Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር በመላምት አይመራም!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከጨበጡ ሦስት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ብዙ ጊዜያቸውን በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ክልሎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲነጋገሩና መልዕክት ሲያስተላልፉ ሰንብተዋል፡፡ በንግግሮቻቸውም የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አዲሱን ካቢኔያቸውን በፓርላማ አፀድቀዋል፡፡ ተጨማሪ ሹመቶችንም ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው ተሿሚዎችን ፓርላማ አቅርበው ሲያፀድቁ ባደረጉት ንግግር፣ ለሙስና ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ጥያቄን በበቂ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችል መልካም አስተዳዳርን የማረጋገጥ ጉዳይ ላይም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት አሥር አዳዲስና ስድስት ከሌላ ኃላፊነት የመጡ ተሿሚዎችን ሲያቀርቡ፣ ባሉበት ሥልጣን የሚቀጥሉ መኖራቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ይኼንንም ያደረጉት የአንድ ዓመት ተኩል የቋሚ ኮሚቴ ዝርዝር ሪፖርትን መነሻ በማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ በሁሉም እርከኖች እንዲረጋገጥ ሲባልም ዕርምጃ መወሰዱን አውስተዋል፡፡ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካደረጉዋቸው ንግግሮች በመነሳት መሠረታዊ ለውጦችን እየጠበቀ ነው፡፡ እነዚህ ለውጦች ዘርፈ ብዙ በመሆናቸው በአዲሱ ሹመት ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው፡፡ አገር በመላምት መመራት ስለሌለበት አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማንሳት የግድ ይሆናል፡፡

ተሿሚዎቹ ስትራቴጂካዊ አመራር የሚሰጡ የፖለቲካ ሹማምንት መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የትምህርት ዝግጅት፣ የብቃት፣ የትጋትና የሥነ ምግባር ጉዳዮች ሊታለፉ አይገባም፡፡ ተሿሚዎቹ ከሚመሩት ተቋም ጋር ተዛማጅነት ያለው የትምህርት ዝግጅትና ልምድም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምሳሌም የሥነ ጽሑፍ ሰው ግብርናን፣ የንግድ ጤናን፣ የግብርና የውጭ ጉዳይን፣ የትምህርት ትራንስፖርትን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሕግ ጉዳይን፣ ወዘተ እንዲመራ ማድረግ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› እንደሚባለው ነው፡፡ ከሰሞኑ ሹመት እንዲህ ዓይት የተጠላለፉ ነገሮች ተስተውለዋል፡፡ በነበሩበት የኃላፊነት ቦታ ላይ አፈጻጸማቸው እዚህ ግባ የማይባል ደግሞ ለሌላ ኃላፊነት ተመርጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ካደረጉት ንግግር ጋር የሚጣረስ ነው፡፡ ምክንያቱም የሹመቱ መለኪያ ተብሎ ከተገለጸው ውስጥ ብቃት ዋነኛው ሲሆን፣ በሕዝብ ዘንድ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ጉዳዮችም አሉ፡፡ በተጨማሪም ከአንዱ ወደ ሌላው ዝውውር ያደረጉ ተሿሚዎች ላይም የተደበላለቁ ስሜቶች አሉ፡፡ አንደኛው ከላይ የተጠቀሰው የብቃት ጉድለትና የተጠያቂነት ጉዳይ ነው፡፡ ሁለተኛው በነበሩበት ኃላፊነት አፈጻጸማቸው አመርቂ የሆኑና ምስክርነት የሚሰጣቸው ተሿሚዎች ጉዳይ ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎች በጥሩ ሁኔታ የጀመሩትን ሥራ ትተው ወደ ሌላ ሲሄዱ የሚፈጠረው ክፍተት ነው፡፡ ይህም በጊዜ፣ በሰው ኃይልና በገንዘብ ሲሰላ ለአገር ኪሳራ ነው፡፡ በዚህ ላይ በሕዝብ ዘንድ ጥያቄ የሚነሳባቸው ተሿሚዎች ጉዳይም ሌላው መነጋገሪያ ነው፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢሕአዴግ አባል ያልሆኑ ተሿሚዎችን ቢያካትቱ ተመራጭ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትልቅ ብክነት የሚታየው ለአገር ጥቅም መሥራት የሚችሉ፣ የአገልጋይነት መንፈስን የተላበሱ፣ አቅምና ብቃት ያላቸው፣ በሥነ ምግባራቸውም ሆነ በልምዳቸው አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያዊያንን አለመጠቀም ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር አገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉና ለዚህም ዝግጁ የሆኑ በርካታ የተማሩና ልምድ ያካበቱ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ ከፖለቲካ ሹመት ዕይታ በመውጣት ለአገር በሚጠቅሙ መስኮች ላይ ለማሰማራት ጥረት ቢደረግ የሚጠቀመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ የፓርቲ ታማኘነትን ብቻ መሥፈርት ያደረገ ሹመት ሲሰጥ በሕዝብ ዘንድ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለሚያደናቅፉ መሰናክሎችም ያጋልጣል፡፡ ተሿሚዎች ከፓርቲ በላይ አገርን እንዲያገለግሉ እንደሚጠበቀው ሁሉ፣ በዚህ ምልከታ መሠረት አገራቸውን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸውን ብቁና ንቁ ዜጎችን በማቅረብ ኃላፊነት መስጠት ለውጡን የበለጠ ያቀላጥፋል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የክህሎትና የአመራር ባለ ተሰጥኦዎችን በሻማ ብርሃን ጭምር በመፈለግ አገራቸውን እንዲያገለግሉ ማድረግ ይጠቅማል፡፡ ለብሔራዊ መግባባትም በር ይከፍታል፡፡ የለውጡ መንደርደሪያ ይኼንንም ማካተት ነበረበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔያቸውን አደራጅተው በሙሉ ኃይል ሥራ ሲጀምሩ በማስጠንቀቂያ ጭምር ውጤት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ሕዝብም ይጠብቃል፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥቱ መዋቅር ውስጥ ያለው የሥራ ባህልና ዝርክርክርነት ደግሞ ይታወቃል፡፡ አዲሶቹም ሆኑ ከቦታ ወደ ቦታ የተዘዋወሩት ወይም ባሉበት የሚቀጥሉት፣ ይኼንን አስመራሪ ቢሮክራሲ እንዴት እንደሚያስተካክሉት ዋል አደር ተብሎ ይታያል፡፡ ሕዝብ በንቃት ሁሉንም ነገር እየተከታተለ ነውና፡፡ ትናንት በሚያምሩ አገላለጾች የተገባው ቃል ተግባራዊ መሆን የሚችለው፣ ከፍተኛ የአገልጋይነት መንፈስና ብቃት ያላቸው ተሿሚዎች ሲኖሩ ነው፡፡ ይኼንንም ከግምት በማስገባት በፍጥነት ዕርምጃ መውሰድ ካልተቻለ ልፋቱ ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ይሆናል፡፡ በሪፖርት ላይ ተመሥርቶ ካቢኔን በፍጥነት ከማደራጀት በፊት የተወሰነ ጊዜ ሰጥቶ ጥልቀት ያለው ጥናት ቢደረግ፣ ከላይ ለመጠቃቀስ የተሞከሩ ነጥቦችን ማዕከል ያደረገ ውሳኔ ላይ መድረስ ይቻል ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን በተቻለ መጠን በሕዝብ ውስጥ መግባባት የሚፈጥር ዕርምጃ በመውሰድ ማስተካከያ ማድረግ የሚቻለው፣ የሕዝብ አስተያየትን በማዳመጥ ነው፡፡ ሕዝብ ጊዜ ሰጥቶ ውጤት ሲጠብቅ ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› የሚለውን ዕድሜ ጠገብ ምሳሌን እያስታወሰ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ወቅት ዘና ብለው የተለመደውን ዓይነት አዝጋሚ ጉዞ የሚያደርጉበት ሳይሆን፣ በብርሃን ፍጥነት የሚወነጨፉበት ነው፡፡ በዚህ ፍጥነት ለመንቀሳቀስ የሚቻለው ደግሞ ሹመቱ ከኮታ ተላቆ አቅምና ብቃትን መሠረት ሲያደርግ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ችግሮች፣ የትምህርት ጥራት፣ የፖለቲካው ምኅዳር፣ መብትና ነፃነቶች፣ የአገልግሎቶች ተደራሽነት፣ የሕግ የበላይነት፣ ወዘተ ጉዳዮች ጠንካራና ብቁ አመራሮችን ይፈልጋሉ፡፡

ቃላት ተሽሞንሙነው ቀርበው ጊዜያዊ ሆታ ቢያስገኙም፣ በአገሪቱ ለዘመናት የተከመሩ ችግሮች በቀላሉ አይናዱም፡፡ እርግጥ ነው በሁሉም ነገር መስማማት አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን የአገር ጉዳይ ሲመጣ ብርቱ ክርክሮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ክርክሮች በመርህ ላይ ሲመሠረቱ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች ይመነጫሉ፡፡ ስሜታዊነትና ግብታዊነት ከጽንፈኝነት ጋር ሲመጋገቡ ግን መነጋገርም አይቻልም፡፡ እስካሁን አገሪቱን ችግር ውስጥ ከከተቱ መሠረታዊ ችግሮች መካከል አንዱ ይህ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባደረጉዋቸው ንግግሮች የተደሰቱ ያሉትን ያህል፣ ትችቶችን በመሰንዘር የራሳቸውን ምልከታም የሚያሰሙ አሉ፡፡ ይህ በራሱ ጤነኛ ነው፡፡ ችግሩ የሚመነጨው ግን የሐሳብ መንሸራሸሮቹ ሕዝብን ማዕከል ማድረግ ትተው የተለመደው የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ የአሁኑ ሹመት ጉዳይም በዚህ አተያይ ውስጥ መነጋገሪያ ከሆነ ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ ነገር ግን መፍትሔ አመላካች እየሆነ የአገሪቱን መፃኢ ዕጣ ፈንታ መሠረት ሊያደርግ ይገባል፡፡ ከመጠን በላይ የተለጠጠ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ ዕርባና ቢስ ነው፡፡ ለአገርም አይጠቅምም፡፡ በፖለቲካዊ ወገንተኝነት ላይ የተመሠረተ እሰጥ አገባ በሹመት ጊዜ ጭምር አሠላለፍን ያበላሻል፡፡ ወገንተኛ በማድረግም ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡

አገሪቱ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከገባችበት የፖለቲካ ቀውስ ለመላቀቅ ገና እንፉቅቅ ላይ ናት፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት ኢኮኖሚው እየተንገዳገደ ነው፡፡ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ እያገረሸ ባለው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ጎስቋላ ነው፡፡ በመኖሪያ ቤት ዕጦት የሚንከራተቱ ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሚሊዮኖች አኗኗር ያሳቅቃል፡፡ ኢፍትሐዊነትና ሙስና አሁንም የአገር በሽታ ናቸው፡፡ በሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ምክንያት ዛሬም የሚያለቅሱ አሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አሁንም ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነት የሚገፋፋቸውና ኢትዮጵያዊነት የማይዋጥላቸው እንዳሉ ሁሉ፣ የዜግነት መብቶቻቸው ተሟልተውላቸው አገራቸውን ለማገልገል የሚፈልጉም ሞልተዋል፡፡ የነገው ብሩህ ሕይወት የሚታየቸው እንዳሉ ሁሉ፣ ነገን አጨልመው የሚያዩም እንዲሁ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ውጥንቅጥ ውስጥ ያለች አገርን ከማጥ ውስጥ ለማውጣት ብርቱ ትግል ማድረግ የሚቻለው፣ በጋራ ጉዳዮች ተስማምቶ እጅ ለእጅ መያያዝ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ መጠነ ሰፊ ፅዳት የሚያስፈልጋቸው የዛጉ መንግሥታዊ ተቋማት ብዙ ናቸው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ጠፍቶ የዘረፋ ምሽግ የሆኑም ብዙ ናቸው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በብልሹ አሠራሮች ተዘፍቀዋል፡፡ የሠራተኞች የሥራ ሞራል የጠፋባቸውም ሆኑ በአገርና በሕዝብ ላይ ኪሳራ እያደረሱ ያሉ የመንግሥት ተቋማት መፅዳት የሚችሉት፣ በጥገና ሳይሆን በመሠረታዊ ለውጥ ነው፡፡ ይኼ መሠረታዊ ለውጥ መምጣት የሚችለው አቅምና ብቃት ከሥነ ምግባር ጋር ባጣመሩ ትጉኃን ነው፡፡ በለውጥ ውስጥ ያለች አገር አዳዲስ ፊቶችም ያስፈልጓታል፡፡ ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ማስተዋል የአመራር ጥበብ ይሰጣል፡፡ ይህ ጥበብ ኢትዮጵያዊያንን በጋራ ጎጆዋቸው ዙሪያ ያሰባስባል፡፡ ለነገዋ ዴሞክራሲያዊ አገር ግንባታ የትጉኃን ኢትዮጵያዊያንን ዕገዛ ማግኘት የግድ ስለሆነ በዚህ መሠረት መንቀሳቀስ ይበጃል፡፡ ለዚህም ነው አገር በመላምት አይመራም የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...