Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ መስመሮች

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀይ መስመሮች

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ነባርና አዲስ አመራሮች ማድረግ ወይም ማለፍ የማይችሏቸውን ቀይ መስመሮች አሰመሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ያቀረቧቸውን የካቢኔ አባላት ማንነትና የሚሸጋሸጉ ሚኒስትሮችን ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ‹‹የሚሾሙትም ሆነ ባሉበት የሚቀጥሉት እንዲገነዘቡ የምፈልገው፣ ሕዝብ ቅሬታ የሚያቀርብበት የአገልግሎት አሰጣጥ ማስተካከል ግዴታና አንደኛው ቀይ መስመር ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሕዝብ የተለየ ነገር ወይም ወርቅ አንጥፉልኝ አላለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ መታወቂያ ለማውጣት ዝምድናና ጉቦ መክፈል እንደማይገባው ነው የሚጠይቀው በማለት በምሳሌ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የአገልግሎት አሰጣጥ ማረጋገጥ ከነበሩትም ከሚሾሙትም ሚኒስትሮች እንደሚፈለግ በፓርላማው ፊት በጥልቅ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ቀይ መስመር ሙስናን የተመለከተ ነው፡፡ ‹‹የሙስና ጉዳይ ሌላኛው ልናልፈው የማንችለው ጉዳይ ነው፡፡ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ የሚደረግ ሙስናን መዋጋት ብቻ ሳይሆን፣ በየተቋማቱ የሚበላን የሀብትና የጊዜ ብክነት መቆም አለበት፡፡ ራሳችን በሙስና ውስጥ ባለመሳተፋችን ንፁህ ነን ማለት አይደለም፡፡ ይህም የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው፤›› ብለዋል፡፡

የካቢኔ አባላት ሹመትን ፓርላማው ካፀደቀ በኋላ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ያቀረቡትን መልቀቂያ አዳምጧል፡፡ ለአንድ ተኩል የምርጫ ዘመን ያገለገሉት አፈ ጉባዔ አባዱላ መልቀቂያቸውን በተመለከተ ከፓርቲያቸው ጋር ተነጋግረው ስምምነት ተደርሶበታል ባሉት መሠረት፣ ፓርላማው ምትካቸው አድርጎ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚልን በኢትየጵያ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት አፈ ጉባዔ አድርጎ መርጧል፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከቀትር በኋላ ከካቢኔ ውጪ ለሆኑ አመራሮች በሰጡት ሹመት ግን፣ የቀድሞው አፈ ጉባዔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት ተቀላቅለዋል፡፡

በሌላ በኩል ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳን የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔርን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ፣ አቶ አህመድ አብተውን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመዋል፡፡

አቶ ሞገስ ባልቻን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የጥናትና ፐብሊኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ፣ አቶ ዓለምነው መኮንን የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት፣ በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም አቶ ያሬድ ዘሪሁን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አድርገው ሾመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ያሾሟቸው 16ቱ የካቢኔ አባላት ዝርዝርም ይህንን ይመስላል፡፡

 1. አቶ ሽፈራው ሽጉጤ – የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር
 2. አቶ ሲራጅ ፈጌሳ – የትራንስፖርት ሚኒስትር
 3. ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) – የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር
 4. አምባሳደር ተሾመ ቶጋ – የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር
 5. አቶ ኡመር ሁሴን – በሚኒስትር ማዕረግ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር
 6. ወ/ሮ ኡባ መሐመድ – የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር
 7. አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)  – የኢንዱስትሪ ሚኒስትር
 8. አቶ ሞቱማ መቃሳ – የአገር መከላከያ ሚኒስትር
 9. ወ/ሮ ፎዚያ አሚን – የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር
 10.  አቶ አህመድ ሺዴ – በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር
 11.  አቶ ጃንጥራር ዓባይ – የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር
 12.  አቶ መለሰ ዓለሙ – የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር
 13.  አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ – ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
 14.  ወ/ሮ ያለም ፀጋዬ – የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች ሚኒስትር
 15.  አቶ መላኩ አለበል – የንግድ ሚኒስትር
 16.  አሚር አማን (ዶ/ር) – የጤና ጥበቃ ሚኒስትር
spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...