Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የዘንድሮን ምርጫ ያራዘመበት ሒደት የሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ

ፓርላማው የዘንድሮን ምርጫ ያራዘመበት ሒደት የሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘንድሮ መካሄድ የነበረበትን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫን ያራዘመበት መንገድ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ምክር ቤቱ ሐሙስ ሚያዝያ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ ዘንድሮ መካሄድ የነበረበት ምርጫ ለ2011 ዓ.ም. እንዲሸጋገር በስምንት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡

አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን በመጥቀስ፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን መሆኑን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ሥልጣን የሚያዝበት የምክር ቤቶች ምርጫ ላለፉት ሁለት ጊዜያት የተካሄደው በሚያዝያ ወር ውስጥ ሲሆን፣ ከተሞቹ የተቋቋሙባቸው ቻርተሮችም ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሄድ ነው የማደነግጉት፡፡

ሌላ አንድ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ምርጫው ወደ 2011 ዓ.ም. እንዲራዘም ሲደረግ፣ የምርጫ ዘመናቸውን የጨረሱ ባለሥልጣናት ጉዳይ ምን ይሆናል? አብሮ ይራዘማል ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለተነሱት የሕጋዊነት ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት መካከል ስብሰባውን የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ሲሆኑ፣ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ምርጫው እንዲራዘም ብቻ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ ብቻ መወያየት እንደሚሻል በመግለጽ የምርጫ ዘመናቸውን ስለጨረሱ ባለሥልጣናት ጉዳይ የተነሳውን ጥያቄ ዘግተው አልፈዋል፡፡

ምርጫ የሚካሄደው በየአምስት ዓመቱ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግግ በማውሳት ማራዘሙ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ግጭት እንደሚፈጥር ለቀረበው ጥያቄ ምንም ዓይነት የሕግ መጣረስ እንደሌለ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንዲራዘምለት ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወቁት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አማኑኤል አብርሃም ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው እንዲራዘምለት ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ያጋጠመው የፀጥታ መደፍረስ ለምርጫው የሚደረጉ ዝግጅቶች የተሟሉ እንዳይሆን ተፅዕኖ ማሳደሩንና ምርጫውን ለማካሄድም እንደማይቻል ገልጿል፡፡ በመሆኑም በምርጫ አዋጅ ቁጥር 532 አንቀጽ 28(2) እና አንቀጽ 29፣ እንዲሁም በፓርላማው የአሠራርና የአባላት ደንብ አንቀጽ 64 መሠረት ምክር ቤቱ ውሳኔውን በማሳለፍ ምርጫውን እንዲያራዝምለት ጠይቋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ የተጠቀሱት አንቀጾች ምርጫውን ለማራዘም የሕግ መሠረት የላቸውም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 28(2) ‹‹ጠቅላላ ምርጫ በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላል፤›› ነው የሚለው፡፡

የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 29 ደግሞ ስለአካባቢ ምርጫ የሚደነግግ እንጂ የምርጫ ጊዜን ስለማራዘም ፈጽሞ አይገልጽም፡፡ የተጠቀሰው የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 64 ላይም የተጠቀሱት ምርጫውን ለማራዘም እንደማይችሉ አቶ አብዱ ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አብዱ ገለጻ አንቀጽ 64 የሚደነግገው ስለምክር ቤቱ ውሳኔ ነው፡፡

ምክር ቤቱ ውሳኔ የሚያሳልፈው ፖሊሲ ለማፅደቅ ወይም ውድቅ ለማድረግ፣ ዕርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ፣ ለአንድ ጉዳይ ወይም ሁኔታ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ለመጠየቅ፣ አንድን የመንግሥት ተግባር ለመደገፍ ወይም ለመቃወም፣ የአቋም መግለጫን በተመለከተና በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ እንጂ ሕግ የማሻሻል ተግባርን ለመፈጸም አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሚመሠረተው በየወቅቱ በሚካሄድ ምርጫ እንደሆነ በአንቀጽ 38 ላይ መደንገጉን ያስረዱት አቶ አብዱ፣ በማናቸውም ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዜጎች እንዳላቸው፣ እንዲሁም ምርጫ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበትና ዋስትና የሚሰጥበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ፓርላማው ይህንን በየወቅቱ የሚካሄድ ምርጫ ዛሬስ ይለፈን ብሎ ነው የወሰነው፤›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ ይህ መሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ሥር ተቀባይነት ካገኙ የሰብዓዊ መብቶች ጋር ጭምር እንደሚጣረስ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከምርጫ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ በየጊዜው (Periodic) መሆኑ ነው፤›› ያሉት አቶ አብዱ፣ ‹‹ይህንን መርህ እስቲ ዛሬ ተውኝ፣ ይለፈኝ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከማንም እንዳይመጣ የሚፈራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ምርጫው ወደ 2011 ዓ.ም. ሲራዘም የሥልጣን ጊዜያቸውን የጨረሱ አመራሮች ምን እንደሚሆኑ ውሳኔ አለመሰጠቱ ሌላው ስህተት መሆኑን አቶ አብዱ ተናግረዋል፡፡

የሞግዚት አስተዳደር በሕግ ሲሰየም ሥልጣኑ እንደሚገደብ፣ በሌላ በኩል ፓርላማው የምርጫ ዘመኑን ሳይጨርስ በሚበተንበት ወቅት እንኳን ምርጫ በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚካሄድ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ያለምክንያት አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በ2011 ዓ.ም. ምን ወር ላይ ነው የሚካሄደው የሚለውን ፓርላማው አለመወሰኑ ደግሞ በስህተት ላይ የተሠራ ሌላ ስህተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ፓርላማው የሁለት ሰዓት ስብሰባ አድርጎ እንደ ተራ ነገር ምርጫውን ማራዘሙ ያለመብሰላችንንና የምርጫ ሕጋችን ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ያሳያል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...