Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምን መቆዘም ነው?

‹‹አንተ በርደህ አታብርደኝ…›› እያለ ወያላው በስልክ እያወራ ነበር፡፡ ማንን እያናገረ እንዳለ ገና አልተገነዘብንም፡፡ አሁንም ወሬውን ቀጥሏል፡፡ ‹‹ነገርኩህ አንተ ውኃ ሆነህ መቀጠል ትችላለህ፡፡ እኔ ግን የማቀልጠው የኑሮ ብረት አለብኝ…›› እያለ እየተጨቃጨቀ ነበር፡፡ ይህንን ወሬውን ሾፌሩ ወቅቱን የጠበቀ እንዳልሆነ እያሰበ ይመስላል፡፡ ‹‹እባክህን ወሬ ማሳመሩን ትተህ ሒሳብ ሰብስብ፤›› ይለዋል፡፡ ወያላው ስልኩን ዘግቶ ወደ ኪሱ እየጨመረ፣ ‹‹ወሬው አማረለት ብለህ ደግሞ በዚህም ልትቀና እንዳይሆን?›› እያለ ይስቅ ጀመር፡፡

አንድ ወጣት መናገር ጀመረ፣ ‹‹መቼም ዘመኑ የወጣት ነው፡፡ በዚህ ልንደሰት ይገባናል፤›› በማለት ወሬውን ለመቀላቀል ያህል አጠር ያለች ሐሳብ ጣል አደረገ፡፡ የተቃወመው አልነበረም፡፡ እንዲያውም አሁን አሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠፍተው ወደ ተፎካካሪነት ተቀይረዋል፡፡ ዳሩ ግን አሁንም ጥያቄው የሚሆነው ኢሕአዴግን ማን ችሎ ይፎካከረዋል የሚለው ነው፡፡ ሌላ ወጣት መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹ዘመኑ የወጣቶች ነው፡፡ እኛ ወጣት! መሪያችንም ወጣት! ስለዚህ ከማንም በላይ መሪያችን ይረዱናል፤›› በማለት ሐሳቡን ጀመረ፡፡ የመጀመርያው ወጣት ‘ማይኩን’ ቀምቶ መናገር ጀመረ፡፡ ‹‹በዚህችው በእኛው ዕድሜ እኮ ወጣትነት እንደ ወንጀል ይታይ የነበረበትን ዘመን አሳልፈን፣ ወጣትነታችንን እኛው ራሳችን የፈራንበትን ዘመን አሳልፈን፣ ይኸው አሁን ለአገር ግንባታ ምሰሶ ናችሁ ስንባል ከዚህ የሚበልጥ ምን ክብር አለ?›› ብሎ ዓይኑ እንባ አቀረረ፡፡

አንዲት ወጣት በዚህ ወሬ የተመሰጠች ትመስላለች፡፡ ‹‹እውነት እኮ ነው፡፡ ወጣትን ያላማከለች አገር መቼም ተስፋ ሊኖራት አይችልም፤›› በማለት ወሬውን ተቀላቀለች፡፡ ታክሲያችን ውስጥ አንድ አዛውንት ይገኛሉ፡፡ ድምፀ ተዓቅቦ ያደረጉ ይመስላሉ፡፡ ያው ዘመኑ የወጣቶች ነው ብለው ይመስላል፡፡ የወሬው ጀማሪዎች የሆኑት ሾፌሩና ወያላው የእነሱ ወሬ መሆኑ ተዘንግቶ፣ የታክሲ ተሳፋሪዎች ወሬውን እያጣጣሙት ነው፡፡ ጉዞዋችን ከስቴዲየም ወደ ቦሌ ነው፡፡ ‹‹ስቴዲዮም ሮናልዲኒሆን ለማየት የመጣው ሕዝብ ሚሊኒየም አዳራሽ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ አክብሮ ከመጣው ሕዝብ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፤›› እያለ ወያላው ጀመረ፡፡ ‹‹ታዲያ ሮናልዲንሆም ኋላቀር ተብላ የምትጠራ አገር ውስጥ ሕዝብ ሁሉ በነቂስ ወጥቶ ሲያጨበጭብለትና ፍቅሩን ሲገልጽለት በመመልከቱ የተሰማውን ታላቅ ደስታ ሲገልጽ ነበር፡፡ እነ ሜሲ፣ እነ ሮናልዶም መጥተው እንደምናይ ምንም ጥርጥር የለኝም፤›› ያለው በሜሲ ፍቅር ያበደ የሚመስል ወጣት ነው፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ ስለሜሲ ድንቅ ብቃት ለረዥም ደቂቃዎች አብራራ፡፡ ‹‹መቼም ከቢራዎቻችን አንዱ ሜሲን በሚቀጥለው ዓመት ካላመጣልን እንደ ቢራም አንቆጥራቸውም፤›› በማለት አስተያየቱን ሰነዘረ፡፡

በዚህ ውጭ ውጭ በሚለው አስተያየት ያልተደሰተው ሌላ ወጣት፣ ‹‹ሜሲ ብለህ ልትሞት ነው እንዴ? ሜሲ ብቻ ከምትል እስቲ ሁለት የቡናን፣ ሁለት የጊዮርጊስን ተጫዋቾችን ጥራልኝ?›› በማለት ጠየቀው፡፡ የተጠየቀውም ወጣት የተጠቀሱትን ቡድኖች መፈጠራቸውን እንኳን የሚያውቅ አልመሰለንም፡፡ ጥያቄ ጠይቆ መልስ ያጣው ወጣት ተበሳጨ፡፡ ‹‹ምንድነው እንደዚህ በአገር ሀብት የማንኮራው? ሁልጊዜ ለሌሎች እያጨበጨብን፣ የሰው እያደነቅን፣ አንድም ጊዜ ዓይናችንን ገልጠን የራሳችን ልጆች ሳናስተውል፣ በሰው ወርቅ የምናጌጥ ምስኪኖች ነን…›› በማለት ረዥም ማብራሪያ ሰጠ፡፡ ‘መጀመርያ አገርህን ዕወቅ፣ ሕዝብን ዕወቅ፣ ስፖርቱን ዕወቅ፣ የሕዝቡን ዝንባሌ የሚወዱትን ዕወቅ ከዚያ ሲያልፍ ሌላውን ዓለምም ሆነ ማንኛውንም ማወቅ ያለብህን ነገር ማወቅ ትችላለህ’ የሚል ሐሳብ ያዘለ ይመስላል ወሬው፡፡

በወጣቱ አስተያየት ፍጹም ያልተደሰተው ልጅ፣ ‹‹ገና ለገና የሁለት ተጫዋቾች ስም አላወቀም ብለህ አገርህን ዕወቅ ትለኛለህ?›› በማለት ጥያቄ ሰነዘረለት፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፣ ‹‹አዎን አላውቃቸውም፣ ላውቃቸውም አልፈልግም፡፡ እዚህ አፍንጫዬ ሥር ሆነው እስከ ዛሬ ድረስ ስቴዲዮም ከመመላለስ የዘለለ ምንም ከቁም ነገር የሚቆጠር ነገር አላየሁባቸውም፡፡ ስለዚህ አላውቃቸውም!›› በማለት የእግር ኳስ ቡድኖቻችንን እንደማያውቃቸው ቁርጥ አቋሙን ገለጸ፡፡ ወያላው ሒሳቡን እየሰበሰበ፣ ‹‹ያው የሰው ወርቅ አያደምቅም፣ ሮናልዲንሆ እንደሆነ ወደ ቤቱ ተመልሷል…›› በማለት ምንም የምደግፈው ቡድን የለም ያለውን ወጣት ተንኮስ አደረገው፡፡ ትንሽ እንደ መክረር ያለውን ጭቅጭቅ ለማርገብ ያህል አዛውንቱ ጣልቃ ገቡ፡፡ ‹‹እንዲያው ልጆቼ በወሬያችሁ መሀል ሳልፈልግ ነው የገባሁት፡፡ እኛ እንደሆነ ደክመናል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የእናንተው ናት፡፡ ከአባቶቻችን እንደተረከብነው እንዲሁ ለእናንተ አስረክበናል፡፡ ታዲያ እናንተም ይህንን የተረከባችሁትን አገር በአግባቡ ለቀጣይ ትውልድ አስረክቡ…›› ብለው ዞር ዞር ብለው አዩ፡፡

አዛውንቱ ቀጥለዋል፣ ‹‹…በሁሉም መስክ ተሰማርታችሁ የዚህችን አገር ክብር ከፍ ከፍ አድርጉ፡፡ ከዚህ በኋላ ይህች አገር ማንም እግር ኳስ ተጫዋች የላትም ያስፈልጋታል ለሚለው ኳስ ተጫዋች ይሁንላት፡፡ አገሬ ኢንጂነር ነው የሚያስፈልጋት ያለውም ኢንጂነር ይሁንላት፡፡ አይ እምዬ የምትፈልገው ሐኪም ነው ያለውም እንደዚያው ይሁንላት፡፡ ማንም ማንንም መኮነን የለበትም፡፡ ሁሉም ሰው ክፍተት ላይ የመቆም ታላቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ መቼም ሮናልዲንሆን ብንወደውም የእኛ አይደለም፡፡ የእኛ ቀለም አበበ ቢቂላ ነው፡፡ የእኛ መልክ ደራርቱ ቱሉ ናት፡፡ ታዲያ እነዚህን የእኛኑ ጀግኖች መተካት የሁላችንም ድርሻ ነው…›› በማለት ረዘም ያለ የአባት ምክራቸውን ሰጡ፡፡

በዚህም ትንሽ ውጥረት ነግሶበት የነበረውን የታክሲውን ድባብ ወደ ሰላም ዓምድ ለወጡት፡፡ ይኼን ጊዜ ነበር ሾፌሩ፣ ‹‹አባቴ እርስዎ ላይ ግን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ሙድ’ ነው የማይብዎት፤›› አላቸው አክብሮት በተሞላው የሾፌር ንግግር፡፡ አዛውንቱም በተረጋጋ አንደበት፣ ‹‹እንዴት እንደዚያ ልትል ቻልክ?›› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት፡፡ እርሱም፣ ‹‹እንዴ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት እኮ የጦርነት ሜዳ ሊሆን ጥቂት ሰኮንዶች የቀሩትን የታክሲውን ድባብ፣ ይኸው ወደ ፍጹም የተረጋጋ የሰላም ወረዳ ቀየሩት እኮ?›› በማለት ታክሲው ውስጥ ለተፈጠረው መረጋጋት ክብር አጎናፀፋቸው፡፡ እሳቸውም የሾፌሩን ወሬ ቀበል አድርገው፣ ‹‹እኔም እኮ ያልኩት እሱን ነበር፡፡ ድርሻችንን እንወጣ ለማለት ነበር የፈለግኩት፡፡ አሁንም ያደረግኩት ይህንኑ ነው፡፡ ሌላ ምንም ልመሰገንበት የሚገባ አንዳችም ነገር አላደረግሁም፤›› በማለት ምሥጋናው አይገባኝም ሲሉ ለሾፌሩ መለሱለት፡፡ ሾፌሩም በአዛውንቱ መልስ የተገረመ ይመስላል፡፡

‹‹ወጣቱ መሪያችን በወጣትነታቸው በእሳት ንግግራቸው ልባችንን እያቀለጡት ይገኛሉ፤›› የሚል ሐሳብ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የማይቀበለው ወጣት አነሳ፡፡ ታዲያ በድጋሚ የኢትዮጵያን እግር ኳስ የማይቀበለው ወጣት ሲናገር ሐሳብ ይመጣለት ይመስል የእርሱን ሐሳብ ተንተርሶ መናገር ጀመረ፣ ‹‹ያው ዘመኑ የማቅለጥ ነው…›› ሲል እንደ ቅድሙ ሊጨቃጨቅ እንዳልሆነ ተገለጠልን፡፡ ንግግሩንም ቀጠለ፣ ‹‹ውስጤ እሳት አለ፤›› ሲል፡፡ አንድ ይኼ ሁሉ ወሬ ሲወራ የት እንደነበረች በውል ያልተረዳናት ሌላ ወጣት፣ ‹‹እሳት? ወይኔ እሳት ተነሳ? ወራጅ ሾፌር አቁምልን ማለቃችን ነው…›› እያለች ታክሲውን አመሰችው፡፡ ዳሩ ግን አብዛኛው የታክሲው ተሳፋሪዎች ወሬውን በትኩረት ይከታተሉ ስለነበር ማንም አብሯት ሊርበተበት አልቻለም፡፡ እንዲያውም ከጎኗ ተቀምጦ ዓይን ዓይኗን ሲመለከት የነበረው ወጣት ይህችን ድንገተኛ አጋጣሚ ተጠቅሞ ማብራራት ጀመረ፣ ‹‹አየሽ አንቺ ውስጥ እሳት አለ፡፡ ይህንን እሳት አውጥተን ብረት ልናቀልጥበት፣ ተራራውን ንደን ሜዳ ልንሠራበት፣ በዚያም የቀዘቀዘውን የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ልናሳድግበት ይገባል…›› እያለ ጅንጀናውን አጠናክሮ ገፋበት፡፡

እኛም የወጣቱን ሥልታዊ መጠጋት እያደነቅን ወደ መውረጃችን ተቃረብን፡፡ ይኼኔ ነበር አዛውንቱ ሲወርዱ መውረጃው ጋ እንደ መቆም ብለው፣ ‹‹በጣም ጥሩ ሾፌር ነህ፤›› የሚል አድናቆታቸውን አበረከቱለት፡፡ ሾፌሩ ግን በምላሹ፣ ‹‹አባባ ይህ የምወደው ሥራዬ ነው የሚጠበቅብኝን ነው ያደረጉት፤›› በማለት ከእሳቸው የተማረውን ሐሳብ አንፀባረቀ፡፡ እሳቸው ግን የዋዛ አልነበሩም፣ ‹‹አየህ ልጄ ስንቶቹ በሚቆዝሙበት በዚህ ዘመን በንቃትና በብቃት መገኘት እኮ መታደል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነ ማንን ነበር ከመቆዘም ወጥታችሁ ጠንክራችሁ ታገሉ ያሉት?›› ብለውት እብስ አሉ፡፡ እኛም የምን መቆዘም ነው እያልን ወደ ጉዳያችን አፈተለክን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት