Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊምርት ገበያ ከማሳ እስከ ምርት መዳረሻ ያለውን ሒደት የሚከታተል አሠራር ሊተገብር ነው

ምርት ገበያ ከማሳ እስከ ምርት መዳረሻ ያለውን ሒደት የሚከታተል አሠራር ሊተገብር ነው

ቀን:

ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ምርት ገበያው በሚያገበያያቸው ሁሉም ምርቶች ላይ፣ በሙከራ ደረጃ የሚተገበርና ከማሳ ጀምሮ ምርቱ እስከሚላክበት መዳረሻ ገበያ ያለውን ሒደት የሚከታተል ሥርዓት እንደሚተገብር  ተገለጸ፡፡

በታዋቂው የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ አይቤኤም የተደገፈው ሥርዓት፣ ምርት የሚያልፍባቸውን የምርት ሒደቶች በመከታተል (ትሬሲቢሊቲ) ስለምርቱ መረጃ የሚሰጥ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ 1.4 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደተያዘለት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኤሌክሮኒክስ ዘዴ የሚታገዘው ይህ ሥርዓት በቡና ላይ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ወደፊት ከቡና በተጨማሪ በሰሊጥ፣ በነጭ ቦሎቄ፣ በቀይ ቦሎቄ፣ በበቆሎና በስንዴ ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡ ፕሮጀክቱ አይቤኤም ኩባንያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተግባር ሥራዎች ላይ የተሳተፈበት ሊሆን ችሏል፡፡  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምርት የተመረተበትንና ያለፈበትን የአመራረት ሒደት የሚያሳይ መረጃ ማቅረብ ግዴታ እየሆነ የመጣበት ጊዜ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤርሚያስ፣ ‹‹የሸማቹ የፍጆታ ጠባይ እየተለወጠ መጥቷል፡፡ በአሁን ወቅት ሁሉም ሰው ስለሚሸምተው ነገር ማወቅ ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ምርቱ ከየት እንደመጣ፣ እንዴት እንደተዘጋጀ፣ የትኞቹን ሒደቶች እንዳለፈ፣ ወዘተ. ያሉትን የምርት ሰንሰለቶች የሚያሳይ መረጃ በምርቱ ላይ በመለጠፍ የሚሠራበት ሥርዓት እንደሚተገበር አስታውቀዋል፡፡

በቡና የሚጀመረው ይህ አሠራር ስለቡና የምርት ሒደት ታሪክ የሚያትት መረጃ ሲያቀርብ፣ ቡናው ከየትኛው ማሳ እንደተለቀመ፣ የትኛው ጣቢያ ላይ እንደታጠበ፣ የት ቦታ እንደተከማቸ፣ መቼ ናሙናው እንደተወሰደና ደረጃ እንደወጣለት የሚያሳይ መረጃ ተዘጋጅቶለት ሲላክ ‹‹የምርት ፓስፖርት›› የሚል ስያሜ የተሰጠው መረጃ አብሮት እንደሚላክ አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ተገቢውን የምርት አመራረት ሒደት መረጃ ለሸማቾች በመስጠት የገበያ ተወዳዳሪነትን የማሳደግ ተልዕኮ እንዳለው አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡ ይህንን አሠራር እንደ ስታርባክስ ያሉ ግዙፍ የዓለም ኩባንያዎች ሲተገብሩት የቆየ መሆኑን፣ እንዲህ ያሉት ኩባንያዎችም ከ65 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ለማካበት እንዳበቃቸው አስታውቀዋል፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ቡና ወደ ውጭ መላክ ከተጀመረ ጀምሮ የተገኘው ገቢ 30 ቢሊዮን ዶላር እንደማይሞላ የሚገልጹት አቶ ኤርሚያስ፣ አዲሱ አሠራር ሸማቹ የሚፈልገውን መረጃ ከመስጠትና የምርት ሒደትን ከመከታተል ባሻገር የሚያስገኘው ጠቀሜታ እንዳለም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡

የምርቱ እያንዳንዱ ሒደት መታወቁ ችግር ያለበትን ቦታ በቀላሉ ለመለየት እንደሚያስችል ገልጸው፣ የምርት ጥራት ላይ በተደጋጋሚ የሚነሱ አቤቱታዎችንና እነሱንም ተከትሎ የሚመጡ የምርት ገበያውን ተዓማኒነት የሚሸርሽሩ ተግባራትን ለማስቀረት ተስፋ የተደረበት ሥርዓት ነው ብለዋል፡፡ ይህ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ሳይዘረጋ በመቆየቱ ሳቢያ ወደ ጃፓን ይላክ የነበረው ቡና ላይ የተከሰተውን የገበያ ችግር ማስቀረት ይቻል እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ በጊዜው ወደ ጃፓን ገበያ ከተላከው ቡና ማዳበሪያ ውስጥ የኬሚካል ቅሪት በመገኘቱ፣ የትኛው ቦታ ላይ የኬሚካል ቅሪቱ እንደተገኘ ሊታወቅ ባለመቻሉ ወደ ጃፓን የሚላከው ቡና በሙሉ እንዲቀር እስከማስገደድ የደረሰ ሥጋት ተፈጥሮ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ምርት ገበያው የሚዘረጋው የምርት ሒደት መቆጣጠሪያ ሥርዓት አምስት ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የሚያካትት እንደሆነ ሲታወቅ፣ አገሪቱ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችላትም ምርት ገበያው ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከ4.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ምርት ገበያው 1.4 ሚሊዮን ዶላር የሚያዋጣበት ሲሆን፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) በአግሪቢዝነስ ገበያ ልማት ፕሮጀክቱ በኩል 1.8 ሚሊዮን ዶላር በማዋጣት የሚሳተፍበት ነው፡፡ ኔስሌ፣ ጃኮብስ ዱዌ ኤበርትስ፣ ማዘር ፓርከርስ ኮፊ ኤንድ ቲ፣ እንዲሁም ዘ ሰስቴይነብል ትሬድ ኢኒሺዬቲቭ የተባሉ ተቋማት በጋራ 1.3 ሚሊዮን ዶላር በመለገስ የሚሳተፉበት ፕሮጀክት እንደሆነ፣ የምርት ገበያው ያሰራጨው መረጃ ይጠቁማል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...