Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርኢፍትሐዊነትና ሙስና ዋነኞቹ የአገር ጠላቶች በአፋጣኝ ይዘመትባቸው

ኢፍትሐዊነትና ሙስና ዋነኞቹ የአገር ጠላቶች በአፋጣኝ ይዘመትባቸው

ቀን:

በመስከረም ወልደ ማርያም

መሰንበቻውን ኢሕአዴግ ሊቀመንበሩን መርጧል፡፡ ተመራጩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ላይ ሆኖ መጪውን መተንበይ ባይቻልም፣ የአገራችን ጠንቅ ከሆኑት መሠረታዊ ችግሮች መካከል ኢፍትሐዊነትና ሙስና ናቸው ብሎ ለማሰብ፣ እንዲሁም የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደር ትኩረት ይሆናሉ የሚል እምነት ስላለኝ እንዲህ አቀርባለሁ፡፡

በተለያዩ የዓለም አገሮች ፈጣንም ይባል ዘገምተኛ ወይም ተከታታይ ይሁን የሚቆራረጥ የኢኮኖሚ ዕድገት እየታየ ነው፡፡ በተለይ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ግሎባላይዜሽንና የመረጃ ዘመን ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት እየለወጠው በመምጣቱ፣ ተያይዞ ከመውደቅ በላይ ተደጋግፎ የመውጣት ምልክት እየታየ ነው፡፡ ለዚህም ዓለም ራሱ በዓመት እስከ ሁለት በመቶ፣ አፍሪካን የመሰሉ ደሃ አኅጉሮች ሳይቀሩም እስከ አምስት በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገባቸውን ለአብነት የሚጠቅሱ ትንታኔዎች አሉ፡፡

- Advertisement -

በሁለት አኃዝ ለሁለት አሥርትና ከዚያ በላይ እየተመነደጉ የመጡት እነ ቻይና፣ ታይዋን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን ዓይነቶቹ ‹‹የእስያ ነብሮችም›› (Asian Tigers) መጠኑ ይለያይ እንጂ ዕድገታቸው አልቆመም፡፡ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ሩዋንዳን፣ ታንዛኒያን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ናይጄሪያን የመሳሰሉ የአፍሪካ ፈጣን አዳጊዎች በግስጋሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ኢትዮጵያ ‹‹የአፍሪካዋ ነብር›› እየተባለች የሚለውን ስያሜ አግኝታ ተጠቅሳለች፡፡

ያም ሆኖ በተለይ የፈጣን አዳጊ የሦስተኛው ዓለም አገሮች ዋነኛ ፈተና ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ ሙስና ነው፡፡ በእርግጥ የዴሞክራሲያዊ ባህል አለመጎልበት፣ ተያያዥ የሆኑት የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሕግ የበላይነት አለመስፈን ፈተናዎችም ክፉኛ እየጎዱ ነው፡፡ የእነዚህ ጎታች አስተሳሰቦች መንሰራፋትም ለሙስናና ለአቋራጭ ብልፅግና ፍላጎት ማባበያ ሆኗል፡፡ ለዚህም ነው በአንዳንድ አገሮች ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት›› የሚሉ ጥገኛ ኃይሎች ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ የሚፋለሙት፡፡

ለዚህ አባባል ቀዳሚዋ ተጠቃሽ አገር ቻይና ነች፡፡ ከወራት በፊት በቻይና ንግሹ ከተማ በተካሄደው የቡድን 20 አገሮች ጉባዔ ላይ የቻይና መንግሥት ይፋ ያደረገው መረጃ ነበር፡፡ ይኼውም በአገሪቱ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ሙስና ፈጽመው በ70 የተለያዩ አገሮች ተሸሽገው ከቆዩ ሁለት ሺሕ ያህል ሰዎች ተመዝብሮ የነበረ 1.12 ቢሊዮን ዶላር ወደ ቻይና እንዲመለስ የማድረጉ ሥራ ነው፡፡ ቻይና ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 300 ሰዎችን በሙስና ወንጀል መቅጣቷ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች 100 ሺዎችን ከሳ በሒደት ላይ መሆኗ ሲታይም ‹‹ልማታዊ›› የሚባለው ሥርዓት ምንኛ ለዘረፋና ለአቋራጭ መንገድ ክፍት በር እንዳለው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ አንዳንዴ የሙስና ዝንባሌው ድንበር ተሻጋሪም ነው፡፡

ማጠንጠኛዬ ወደ ሆነው ኢትዮጵያ ሁኔታም ስንመለስ የተጀመረውን የዕድገት ጎዞ እየፈተነው ያለው ሙስናና ኢፍትሐዊነት መሆኑ ቁልጭ ብሎ ታይቷል፡፡ በተለይ መንግሥት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ብሎ በጀመረው ችግርን የመለየትና መፍትሔ የማምጣት ትግል እንደተረጋገጠው በአቋራጭ የመበልፀግ፣ ሥልጣንን ያላግባብ የመጠቀም፣ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን ብሎ ለዘመድ፣ ለወዳጅና ለሚቀርብ ሁሉ ‹‹መሯሯጥ›› መጠኑ ይለያይ እንጂ በዝቶ ታይቷል፡፡ አልፎ አልፎ ተቋማዊ አሠራርን በመሸራረፍ ለአንድ ወገን ጥቅም መሥራት የሚመስሉ ብልሹ ድርጊቶችም ሊወገዙ በሚገባበት አኳኋን ሲጠቀሱ ተደምጧል፡፡ አሁን ግን በአጭሩ መቀጨት አለባቸው፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ሕዝብና መንግሥትን ለማገልገል በታማኝነት ስም የተቀጠሩ የፋይናንስ ኃላፊዎች፣ የሒሳብ ሙያተኞችና ሠራተኞች በማጭበርበር ተግባር ላይ ሲወድቁም ታይቷል፡፡ በተለይም የአገር ገንዘብን እንደ ራስ ቆጥሮ የመሰወር ድርጊት፣ ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዝና የብዙዎችን ገንዘብ (በመኪና ልግዛላችሁ፣ ውጭ ልውሰዳችሁ፣ አክሲዮን ላደራጃችሁ፣ . . . ስም) አጭበርብሮ መሰወር ተደጋግሞ ይታያል፡፡ ወደ ማኅበረሰቡ ወረድ ሲባል ያለው አጭበርባሪነትና በአቋራጭ የመበልፀግ ደረቅ ወንጀልም ብርቱና ሕጋዊ ትግል ካልተካሄደበት፣ ለዕድገቱ አደናቃፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው፡፡

የዕድገቱ ፍትሐዊነት ይታይ

በአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ስለመምጣቱ የነፍስ ወከፍ ገቢን ወይም አጠቃላይ አገራዊ ምርትን (GDP) ማየት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም መጠኑ ይለያይ እንጂ በገጠርም ይሁን በከተማ ሕይታቸው የተቀየረ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው፣ ብሎም ሀብት እያፈሩ የመጡ አዳዲስ ባለሀብቶች መታየት መጀመራቸው ነው፡፡ በመጠኑም ቢሆን ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የጥቃቅን አንቀሳቃሾችን ልብ ይሏል፡፡

አሁንም ቀላል የማይባል ድህነት (እስከ 22 በመቶ ከዚህ ውስጥም 17 በመቶ ሥራ አጥ) ቢኖርም፣ በገጠር የአብዛኛው ዜጋ አኗኗር ለውጥ እየታየበት ነው፡፡ አርሶ/አርብቶ አደሩ ለበጋና ለክረምት ያለው ቅርበት ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከነበረበት 200 ፐርሰንት አድጓል፡፡ የመጠጥ ውኃ የማግኘት ዕድሉም ከሁለት እጥፍ በላይ ማደጉን የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. የ2016 የልማት ሪፖርት አሳይቷል፡፡ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የእህል ወፍጮ፣ የቀበሌ አስተዳደር ሥርዓትና ፍትሕ በማግኘት በኩልም ለለውጥ የሚያነሳሳ አዲስ አብዮት ተቀስቅሷል፡፡ ለዚህም ነው የገጠሩ ሕዝብ አኗኗር (አለባበስ፣ አመጋገብና መጠለያ አሠራር፣ . . .) የሚፈለገውን ያህልም ባይሆን መሻሻል እያሳየ የመጣው፡፡ እንደ አገር የዜጎች የመኖር አማካይ ዕድሜም እስከ 20 ዓመት መጨመሩም ዓለም አቀፍ መረጃ ይፋ እየሆነ ያለው፡፡ 

በከተሞች ያለው የተጠቃሚነት ተስፋም ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተለይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ (በመንግሥት፣ በግል ባለሀብቶችም፣ ሆነ በራሱ በዜጋው) ትንሽ የማይባል ውጤት እየመጣ ነው፡፡ አሁን አሁን በአገሪቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሆቴሎች፣ ኢንዱስትሪዎችና የግል ኩባንያዎች ባለቤቶች ግለሰቦች ናቸው፡፡ ከውጭም ሠርተው ይሁን በአገር ውስጥ ባፈሩት ገንዘብ የመኖሪያ ቤት፣ ተሽከርካሪና ዘመናዊ አኗኗር እየጀመሩ ያሉትም ተበራክተዋል፡፡ በእርግጥ በከተሞች አሁንም ዋነኛ ፈተና የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ነው፡፡ መንግሥትና የግል ባለሀብቱ በመስኩ ቢሰማሩም ብዙኃኑን ደሃ እያረካ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ በማኅበር ቤት መሥራትን ማበረታታት የተጀመረውም (በትግራይና በኦሮሚያ) ገና በቅርቡ ነው፡፡

የከተሞች መሠረተ ልማት መሻሻል በተለይ በመንገድ፣ በባቡር መስመር፣ በቴሌኮም፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ማጠናከር ኑሮን ይበልጥ አመቺ እያደረገ ነው፡፡ በማኅበራዊ ልማት መስክ (ትምህርትና ጤና) ረገድም ተስፋ ሰጪ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡

አሁን በስፋት እየተሰማ ያለው ግን የፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄ ሆኗል፡፡ በተለይ በከተሞች ዓመት ሙሉ ካለሥራ ተቀምጠው እየዋሉ (በየጫት ቤቱ) በሀብት ላይ ሀብት የሚያጋበሱ አዳዲስ ቱጃሮች እየታዩ ነው፡፡ በደላላ፣ በጉዳይ ገዳይነትና ገቢና ወጪው በማይታወቅ የኮንትሮባንድና የኪራይ መሰብሰቢያ ሥልት ሕይወታቸውን የመሠረቱ አሉ፡፡ መንግሥት ይኼንን ድርጊት በፖሊሲና በሕግ ጭምር እንደሚያወግዘው ቢታወቅም፣ በተግባር ግን ለእንዲህ ዓይነቶቹ ፀረ ሥራ ኃይሎች መፈልፈል እያገዘ ያለው ሥርዓቱ ራሱ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡

የሕዝብ አደራን እየበሉ ያሉ አንዳንድ ኃላፊነት የማይሰማቸው ባለሥልጣናት ራሳቸውንና የቀረባቸውን በአቋራጭ ለማበልፀግ የሄዱበት ርቀትም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ትናንት ምንም ያልነበራቸው ባለሕንፃዎች፣ ባለቪላ ቤቶች፣ ከአንድም ሦትና አራት ቦታ የያዙ ዜጎች፣ . . . የሀብት ምንጫቸው ግልጽ አይደለም፡፡ የዚህ ነገር እየተባባሰ መምጣት ደግሞ በተቃራኒው በየጎዳናው ተደፍተው የሚያድሩ፣ በየቤቱ እምነቱና አድባራቱ የሚኮለኮሉ አረጋውያንና ሕፃናትን እየበረከቱ እንዲሄዱ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ በመልሶ ማልማትና በሕገወጥ ግንባታ ስም ካለመጠለያ እየቀረ ያለው ነባሩ የከተማዋ ነዋሪን የመታደግ ጉዳይ ትኩረት ካላገኘ፣ ኢኮኖሚያዊ ‹አፓርታይድ› እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርግ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕዝቡ በይፋ እየገለጸ እንዳለውም (ምንም እንኳን የተጋነነ መረጃ እንደሚኖር ቢጠረጠርም) አንዱ አካባቢ ይበልጥ እየተጠቀመ ሌላው እየተጎዳ እንደሆነ የሚሰማ ስሜት ሕዝቡ ውስጥ ሰርጓል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋና ዋግ ህምራ ዞኖች በሕዝብ ልማት ጭምር ወደ ኋላ እንደቀሩ የክልሉ መንግሥት ሳይቀር ይቅርታ የጠየቀበት እውነታ ነው፡፡ ከአገሪቱ ዋና ከተማ 200 ኪሎ ሜትር የማይርቁ የሰሜን ሸዋ ነባር ወረዳዎች የአስፋልት መንገድ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማግኘት ፈጣሪን ሲማፀኑ ማየት በየትም ቦታ የሚኖረውን የየአካባቢዎቹ ተወላጅ ግፍ እንዲሰማው እያደረገ ነው፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በባሌና በአርሲ እንዲሁም በምዕራብ ሸዋና በወለጋ ሁሉም ዞኖች በሚገኙ አንዳንድ ወረዳዎች ያለው ሥራ አጥነት የገዘፈ ነው፡፡ አካባቢዎቹ በሕዝባዊ ልማት (መንገድ፣ ውኃና ኤሌክትሪክ) በተሻለ ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ ብዙኃኑን የአዲሱ ትውልድ ዜጎች የሥራ ዕድል ድርቅ መትቷቸዋል፡፡ በተሃድሶው እንደሚታየውም እንዲያውም የመልካም አስተዳደር ዕጦቱና ሙስናው ተወላጁ እንደተበዘበዘ እንዲሰማው ከማድረግ አልፎ በቀላሉ በሥርዓቱ ላይ አስነስቶታል፡፡

መንግሥት በታዳጊ ክልሎችና በአናሳ ማኅበረሰቦች በኩል የሰጠውን ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊው ሕዝብ ባለባቸው አካባቢዎችም እየደገመው አይመስልም፡፡ ለዚህ አባባል አንዱ ማሳያ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ሕገወጥ ስደተኞች በየወሩ የሚፈልሱባቸው የሐዲያ፣ የከምባታ፣ የጋሞና የወላይታ ዞኖች ገጽታ ነው፡፡ እነዚህ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ዞኖች ወጣቶቻቸውን በገፍ የሚሰዱት ወደ ባህር ማዶ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው አገሪቱ ትልልቅ ከተማዎች (አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ደብረ ዘይትና ሻሸመኔ) ጭምር ነው፡፡

በድምሩ በሙስናም ይሁን በኢፍትሐዊነት ወይም ተደጋግሞ እንደሚባለው በአቅም ማነስ እየመጣ ያለው የፍትሐዊነት ጥያቄ መልስ የሚያሻው ነው፡፡ ብዙኃኑን ጥሎ ጥቂቱን አንጠልጥሎ የሚደረግ ‹‹ዕድገት›› መቋጫው አያምርም፡፡ ያውም የብሔር ፖለቲካው እንደ እሳተ ገሞራ በሚንተከተክበት በዚህ ጊዜ አካባቢያዊ የሚመስሉ የፍትሐዊነት ቅሬታዎችን አለመመለስ ዘላቂ ለውጥን ያደናቅፋልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ሙስና በግልጽ ቢኖርም አልተፋለምነውም

ሙስና የኢትዮጵያ ብቻ ወረርሽኝ አይደለም፡፡ ብዙዎች ታዳጊና የሠለጠኑ አገሮችን አንቀጥቅጧል፡፡ ብርቱዎቹ አደጋውን ተገንዝበው በፅናት ተፋልመው ቢያንስ ከሕዝባቸው ታርቀው በሥርዓት እያረሙት ዘልቀዋል፡፡ ሙስና፣ ኢፍትሐዊነትና የሕግ የበላይነት ጥሰት ያሸነፋቸው የውድቀት ምሳሌዎች (ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ናይጄሪያና ማዕካላዊ አፍሪካ . . . ) ግን ያሉበትን ደረጃ ማጤን ብቻ በቂ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ሙስናን ሳያቅማሙ የመታገልን ጉዳይ ለነገ ሊሉት አይገባም፡፡ ዓለም አቀፎቹን ትራንስ ፖረንሲ ኢንተርናሽናልን በመሳሰሉ ድርጅቶች ከሚካሄዱት ጥናቶች በላይ፣ መንግሥት ራሱ በከፈተው ‹‹ተሃድሶው መድረክ›› ሕዝቡ በይፋ እያወጣው ያለው መረጃ ካልተድበሰበሰ አስተማሪና ጠንካራ ዕርምት ለመውሰድ ያስችላል፡፡ ግን በመንግሥት በኩል እዚህ ግባ የሚባል ዕርምጃ ባለመታየቱ፣ አንዳንዶች ‹‹ከሥርዓቱ ጋር ፖለቲካዊ ግጭት አትፍጠር እንጂ ሙስና በተናጠል አያስጠይቅህም፤›› እስከ ማለት አድርሷቸዋል፡፡

ለአብነት ያህል የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ተቀምጠው ባለኮከብ ሆቴል የገነቡ፣ ሕንፃዎች የገነቡና ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች የከፈቱ እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ወገኖች ተበድረው ሠሩ፣ በባለቤታቸው ስም ፈቃድ አውጥተው ነገዱ ቢባል እንኳን በሥልጣናቸው መሬት፣ ብድርና የግብር ጣጣን አቀላጥፈዋል፡፡ በአንድ የሚዲያ ተቋም ኃላፊ የነበሩ አንድ ግለሰብ ደግሞ የካርጎና የመርከብ ጉዞ ላይ የግል የግንባታ ዕቃን በሚመሩት መሥሪያ ቤት ስም እስከ ማስገባት የመድረሳቸው ድፍረትም ተጋልጧል፡፡

አንዳንዱ ደፋር ‹‹ቱባ›› ባለሥልጣንም በቅርብ ወዳጁ ስም የቢስነዝ ግሩፕ ፈጥሮ ‹‹ሞኖፖል›› በሚመስል ደረጃ እየተወራ መገኘቱ ግልጽ ነው፡፡ የግል ኮሌጁን፣ ሆስፒታሉን፣ ሕንፃና የቢዝነስ ማዕከሉን፣ . . . ሁሉ እያግበሰበሱ ለመንጠቅ ጠንካራ መንግሥታዊ ጀርባ ማስፈለጉ አይቀርም፡፡ ይኼን ተጠቅሞ በግላጭ ሰማይ የነካን ሰው ተግባርና ሕገወጥ ኔትወርክ ለመደበቅ መሞከር፣ ግመል ሰርቆ እንደመሸሸግ የሚቆጠር ነው፡፡ ሕዝቡም በምንም ተዓምር ሊቀበለው አይችልም፡፡

እነዚህንና መሰል የሙስና ወንጀሎችና ንፋስ አመጣሽ ሀብት የማካበት ድርጊቶችን በይፋ ያወገዘው መንግሥት፣ በመረጃ ላይ ተመሥርቼ የሚጠየቀውን እከሳለሁ፣ የሚጠረጠረውንም የሕዝብ ኃላፈነቱን አስረክቦ ወደ ራሱ መንገድ እንዲሄድ አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ የበታች ሹማምንትን ሲከስ፣ አሁንም ድረስ በላይኛው ደረጃ መነካካት አልታየበትም፡፡ የሚከሰስ፣ የሚወረስም ሆነ ከወንጀል ነፃ የሚል መረጃም ‹‹ውሾን ያነሳ ውሾ . . . ›› መስሏል፡፡ 

በመንግሥት በኩል ሥልጣንን ያላግባብ የመጠቀም ችግር (መኖሪያ ማድረግና የሀብት ማጋበሻ መሆን) እየከፋ መምጣቱ ተገልጿል፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስም በፌዴራል መንግሥቱና በክልል ደረጃ ባሉ የካቢኔ አባላት ላይ ሹምሽር አድርጓል፡፡  አዳዲስ ምሁራንን ወደፊት መስመር የማምጣቱ ጅምር ግን በመካከለኛ ደረጃ (በኤጀንሲ፣ በኮርፖሬሽን፣ በድርጅቶችና በጽሕፈት ቤቶች) የሚገኙ ሥራ አስኪያጆችን አልዳሰሰም፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹ጥልቅ ተሃድሶውን›› እንደ መድረክ ራሳቸው መርተው፣ ያን ሁሉ በረዶም ወርዶባቸው፣ አሁንም ባለመዱት ኮርቻ ላይ ተፈናጠው ለመቀጠል ሸሚዛቸውን የቀየሩ ‹‹ሙሰኛ›› አመራሮች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡

የሚያሳዝነው የሕዝብ ሥልጣን ቢያንስ ‹‹የብዙዎች መኖሪያና መንደላቀቂያ ሆኗል›› ብሎ ያረጋገጠ መንግሥት ከአንድም ሁለት ሦስት ተሽከርካሪ የሚጠቀሙ አመራሮች፣ ከላይ እስከ ታች ራሳቸውን ሸፍነው በድብቅ ተሽከርካሪ የሚጓዙ ፀረ ዴሞክራቶችን ድርጊት አላስቆመም፡፡ በግላቸው ሁለትና ሦስት የመንግሥት ቤት ይዘው ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ይፋፋማል!›› የሚል መፈክር የሚያስጮኹትም አሉ፣ እኛም አለን፡፡

ከሁሉ በላይ የብሔርና የዘመድ ኔትወርክን በመሳሳብ እያደራጁ የሥርዓቱን መልካም ገጽታ ያጎደፉ ሰዎች ጉዳይ አፋጣኝ ዕርምትን ይሻ ነበር፡፡ ምናልባት እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ኢቢሲ (የቀድሞ ኢቴቪ) መሥሪያ ቤቶች ላይ የተሞካከሩ ነገሮች ቢኖሩም በብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ግን ለይሉኝታ ያህል እንኳን ዕርምት አልተደረገም፡፡ ከአቅም ማነስ፣ ከዳተኝነትም ሆነ ከሌብነት በተነሳ ጥፋት የተጎተቱ ፕሮጀክቶች ሀብታቸው ‹‹ባከነ›› (በፀረ ሙስናና ዋና ኦዲተር ጭምር) የተባሉ ተቋማት ጉዳይስ እንዴት ሊዳፈን ይችላል?

መንግሥት ተሃድሶ ውስጥ ገብቶ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ፣ በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራና ፍትሐዊ ልማት ረገድ (ብዙ ያልተጠበቁ የመንገድ ልማቶች ፕሮጀክቶች ይፋ እየሆነ ስለሆነ) ሥራ ጀምሯል፡፡ በተሃድሶው መሠረት የተነሱ የአመራር፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጦችን ፈጥኖ በማስተካከልና ከስብሰባ ወጥቶ በቁርጠኝነት ለውጥ ማሳየት ላይ ግን ግብዝነት ታይቶበታል፡፡ ለአብነት ያህል የኢንዶውንመንትና የመንግሥት ተግባራቸው የተደበላለቀው ድርጅቶች አካባቢ ያለው መብላላት፣ በአንዳንድ የልማት ማኅበራት ውስጥ ያሉ የሥነ ምግባር ጥሰቶች መቼና እንዴት ሊታረሙ ነው? በገቢዎችና በጉምሩክ ዘርፍ በብረትና በሌሎች የቀረጥ ነፃ ውንብድና የፈጸሙ 186 ሰዎች ጉዳይ፣ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በብረታ ብረት ኮርፖሬሽንና በመስኖ ፕሮጀክቶች አካባቢ ያለው መዝረክረክ በምን ሊቋጭ ነው? . . . ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በአገሪቱ የጀመረውን ዕድገትና ለውጥ ማስቀጠል ስላለበት፣ ሙስናና ኢፍትሐዊነትን በትጋት መታገል አለበት፡፡ አንዱን ይዞ ሌላውን ለቆ ወይም የኢትዮጵያ ’FBI’ ተቋቁሟል እያሉ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽንን በማዳከም ችግሩን እሻገራለሁ ማለት ግን ራስን ማታለል ነው፡፡ የተባለው ተቋም የሠራው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑም ‹‹ዶሮን ሲያታልሏት . . . ›› እየመሰለ ስለመጣ መንግሥት በጥብቅ ሊያስብበት ይገባል፡፡ የተሃድሶ አጀንዳው ሳይዳፈን ለላቀ ውጤት ሊበቃ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

      

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...