሬ ከሚመረትበት እርሻ የትግራይ ማር የሚመረትበትን የንብ ቀፎዎች በርቀት ይመለከታሉ፡፡ በዚህ የፍራፍሬ ጫካ ውስጥ ድንኳን ጥለው የሚዝናኑበትም ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ በዚህ የፍራፍሬ ጫካ ውስጥ ሌላው ዘና የሚያደርጉት የቡና ዛፎ ናቸው፡፡ የቡና ዛፎቹ ነጫጭ አበቦችን አፍክተው ሲታዩም፣ የሆቴሉም ምድረ ግቢ ለየት ያለ ገጽታ ያላብሱታል፡፡ እርሻውን የሚጎበኙ እንግዶች የእርሻውን ውጤቶች በግዥ መጠቀም የሚችሉበት አሠራርም ሆቴሉ ዘርግቷል፡፡

ከሆቴሉ ጀርባ ከሚታው የፍራፍሬ ማሳ በተጓዳኝ፣ ዘመናዊ የከብቶች ዕርባታ የሚካሔድበት የግብርና ዘርፍም የሆቴሉ ደንበኞች በቅርብ ርቀት ዕይታ ውስጥ ከሚገቡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከሚታለቡት ላሞች በቀን 200 ሊትር ወተት ለገበያና ለሆቴሉ ይቀርባል፡፡ ሆቴሉ በከተማዋ መነቃቃትን እንደፈጠረ በሚያሳየው ደማቁ የኤሌክትሪክ ኃይል የደመቀው የሆቴሉ መናፈሻም፣ በከተማዋ ነዋሪዎች የሚዘወተርና ለመዝናናት የሚጎርፉበት ቦታ ለመሆን በቅቷል፡፡

አቶ ኢሳያስ በእነዚህ ሥራዎች ውስጥ ስላጋጠሟቸው ችግሮች ሲገልጹም፣ ‹‹ሐሳቤን ከመቃወም ጀምሮ ፕሮጀክቱን እስከማጓተት የሚደርሱ ነገሮች ገጥመውኝ ነበር፡፡ ለሆቴሉ ግንባታ በትንሹ ከ180 እስከ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓጓዝ ነው የሠራሁት፡፡ ይህ በራሱ ከፍተኛ ትዕግሥት የሚጠይቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትም ገጥሞኝ ነበር፡፡ እኔ ወደዚህ ሥራ ስገባ በከተማዋ የግንባታ ባለሙያዎችና የማቴሪያል እጥረት ነበረብኝ፡፡ ችግሩ በርካታ ነበር፡፡ ግን የተሻለ ሐሳብ በመሆኑ በዚያው ልክ ባይሆንም ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው ጥቂት ሰዎች በመኖራቸው ሥራው ለዚህ ደርሷል፡፡››

አቶ ኢሳያስ ከ320 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን በመቅጠር እያስተዳደሩ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ ወደፊትም በአግሮ ፕሮሰሲንግና በታሸገ ውኃ አምራችነት መሠማራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች