Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዲሶቹ ታሪክ ተረካቢዎች

በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አዲሶቹ ታሪክ ተረካቢዎች

ቀን:

እንደዛሬው አትሌቲክስ ትኩረት ባላገኘበት ዘመን ክልልንና ወረዳውን ወክሎ የመሳተፍ ሚና ትልቅ ሙገሳ አድናቆት ያስገኝ የነበረው ከቀዬ ጀምሮ ነበር፡፡ አትሌቶችም ቢሆኑ፣ ባልተሟላ ትጥቅ ወረዳዎቻቸውን የመወከል ዕድል ሲያገኙ ደስታቸው ብቻም ሳይሆን ወኔያቸውም ትልቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ መድረክ በታሪክ መጻሕፍት ስሟ በጉልህ ከሰፈረ ጀምሮ በየጊዜው የድል ቀንዲል ተላብሳለች፡፡ አንጋፋ አትሌቶቿም የአገራቸውን ባንዲራ በዓለም መድረክ አሸንፈው እንዲውለበለብ ባስቻሉ ጊዜ በእንባቸው ሲገልጹ የሚታየው ስሜት ብዙዎችን በሐሴትና በደስታ እየሞላ የሚኖር ክስተት ነው፡፡

በኦሊምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና፣ በወጣቶች ሻምፒዮና አኅጉራዊ ሻምፒዮናዎች ድል የተቀናጁ አትሌቶች መነሻቸው የአገር ውስጥ ውድድሮች መሆናቸው ሀቅ ነው፡፡ ከእነዚህ ሻምፒዮናዎች ውስጥም ዓመታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጠቃሽ ነው፡፡ ሻምፒዮናው በዓለም አቀፍ መድረክ የአገራቸውን ስም ያስጠሩ ብርቅዬ አትሌቶች ታሪክ እንዲጽፉ መነሻ መድረክ በመሆን ቆይቷል፡፡

ከማክሰኞ ሚያዝያ 9 እስከ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀን ድረስ እየተካሄደ ያለው 47ተኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከተጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል፡፡ ሻምፒዮናው ሁሉንም ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች እያሳተፈ ሲሆን፣ ከ40 በላይ ቡድኖችና ተቋማት ተካፋይ ሆነውበታል፡፡

42 የስፖርት ዓይነቶች የመወዳደሪያ መስኮች በመሆን እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በሁለቱም ፆታ የሚያሳትፈው ሻምፒዮናው ከ1,000 በላይ ተሳታፊዎች እየተካፈሉበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ይመለከታል፡፡

በአንጋፋ አትሌቶች መመራት የጀመረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ቀዳሚ ተግባሩ የአገር ውስጥ ውድድሮችን ቁጥር ማበራከት እንደሆነና አትሌቶችም ራሳቸውን ለመገምገም እንደሚያግዛቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተናግሯል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የረዥም ርቀት ሩጫ እንዲሁም በአጭርና መካከለኛ ርቀቶች የሚወዳደሩ አዳዲስ ተሳታፊዎችን ለማፍራት ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርቷል፡፡ በሻምፒዮናው ከአዳዲስ አትሌቶች ባሻገር ነባር አትሌቶችም በመካፈል አቅማቸውን ለመፈተሽ እንደሚያግዛቸው ተገልጿል፡፡

በዓለም ሻምፒዮና ሞ ፋራን መርታት የቻለው አትሌት ሙክታር እድሪስ፣ አትሌት ጀማል፣ አትሌት ይመር፣ አትሌት አንዱአምላክ በልሁ በወንዶች ምድብ በሻምፒዮናው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ ሲሆን፣ በሴቶች በኩል አትሌት በላይነሽ ኦልጀራና ሩቲ ኦጋን የመሳሰሉ ነባር አትሌቶች ተካተዋል፡፡

በመጪው ነሐሴ ወር በናይጄሪያ በሚካሄደው 22ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ የሚያስችል ዓላማን እንዳነገበም የፌዴሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ስለሺ ብሥራት ለሪፖርተር አብርተዋል፡፡ ከመም ውድድሮች በተጨማሪ በሜዳ ውስጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ሌሎቹ የሻምፒዮናው አካል ናቸው፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆነ፣ በዘንድሮው ሻምፒዮና አዳዲስ የአትሌቶች ተቋማትና የስፖርት ክለቦችም ተሳትፈዋል፡፡ የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ ባለፉት ሻምፒዮናዎች አንጋፋ አትሌቶችን ማለትም ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ስለሺ ስህን፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያምን ለማፍራት አስችለዋል፡፡ በሴቶች በኩልም አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርን የመሳሰሉ አትሌቶች ከዚህ ሻምፒዮና የተገኙ ናቸው፡፡

በዘንድሮው ሻምፒዮና አዳዲስና ተተኪ አትሌቶችን ማብቃት ዋነኛው ግብ እንደሆነ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በሻምፒዮናው በተለይ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስካለፈው ዓርብ ምሽት ድረስ ለ39 ዓመታት ተይዞ የነበረውን የመቶ ሜትር ክብረ ወሰን አትሌት በይሩ መሐመድ ከመከላከያ ስፖርት ክለብ በ10፡10 ሠዓት በማጠናቀቅ አዲስ ታሪክ ጽፏል፡፡ በሜዳ ተግባር የከፍታ ዝላይ 4፡41 ሜትር በመዝለል የመከላከያው ሳምሶን ባሻ ተጠቃሽ ነው፡፡

በሻምፒዮናው አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች በድምሩ የ480 ሺሕ ብር ለሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡ ምንም እንኳ ማንኛውም ተመልካች በአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም በመገኘት ውድድሮችን በነፃ እንዲከታተል በሮች ክፍት ቢሆኑም፣ የሚታደመው ተመልካች ቁጥር ዝቅተኛ እንደሆነ አቶ ስለሺ አስታውሰዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...