Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይሁን ብለናል!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ሰንብታችኋል ውድ ደንበኞቼ፡፡ ከመላው ቤተሰቦቼ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ፡፡ ‹‹ሰላምታ አታብዛ፣ ሰላምታ ኪስ አይገባም…›› እያለ የሚያደርቀኝ አድራቂ ወዳጅ አለኝ፡፡ ታዋቂ ሆነው አድናቂ ቢነሳችሁ፣ አድራቂ ታጣላችሁ ብዬ አልጠረጥርም፡፡ ሰውን ለማድረቅ የተካኑ ስንት አሉ መሰላችሁ? እስቲ ሬድዮናችሁን ክፈቱ፣ እስቲ አንደኛው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ አድርጉት፣ ከሃያ ከማያንሱት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ውስጥ አንድ አዕምሮ ላይ ወይም ልብ ላይ ጠብ የሚል ነገር አጥተውና ድርቅ ብለው፣ ቲቪውን ድርግም አድርገው ወደ ፌስቡካችሁ ልትሄዱ ትችላላችሁ፡፡ ሌላ አድራቂ በፌስቡክ መስኮት ይጠብቃችኋል፡፡

ይኸው የእኔው ድንቁ አድራቂ ‘ሰላምታ አበዛህ…’ እያለ ያደርቀኛል፡፡ የሰላምን ጥልቅ ሚስጥር ባሻዬ ይናገሩት፡፡ እኔ እንኳን በደጉ ዘመን የተወለድኩ ክፉና ደጉን የማላውቅ፣ ቦምብና ጥይት የማላውቅ፣ አፕል እየበላሁ ያደግኩ ትውልድ ነኝ፡፡ ባሻዬ ስለሰላም አውርተው አይጠግቡም፡፡ ልጃቸውም ቢሆን ይህንን ሐሳባቸውን ሁሌ እንደ ደገፋቸው ነው፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ቤቱን ወዲህና ወዲያ ያተራመሰው ጉዳይ አለ፡፡ አሜሪካ አወጣችው ስለተባለው ኤችአር 128 ስለሚባለው ነገር የባሻዬ ልጅ በታላቅ ብስጭት ሲራገም ነበር፡፡ ‹‹አልፈርስ አልናቸዋ! አልወድም አልናቸዋ! ይኸው ሲጠብቁን፣ ሲጠብቁን ይባስ እየለመለምን እያበብን ስንመጣ ተመልክተውና የሆነ መንገድ ሲፈልጉ ከርመው አሁን መጡብን፤›› በማለት ብሶቱን ተናገረ፡፡

ባሻዬም ቢሆን፣ ‹‹ይህ ደንብ መውጣት ከነበረበት ከዚህ ቀደም ብሎ ብዙ ውጥረት በነገሠበት ወቅት መሆን ነበረበት፣ አሁንማ ሰላም ወርዶ የዕርቅ ጅማሮ እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት ማውጣታቸው በጣም የሚያሳዝን ነው፤›› በማለት ተማረሩ፡፡ ልጃቸውም ቢሆን ‹‹ሊበታትኑን ቆርጠው ተነስተዋል፡፡ ቢያዩን ቢያዩን አንበተን አልናቸው፤›› በማለት ተራገመ፡፡ ነገም ይዘው የሚመጡልን ነገር አይጠፋም፡፡ ‹‹መቼም…›› አለ የባሻዬ ልጅ፡፡ ‹‹…አሜሪካ እጇን አስገብታ ሰላም የወረደበት አንድም የምድራችን ክፍል የለም፤›› በማለት ምሬቱን ቀጠለ፡፡ እኔም በኋላ ሄጄ ለጓደኞቼ የማወራላቸውን ጮማ ወሬ ለመቃረም የባሻዬን ልጅ ማብራሪያ ተጠማሁ፡፡

እሱም ቢሆን አላሳፈረኝም ነበር፡፡ እንዲህ በማለት አጫወተኝ፡፡ ‹‹አሜሪካ የትም ገብታ በሰላም ወጥታ አታውቅም፡፡ መቼም ለአንተ የአገሮቹን ስም አልጠቅስልህም…›› ሲለኝ ገርሞኝ አሜሪካ ለሆነ ጉዳይ ገብታ በሰላም የወጣችበትን ምድር ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ወዲያው በአዕምሮዬ እነ ኢራቅ፣ እነ ሶሪያ፣ እነ ሊቢያ፣ እነ አፍጋኒስታን ወደ አዕምሮዬ ተንጋግተው መጡ፡፡ ድንገት ግንባሬን ላብ ሽፍ አለብኝ፡፡ ያው የዚያን ያህል የሚያሠጋ ሆኖ ሳይሆን፣ አለች አይደል የደላላ ሥጋት፡፡ የባሻዬ ልጅ እንዳለው አሜሪካ ገብታበት ከተማው ዶግ አመድ ሳይሆን በሰላም ያለቀ ጣልቃ ገብነት ታይቶ አታውቅም፡፡ አውድማና አፈር አስቅማ በሰበብ አስባቡ እሽት አድርጋ የ200 ዓመታት የቤት ሥራ ሰጥታ የምትሄድ አገር መሆኗን ተገንዝቤ፣ አሜሪካን መፍራትና መጠርጠር ጀምሬአለሁ፡፡

ባሻዬ፣ ‹‹አሜሪካ እጇ የገባበትን ሁሉ የምታደባይ ክፉ አገር ናት፤›› እያሉ ሲያወሩ ነበር፡፡ የባሻዬ ልጅም ቢሆን፣ ‹‹አሜሪካ ለማንም አገር ተቆርቁራ አታውቅም፡፡ አንድ አገር ውስጥ የምትገባውም የምትወጣውም ለገዛ ጥቅሟና ለገዛ ጥቅሟ ብቻ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የፈለገችው ነገር ቢኖርና በሩ ሁሉ ስለተቆላለፈባት ነው እንጂ፣ ጥቅም ባትፈልግ ወይ ፍንክች ዝርም አትልም በማለት የአሜሪካ ጥቅመኝነት ላይ ማብራሪያውን ሰጠ፡፡ እባክሽ ተይን ለምን በሰላም አደሩ ብለሽ ከሆነ እንዲያውም ከዚህ በኋላ በሰላም የምናድርበት፣ በመልካም አስተዳደር የምንካስበት በጎ ዘመን ውስጥ ነው ያለነው ማለት የለብንም?

ወዳጆቼ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ቤታችሁ ድረስ ካልገባሁ የማለቷን ጉዳይ ምንም አልተዋጠልኝም፡፡ እንዲያውም አንድ የእኔው ቢጤ ደላላ፣ ‹‹አሜሪካ ደስ የምትለው ስንሄድባት ብቻ ነው እንጂ ስትመጣብን አይደለም፤›› በማለት ሲቀልድ ነበር፡፡ መቼም አሜሪካ አንድ ግዳይ ቢጤ ካላሰበች በስተቀር በምንም ሁኔታ ወደ አንዲት ሉዓላዊት አገር አትመጣም፡፡ የሆነ ጥቅም በሆነ አቅጣጫ እንደሚነካባት ካሰበች በረዥም እጇ ማተራመሷን ትጀምራለች፡፡ እንግዲህ ማን ይጠይቃታል፡፡ በምድራችን ከሚነሱት ታላላቅ ዕልቂቶች ውስጥ አሜሪካ እጇን ያልሰደረችበት አንድም አይገኝም፡፡ የተቆረቆረችና ያዘነች መስላ ተጠግታ በሥውር እጇ በያዘችው አጥፊ መሣሪያ ማደባየት ሥራዋ አድርጋ ከያዘች ቆይታለች፡፡

የባሻዬ ልጅ አሜሪካ በሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እጅግ እየተበሳጨ ሲረግማቸው ነበር፡፡ ‹‹እነዚህ የፖለቲካም ሆነ የአገር ትርጉሙ በጭራሽ ያልገባቸው፣ እነሱ በተደላደለ ሥፍራ ተቀምጠው ሁከት እየዘሩብን ናቸው፤›› በማለት ዝም ብለው ወሬ የሚነዙትን ሲቃወማቸው ነበር፡፡ በዚህ ብቻም አላበቃም፡፡ ‹‹የተጀመረውን የሰላምና የዕርቅ ሒደት በጥሞና እየተመለከትነው ነው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በተመረጡ ማግሥት ነው ወዲህ ወዲያ ብለው አንዴ ጅጅጋ፣ አንዴ አምቦ፣ አንዴ መቀሌ ብለው ለማረጋጋት እየተፍጨረጨሩ የሚገኙት፡፡ ባሻዬ ደግሞ፣ ‹‹አገር በአንድ ጀንበር አትገነባም፡፡ ጊዜ ያስፈልጋል፣ ትዕግሥት ያስፈልጋል…›› እያሉ ሲናገሩ ነበር፡፡ እሳቸው በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ደፋ ቀና ማለት ተማርከዋል፡፡ እንዲያውም የወለደ አንጀታቸው እየተላወሰ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ንግግር አደረጉ ሲባል ከሰሙ፣ ‹‹እኔ ልሯሯጥልህ… እኔ ወዲህ ወዲያ ልበልልህ…›› እያሉ እንደ ልጅ ያበረታታሉ፣ ያደንቃሉ፣ ይፀልያሉ፡፡

በእርግጥ ልጃቸው፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ልብ የሚያንቀሳቅሱዋቸው አዳዲስ መመርያዎችን ካላወጡ በስተቀር፣ አሁንም ቢሆን ኢሕአዴግ ባሰመረላቸው መስመር ውስጥ ብቻ ሆነው ነው ወዲህ ወዲያ የሚሉት፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለባቸውን የመመርያ አጥር ሲያብራራ ነበር፡፡ በእርግጥ የምን መመርያ እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ባሻዬ በልጃቸው ሐሳብ አልተስማሙም፣ ‹‹መቼም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን መሥራት አልቻልኩም ብለው አልነበር እንዴ?›› በማለት ልጃቸውን ጠየቁት፡፡ ልጃቸውም፣ ‹‹ያው በለው ከዛ የማይተናነስ ነገር ነው የተናገሩት…›› ብሏቸው፣ ‹‹ምን መሰለህ አባባ ሁሉም ነገር በአጥርና በቅጥር የተዘጋ ነው፡፡ ‹በነገራችን ላይ አባባ መመርያ እኮ ከኤችአር 128 አይተናነስም፤›› በማለት ራሱ ፈገግ አለ፡፡

ባሻዬ አሁንም አልተቀበሉትም፣ ‹‹እኛም እኮ የእርሱን መመረጥ እሰይ ብለን የተቀበልነው ከአጥሩና ከቅጥሩ በላይ ይሄዱልናል፣ ሕዝቦችን የሚጎዳ ማንኛውንም መመርያ በፅናት ይጋፈጡልናል ብለንም አይደል እንዴ መመረጣቸው በደስታ ያሰከረን?›› በማለትት መልሰው ልጃቸውን በጥያቄ ሞገቱት፡፡ ልጃቸውም ቢሆን ለዚህ የሰላ ሙግታቸው የሚሰጠው መልስ ለማዘጋጀት የፈለገ አይመስልም፡፡ እሳቸውም ይህንን አጋጣሚ ወሬያቸውን የማስፋፊያ ምቹ ዕድል አድርገው ተጠቀሙበት፡ ‹‹ትንንሾቹን ጅምሮች በማክበርና በመቀበል ወደ ትልልቅ ለውጦች የምናደርገውን ግስጋሴ መጀመር አለብን፡፡ ለዘመናት የቆየው ዘርፈ ብዙ ችግር በአንድ ጀንበር ተነቅሎ ወደ ባህር ይገባል ማለት ሊጨበጥ የማይችል የቀን ቅዥት ነው፤›› እያሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ እስኪመስሉ ድረስ እየተከራከሩላቸው አመሹ፡፡

‹‹እኛም ብንሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠበቃ በመሆን ከጎናቸው ልንቆም ያስፈልጋል…›› በማለት ልጃቸውም ከአባቱ ሐሳብ ጋር ተደመረ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩን የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ጠበቃ ያስፈልጋቸዋል፤›› በማለት ከጎናቸው ለመቆም ወሰነ፡፡ የባሻዬ ልጅ አክሎም፣ ‹‹እኚህ ታላቅ መሪ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ጥብቅና ካገኙ ምንም ኃይል ሊያቆማቸው አይችልም መመርያም ቢሆን…›› በማለት ፈገግ አለ፡፡ ‹‹እንግዲህ 100 ሚሊዮን ጠበቆቻቸውን ተሰባስበው ሰላማዊ ሠልፍ ውጡ ብለው ቢጠይቁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነቅሎ ይወጣል፡፡ በዚህም የታላቂቷን የአሜሪካ ክንድ ለመመከት እንደ ትልቅ ጋሻ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ መቼም ሕመማቸው ያመኛል፣ መብት ረገጣው ይቆረቁረኛል ያለችለት ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቆሞ ስትመለከት ከዚህ የሚበልጥ ታላቅ ሽንፈት ይኖራል ብዬ አልገምትም…›› እያለ ረጅሙን ማብራሪያውን ገፋበት፡፡

እስቲ ከፖለቲካው እየወጣን እንሰነባበት፡፡ ባሻዬ ስለዳግማዊ ትንሳዔው እንዳጫወቱኝ ከሆነ፣ ‹‹የክርስቶስ ተከታይ ደቀ መዛሙርት የክርስቶስን መነሳት ማመን ተስኗቸው ያድነናል ያሉት ጌታ ከመቃብር በታች እንደ ቀረ አስበውና ጠውልገው ኤማኡስ ወደሚባል መንገድ ሲያዘግሙ ነበር፡፡ በድንገት አብሮ ተቀላቅሏቸው ሲያወራቸውና ሲጠይቃቸው የነበረው ማ አትሉኝም? ሞቶ ቀረ ያሉት ጌታ፡፡ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ስለእርሱ ለራሱ እያሙለት ረዥም መንገድ አብሯቸው ቢጓዝም እንኳን አላስተዋሉትም ነበር፡፡ ዳሩ ግን በመጨረሻ ምግብ አንስቶ ሲባርክ አወቁት፡፡ እንግዲህ እግዜሩ ያሳያችሁ የሚፈልጉት ጌታ ፊታቸው መጥቶ አለማወቃቸው፡፡ መቼስ ምን እላለሁ? እንደ ቤተሰብ በዳግማዊ ትንሳዔ ወደ እናንተ የሚመጡ ነገሮችን ሁሉ ታስተውሉ ዘንድ ዓይናችሁ እንዲገለጥ እየፀለይኩ፣ የዛሬን እዚህ ላይ ልሰናበታችሁ፡፡ እስቲ ምርቃቴን ‹‹አሜን›› በማለት አሳርጉልኝ፡፡ ታዲያ የተሰጠንን ማየት ብሎም ማስተዋል ይሁንልን፡፡ ይሁን ብለናል፡፡ አሜን! መልካም ሰንበት!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት